Sunday, 30 July 2017 00:00

የሕዳሴው ንጉስ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

 የህዳሴ ጥንስስ
የሮማ ስርወ መንግሥት ውድቀትን ተከትሎ የመጣው ዘመን፣ በምዕራብዊያን ዘንድ በበጎ የሚታወስ አይደለም። በግሪክ ፍልስፍና ተፈንጥቆ የነበረው ጭላንጭል የንቃት ዓለም፣ በሮማ ካቶሊካዊ ቀኖና እስከ እነካቴው ደብዛው ጠፋ፡፡ በዚህም ምክንያት ድፍን አውሮፓዊያን ለብዙ መቶ ዘመናት ፍጹም ጽልመታዊ ድባብ ውስጥ እየዳከሩ በደመነፍስ አዘገሙ፡፡ የዚህ የጽልመት ዘመን ሥርዓትና ወግ መንጋዊ ነበር፡፡
በንጉስ ወይም በመለኮታዊ ኃይል ፊት ቅቡል ያልሆነ አመለካከት ውግዝ ነው፡፡ ግለሰባዊ መውተርተር፤ በድንጋይ መወገርን፣ በቁም በተማሰ ጉድጓድ ውስጥ መቀበርን፣ ከአንገት ላይ ወፍጮ ታስሮ ወደ ባሕር መጣልን ያስከትላል፡፡ በአጠቃላይ አውሮፓዊያኑ በጨለማው ዘመን የነበራቸው ቅኝት ደቦዋዊ (collective)፣ከአምክንዮ የተራቆተ ግትር ዕምነት (thestic) እና በዕጣፋንታ የተቀየደ (static)  ስነልቦና በብርቱ ተጣብቷቸው ነበር፡፡ ይህ እንደ ንፍፊት ሰፍቶ የያዛቸው፣ መንጋዊ አስተሳሰብ ያከትም ዘንድ ዘመነ ህዳሴ ለዓይነ ሥጋ መብቃት ነበረበት፡፡
በመካከለኛው ክ/ዘመን መባቻ አካባቢ መናኘት የጀመረው ዘመነ ሕዳሴ፤ መላ አውሮፓዊያንን እንደ መርግ ተጭኖ የኖረውን ሸክም ለማቅለል ብሩህ ተስፋን ሰንቆ በታሪክ ፊት ተከሰተ፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስ፤ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በሚለው መጽሓፋቸው፤ የአውሮፓዊያኑን ሕዳሴ በዚህ መልኩ ይገልጹታል፡-
“መንፈስ ለብዙ ዘመናት ደስ ብሎት ሞቆት ኖረ። ግን ከጊዜ ብዛት ያለበት ቤት ጥበቱ ተሰማው። ሌላ ፈለገ፡፡ ወደ ኋላ ሔዶ ሲፈልግ ሰፋፊ ቤቶች አገኘ። እኒህም የጽርዕ የፍልስፍና ሲሰተሞች ናቸው፡፡ እንደገና ወደ ሕይወት ለመምጣት ለመውሰድ ተጣጣረ፤ Renaissance  የሚባለው የታሪክ ጣቢያ ተፈጠረ። ዳግም ልደት ማለት ነው። ያው አልተወለደም፡፡ መሰሉ ነው፡፡ እነ ጋሊሌኦ፣ ጆርዳኖ፣ብሩኖ፣ ዴካርት ሌሎችም በቀድሞው የጽርዕ ፍልስፍና ሰክረው፣ ያንኑ እንደገና ለማስገኘት የተጣጣሩ፣ ያዲሱ ዘመን ፈላስፎች በዚያ ፈንታ አዲስ ፈጠሩ፡፡ ያለፈ ነገር አይመለስም፡፡ ታሪክ አይደገምም፡፡ የጽርዐውያንን ፍጥረት ለመምሰል በመጣጣር፣ ምዕራባውያን አዲስ በዚያ ላይ የተመሠረተ ሥልጣኔ አቁመው ወደፊት ቀጠሉ። ይህ ሥልጣኔ እንደ ትልቅ ዋርካ ተስፋፍቶ፣ ጥላው የመላ ዓለም መጠለያ ሆኗአል፡፡”
