Saturday, 29 July 2017 12:33

“ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የሆቴልና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የመክፈት ዕቅድ አለን”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

   - ነገና ከነገ ወዲያ ቡናና ሌጦ እየሸጡ መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል
                    - ‹ማግኖሊያ› የሚለውን ብራንድ ወደ ውጭ ይዘን የመውጣት ዕቅድ አለን
                    - ባንኮች ማበረታታት ያለባቸው አገር በቀል ሆቴሎችን ነው
             “የአገሪቷ ሁኔታ የተሻለ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ሰው ላይ ነው ኢንቨስት መደረግ ያለበት፡፡ ሰውን እንደ ሀብት (እሴት) ማየት ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ላይ የራሳችንን አሻራ ማሳረፍ እንፈልጋለን፡፡ ከውጭ ተቋም ጋር በመተባበር ሆቴሉን የተግባር ማስተማሪያ አድርገን፣ የምግብና የመጠጥ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ለማድረግ እቅድ አለን፡፡ ብዙ አገሮች ወደ ውጭ አገራት እየላኩ ነው የሚያሠለጥኑት፡፡ እኛ በምሥራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሆቴል ሙያና መስተንግዶ (ሆስፒታሊቲ) ማሠልጠኛ ኮሌጅ የመክፈት ሐሳብ አለን፡፡
“ይኼ ሐሳብ የእኔ ብቻ ሳይሆን በቦርዱ ውስጥ በሆቴል ሙያ 30 እና 40 ዓመት የሠሩ፣ እውቅና ያላቸውና ለአገራቸው የድርሻቸውን ማበርከት የሚፈልጉ ሰዎች ስብስብ አለ፡፡ አሁን እንደሚታየው የኮሌጆች መብዛት ሳይሆን፣ በጥራት በማሠልጠን የታወቀና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ኮሌጅ ሆኖ፣ የአካባቢ አገሮችንም ገበያ ለመሳብ የታለመ ነው፡፡
“በረዥም ጊዜ እቅዳችን ደግሞ “ማግኖሊያ” የሚለውን ብራንድ ወደ ውጭ ይዘን ለመውጣት እቅድ አለን፡፡ ብዙ ጊዜ የውጭ ብራንዶች ወደ አገራችን መጥተው፣ እዚህ ያፈሩትን ገንዘብ፣… ይዘው ይወጣሉ፡፡ ባንኮች ሳይቀሩ እነዚህን ድርጅቶች በጣም ሲያበረታቱና ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ሳይ በጣም ይገርመኛል፡፡ ባንኮች ማበረታታትና መደገፍ ያለባቸው አገር በቀል ሆቴሎችን ነው፡፡ እኛ ከተበረታታንና አቅማችን ከዳበረ ወደ ውጭ አገር ወጥተን የማንሠራበት ምክንያት የለም፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ቡናና ሌጦ ብቻ እየሸጡ መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የቱሪዝም መዳረሻ ወደ ሆኑ አገሮች ሄዶ በመክፈት፣ ለአገሪቷም የውጭ ምንዛሪ ማምጣት እንችላለን፡፡
“በረዥሙ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለረዥም ጊዜ የሚታሰብ ነገር መሠረት ይኖረዋል፡፡ መሰረት ያለው ነገር ደግሞ ሰፋ ብሎ ሲመጣ ትልቅ ኬክ ይሆናል። ትልቅ  ኬክ ደግሞ ብዙ ሰው ይካፈለዋል፡፡ ኬኩን ትልቅ ለማድረግ በጣም የሚያስፈልገው ነገር እውቀት ላይ መስራት ነው፡፡ እውቀት ላይ ሲባል ደግሞ ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እውቀት ላይ መሥራት በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን፣ የሕዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ ጠንካራና የበለፀገ ኢኮኖሚ ያላቸውን አገሮች በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ አደጉ የምንላቸው አገሮች የበለፀጉት በተፈጥሮ ሀብት (ሪሶርስ) ሳይሆን በእውቀት ነው” ያሉት የዛሬ ሳምንት በሶፍት ኦፕኒንግ ሥራ የጀመረው “የማግኖሊያ” ሆቴል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ነጋ ናቸው፡፡ “ማግኖሊያ”፣ ግሩም መዓዛ ያላት ነጭ አበባ ስም ነው፡፡
የአቶ ሳምሶን ነጋና የባለቤታቸው የወ/ሮ ሳባ ጴጥሮስ ንብረት የሆነው ማግኖሊያ ሆቴል  በቦሌ መንገድ “2 ሺህ ሀበሻ” ምግብ ቤት አጠገብ የሚገኝ ሲሆን፤ አምስት ደረጃ ያላቸውና ሁሉም አገልግሎት መስጫ ቁሶች የተሟላላቸው፤ ሰፊ የእንግዳ ማረፊያ፣ መኝታ ክፍል፣ ጃኩዚና ሻውር ያለው አምባሳደር ሱት፣ ጃኩዚና ሻወር  ያላቸው 3 ላግዥሪ፣ ጃኩዚና ሻወር ያላቸው 7 ኤክሲኩቲቭ፣ 24 ቲዊንና 52 ስታንዳርድ ሱትስ አሉት፡፡ የሕንፃ ውስጥ መዋኛ፣ አነስ ያሉ ሰዎች መያዝ የሚችሉ ሁለትና 600 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽ፣ አንድ ትልቅ ሬስቶራንት፣ ሁለት ባር፣ የፒያኖ መዝናኛ፣ ፀጥታና ሰላም የሚፈልጉ ሰዎች እንደሚመርጡት፣ በአሁኑ ወቅት ለ130 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር ደግሞ 150 ሰራተኞች እንደሚኖሩት የሆቴሉ የገበያና የጥናት ዳይሬክተር አቶ ፋሲል አያሌው ገልፀዋል፡፡
