Print this page
Saturday, 29 July 2017 12:09

የጃንሆይ ውለታ፣ ለትምህርትና ስነ ጥበብ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 “ንጉሱ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት አባት ናቸው”

                        “ሀብቴም፣ ጉልበቴም፣ ዕውቀቴም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተማር ይውላል” ቀ.ኃ.ሥ
                              
      “ጃንሆይ - ለትምህርት”
የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1923 ዓ.ም ንጉሠ ነገስት ተብለው የአፄውን አክሊል ሲደፉ፣ አገሪቱን ወደ ስልጣኔ ለመምራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን በእርጋታ እንደመረመሩ አምባሳደር ሞገስ ሀብተ ማርያም ይገልፃሉ፡፡
ከእቅዶቻቸው ሁሉ ቅድሚያ የተሰጠው ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ለሁሉም መሰረት ነው የሚለው ሀሳብ ነበር፡፡ በ1917 ዓ.ም ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተፈሪ መኮንን ት/ቤት፣ የሀገሪቱን የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ማርካት እንደማይቻል የተገነዘቡት ጃንሆይ፣ በየከተሞቹ ት/ቤቶች በፍጥነት እንዲከፈቱ በሰጡት መመሪያ፣ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ ባሉ አስር አመታት ውስጥ የሚሊዮኖችን አዳሪ ተማሪ ቤቶች ጨምሮ ወደ 60 የሚሆኑ ት/ቤቶችን መቀሌ፣ ደሴ፣ አምቦ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬደዋ፣ አሰበ ተፈሪ በመሳሰሉ ከተሞች እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡
ጃንሆይ ይህም አላረካቸውም፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን ከአውሮፓውያን መቅዳት እንደሚያስፈልግ ተገነዘቡ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ጥቅምት 21 ቀን 1919 ዓ.ም 33 ወጣቶችን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አሰባስበው ወደ ውጭ ሀገር ላኩ። በወቅቱ ተማሪዎቹን ሲሸኙ፤ “እኔ ሰው ነኝ፤ ሟች ነኝ፣ ለማትሞተው አገራችን ረዳት እንድትሆንዋት እግዚአብሔርን እለምንላችኋለሁ” የሚል ንግግር ማድረጋቸውን አምባሳደር ሞገስ፣ ስለ አፄው ዘመናዊ ትምህርት ማስፋፋት ባቀረቡት ፅሁፋቸው ጠቁመዋሉ፡፡
ከጣሊያን ወረራ በፊት በዚህ ውጥናቸው ከ200 በላይ ወጣቶችን ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት ለከፍተኛ የትምህርት ስልጠና የላኩት ጃንሆይ፤ ከወረራው በፊት በተከፈቱ 30 ትምህርት ቤቶች 5 ሺህ ያህል ተማሪዎች እውቀት ይገበዩ ነበር፡፡
ጣሊያን ሀገሪቷን ሲወርር፣ ለኢትዮጵያውያን የፈቀደው ትምህርት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ብቻ ነበር፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸውን ት/ቤት የመላክ ፍላጎታቸው እምብዛም ነበር፡፡
ከወረራው በኋላ ግን ንጉሠ ነገሥቱ አሁንም “ሀገሪቱን የሚለውጠው ትምህርት ነው” የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ፣ ት/ምህርት ቤቶች ወትሮ ከነበረው ይበልጥ እንዲስፋፉ መመሪያ ሰጡ፡፡
ስልጣናቸው እስካበቃበት 1966 ዓ.ም ድረስም በአስራ አራቱም ጠቅላይ ግዛቶች ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥባቸው 1655 ት/ቤቶች አቋቋሙ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት በሸዋ 292 ሲሆን፣ በኤርትራ ደግሞ 201 ት/ቤቶች ነበሩ፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍልን የሚያስተምሩ 67 ት/ቤቶች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 7 ያህሉ በኤርትራ ነበሩ፡፡ ይኸም ከሸዋ ከነበሩት 13 ት/ቤቶች ቀጥሎ መጠኑ ከፍ ያለው በኤርትራ እንደነበር ያስረዳል፡፡