አውሮፓዊያን ለዘመናት ከወደቁበት ጥልቅ ድንዛዜ በድንገት ነቁ፡፡ ዙሪያ ገባቸውን ገርምመው፣ የተዳፈነ ማንነታቸውን በርብረው፣ ትንሳኤያቸውን በይፋ አወጁ። በዘመነ ሕዳሴ ላይ በፊት አውራሪነት ብቅ ማለት የቻለው ጠቢብ ፍራንሲስ ባኮን፤ ሳይንሳዊ  መንገድን በማስተዋወቅ፣  ፅልመት የሚገፍ ወጋገን ፈነጠቀ፡፡ በዚህም መለኮታዊ ኃይል ወይም ንጉስ ብቻ የጥበብ ምንጭ ሆነው የኖሩበትን የዕውቀት ንግስና ዘመን መነቀነቅ ጀመረ። በፍልስፍናውም ዓለም ዴካርት፤ በመጠርጠር እርግጠኛ የሚኮኑበትን (Cogito ergo sum) ቀመርን ዕውን በማድረግ፣ የጋርዮሽ ማኅበረሰባዊ አስተሳሰብን የሚንድ፣ የጥርጣሬ ችቦን ለኮሰ፡፡ ከፍራንሲስ ባኮን እና ዴካርት ለጥቀው የመጡት ጠቢባን፣ ሲወርድ  ሲዋረድ የመጣውን  ቀያጅ ባህልን በማፈራርስ፣ ግለሰባዊ  የአስተሳሰብ ነፃነትን በምዕራቡ ዓለም በማንገስ ፋና ወጊ መሆን ችለዋል። በዚህም ምክንያት መላ አውሮፓዊያን ተፈጥሯዊ ስልትን በጠበቀና እንደ እምቡጥ ጽጌሬዳ ከውስጥ ወደ ውጪ በሚፈነዳ ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ማዕበል ለመጥለቅለቅ በቅተዋል፡፡
በአጠቃላይ የምዕራባዊያን ዘመነ ህዳሴ፣ ሥጋ ለብሶ በገሃድ እንዲገለጥ፣ ጥልቅ አሳቢዎቻቸው ለዘመናት በብርቱ ማማጥ ነበረባቸው፡፡ እነዚህ ታላላቅ ፈላስፎች ናቸው፣ ብዙኃኑን ከሰጠመበት የጽልመት መቀመቅ ነፃ አውጥተው፣ እንደ ሙሴ በትር እየመሩ፣ ከተድላና ፍስሃ ዓለም ጋር ያወዳጁት።
እኛ እና ህዳሴ
የሀገራችን የዘመናዊ ሥልጣኔ ታሪክ እንደ አውሮፓዊያን የሚያመረቃ አይደለም፡፡ ታሪክን የኋሊት ተጉዘን በመረመርን ቁጥር የሚያጋጥሙን ኩኽነቶች፣ ለአእምሮ ሰላም በማይሰጡ ቁጭቶች የተሞሉ ናቸው። ልክ እንደ አውሮፓዊያን ጥልቅ አሳቢዎች፣ሰፊውን ማኅብረሰብ በለውጥ ማዕበል ያናወጡ፣ የህዳሴ መሪ ተዋናዮች በሀገራችን የታሪክ ኡደት ላይ መከሰት አልቻሉም፡፡ የማኅበረሰባችን ስነልቦናዊ ቅኝት ደቦዋዊ (collective)፣ ከአምክንዮ የተራቆተ፣ የገነገነ ዕምነት (thestic) እና ለለውጥ ደፋ ቀና የማይል (static) ማንነትን የተላበሰ እንደነበረ እሙን ነው፡፡ ይህ ግን ሊደንቀን አይገባም። ምክንያቱም አውሮፓዊያኑም በተመሳሳይ የታሪክ ዝግመተ ለውጥ ሐዲድ ላይ ነጉደዋልና፡፡ ትልቁ ልዩነት የእነርሱ ታሪክ ሆኖ ሲቀር፣ የእኛ ግን እንዳስቀመጡት መገኘቱ ነው። በእኛ ዘመነ ህዳሴ ታሪክ፣ አንድ ለእናቱ ሆነው ብቅ ያሉት ታላቁ ባለራዕይ አጼ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ ታላቁ ንጉስ አለዘመናቸው ነበር የተፈጠሩት፡፡ እናት ሀገራቸውን ዳግም ወደ ታላቅነት ለመመለስ በአጭር የሥልጣን ዕድሜያቸው ሌት ተቀን ተዋከቡላት። መዋከባቸውን ከፍሬ የሚጥፍ ነባራዊ ሁኔታ ግን  በወቅቱ  አልነበረም፡፡ ለመሆኑ አጼ ቴዎድሮስ፤ የሀገራቸውን የህዳሴ ወጋገን ለመፈንጠቅ የሄዱበት ርቀት እስከ ምን ድረስ ነበር?
