Saturday, 29 July 2017 12:07

አዚማሙ

Written by  ሚኪያስ ጥ - ከባህርዳር
Rate this item
(11 votes)

   «በአንድ ምሽት የተገመደዉ የወዳጅነት ትስስሮሽ፣ ለበርካታ ዓመታት ሊዘልቅ በቅቷል።»
በወረቀት ላይ ፃፈዉ፤ በሚነበብ መልኩ አሰፈረዉ። ግን የ’ርሱንና የጨረቃን ወዳጅነት ቢተርክ፣ማን ያምነዋል፤ማንስ «ዕዉነት ነዉ!» ብሎ ይቀበለዋል? ግራ ገባዉ። ትዝታዉን ለማስፈር ወረቀትና ብዕር አሰናኘ፤ አሰናኝቶም ታሪኩን ይፅፍ ቀጠለ፤ የተገናኙበትን ቀን ተረከ...
«ከበርካታ ዓመታት በፊት፣እኔ የመንግስት ተቀጣሪ ነበርኩ። በትርፍ ጊዜዬ፣ ሴቶችን አፈቅር ነበር። በአቅሜ ነዉ የማፈቅረዉ። ሃብታም ሴት አላፈቅርም፤ ድሃም አላፈቅርም። መካከሉ ላይ ያለች ግን ከነፍሴ ነዉ የምወድደዉ። እንደምኞቴ፣ መካከሉ ላይ  የምትገኝ  ቆንጆ  ሴት አፈቀርኩ። የመልኳ ትዕምርት አይወራ-አይነገር! ከንፈሯ የሞላ- ሰዉነቷ የሞላ- ባቷ የሞላ- ጭኗ የሞላ... ብቻ፤ ሁሉም ነገሯ ‘ሞላ’ በሚለዉ ቃል የሚገለፅ። [...] ወደድኳት፤ አንገቴና ሸሚዜ’ጋ አብሬ እንደማስረዉ ክራቫት፣ እርሷንም አጥብቄ ወደድኩ። ስጦታ እገዛለሁ፤ እልካለሁ (የቤት አስቤዛ!)። ትቀበላለች፤ ታበስላለች፤ ባሏንና ቤተሰቧን ትመግባለች! (አሃ! ለካንስ ባል ነበራት? አይይ... አለማወቄ!)
ይገዛል - ይላካል። የፍቅሬን መጠን ‘ትረዳለች’ ብዬ ነበር። ሙከራዬ ሁሉ ከሸፈ። የእርሷን ልብ መማረክ አልቻልኩም። (አቤት - ’አይሆንም’ ያለችኝ ቀን ያለቀስኩት ለቅሶ! ስለ’ዛ ቀን በኋላ ላይ በዝርዝር እፅፋለሁ!) ቆፍጠን ያለ ዉሳኔ ለመወሰን ተነሳሁ፤ እርሷን መተዉ።
ተዉኳት፤ ፍቅሯ ባሰ እንጂ መተውስ ጥሩ ነበር።
የበረታዉ ፍቅሯን ለማስታገስ ደ’ሞ ምን ባደርግ ጥሩ ነዉ - ጨረቃን መመልከት። ጨረቃን አያለሁ፤ ምን እንደሆነች እመራመራለሁ (ኮከብ ነች፤ አይደለችም? እያልኩ)፤ ትዝታዬን እወጣባታለሁ።
‘አስታግሰዋለሁ’ ያልኩት ፍቅር፤ ከሴትዮዋ ወደ ጨረቃዋ፣ በነፃ ተዘዋወረ- ምንም ክፍያ ሳያስከፍል። በጨረቃ ፍቅር ‘ክንፍ’ አልኩ። በጣም ወደድኳት! እርሷን አግብቼ፣ በብርሃኗ ማዕጥነት ታጥኜ፣ በተስፋ መዓዛዋ ተፈዉሼ መኖርን ተመኘሁ። ግን አይነኬ ናት፤ ለዚያዉም አይደረሴ። በምን መንገድ ላዉራት? በምኔ ልጀንጅናት? (‘foolish! ‘በምላሴ’ኮ ነዉ የምጀነጅናት)
ግራ ገባኝ። ቢጨንቀኝ የሁሉ ነገር ፈጣሪዉን - እግዚአብሄርን ጠየቅኩት፤ ‘እንዴት ላዉጋት?’ ብዬ። እርሱም ጎርነን ባለዉ ድምፁ ፤ ’እኔ በፈጠርኩልህ ምናብ አዉራት፤ ታምንሃለች!’ ብሎ፣ ለጥያቄዬ አነስተኛ ምላሽ ለገሰኝ።
‘ምናብ?!’ ራሴን ጠየቅኩ።’ የምናቤ ሙሃቲት ከሟሸሸ ቆዬ’ኮ። ታዲያ! ምን ላድርግ?’
