Print this page
Saturday, 22 July 2017 15:57

የቆሬ (ቆሼ) አካባቢ ልጆች የስኬት ጉዞ ጅምር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ሜላት ተመስገን፣ የ15 ዓመት ታዳጊ ስትሆን የአንደኛ ደረጃ መልቀቂያ (8ኛ ክፍል) ፈተና ወስዳ አጥጋቢ ውጤት በማምጣት (85.5 በመቶ) ወደ 9ኛ ክፍል ተዛውራለች፡፡ ሜላት፣ ከአያቷ ጋር ነው የምትኖረው፡፡ አያቷ ደግሞ ሁለቱን ማኖር የሚያስችል ገቢ የላቸውም፡፡ በየሰው ቤቱ ልብስ እያጠቡ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ይህ የአያቷ አቅመ ደካማነትና የገቢ ማነስ ነው በብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዲደረግላት ያስመረጣት፡፡
ብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ፤ ለሜላትና ለሌሎች የተመረጡ ተማሪዎች ምን ዓይነት ድጋፍ እያደረገ ይሆን? ሜላት እንዲህ ትገልጻለች፡- “ድርጅቱ አሪፍ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ ለምንማርበት እውቀት በኅብረት  ት/ቤት የዓመት  ይከፍልልናል። ለመማር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ መጻሕፍት፣ ቦርሳ፣ ልብስ ይሰጠናል። በትምህርታችን ጎብዘን፣ ውጤታማ ሆነን የተሻለ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግልናል፡፡ ድሮ የነበረንን የአጠናን ዘዴ ቀይረን፣ አዲስና ውጤታማ የጥናት ዘዴ እቅድ እንድናወጣ ረድተውናል፡፡ በዚህም ዘዴ ተሳክቶልኛል፡፡ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስጄ 85.5 በመቶ ነው ያመጣሁት” ብላለች።
ሲሳይ ኃይለየሱስ የ14 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፣ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ውጤት ስላልመጣለት ደጋሚ ነው፡፡ ሲሳይ እናቱ በህይወት ስለሌሉ የሚኖረው ከአባቱ ጋር ነው፡፡ አሁን እንኳ አነስተኛ ግሮሰሪ ስለከፈቱ ትንሽ ይሻላል እንጂ ከ3 ዓመት በፊት እሱ በብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዲደረግለት ሲመረጥ የአባቱ ገቢ የሚያወላዳ አልነበረም። ዘነበወርቅ ሪፈራል ሆስፒታል (አለርት) ውስጥ ካርድ ጠሪ ስለሆኑ ገቢያቸው በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ሲሳይ፤ ብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ ስለሚያደርግላቸው ድጋፍ ሲናገር፤ ሜላት ያለቻቸውን አገልግሎቶች ጠቅሶ፤ “በየቀኑ ምሳና ራታችንን ያበላናል፡፡ 9፡30 ከት/ቤት ወጥተን ወደ ግቢ ነው የምንሄደው፡፡ እዚያ በጎ ፈቃደኞች ስላሉ ያስጠኑናል፡፡ በክረምት ደግሞ አስጠኚ መምህራን ይቀጥሩልናል፡፡ ንጽህናችንን እንድንጠብቅ በየሳምንቱ የተለያዩ ሳሙናዎች ይሰጡናል፡፡ ልብሳችንን እናጥባለን፤ ገላና ፀጉራችን እንታጠባለን፡፡ ሴት ተማሪዎች ፀጉራቸውን ተጣጥበው እርስ በርስ ይሰራራሉ” በማለት ገልጿል።
ሃዳስ ዘሩ አባቷን በሞት ስለተነጠቀች ከእናቷ ጋር ነው የምትኖረው፡፡ ወደፊት ሐኪም  የመሆን ህልም እንዳላት የጠቀሰችው ሃዳስ፣ የ16 ዓመት ታዳጊ ስትሆን  በ1ኛ ሴሚስተር 2ኛ፣ በ2ኛ ሴሚስተር ደግሞ 3ኛ ደረጃ አግኝታ በአማካይ ውጤት 86 በማምጣት፣ ወደ 10ኛ ክፍል ተዛውራለች፡፡ እናቷ ምንም ገቢ የላቸውም፡፡ “ገቢያችን የሰው እጅ ማየት ነው” ብላለች ሃዳስ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ጥሩ ውጤት እያላቸው በድጋፍ እጦት ትምህርታቸውን ማቋረጥ የለባቸውም ተብሎ፣ ጥሩ ውጤት ስለነበራት መመረጧን ተናግራለች፡፡ ብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ፣ ቀደም ሲል ሁለቱ ተማሪዎች እንዳሉት በማድነቅ ዘርዝራ፣ ለጥናት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጻለች፡፡ ‹‹ክረምት ላይ አስጠኚ መምህራን ይቀጠራሉ፤ከመስከረም-ሰኔ ድረስ ግዙበራ ሳህና በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ እንድታጠና ይደረጋል›› ብላለች፡፡