በዘመነ መሣፍንት ውልቅልቋ የወጣችውን ጥንታዊት ሀገር፣ ዳግም የማጽናቱን ኃላፊነት፣ ታሪክ የጣለው በመይሳው ካሳ ትከሻ ላይ ነበር፡፡ ንጉሱ በዘመኑ የገጠማቸውን መሰናክል በድል ተወጥተው፣ ማዕከላዊውን መንግሥት የበለጠ ለማጠንከር ላይ ታች ማለትን አበዙ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ የማእከላዊ መንግሥትን ለማቆም ባደረጉት ተጋድሎ ላይ ብቻ የተወሰነ ትንታኔን ማቅረብ አብዛኛው የሀገራችን ጸሓፍት እንደሚመርጡ የታወቀ ነው፡፡ ይህ አተያይ ግን ታላቁን የዘመናዊ ሥልጣኔ መሐንዲስ ገድል በእጅጉ የሚያንኳስስ ይሆናል። በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ከአጼ ቴዎድሮስ ቀደም ባሉት ሺህ ዘመናት በየጊዜው ጉልበትና ኃይሉን የተላበሱ ጠንካራ ነገስታት፣ ማእከላዊ መንግሥትን በቁጥጥር ሥራቸው ሲያደርጉ መመልከት ብርቅ አልነበረም። በመሆኑም የመይሳው ካሳ ተግባር ቀድመው ከነገሱት ነገሥታት በልዩነት ሊታይ አይገባም። የአከሱም ዘመነ መንግሥት፣ ዛጎዌና ቀጥለው የመጡት ሰለሞናዊ ዘመነ መንግሥታትን አብነት ብናደርግ እንኳን ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥትን በማንበሩ ረገድ የተዋጣላቸው እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ምንአልባትም አጼ ቴዎድሮስ፣ ሀገራቸውን ለማዘመን ካደረጉት ተጋድሎ ይልቅ የወንድ ቁንጮነታቸው ከፍ ብሎ፣ በማኅበረሰባችን ዘንድ የሚወሳው፣ ለጀግንነት ወይም ለኃይለኝነት ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጠው ጥንታዊ ባህላችን ተጽዕኖ ምክንያት እንደሆነ የታሪክ ሊቃውንት ያብራራሉ፡፡
መይሳው ካሳ ከጀግንነታቸው ባልተናነሰ ዝንተዓለም የሚዘከሩበት፣ ትውልድ የሚሻገር አብርክቶት አላቸው፡፡ አውሮፓዊያኑ የአቴናን ሥልጣኔ እንደ ነዳጅ ተጠቅመው፣ ወደ ላይ መመንደግ የጀመሩበትን ስልት በመታዘብ፣ ሀገራችውን ሁለንተናዊ ከሆነ ኋላቀርነት ለማላቀቅ ደፋ ቀና ማለታቸውን ስለ እርሳቸው የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ፕሮፌስር መስፍን ወልደማሪያም፤ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ስለ አጼ ቴዎድሮስ ሰብዕና ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
“የአጼ ቴዎድሮስ ገናናነት የተመሠረተው ባከናወኑት ወይም በፈጸሙት ነገር ላይ ሳይሆን በነበሯዋቸው ጥሩ ጥሩ ዓላማዎች ላይ ነው፤  ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሯዋቸው ለማለት ይቻላል፤ አንደኛ የአምባገነኖቹን መሳፍንትና መኳንንት ኃይል ለመሰባበርና የአገሪቱን አስተዳደር በማእከላዊ አመራር ላይ ለመመሥረት፤ ሁለተኛ የኢትዮጵያን አንድነት ወደ ጥንት ይዞታው ለመመለስና በማያወላውል መሠረት ላይ ለመገንባት፣ ሦስተኛው  የኢትዮጵያ ሕዝብን እድገትና ልማት ዘመናዊ ሥልጣኔን ለማስገባት ነበር፤”