አሰብኩ። የተገለጠልኝ ነገር ቢኖር፣ እኔ ባለምናብ እንደሆንኩና ማስተዋል እንደምችል ...! አቤት- የተሰማኝ በራስ መተማመን!
ደረቴን ነፋሁ፤ ቆፍጠን አልኩ።
ከመቆፍጠኑና ከመነፋፋቱ መለስ አልኩና፣ ምናቤን ወደ’ማሰራቱ ገባሁ። እንዝርቱ ሾረ - የምናቤ።
ጨረቃን በደንብ አወራኋት፤በጣም አወራኋት!
...’አቢዬ! አንተ እንዴት ያለህ ሰዉ ነህ?’ ጠየቀችኝ፤ ድምጿን አለዝዛ።
‘እንደዚሁ። ዝም ብዬ የምኖር፣ ዝም ብዬ የምናገር፣ ዝም ብዬ የማፈቅር!’ ተከዝ ብዬ።
‘ዝም ብለህ ነዉ ያፈቀርከኝ?’
‘ዝም ብዬ’ማ አይደለም። በአስተዉሎት አይቼሽ፣ ከሌሎቹ’ጋ አመዛዝኜ ነዉ። በከንቱ ያ’ንቺን ዉበት ገርምሜ እንደወደድኩሽ ካመንሽ፣ አንቺ ስህተተኛ ነሽ! እኔ’ኮ ባ’ንቺ ፍቅር ከነደድኩ ዓመታት አለፉ፤ ደግሞ ላወራሽ አቅም አጥሮኝ ነበር።’
‘ለምን?’
‘ፍቅርሽ ከብዶኝ!...’
‘እኔም’ኮ ታሳዝነኝ ነበር። ያቺ የምትወዳት ሴት ፍቅርህን ለመረዳት አቅም ሲያጥራት ስመለከት፣ በ’ዉነት አዝኜልህ ነበር። ይህን ሰዉ አፅናንቼዉ ቢጠነክር!- እያልኩ ሳስብ፣ ይኸዉ ማንም ሳይጠራህ፣ እኔም ናልኝ ሳልልህ፣ በሃሳብህ ፈረስ ጋልበህ፣ ከ’ኔ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ መጣህ። ኡህ! ...የልብ ሃሳብ ሲሰምር፣ እንዴት ደስ ይላል!’
‘በጣም! እኔም ከመቼዉ አቅፌ በሳምኳት ስል ነበር። ዛሬ የሩቅ ምኞቴ ተሳካ!’
‘በል እቀፈኝ!...’
ከዚህ በኋላ ያለዉ ነገር የሚወራ ስላልሆነ አልፅፈዉም። (ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ፣ ትራሴን አቅፌ ብቻዬን ሳወራ ነበር፤ ቤቴ ግቢ ዉስጥ ስንገላጀጅ ነበር። ጨረቃን ያቀፍኩ መስሎኝ!)