አቶ ሳምሶን ነጋ፣ በ1955 ዓ.ም በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ተወልዶ፣ በ1963 ዓ.ም ከቤተሰቦቹ ጋር አዲስ አበባ መጥቶ መኖር ጀመረ። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ንፋስ ስልክ 2ኛ ደረጃ ተማረ፡፡ የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወስዶ፣ ንግድ ስራ ኮሌጅ (ኮመርስ) ገብቶ በፋይናንስ በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሂሳብ አያያዝ (አካውንቲንግ) የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ ወደ እንግሊዝ አቅንቶም ከኦፕን ዩኒቨሲርቲ ኤምቢኤ (በማሰተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚነስትሬሽን- MBA) ተመረቁ። በ1985 ዓ.ም ከአዲስ ከአበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ከተመረቁት ከወ/ሮ ሳባ ጴጥሮስ ጋር ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ከሚስታቸው ጋር በመሆን ወደ ግል ሥራ ገቡ፡፡
የዛሬው ኢንቨስተር ሥራ የጀመሩት በለጋ ዕድሜያቸው ነበር፡፡ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው፣ አባታቸው አቶ ነጋ ቦንጋር በተሰማሩበት የሆቴል ሥራ በትርፍ ሰዓታቸው ይረዷቸው ነበር፡፡ ከአባታቸው ጋር ብዙ ዓመት ሠርተዋል፡፡ አቶ ሳምሶን በ1978 ዓ.ም ከአ.አ.ዩ እንደተመረቁ ነው የግል ሥራ የጀመሩት። በዚህ ጊዜ ውስጥ የግል ንብረት አፍርተው ነበር፡፡ ንብረቶቹን አስይዘው፣ 6 ሚሊዮን ብር ያህል ከባንክ ተበድረው፣ ከባለቤታቸው ጋር በመመካከር፣ በ1983 ዓ.ም በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ የመኖ ማምረቻ ፋብሪካ አቋቋሙ። ‹‹ጥሬ ዕቃው እንደ ልብ ስለማይገኝ ችግሮች አሉት እንጂ፣ እንደኛ አገር በእርሻ ላይ ለተመሠረተ አብይ (ማክሮ) ኢኮኖሚ፣ መኖ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው›› ይላሉ አቶ ሳምሶን፡፡
ባለሀብቱ፤ የመኖ ፋብሪካ ባቋቋሙበት ወቅት የሥራ ሥነ-ምግባር ያለው የሰው ኃይል የማግኘት ፈታኝ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ያለን የሥራ ባህል ጠንካራ ነው የሚል እምነት የለኝም›› የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ ‹‹በአጭር መንገድ የመክበር ቫይረስ ተፈጥሯል” ባይ ናቸው፡፡ ‹‹ቢዝነስ›› የሚለው ሐሳብ  ‹ዝም ብሎ ገንዘብ ማግኘት› ወደ ሚለው፣ ተለውጦ፣ ‹‹በአጭር ማደግ፣ በአጭር መክበር›› ገኖ የወጣ ይመስላል፡፡ ይህ ችግር ገኖ እንዳይወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ደግሞ መንግሥት  ብቻውን መወጣት ያለበት አይመስለኝም፡፡ የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ትኩረት መሆን አለበት። ‹እንዲህ ያለው አመለካከት በምንኖርባት አገር ምን ዓይነት ቀውስ ይፈጥራል?› በማለት አስቦ፣ ይህ ችግር ብዙ አደጋ ሳያስከትል በአጭሩ የሚወገድበትን ዘዴና መፍትሔ መፈለግ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
‹‹ከአንድ አገር እሴት አኳያ ስናየው፣ የመጀመሪያው ኃላፊነት የቤተሰብ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሃይማኖት፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችና የፖለቲካ ተቋማት ናቸው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ኃላፊነት እንዳይፈርስና እንዳይደናቀፍ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ተቋማት የምንለው ይኼ አሁን እየሠራንበት ያለው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥሩ መሠረት እንዲኖር ከተፈለገ፣ ከቤተሰብ መሠረት ያለውን ነገር ይዞ መምጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ጥሩ እሴት እንዲኖር ካስፈለገ፣ በሁሉም ዘርፍ የመከባበር እሴት እንዲኖር የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ማኅበራዊ ተቋማት ያላቸው ሚና የተያያዘ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ማለፍ ከተቻለ አስተዋጽኦው ትልቅ ይሆናል። የዕድገት ስልቱም ሩቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሰው ካደገ፣ አገርም ያድጋል፡፡