ከ9 እስከ 12ኛ የሚያስተምሩ ት/ቤቶችን በመላ ኢትዮጵያ 277 ደርሰው የነበረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 56ቱ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ 39ኙ ደግሞ በኤርትራ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ከ1ኛ እስከ 12ኛ የሚያስተምሩ 1999 ት/ቤቶች፣ 14 ኮሌጆች፣ 4 ከፍተኛ የትምህርት መስጫ (በዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚያበቁ) ተቋማት እንደነበሩ አምባሳደር ሞገስ ገ/ማርያም ያስረዳሉ፡፡
እነዚህን በየደረጃው ያሉ ካቋቋሙ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ሊኖር እንደሚገባ ወሰኑ፡፡ ከአባታቸው በውርስ ያገኙትን “ገነተ ልኡል” ተብሎ የሚጠራ ቤተ መንግስታቸውን ዩኒቨርሲቲ አድርገው፣ ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ለህዝብ አበረከቱ፡፡
በዚህ የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የሚከተለውን ንግግር እንዳደረጉ አምባሳደር ሞገስ ይገልፃሉ፡- “ይህን ቤተ መንግስት ከቦታው ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክተናል፡፡ ይህን ዩኒቨርሲቲ ስንመርቅ፣ ይህ ቀን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት ላደረግነው የረጅም ዘመን ድካም አክሊል ይሆናል ብለን የምንገምተው ነው፡፡ ነዋሪ (ቋሚ) መታሰቢያችን ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንውልለት ትምህርት ስለሆነ፣ ውለታው የማይረሳ ህዝባችን ለሃውልታችን ማሰሪያ እንዲሆን በፍቃዱ ያዋጣውን ገንዘብ (በወቅቱ ለሃውልታቸው ማሰርያ ህዝቡ ገንዘብ አዋጥቶ ነበር) ለዚህ ዩኒቨርሲቲ ስራ እንዲውል አድርገናል” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “በዚህ ዩኒቨርሲቲ ተምራችሁ የጥበብ ባለቤት ሆናችሁ ስትወጡ፣ አገራችሁ ኢትዮጵያ በእርሻ የምትሻሻልበትን፣ በፋብሪካ የምትስፋፋበትን ስራ ስሩ፣ ከምድሯ የሚገኘውን ማዕድን ቆፍራችሁ አውጥታችሁ፣ ይህ ሳይማር ያስተማራችሁን፤ በድህነት በችግር በበሽታ የሚሰቃየውን ህዝብ እንደሚያልፍለት አድርጉት … ትምህርት ቤቱንም ከዚህ አላማ ውጪ ለሆነ ለሌላ ተግባር አታድርጉት” ብለው ነበር፡፡
የጃንሆይ የተማሪ ምልመላ ጥበብ ተደናቂ ነበር። ከሀረርጌ የአደሬ፣ ከሶማሌ፣ ከኦሮሞ እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰቦች ልጆችን ራሳቸው በየጠቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ አዲስ አበባ አምጥተው ያስተምሩ ነበር፡፡
በሚጓዙባቸው አካባቢዎች ልጆች ሰብሰብ ብለው ሲጫወቱ ከመኪናቸው ወርደው መማር ይፈልጉ እንደሆነ በመጠየቅ፣ ፍቃደኛ የሆኑትን ቤተሰባቸውን አነጋግረው፣ በመኪናቸው ጭነው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በአዳሪ ት/ቤት ያስተምሩ ነበር፡፡ ጃንሆይ ለእነዚህ ልጆች የቀን ተቀን ክትትልም ያደርጉ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት የጃንሆይ 125ኛ የልደት በዓል በዋቢ ሸበሌ በተከበረበት ልዩ ዝግጅት ላይ ከተገኙ እንግዶች መካከልም አንድ አስተያየት ሰጪ “ጃንሆይ ከገጠር ካመጧቸውና ካስተማሯቸው አንዱ ነኝ … ለቁም ነገር እንድበቃ፣ ሀገሬን በእውቀቴ እንዳገለግል አድርገውኛል … ዛሬ ግን ትውልዱ ውለታቸውን ዘንግቶታል፡፡ ሲሉ በቁጭት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ አወያይ ሆነው የተሰየሙት ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ በበኩላቸው ንጉሡ ለትምህርት መስፋፋት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ የመጀመሪያው ሚኒስትር ራሳቸው በመሆን ትምህርት ሚኒስቴርን እንዳቋቋሙ፣ ለተማሪዎች ማበረታቻ ይሆን ዘንድ እስክሪብቶ፣ ደብተር፣ መፅሐፍና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች በነፃ ይቀርብላቸው እንደነበር ምስክርነታቸውን አጋርተዋል፡፡
