Saturday, 29 July 2017 12:15

“ሚክሎል” ከ15 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ለንባብ በቃ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በደራሲ ስዩም ገብረ ሕይወት ተጽፎ በ1994 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃውና በድጋሚ የታተመው “ሚክሎል - የመቻል ሚዛን” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ ዛሬ ተሲያት ላይ በጁፒተር ሆቴል ተመርቆ በገበያ ላይ እንደሚውል  ደራሲው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡
ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ስራዎቻቸውን በሚያቀርቡበትና የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች በተካተቱበት ፕሮግራም የሚመረቀው “ሚክሎል - የመቻል ሚዛን”፣ በደርግ መንግስት የመጨረሻ አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ዘመቻ ዋዜማ ላይ መቼቱን በማድረግ፣ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን በፍልስፍና እየነቀሰ የሚተነትን መጽሃፍ ነው፡፡
መጽሃፉ ጠንካራና ፈታኝ ሀገራዊ ጉዳዮችን በሠመረ ኪናዊ ውበት የሚዳስስ፣ የተሻለ ሀገራዊና ግለሰባዊ የእድገት ጥያቄዎችን እያነሳ ልማዳዊውን የማንነት ገበና የሚጋፈጥ፣ ሀገራዊ ብልፅግናን ከተፈጥሮአዊ አቅም ጋር አስተሳስሮ የሚመረምር፣ ለአንባቢ እጅግ የነጠሩ ቁም ነገሮችን የሚያስጨብጥና የሚያነቃ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የሥነጽሁፍ ባለሙያዎች መስክረዋል፡፡
በ395 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፣ በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ አሳታሚነት በድጋሚ ታትሞ ለንባብ የበቃ ሲሆን፣ በተለያዩ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በ150 ብር የመሸጫ ዋጋ ለገበያ ቀርቦ እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በእንግሊዝ አገር ያደረገው ደራሲ ስዩም ገብረ ሕይወት፣ የ“ሚክሎል - የመቻል ሚዛን” ቀጣይ ክፍል የሆነውና ከ15 አመታት በፊት የጻፈውን “የማቃት አንጀት” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ በቅርቡ ለንባብ ለማብቃት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽንና ኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው ደራሲ ስዩም ገብረ ሕይወት፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ቤተ መጽሃፍትና ኮምፒውተር ማዕከል በማቋቋምና በማስተማር ያገለገለ ሲሆን፣ በብሪቲሽ ካውንስል በፕሮጀክት ማናጀርነትና በቤተ መጽሃፍትና ኢንፎርሜሽን አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ለሰባት አመታት ያህል ሰርቷል፡፡

Read 1266 times