‹‹ሂዩማን ዲቬሎፕመንት ኢንዴክስ›› የሚባለው የዕድገት መለኪያ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እነሱ ባደጉ ቁጥር፣ የሰው አስተሳሰብ፣ የአኗኗር ሁኔታቸው… እያደገና እየተለወጠ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ መለወጥ ያለበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይኼ የሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነት ነው፡፡ ማኅበራዊ ተቋማት ፒራሚድ ናቸው፡፡ ከላይ ከአናት የፖለቲካ ተቋም አለ፡፡ ከስር ደግሞ ቤተሰብ አለ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሃይማኖት፣ የትምህርትና የኢኮኖሚ ተቋማት መሃል አሉ፡፡ በፒራሚዱ ላይ የተቀመጡት ሁሉም ተቋማት ራሳቸውን ፈትሸው ማስተካከል ከተቻለ የተቋማት ክስረት አይኖርም ማለት ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ጥፋቱ (ዲስቶርሽኑ) እየበዛ ይሄዳል፡፡ ልክ እንደ ሱቅ ማለት ነው፡፡ የሶሾሎጂ ተቋማት ይከሰራሉ፡፡ ከከሰሩ ደግሞ መውጫ የላቸውም፡፡ በአሁኑ ይዞታ ከቀጠሉ የመክሰራቸው ሁኔታ አይቀሬ ይመስላል። ስለዚህ ይህ ችግር ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። ለግለሰብም የሚተው አይደለም። ሁሉም ሰው ሊመጣ (ሊከሰት) የሚችለውን ኪሳራና ቀውስ ተገንዝቦ፣ አንድ ነገር ማድረግ ያለበት ይመስለኛል›› በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመኖ ሥራውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት በሚገባ እንዳይሠሩ ስላደረጋቸው ባለቤታቸው መሃንዲስ ስለሆኑ ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ገቡ። በዚህ ዘርፍም የመንገድ፣ የውሃ የግንባታ፣ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ተጫርተው እያሸነፉ ብዙ መሥራታቸውን፤ ወደ ኋላ ላይ ደግሞ ከሲቪል ኢንጂነሪንጉ ይልቅ ኤሌክትሮመካኒካሉ ይሻላል በማለት በከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ፤ ፓምፖችን፣ የተለያዩ ጀኔሬተሮችን ማስመጣትና መግጠም፣…. እስካሁንም ድረስ እየሠሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሳምሶን በስራዎች ውስጥ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በመስራት ማመን ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ አቶ ሳምሶን፤ የባለቤታቸውን የወ/ሮ ሳባ ጴጥሮስ ስም ጠርተው አይጠግቡም ማለት ይቻላል፡፡ “ፈታኝ ችግሮች ብዙ ጊዜ ያጋጥማሉ፤ ነገር ግን ቤት ውስጥ በባለቤትህና በልጆችህ መሃል ሰላም ካለ፣ ሌሎች ችግሮችን መወጣት ትችላለህ፡፡ ለእኔ (ለእኛ) እዚህ ደረጃ መድረስ ትልቁ ምክንያት የባለቤቴ ድጋፍ ይመስለኛል፡፡ እንደ ከተማ ሴት መዋብ፣ መሽቀርቀር እንደፈለግሁ ልሁን የምትል አይደለችም፡፡ በእልህና ትግል ነው የምትሰራው፤ በጣም ጠንካራ ሴት ናት” በማለት የባለቤታቸውን ሥራ ወዳድነት ገልጸዋል፡፡
አቶ ሳምሶን ስለ ማግኖሊያ ሆቴል ግንባታ ሲናገሩ፤ ሰባት ዓመት ተኩል መፍጀቱን ገልጸዋል። ‹‹አብዛኛውን ድርሻ የወሰደው የሕንፃው ወይም የሲቪል ኢንጂነሪንጉ ሥራ ሳይሆን  ከሌላው ለየት ተደርጎ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ስለሆነ አሌክትሮ መካኒካል ሥራው ነው ብዙ ጊዜ የወሰደው›› ብለዋል። ለመዘግየቱ ሌላም ምክንያት አለ፡፡ ዕቃዎቹ በሙሉ የተገዙት ከውጭ  ሲሆን ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ነው የተገጠሙት፡፡
“ሌላው አሰልቺና አታካች የነበረው የኤልሲ ሂደቱ ነው፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ ይታወቃል። ከውጭ ላስገባናቸው ዕቃዎች በርካታ ኤል ሲዎች ተከፍተዋል፡፡ አንዱ እስከ ፈቃድ ያለውን ውጣ-ወረድ መገንዘብ ይቻላል” በማለት የዘገየበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡

Read 1969 times