አሁን ያለንበት የፍቅር ሁኔታ ሌሎችን ያስቀናል ቢባል፣ ማጋነን አይሆንም። እኔ ለእርሷ አሳቢ ነኝ፤ እርሷም ለእኔ አሳቢ ነች። በጥቅሉ እንተሳሰባለን። ፍቅር ዉስጥ መተሳሰብ ሲደረጅ፣ እንዴት ደስ አይል? መቼም ‘ከጨረቃ ጋር ፍቅረኛ ከሆንክ፣ ስንት ልጅ ለመዉለድ በቃህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ ሰዉ አይኖርም።
ልጆች- አዎ- ተወልደዋል። ‘ልጆቼ’ የምላቸዉ፣ እንዲሁ ስጋ የለበሱ፤ የነፍስ እስትንፋስን ያዘሉ ሳይሆኑ፣ በወረቀት ላይ የነገሱ- ሲያነብቧቸዉ ቀልብን የሚገዙ ረቂቅ የልቦለድ ስራዎቼ ናቸዉ። (አሃ! ፀሃፊ መሆኔን አልተናገርኩም ለካ!) ባይታተሙም፣ በጨረቃ አጋዥነት ከቀን ወደ ቀን እያጎለመስኳቸዉ መጥቼያለሁ። በሁሉም ነገር ደስ ብሎኛል።
ስለእዛች ልበ - ድንጋይ ሴት እንዴት እንዳዘንኩ ወደ መጨረሻ ላይ ‘እናገራለሁ’ አላልኩም ነበር? አልረሳሁትም፤ እናገራለሁ!
ያን ቀን አልረሳዉም። በህይወቴ ላይ ጥቁር ማህተም የታተመበት ዕለት ነበር። ‘እኔ ከአንተ’ጋ መቀጠል አልፈልግም። ባለትዳር ነኝ። ‘ስትለኝ፣ የደሜ ፍላቴ በጣም አየለ። ከዱላ ይልቅ እንባን ማንጠባጠቡ ቀለለኝ። ለጥፊ ያነሳሁት እጄን በቀስታ ወደፊቴ ከነበልኩ።
ለቅሶ በዛ። እዛዉ በቆመችበት ጥዬኣት ሄድኩ።
ቀጥታ ያመራሁት - በጥርጊያዉ አሳብሬ - ወደ መጠጥ ቤት ነበር። ባለጌዉ ወንበር ላይ ተቀምጬ፣ መጠጥ አዘዝኩ - ከገብስ የተጠመቀ ለስላሳ (ጅል ነኝ!)። ሰዎች ሳቁ፤ ምድረ - ሰካራም ሁላ በሳቅ ሲቃ ተያዘ። አስተናጋጁ ራሱ ሳቀብኝ። ‘ለምን የህፃን መጠጥ ይጠጣል?’ ብለዉ ይሆናል የሚስቁት። እኔ ስናደድ መንፈሴ ወደ ህፃንነት ዘመኔ ይመለሳል። ለህፃን ደግሞ ከባድ መጠጥ አይመከርም፤ አጠጣጡን አያዉቅበትምና። ስለዚህ ለህፃን የሚያስፈልገዉ የህፃን መጠጥ ነዉ። እኔ በዚህ አቅጣጫ ተመልክቼ ነዉ - የለሰለሰ መጠጥ ያዘዝኩት። ሰዉ ግን የደረጀ ገላዬን አይቶ ይዘባበትብኛል።
በዝምታ ጠጥቼ፣ የሽሙጥ ሳቅን ተሸክሜ፣ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፤ ከጨረቃ’ጋ ፍቅር ለመስራት በቃሁ!»
ፅፎ ጨረሰ። ከአቀረቀረበት ቀና አለ። ጨረቃን አያት። አይኑን ጨፍኖ፣ ከንፈሩን አሞጠሞጠ።
ጨረቃን በምናቡ ሳማት - ከንፈሯን መጠመጠዉ።
«እህ!...እንዴት ከንፈርሽ ይጥማል!» በለሆሳስ አወራ።
የመተዘትና የመፋዘዝ ዘመኑ ቀጠለ።                   

Read 6277 times