Saturday, 07 April 2012 07:52

ሁለቱ ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት የማናቸው?

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ላለፉት ሀምሳ አመታት በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምነታቸው የምናውቃቸው የአለም ባንክና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የተቋቋሙት በሁለተኛው የአለም ጦርነት የተነሳ የፈራረሠውን፣ የአውሮፓንና የአለምን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ታላላቅ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ባላቸው ከፍተኛ የማበደር አቅምና ብድራቸውን በመስጠትና በመቀበሉ ሂደት በተበዳሪው ሀገር የኢኮኖሚ ፖሊሲና ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ ላይ በሚጭኑት ቅድመ ሁኔታ የሚታወቁ በአለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ በሚያሳድሩት ከፍተኛ ተጽዕኖም ገናና ስም አላቸው፡፡

የብሪትን ውድ ተቋማት እየተባሉ በቅጽል ስማቸው የሚጠሩት እነዚህ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ የአለማችንን ታላላቅ በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገራትን ጥቅምና ፍላጐት ብቻ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ሲሆን በተበዳሪ ሀገራት በተለይ ደግሞ እንደ አፍሪካ ባሉ ድሀ ሀገራት ላይ ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ቅድመ ሁኔታና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ በማስገደድ ከገቡበት የኢኮኖሚ ችግር ከማላቀቅ ይልቅ ጭራሹኑ በቀላሉ ከማይወጡበት አዘቅት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በበርካቶች ዘንድ ክፉኛ ሲብጠለጠሉና ሲወገዙ የኖሩ ተቋማት ናቸው፡፡

ልማታዊ መንግስት ነን የሚሉ አንዳንድ የአፍሪካና የእስያ ሀገራት መንግስታት ደግሞ ምንም እንኳ የጠየቁትን ብድር እንዲሠጣቸው ደጅ መጥናታቸውንና በተግባር ላይ እንዲያውሉ የተጠየቁትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ከመውሰድ ወደ ሁዋላ ባይሉም፤ የርዕዮተ አለም ልዩነት መስመር አበጅተው፣ እነዚህን የገንዘብ ተቋማት በኒዮሊበራል የርዕዮተ አለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስፈፃሚነት አምርረው ይወቅሷቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከመውቀስም አልፈው ቀደም ባሉት አመታት በአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ላይ ያቀርቡት እንደነበረው፣ ሀገራቸው ለገባችበት የተለያየ የኢኮኖሚ ቀውሶች ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂ በማድረግ ይከስሷቸዋል፡፡

ሀገራቱ የፈለገውን አይነት ክስና እርግማን እየደረደሩ ቢያወግዟቸው፣ የአለም ባንክም ሆነ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቁብ የሚሰጣቸው ዓይነት አይደሉም፡፡ ለምን መሠላችሁ? ያላቸው ሀይል ሀገራቱ በተናጠልም ሆነ በመተባበር ካላቸው ሀይል ስለሚበልጥና ሀገራቱ አድርጉ ያሏቸውን ሁሉ እየተነጫነጩም ቢሆን ከማድረግ ወደኋላ ስለማይሉ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ የአለም ባንክ እንደ አሜሪካ ድርጅትነት፣ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ደግሞ እንደ የአውሮፓ ድርጅትነት ይታወቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእርግጥም እውነት ነው፡፡ ሀገራቱ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድርሻ መሠረት በዋናነት አመራሩንና አሠራሩን በበላይነት ይቆጣጠራሉ፡፡ በዚህም መሠረት አሜሪካ በአለም ባንክ ውስጥ ባላት ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ (Controlling shares) አማካኝነት፣ የባንኩን የስራ አመራር ቦርድ በበላይነት ትቆጣጠራለች፤ ትመራለች፡፡ የባንኩን ፕሬዚዳንትም መርጣ በማቅረብም ታሾማለች፡፡ በዚህ የተነሳ የአለም ባንክ እንደ አሜሪካ የባንክ ተቋም ተደርጐ በብዙዎች ዘንድ ቢቆጠር የሚገርም ሊሆን አይችልም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ውስጥ የአውሮፓ ሀገራት ባላቸው ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ መሠረት፣ የተቋሙን ቦርድ ይቆጣጠራሉ ይመራሉ፡፡ የተቋሙን ፕሬዚዳንት ከአውሮፓ ውስጥ ብቻ በመምረጥ ያሾማሉ፡፡ ስለዚህ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ወይም አይ ኤም ኤፍ እንደ አውሮፓ የገንዘብ ተቋም ተደርጐ ይታሰባል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በአሜሪካ አርፈውበት በነበረው ሆቴል ውስጥ ሠራተኛ የሆነችውን ሴት አስገድደው ደፍረዋል ተብለው በመከሠሳቸው የተነሳ በተፈጠረው የቅሌት አቧራ፣ ከአይ ኤም ኤፍ ፕሬዚዳንትነታቸው የለቀቁትን ፈረንሳዊውን ለትራውስ ካንን በመተካት፣ ሌላዋ ፈረንሳዊትና የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ክርስቲን ላጋርድ በፕሬዚዳንትነት እየመሩት ይገኛሉ፡፡