የአጼ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ሕልም ለጥቀው ከመጡት ነገስታት ጋር ሲነጻጸር ትልቅ ሥፍራ ላይ የሚያስቀምጠው ሥልጣኔን ሀገር በቀል ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ነው፡፡ የንጉሱ የዘመናዊነት አተያይ ከውስጥ ወደ ወጪ የተቀሰተ ነበር፡፡ ሀገሪቱ ያፈራቻቸውን የምርምርና የዕውቀት ድርሳናትን ከየተሸሸጉበት አድባራት በማስወጣት ትልቁን ቤተ - መጽሐፍት መቅደላ ላይ አቋቋሙ፡፡ የዚህም ምክንያት የሀገራቸው ሕዝብ ዘንግቶት የኖረውን ጥንታዊ ፍልስፍና፣ ምርምርና ዕውቀት ከራሱ ማሕጸን በወጡ ጥልቅ አሳቢዎች ለማነጽ ነበር፡፡ ይህ መታነጽ ውሎ አድሮ ለዘመናዊ ሥልጣኔ የተዘጋጀ ሥልጡን ማኅበረሰብን ይወልዳል፡፡ በዚህም የተነሳ ዘመናዊ ሥልጣኔ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ፣ ከሀገር በቀል በተገኙ ልምዶች፣ ዕውቀቶች እና ተሞክሮዎች መፋፋም ይጀምራል ማለት ነው፡፡
ንጉሱ ሥርነቀል የባህል አብዮትን ዕውን ለማድረግ፣ የኢንዱስትሪ አብዮትን በአፍሪካ ሰማይ ላይ ጎህ የቀደዱ ብልህ መሪ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋቢ ምስክራችን ሰባስቶፖል መድፍ ይሆናል፡፡ የሰባስቶፖል መድፍን የማቆም ጥንስስ፣ የንጉሱን የዘመናዊነት ህልም በሽል ደረጃ ሲገላበጥ በጉልህ ያሳያል፡፡ ትልቁ ቁምነገር የሰባስቶፖል መድፍን በማነጽ ተግባር ላይ ተቀንብቦ የሚቀር አይደለም። የመድፉን ለፍሬ መብቃት ተከትሎ የሚፈጠረው ማኅበረሰባዊ መነቃቃት ቀላል አይሆንም ነበር። የንጉሱ የአብራክ ክፋይ ሰባስቶፖል መድፍ ግን ብዙም ሳያስመካቸው አንዴ አጓርቶ ከሸፈ፡፡ እዚህ ጋ ነው የሀገራችን የዘመናዊነት ጽንሰ የተቋረጠው። የአጼ ቴዎድሮስ የኢንዱስትሪ አብዮት መጨናገፍን ተከትሎ፣ ሀገሪቱ በምስቅልቅል ፖለቲካዊና ማኅበራዊ  አውድ ውስጥ መዋጀት ጀመረች፡፡
የኢንዱስትሪ አብዮቱ መክሸፍ ያስከተለውን ጦስ ለመመልከት አጼ ምኒሊክ ወደ ደቡብ  ያደረጉትን ዘመቻ ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ አብዮቱ ግቡን መትቶ ቢሆን ኖሮ፣ የዘመቻው ዓላማ ተጨማሪ ገባር መሬትን ለመጠቅለል በሚል ዕሳቤ ፈንታ፣  ልክ እንደ አውሮፓዊያኑ ሀገርን የማዋሀድ ዘመቻ፣ በኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት የተፈጠረውን የግብዓት እጥረት ለመቅረፍና ለኢንዱስትሪው መተንፈሻ ተጨማሪ ምህዳር ለማግኘት በሚል ዓላማ ይቀር ነበር። በዚህም የተነሳ ወደ ማእከላዊ መንግሥት የተጠቃለሉትን ሕዝቦች፣ የኢንዱስትሪው አብዮት በሚፈጥረው የባህል አብዮት ተጠቃሚ በማድረግ፣ የሁለንተናዊው ሥልጣኔ ተቋዳሽ መሆናቸው አይቀርም ነበር፡፡ የጀርመኑ ቢስማርክ፤ ሀገር በማወሀድ ዘመቻ ላይ ያካሄዳቸው አሰቃቂ ጦርነቶች፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበሩት ወደ ማእከላዊው መንግሥት የተጠቃለሉት ግዛቶች፣ የኢንዱስትሪው አብዮት በፈጠረው ሲሳይ፣ ከተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ጋር በፈጣን የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት መዋሀድ በመቻላቸው ነው፡፡ በቢስማርክ ዘመቻ የተፈጠሩት መጥፎ ታሪካዊ ኩኽነቶች፣ ለጀርመናዊያን ከተረት ተረት የበለጠ ሙቀት መፍጠር አይችሉም፡፡ በአንጻሩ የእኛ የሀገር የማዋሀድ ዘመቻ ላይ የተከሰቱት መጥፎ የታሪክ ክስተቶች ለሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ዘውጌ ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ አጀንዳ ሆነው ፍዳችንን እያሳዩን ይገኛሉ። የዚህ ሁሉ ጦስ ዞሮ ዞሮ የቴዎድሮስ ርዕይ መክሸፍ ነው፡፡ እውነተኛው የህዳሴያችንም ትልም ከመይሳው ጋር አፈር ለበሰ። ሩቅ አሳቢው ቅርብ አዳሪው፣ ጀግናው፣ የቋራው ካሳ፣ እናት ሀገሩን ሞቶ ሊያኖራት፣ እንዳይሆኑ ሆኖ አከተመ፡፡
የዘመናችን ህዳሴ  
የኢህአዴጉ ህዳሴ በግብር የአውሮፓዊያንንም ሆነ የአጼ ቴዎድሮስን ህልም አይመስልም። ህዳሴው የተዳበለው ምርጫ 97ን ተከትሎ፣ በሰፊው መቀንቀን ከጀመረው ልማታዊ መንግሥት ጽንሰ-ሐሳብ ጋር ነው፡፡ የኒዮ ሊብራል ጽንሰ-ሐሳብ በደሀ ሀገር ውስጥ ሊተገበር አይችልም፣ በመሆኑም በልማታዊ መንግሥት ትክክለኛው የዕድገት ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለመፍጠር መንገዱ አልጋ በአልጋ ይሆናል፤ ይላል - የልማታዊ የመንግሥት ትንታኔ። የኢህአዴግ ህዳሴ ሥር ነቀል ሀገራዊ ለውጥ በማምጣት ፋንታ ትልልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣መንገዶች እና ፋብሪካዎችን በመገንባት ላይ የተጠመደ ነው፡፡ የዜጎችን አእምሮ በማልማቱ ረገድ የሄደበት ርቀት እምብዛም ነው። ህዳሴው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ከሚጫወተው ሚና ይልቅ ሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት የሚያበረክተው ፖለቲካዊው ፋይዳ ይበዛል፡፡ ህዳሴው ለገዢው ፓርቲ  የሥልጣን ተቀናቃኞቹን እየጠራረገ፣ ማእከላዊነትን የበለጠ የሚያጠናክርበት ኹነኛ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከመሆን የዘለለ ሚና እንደሌለው ተቺዎች ያስረዳሉ።
እንደ ማጠቃለያ
አውሮፓዊያን ከወደቁበት ጥልቅ ድብታ ቀና እንዳሉ፣ አስደንጋጭ ኋላቀርነት አባነናቸው፡፡ እናም ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ታላቅነት ዘወር ብለው በመፈተሽ ፍልስፍናቸውን፣ስነልቦናቸውንና የኋላ ገናና ሥልጣኔያቸውን መርምረው፣ ከሚያስቀና የዕድገት ደረጃ ላይ ለመቆናጠጥ በቁ፡፡ ህዳሴያቸው የምር ህዳሴ ሆኖ በውስጥ ያዘለውን የሥልጣኔ ትሩፋት፣ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አስተጋባ፡፡ እኛ ግን ዘመናትን እንደ አሸለብን አዘገምን፡፡ የኋላ ማንታችንን፣ ሽንፈታችንንና ጥንካሬያችንን መሠረት ያላደረገ ህዳሴ፣ ከቃል ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው ለማወቅ ተንታኝ አያስፈልገውም፡፡ የቴዎድሮስ ርዕይ፣ አኑሮልን ያለፈው ትልቅ ቁምነገር ይህን ነው፡፡

Read 1160 times