ንጉሡ ለየት ያለ የማበረታቻ ዘዴም ነበራቸው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጥጋቢ ውጤት አምጥተው ወደ ሁለተኛ ደረጃ የተሸጋገሩ ተማሪዎች፣ በየወሩ የተወሰነ የኪስ ገንዘብ ይሰጣቸው እንደነበር ዶ/ር ዳዊት ያስታውሳሉ፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች ደግሞ የአዳሪ ትምህርት ሙሉ ወጪያቸው በመንግስት የሚሸፈን ሲሆን ነበር። በተለይ ከዳር የሀገሪቱ ግዛቶች ለሚመጡ ወጣቶች በዚህ ረገድ ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ ለትምህርት ወደ ውጪ ሲላኩም አልባሳትና ገንዘብ ይሟላላቸው ነበር” ይላሉ ዶ/ር ዳዊት፡፡ የኤርትራ ወጣቶች ደግሞ የተለየ እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር፤ ዛሬ ኤርትራ በርካታ የተማሩ አዛውንቶች ባለቤት የሆነችው በዚህ የንጉሱ የተለየ ድጋፍና ማበረታቻ ነው፡፡
በዚህ ለንጉሡ ክብር በተዘጋጀው የልደት በዓል መታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ግርማዊነታቸው በዘመነ መንግስታቸው ለትምህርት መስፋፋት ያደረጉትን አስተዋፅኦ በጥናታዊ ፅሁፍ የዳሰሱት የስነ ትምህርት ምሁሩ ዶ/ር አግደው ረድኤ ንጉሡና የንጉሣውያን ቤተሰቦች የሚሣተፉባቸው “ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ላኩ” የሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳዎች በተለያዩ መንገዶች ይካሄዱ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ለትምህርት ማስፋፋትም በዘመኑ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ይመደብ እንደነበር ዶ/ር አግደው አውስተዋል፡፡
በወቅቱ የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ፍልስፍና፤ “ትምህርትና ስነ ጥበብን ማበልፀግ” የሚል እንደነበር የሚጠቅሱት ዶ/ር አግደው፤ መሪ ቃሉም ከመፅሐፍ ቅዱስ የተወረሰው “የምትሹትንና የምትፈልጉትን መርምሩ፤ የሚስማማችሁን መርጣችሁ ያዙ” የሚል ነበር ይላሉ “ትምህርት ለምርምር” የሚል መርህም ነበረ በዘመኑ፡፡ የትምህርት ስርአቱ በነዚህ መርሆች ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ነበር፡፡
“ትምህርታቸውን በየደረጃው ያጠናቀቁ ተማሪዎችን ከስራው ጋር ማቆራኘት” የሚለው ደግሞ ተማሪዎችን በተማሩበት ሙያ መስክ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የተቀመጠ የፖሊሲ አቅጣጫ ነበር፡፡
ከመደበኛ የቀለም ትምህርት ጎን ለጎንም፣ የተለያዩ የወታደራዊ ጥበብ ትምህርቶች፣ የቴሌ ኮሚኒኬሽን፣ የእደ ጥበብ የመሳሰሉ የሙያ ትምህርት ቤቶችም መስፋፋታቸውን ዶ/ር አግደው አስረድተዋል፡፡
በእነዚህ ፖሊሲዎችና መርሆዎች እስከ 1966 አብዮት፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ በሁሉም ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ቁጥር 4.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በየደረጃው 340 ሺህ መምህራን ነበሩ፡፡
በአንድ ወቅት የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ያየህራድ ቅጣው በበኩላቸው፤ ጃንሆይ ለከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት በተለይ ለዩኒቨርሲቲ መስፋፋት ያደረጉትን አስተዋፅኦ በዳሰሱበት ፅሁፋቸው፤ “ንጉሡ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት አባት ናቸው” ብለዋል፡፡