የአለም ባንክን ደግሞ ከባንኩ ህግና ደንብ ውጭ የሴት ጓደኛቸውን በባንኩ ውስጥ በሠራተኝነት እንድትቀጠር በማድረግ በፈፀሙት የሙስና ወንጀል በቅሌት የለቀቁትን ይሁዲውን ፕሬዚዳንት ወልፎ ዊትዝን በመተካት፣ እስካሁን ድረስ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩት የነበሩት ሌላው አሜሪካዊ ሮበርት ዘሊክ ናቸው፡፡ የእኒህ ሠው የፕሬዚዳንትነት ዘመን በመጠናቀቁ፣ ተተኪ ፕሬዚዳንት የሚሆን ሁነኛ ሠው በማፈላለግ አሜሪካ ያለፉትን ወራቶች ከወዲያ ወዲህ ደፋ ቀና ስትል ከርማ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ሳምንት ግን ተፈላጊውን ሠው እንዳገኘች ይፋ አድርጋለች፡፡

በዚህም መሠረት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ጂም ዮንግ ኪም የተባሉትን ባለሙያ አስራ ሁለተኛው የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በእጩነት አቅርባለች፡፡ በእጩነት የቀረቡት ጂም ዮንግ ኪም በኮሪያ የተወለዱ ኮርያዊ አሜሪካዊ ሲሆኑ የዳርትሙዝ ኮሌጅ ፕሬዚዳንትና በአለም የጤና ድርጅት የኤች አይ ቪ ኤድስ መምሪያ ሀላፊ የነበሩ ሠው ናቸው፡፡

እንግዲህ ከዚህ በላይ ያተትነው ስለ አለም ባንክና ስለ አይ ኤም ኤፍ ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲኖረን ለመንደርደሪያ ያህል የቀረበ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን ግን ከዚህ የሚከተሉት ነገሮች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የአለም ባንክን ከመሩት አስራ አንድ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ ምን ያህሉ ምን አይነት ትምህርት የተማሩ ነበሩ? ምን ያህሉስ ሴቶች ነበሩ? ከየትኛው ሀገር ወይም ከተማስ ተወለዱ? ዘርና ቀለማቸውስ? ስለ አለም ባንክ ያለንን ጠቅላላ እውቀት የበለጠ ለማጠናከር ጽሑፉ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡

ምን ያህሉ ሴቶች ናቸው በሚለው እንጀምር፡፡ አዲሱን ፕሬዚዳንት ለመሠየም ፕሬዚዳንት ኦባማ የፔፕሲ ኮላ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት የህንድ ተወላጇ ኢንድራ ኖይ፣ የብራውን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ሩት ሲመንስ፣ ከዲፕሎማቷ ሱዛን ራይስና የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ከሆኑት ከላውራ ዲአንድርያ ታይሰን መሀል አንዳቸውን በመምረጥ በባንኩ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ያሾማሉ ተብሎ በእጅጉ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም የእሳቸው ቀልብ ግን በጂም ዮንግ ኪም ላይ አርፏል፡፡ የአለም ባንክ ቦርድ ተቀብሎ ሹመታቸውን ካፀደቀውም ኪም አስራ ሁለተኛው ወንድ የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአለም ባንክ የፕሬዚዳንትነት ውቃቢ ዘንድሮም ሴቶችን ለመታረቅ አሻፈረኝ ብሏል፡፡

የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት በአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሚመረጥ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው እንደሆነ ቢያውቁም፣ ታዳጊ ሀገራት የራሳቸውን እጩ ከማቅረብና እንዲመረጥላቸውም አሜሪካንን ከመወትወት ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ዘንድሮም የአፍሪካ ሀገራት የናይጀሪያዋን የገንዘብ ሚኒስትርና የቀድሞ የአለም ባንክ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትን ንጐዚ ኦኮንጆ ኢዌላን በእጩነት ሲገፉ፤ ብራዚል በበኩሏ ኮሎምቢያዊውን ኢኮኖሚስት ሆዜ አንቶኒዮ ኦካምፓን በእጩነት እንዲቀርቡላቸው ደጅ በመጥናት ላይ ይገኛሉ፡፡ የባንኩ የኤክስኩዩቲቭ ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ በቀጣዩ ወር ተሠብስቦ ተወዳዳሪ እጩዎችን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተመራጩ የተበላ እቁብ ቢሆንም ቅሉ፡፡

