Sunday, 30 July 2017 00:00

ቻይና፤ በኤርትራ-ጅቡቲ ድንበር ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ልታሰፍር ትችላለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ኳታር ባለፈው ወር በኤርትራና ጅቡቲ ድንበር ላይ አስፍራቸው የነበሩ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ቻይና ይህንን ክፍተት ለመሙላት በአካባቢው የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ልታሰፍር እንደምትችል የአገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ማስታወቃቸውን ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ኩዋንግ ዌሊንን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ቻይና ጥያቄው ከቀረበላት በሁለቱ አገራት መካከል ለአመታት የዘለቀውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ለመፍታት የአደራዳሪነት ሚናን ለመጫወትም ዝግጁ ናት፡፡
ቻይና ከግዛቷ ውጭ ያቋቋመቺው የመጀመሪያው የጦር ሰፈር ወደሆነውና ጅቡቲ ውስጥ ወደሚገኘው የጦር ሰፈር በዚህ ወር መጀመሪያ በርከት ያሉ ወታደሮቿን መላኳን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም አገሪቱ የኢኮኖሚ ፍላጎት በምታሳይባቸው አካባቢዎች በምታደርገው የጦር ሃይል መስፋፋት ውስጥ እንደ አንድ ቁልፍ እርምጃ ተደርጎ እንደሚወሰድም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ቻይና ምንም እንኳን በሰላም ማስከበር መስክ የአጭር ጊዜ ልምድ ቢኖራትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰላም አስከባሪ  ወታደሮችን ከሚያሰማሩ አምስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሰው ዘገባው፣ እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያሰማራቻቸው ወታደሮች ቁጥር ከ2 ሺህ 500 በላይ መድረሱንም አመልክቷል፡፡

Read 1650 times