ንጉሡ፤ “ሀብቴም፣ ጉልበቴም፣ ዕውቀቴም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተማር ይውላል” የሚል አባባል እንደነበራቸው ዶ/ር ያየህራድ ይጠቅሳሉ። የትምህርት ስርአቱን አተገባበርም እስከ ስልጣናቸው ፍፃሜ በፅኑ ይከታተሉ እንደነበር ምሁሩ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ህዝብ ወኪሎች፤ “ህዝቡ ለእርስዎ ሃውልት ለማሰራት ገንዘብ አሰባስቧል፣ እንድናሰራልዎ ይፍቀዱልን” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ንጉሡ፤ “አንድ ህዝብ የማይጠፋው መታሰቢያው፣ የሚተውለት ቅርስ የአዕምሮ ህንፃው ነው” በሚል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው፣ “ሃውልት ከምታሰሩልኝ ዩኒቨርሲቲ ብታሰሩ ይሻለኛል” በሚል ገነተ ልዑል ግቢ ውስጥ የትምህርት መስጫ ህንፃዎች አሰርተው፣ ዩኒቨርሲቲውን “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚል ተመርቆ፣ በ1954 አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ስራ ሲጀምር የትምህርት ስርአቱ ሀገሪቱ ከምትፈልገው የሰው ኃይል ጋር እንዲተሳሰር፣ የነፃ አስተሳሰቦች ማራመጃ እንዲሆን፣ በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን መምህራን በብዛት እንዲመረቁ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫም ንጉሡ አስቀምጠው ነበር፡፡ በወቅቱ የአካዳሚክ ነፃነቱም ምንም ገደብ የሌለበት፣ ነፃ አስተሳሰቦች የሚራመዱበት እንደነበር ተገልጿል፡፡ የተለያዩ አዳዲስ ምርምሮችም ይከናወኑበት ነበር - ዩኒቨርሲቲው፡፡  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአስተሳሰብ ነፃነቶች የመኖራቸው የመጨረሻው ማንፀባረቂያ ሆኖ የታየውም በተማሪዎች የአመፅ እንቅስቃሴ መሆኑን ምሁራኑ ይጠቅሳሉ፡፡ የንጉሡ የስልጣን ፍፃሜም እንደ አባት ተንከባክበው ባሳደጓቸው ተማሪዎቻቸው ሆኗል፡፡
ጃንሆይ ለስነ - ጥበብ
አፄ ኃይለ ሥላሴ ለስነ ጥበባት ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው በፅሁፋቸው የዳሰሱት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ታሪክ ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው ናቸው፡፡ ንጉሡ ለስነ ጥበባት ያላቸውን ፍቅር ማንፀባረቅ የጀመሩት ገና በአልጋ ወራሽነት የስልጣን ዘመናቸው መሆኑን አቶ አበባው ያስረዳሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ነገስታት መታሰቢያ ሰሩ ቢባል ቤተ ክርስቲያን ከማሳነፅ የዘለለ ቅርስ አያኖሩም ነበር” የሚሉት አቶ አበባው፤ የመታሰቢያ ሀውልቶችን ማስቀረፅ የጀመሩት ጃንሆይ ናቸው ይላሉ፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ዛሬም ድረስ ቆመው የሚታዩትና ለከተማዋ ግርማ የሰጧት የድል ሀውልት፣ የአፄ ምኒልክ ሃውልት፣ የሞአ አንበሳ ሀውልት፣ የሰማዕታት ሃውልት የተሰሩበት ከንጉሡ የስነ ጥበብ አፍቃሬነት የተነሣ መሆኑን አቶ አበባው ያወሳሉ፡፡ ንጉሡ በሀውልቶቹ ግንባታ ላይ የማማከሩንም ሆነ ዲዛይኖችን የመምረጥ ስራ ያከናውኑም ነበር፡፡ በተለይ የየካቲት 12 መታሰቢያ ሀውልት (6 ኪሎ የሚገኘውን) ዲዛይን ከሶስት አማራጮች አሁን የሚታየውን የመረጡት ንጉሡ ናቸው ይላሉ፤ አቶ አበባው፡፡ በሀውልቱ ላይ የሚገኙትን የነሐስ ማስታወሻ ቅርፆችም የተቀመጡት በንጉሡ ምርጫና ክትትል ነበር፡፡
“የሀገሪቱ ታላላቅ ምልክቶች የሆኑ ነገሮች በሙሉ በንጉሡ ዘመን የተሰሩ ናቸው” የሚሉት አቶ አበባው፤ የብሄራዊ ቲያትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ የመሳሰሉትን እየተከታተሉ ያስነገቡት ንጉሡ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ጃንሆይ ለስዕል ጥበብም የተለየ አትኩሮትና ፍቅር ነበራቸው፡፡ ይህን ምናልባት ከልጅነት መምህራቸው ጃንሩሶ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ አውሮፓን መጎብኘታቸው ንቃተ ህሊናቸውን ሳያዳብረው እንዳልቀረ አቶ አበባው ያስረዳሉ፡፡
ንጉሡ የተለያዩ የስዕል ኤግዚቢሽኖች እንዲከፈቱ በማድረግ ይጎበኙ ነበር፡፡ በ1946 ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጁትን የስዕል ኤግዚቢሽን ጎብኝተው ተደስተው “በሰራችሁት ስራ እጅግ ደስ ብሎናል … ትምህርት ቤትን የከፈትነውና እንድታማሩ ያደረግነው ይህን በመሳሰለው ጥበብ እንድትሰለጥኑ ሲሆን እናንተም ይህን አከናውናችሁ ስታሳዩ እጅግ ደስ ያሰኛል” ማለታቸውን አቶ አበባው ይጠቅሳሉ፡፡