ከአለም ባንክ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ ከአሜሪካ ውጪ የተወለደ ቁጠሩ ብንባል የምናገኘው በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ የተወለዱትን ጀምስ ወልፈንሠንን ብቻ ነው፡፡ ጀምስ ወልፈንሠን የኢንቨስትመንት ባንክ ባለሙያ ሲሆኑ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ያገኙት እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም ነው፡፡ ጀምስ ወልፈንሠን ከ1995 እስከ 2005 ዓ.ም ሁለት ጊዜ በመመረጥ ለአስር አመታት የአለም ባንክን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡

ደቡብ ኮርያ ሴኡል ከተማ ውስጥ በ1959 ዓ.ም የተወለዱት አዲሱ እጩ ኪም ከተመረጡ ሁለተኛውን ከአሜሪካ ውጭ የተወለዱ የአለም ባንክ ፕሬዚዳንትን እናገኛለን ማለት ነው፡፡

ለመሆኑ የአለም ባንክን በፕሬዚዳንትነት ከመሩት ውስጥ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ስንት ይሆናሉ? ሁለት ብቻ ነበሩ - ሮበርት ማክናማራ እና ፖል ወልፎዊትዝ!

ሮበርት ማክናማራ በፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ለመከላከያ ሚኒስትርነት ከመመረጣቸው በፊት የፎርድ ኩባንያ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በሁዋላ፣ የአሜሪካ - ቪየትናም ዘመቻን በዋናነት መርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ ጦር በቪየትናም ጦርነት አይሆኑ ሆኖ በመሸነፉ በ1968 ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡

ወዲያው ግን ፕሬዚዳንት ኬነዲን ተክተው ፕሬዚዳንት የሆኑት ለንደን ጆንሠን የአለም ባንክን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መረጧቸውና እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ ለመምራት ቻሉ፡፡

ፖል ወልፎዊትዝ ደግሞ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካ የመከላከያና የደህንነት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የአሜሪካ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዚህ ስልጣናቸው እያሉ የኢራቅን ወሪራ በዋናነት እንዳቀነባበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ወልፎዊትዝ የአለም ባንክን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ለሁለት አመታት ብቻ ነው፡፡ ስልጣናቸውን የለቀቁት በስነ ምግባር ቅሌት ነው፡፡

ሦስት ፕሬዚዳንቶች ደግሞ ከአንድ ጊዜ በላይ በመመረጥ ረዘም ላለ ጊዜ ባንኩን በበላይነት መርተዋል፡፡ እነሱም ዩጂን ብላክ ከ1949 እስከ 1963 ዓ.ም፣ ሮበርት ማክና ማራ ከ1968 እስከ 1981 ዓ.ም፣ ጀምስ ወልፈንሠን ደግሞ ከ1995 እስከ 2005 ድረስ ናቸው፡፡ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሮበርት ዞሊክ በፕሬዚዳንት ቡሽ የተሾሙት በ2007 ዓ.ም ሲሆን የስልጣን ዘመናቸውም በጁን ወር 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ከመሩት አስራ አንድ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ ደግሞ ሠባቱ የባንክ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ዩጂን ሜየርና ዩጂን ብላክ የቸዝ ባንክ ባለስልጣኖች ነበሩ፡፡ ጆርጅ ውድስ የፈርስት ቦስተን ባንክ፣ ልዊስ ፕሪስተን የጄፒ ሞርጋን ባንክ፣ አልደን ክላውሰን የአሜሪካ ባንክ፣ ጀምስ ወልፈንሠን የሰሎሞን ወንድማማቾች ባንክ እንዲሁም የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሮበርት ዞሊክ የጐልድማን ሳሽ ባንክ ባለስልጣኖች ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሆነው ያገለገሉ የባንኩ ፕሬዚዳንት ባር በር ኮናብል ብቻ ነበሩ፡፡ ባርባር ኮናብል በ1986 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ሬገን ለባንኩ ፕሬዚዳንትነት ከመሾማቸው በፊት ለሀያ አመታት የአሜሪካ ኮንግረስ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡

በመጨረሻ አንድ አሪፍ ጥያቄ እናቅርብና ጉዳያችንን እንደምድም፡፡ የአለም ባንክ ከተመሠረተበት ከዛሬ ስልሳ ስድስት አመት ጀምሮ በታሪኩ ጥቁር ፕሬዚዳንት ኖሮት ያውቃልን? የዚህ ጥያቄ መልስ አጭርና ቀላል ነው፡፡ ጥቁሩ ፕሬዚዳንት ኖሮት አያውቅም!

 

 

 

Read 4064 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 07:57