Saturday, 29 July 2017 11:55

ታሪከኛው ታሪካችን (፪)

Written by  ቤተማርያም ተሾመ betishk@gmail.com
Rate this item
(5 votes)

  “-- እያንዳንዱ የታሪክ ክስተቱ በመለኮት አጥር የተተበተበ ህዝብ፣ እንደ ሃበሻ ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዴት? በሉ፡፡ የነገሰ ንጉስ ሁሉ በበቃና በነቃ እድሜ
ጠገብ አባት፤ ጢሙ መሬት አበስ፣ ሹሩባው ሰማይ ጠቀስ፣ ቅዱስ ራእይ የታየለት፣ ህልም የታለመለት፤ የህዝብ አመራር ጥበብ በጥራዝ መልክ ከደመና
የወረደለት፤ በየጦርነቱ መላዕክት ከፊት የመሩት፤ የእሳት ሰረገላ በደመና የከነፉለት አይነት ታሪኮቻችንን እስቲ ቆም ብለን እናስታውስ”--
                 
      ይህ ሁሉ የቀመር ጋጋታና ልፋት ደግሞ በተለይ ከታሪክ ድርና ማግ ለተበጀ እንደ ሃበሻ ላለ ማህበረሰብ ቅንጦት ሳይሆን የ”መሆን ወይም ያለመሆን” ጉዳይ ስለሆነ ነው ተባብለናል፡፡ ምክንያቱም ዛሬያችን እጅጉን አብዝቶ ትናንት ላይ በመንጠልጠሉና የሚፈታ በማይመስልና ባልተገባ፤ አንዳንዴም አስቂኝ በሆነ የ”ማን ነኝ?” “ከየት መጣሁ?” ፍለጋ አዙሪት ተተብትበን፤ ውጤቱ አብሮ ደምቆ መኖርን የሚያደበዝዝ፤ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየነዳን ያለን ያልተገባ አካሄድን ለመገምገም ነው፡፡
ታሪክ መኩሪያ የሚሆነው፣ ለዛሬ ማንነት ተጨባጭ ፋይዳ ሲኖረው ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ፡-
1ኛ-ተጨባጭና ተአማኒ ሲሆን
2ኛ-በጊዜ ሂደት ተከስተው የነበሩ ስህተቶችን እንደ መማሪያ ቆጥሮ ይቅር ተባብሎ ወደፊት ለመቀጠል እንጂ አቂሞ ለመወነጃጀል ሳይሆን ሲቀር ይመስለኛል፤ ነውም፡፡
አዎ ታሪክ አለን፤ so what? ይላል ፈረንጅ፤ (እና ምን ይጠበስ?! ለማለት) የ”ማን ነን?” ጥያቄ ወደ ኋላ ጎትቶ፣ ወደፊት ካላስፈነጠረን ምን ዋጋ አለው? ተጎትቶ ኋላ መቅረት እንጂ፡፡ ለዚህ ነው እንደ ዋና ግብአት የወሰድናቸውን የታሪካችንን ተጨባጭነት መመዘኛ ነጥቦች በአንክሮና በቅንነት መመርመር ያለብን፡፡ እስቲ እንያቸው፡፡
ጊዜ(T)
ካለንበት ጊዜ እጅግ ርቀው የተከወኑ ክስተቶች ለብዙ ስህተቶች የተጋለጡ ናቸው፤ ማስረጃ የላቸውም፤ አለ ቢባል እንኳን ለተአማኒነትና ለትንተና ያስቸግራሉ፡፡ ከዛም በላይ ለአሁን ማንነትና ለወደፊት ተስፋ የሚያበረክቱት ፋይዳ በእጅጉ ይደበዝዛል፡፡ እናም በእኛ ሁኔታ የዛሬ 2 ሺህ እና 3ሺህ አመት ታሪክን ፈልፍሎ ከመቀዣበር፣ የዛሬ 100 አመት የተደረገን የአብሮነት ገድል፤ የአድዋን ታሪክ መመርመር፤ ከ50 አመት በፊት የተፈጸመን የአባቶቻችን እልህ አስጨራሽ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል መፈተሽ አብዝቶ የተሻለ እንደሆነ ቀመራችን ያሳያል ፡፡