የሀገሪቱ የስዕል ጥበብም ወደ አውሮፓ ያልሄደ፣ የሀገር ውስጡን እንዳይለው ለተማሪዎች ምክር ይሰጡ ነበር፡፡ የሀገሪ ተጠቃሽ ሰዓሊያን የመጡትም በዚሁ የንጉሡ የስነ ጥበብ ማበረታቻ ነው፡፡ ከነዚህም ተጠቃሾቹ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ በላቸው ይመር፣ እመአዕላፍ ህሩይ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ ማመጫ፣ ይገዙ ብስራትን የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ጃንሆይ የስነ ጥበብ ፍቅራቸውን የገለፁበት የመጨረሻው መንገዳቸው 66ኛ የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት በ1950 ሐምሌ 16 ቀን አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የተጠቃለለውን “የአዲስ አበባ ስነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤትን መርቀው ከፍተዋል፡፡
አንድ ንጉሠ ነገሥት ለስነ ጥበብ ወደፊት መራመድ ራዕይ አስቀምጦ፣ መሰረቱን ከማስቀመጥ ውጪ ሊያደርገው የሚችለው የለም የሚሉት አቶ አበባው፤ በየዓመቱ በዚህ የስነ ጥበብ ት/ቤት ሐምሌ 16 ከሰዓት በኋላ ልደታቸውን በማስመልከት የስዕል ኤግዚቢሽን ይመለከቱ እንደነበር ያወሳሉ። በኤግዚቢሽኑ ላይም ስዕሎችን ይገዙ እንደነበርና ይህ ልማድም በሌሎቹ መሳፍንቶች እንዲሰርፅ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ ጃንሆይ ለስነ ጥበብ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በእንዲህ መልኩ ያወሱትት አቶ አበባው፤ “በአሁን ዘመን የፖለቲካ አመራሩ ከስነ ጥበብ ተፋቷል” ሲሉ አሁን ያለውን ሁኔታ ገልፀውታል፡፡
“የንጉሡን ክብር
ለመመለስ …”
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተዘጋጀው የግርማዊነታቸው 125ኛ የልደት በዓል ላይ የተገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወደልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ንጉሡ ለሀገር ያበረከቱት ውለታ እንዲህ በቀላሉ ሊዘነጋ እንደማይገባና የአፍሪካ መሪዎች በተለይም በወቅቱ የጋና ፕሬዚዳንት አሳሳቢነት ለግርማዊነታቸው ሃውልት ለማቆም መወሰናቸው ቢዘገይም መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሃውልቱም መቆም ያለበት አሁን የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የሚገኝበት ቅፅር ግቢ ሳይሆን ግርማዊነታቸው መጀመሪያ ባሰሩት “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት” መሰብሰቢያ አዳራሽ ፊት ለፊት ሊሆን እንደሚገባ ጥያቄ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
ንጉሡ በብዙ ድካም ያቋቋሙት የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ በእሳቸው ስም ይጠሩ የነበሩ ተቋማትም ወደ ቀድሞ ስማቸው እንዲመለሱ መንግስት መጠየቁ፣ በየጥጋጥጉና በየመጋዘኖች ተከማችተው የሚገኙ የእሳቸው ሃውልቶችና ቅርፃ ቅርፆች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ጥያቄ መቅረቡን በተለይ ለአዲስ አድማስ ያስረዱት ደግሞ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማህበር፣ የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ ናቸው፡፡
በአሁን ወቅት በንጉሡ ስም የሚደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ፣ ምስሎቻቸውም በህገ ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ የጠቀሱት ሊቀ ካህናት አባይነህ፤ ማህበሩ እነዚህን ጉዳዮች መስመር ለማስያዝና የንጉሱን ክብር ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በ125ኛ የልደት በዓል መታሰቢያ ስነ ስርአቱ ላይ ራስ መንገሻ ስዩምን ጨምሮ የንጉሠ ነገስቱ የልጅ ልጆችና ሌሎች ልኡላን ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡          

Read 7674 times