የታሪክ ዘጋቢው
የወገንተኝነት ደረጃ (P)
ታሪክ ጸሃፊ (ዘጋቢ) መቶ በመቶ ከወገንተኝነት ሊጸዳ አይችልም፡፡ ነገር ግን እስቲ ልብ ብለን የታሪክ ምንጮቻችንን እንመልከት፡፡ እጅግ የሚበዙት ገድላትና ዜና መዋእል (chronicle) አይደሉም እንዴ? የአንድ ንጉስ ዜና መዋእል ጸሃፊስ? “እነሆ በዚህ እለት፣ እንዲህ ባለ ቀን፣ በወሩም በዚህኛው ሰአት ጃንሆይ ከሰማይ በተዘረጋ መሰላል በመልአክት ታጅበው ወደ ቤተመንግስት ሲገቡ በአይኔ አየሁ፤ እኔም ምስኪን ባሪያቸው ይህንኑ ለታሪክ ጻፍኩ” የሚመስሉ ማጣቀሻዎች ሲከብቡን ግን እንዴት ባለ አይን ልናያቸው እንደሚገባ፣ ለእናንተ መንገር አያስፈልግም፤ ቀመሩ ይንገረን፡፡
የተጨባጭ መረጃ (ሰነድ) (D)
ተጨባጭ ማለት ተጨባጭ ማለት ነው፡፡ የአንድን ታሪክ ተአማኒነት ለማረጋገጥ በቁፋሮም ይሁን በሌላ የተገኙ ሰነዶችን ትክክለኛነት፤ አለመደለዝና አለመሰረዝ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ልናጣራ ይገባል እንጂ “ይህ ያገኘሁት ሰነድ ጋራውን አልፎ ፤ወንዙን ተሻግሮ፤ በፈራረሰ ጥንታዊ ገዳም ውስጥ በአለት ንቃቃት መሃል ተሰውሮ፤ ከትውልድ ትውልድ በሚስጥር ሲተላለፍ የቆየና ለእኔ ለምስኪኑ በድንገት ሳይታሰብ የደረሰ ውድ መረጃ ብቻ ሳይሆን የታሪክ እዳና ዱብ እዳ ነው” አይነት ክርክር የሚዳዳቸው መረጃዎች እንደከበቡን ግልፅ ነው (አንድ የቅርብ ምሳሌ ልሰጥ ነበር ….ተውኩት) ይህ አካሄድ ደግሞ የወደረኛን ስነልቡና ሆነ ብሎ ለመጫንና “እንዳትከራከረኝ! ለመከራከርስ አንተ ማን ነህ ?” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ለማስተላለፍ እንጂ በእርግጥ ተጨባጭና ምሁራዊ የክርክር ዘይቤ ነው ወይ? ውጤቱስ?
የወቅቱ የታሪክ ተቀባይ ህዝብ የመረዳትና የማገናዘብ ደረጃ (I)
ግድ የላችሁም፤ ይቺን ሃሳብ ልዝለላት፤ ለምን ቢባል?
1ኛ -እንተዋወቃለን
2ኛ-የትኛው ያልተጨበጠ ወሬ፣ እንዴት እንዴት እንደሚያደርገን፤ በአንድ ቀን ጀንበር የተፈጠሩ የ”በሬ ወለደ” አይነት ተረቶች፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደወዘወዙን ለማስታወስና ግለ-ሂስ ለማድረግ ቆም ብሎ ማሰብ ብቻ ስለሚበቃ፡፡
3ኛ-”አናገናዝብም፤ እምነት አይጣልብንም” ብሎ መከራከር ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ስላልሆነ፡፡
የመለኮት ጣልቃ ገብነት(R)
እያንዳንዱ የታሪክ ክስተቱ በመለኮት አጥር የተተበተበ ህዝብ፣ እንደ ሃበሻ ያለ አይመስለኝም። እንዴት? በሉ፡፡ የነገሰ ንጉስ ሁሉ በበቃና በነቃ እድሜ ጠገብ አባት፤ ጢሙ መሬት አበስ፣ ሹሩባው ሰማይ ጠቀስ፣ ቅዱስ ራእይ የታየለት፣ ህልም የታለመለት፤ የህዝብ አመራር ጥበብ በጥራዝ መልክ ከደመና የወረደለት፤ በየጦርነቱ መላዕክት ከፊት የመሩት፤ የእሳት ሰረገላ በደመና የከነፉለት አይነት ታሪኮቻችንን እስቲ ቆም ብለን እናስታውስ፡፡ በትንሷ የቀበሌ አስተዳዳሪነት በአለ ሲመት ላይ እንኳን ከዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ፤ ከትምህርትና የስራ ልምዳችን ይልቅ ያንዲት እድሜ ጠገብ “ጎረቤታችን ህልም አይቼ ነበር” ማስረጃ፣ ልባችንን የሚያሞቀው ህዝቦች አይደለን፡፡ (ፈጣሪ ነገስታትን አይሾምም አላልኩም፤  የኛ ግን በዛ)፡፡
ብዙም ሳንርቅ modern የምንለው የቅርብ ታሪካችን፤ ይሄንን በደንብ ያስረግጥልናል። የጨቋኙ ፊውዳል ስርአት ፊት አውራሪ፤ “የምድራችን እረጅሙ ንጉሳዊ ስርአት (the longest daynasty) አካልና ስዩመ እግዚአብሄር ናቸው፤ ዝም በሉ እንዳትቀሰፉ” እየተባሉ አይደል ያደጉት ወላጆቻችን። ፈጣሪን የማይፈሩ ኮሚኒስት ተማሪዎች፤ እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ አወረዷቸው እንጂ!
 (አሃ .. ታዲያ እኮ ተቀሰፉ መሰለኝ፤ ቀይ እሳት፤ ቀይ ሽብር ሙልጭ አድርጎ በላቸው አደል። የሚል ሃሳብ ሽው አለብኝ)፡፡
ከዚህ በመነሳት ከላይ የቀመርነው ቀመር እንዲህ አይነት ባህርይ ያላቸውን ግብአቶች መስተጋብር ሲያሰላልን ውጤቱ ዜሮ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ከባድ መልእክት ትቶልን ያልፋል። ከየትም እንምጣ፤ ማንም እንሁን ብቻ አንድ ያልታወቀ የታሪክ አጋጣሚ ሊታይና ሊረዱት በማይቻል ውስብስብ ስውር ስፌት የሰፋን፤ እጅግ ብዙ ክፉና ደግ ያሳለፍን፤ በችጋርና ጠኔ ተምሳሌትነት አብረን የተጠራን፤ በብዙ ጦርነቶች አብረን የቆረቆዝን፤ በአድዋ ድል ለጥቁር ህዝብ ብርሃን የፈነጠቅን፤ ብንኳረፍም የማንበላላ፤ ብንጎነታተልም አምርረን የማንጣላ ወንድማማቾች ነን፡፡ ይህን ቀላል እውነት መቀበል ብዙ ነገር ያቀልልናል፡፡
እኛም አለምም በውል የማናውቀው አንዳች ስውር ስፌት ጠብቀን የተሰፋን የምንዋደድ ህዝቦች ነን፡፡ ይሄንን ብቻ ሰንቀን ወደፊት ካየን በእርግጥ ነገ ብሩህ ነው፤ ከትርጉም አልባ የታሪክ ንትርክ እንውጣ፤ ያ ከሆነ በእርግጠኝነት ነገ በእጃችን ነው፡፡
ፈጣሪ ሃገራችንን ይባርክ!!

Read 2210 times