ተማሪዎቹን አግኝተን ያነጋገርነው በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ነው፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ኔልሰን ማንዴላ በሕይወት ቆይተው ቢሆን ኖሮ 99ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከብሩ ነበር፡፡ በሕይወት ባይኖሩም፤ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በ2001 ዓ.ም ኔልሰን ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካና ለመላው ዓለም ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ የልደታቸው ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር በወሰነው መሠረት፣ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲም ዕለቱን፣ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ጥሩ ተግባር እየፈፀመ የሚገኘው ብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርግላቸውና ከ12-16 ዓመት ዕድሜ ካላቸው 39 ህፃናት ጋር አሳልፏል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የኔልሰን ማንዴላ የልደት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያንዳንዱ አገር እንዲያከብረው ከመወሰኑ አንድ ዓመት በፊት፣ ማንዴላ ለድርጅቱ ስልክ ደውለው፤ ‹‹እያንዳንዱ የዓለም ዜጋ ዓለምን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመለወጥ በተለይም ለሕፃናት፣ ቢያንስ የ67 ደቂቃ መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅበታል›› ብለው ባሳሰቡት መሠረት፣ የኤምባሲው አባላት ጊዜአቸውንና ከግል ገንዘባቸው 85 ሺህ ብር በማውጣት ለተጠቀሱት ሕፃናት ስጦታ (የተለያዩ ልብሶችና ጫማዎች) ገዝተው ማበርከታቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የብዙ ልጆች ወላጆች አካል ጉዳተኞች ናቸው። የአምስት ልጆች ወላጆች ማየት አይችሉም፡፡ ሌሎች ደግሞ የተለያየ የአካል ጉዳት፣ ሥጋ ደዌ፣ ኤችአይቪ/ ኤድስ ያለባቸው ናቸው፡፡ ተስፋቸው ልመና ብቻ ነው፡፡ ልጆቻቸው ካልደረሱላቸው ሕይወታቸው አይለወጥም፡፡ እነዚህ ልጆች ድጋፍ አግኝተው፣ ተምረው፣ ሕይወታቸው ተለውጦና ውጤታማ ሆነው ለቤተሰቦቻቸው ሲደርሱ ማየት ነው ግባችን፡፡ ልጆቹ ተምረው ራሳቸውን ከቻሉ የቤተሰቦቻቸው ህይወት ይለወጣል የሚል እምነት አለን፡፡ ለአካባቢውም ሞዴል ይሆናሉ፡፡ ቆሬ አካባቢ የተማረ ኅብረተሰብ ማየት ነው ዓላማችን›› ያሉት ደግሞ የብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ መንበረ በቀለ ናቸው፡፡
“ዋናው ትኩረታችን፣ ተማሪዎች የትምህርት እገዛ አግኝተውና  የተሻለ ውጤት አምጥተው አካባቢውን የሚለውጡ ዜጎችን መፍጠር ነው፡፡ ቆሬ አካባቢ ያለ ሰው አብዛኛው ድሃ ነው፡፡ የምንረዳቸው ልጆች ወላጆች አብዛኞቹ በልመናና ቆሻሻ በመልቀም የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ተማሪዎች በቂ ምግብ አያገኙም፡፡ ተምረውና ሕይወታቸው ተለውጦ የተሻለ ሰው እንዲሆኑ እገዛ እናደርጋለን ያሉት ወ/ሮ መንበረ፤ ለሰው ልጅ  ዋነኛው አስፈላጊ ነገር ምግብ ስለሆነ በየቀኑ ምሳና እራት ይመገባሉ፡፡ ደብተርና መጻሕፍት መያዣ ቦርሳን ጨምሮ የትምህርት መሳሪያ ወጪያቸው ይሸፈናል፡፡ ለሚማሩበት ት/ቤት ዓመታዊ ወጪ ይከፈላል፡፡ ዩኒፎም፣ ልብስና ጫማ ይገዛላቸዋል፡፡ ጤናቸውን እንከታተላለን፡፡ የታመመ ልጅ ካጋጠመን እናሳክማለን፡፡ ፈቃደኛ በጎ አድራጊ ሐኪም ሲገኝ ደግሞ ሁሉም የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ የጥናት ፕሮግራምም ቀርፀው እንዲያጠኑ እናደርጋለን፣ በጥብቅ እንከታተላለንም›› ብለዋል ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፡፡
ብርሃን ይሁን ኢትዮጵያ የራሱ ገቢ የለውም። ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችንን፣ ጓደኞቻችንንና ቤተሰቦቻችንን ድጋፍ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን። የአንድ ወይም የሁለት ልጅ የወር ወጪ የሚያግዙን ሰዎች አሉ፡፡ ከውጭ የምናገኘው ድጋፍ በጣም ትንሽ ስለሆነ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጅምራችን እንደተገለፀው ነው፡፡ መጨረሻችንም ያማረና ስኬታማ፣ ልጆቹም ተለውጠው፣ የወላጆቻቸውን ሕይወት የሚለውጡና ጥሩ አገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የተቻላችሁን ድጋፍ እንድታደርጉልን እጠይቃለሁ›› ብለዋል ወ/ሮ መንበረ በቀለ፡፡
የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ገንዘብ አዋጥተው የገዙትን ልብስ፣ ጫማ፣ የትምህርት ቁሳቁስ፣ የንጽህና መጠበቂያ፤…. ስጦታ ለተማሪዎቹ የሰጡት በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር፣ በአፍሪካ ኅብረትና በመንግሥቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ፣ ሚ/ር አዱሚዶ ኒሺንጋ ሲሆኑ አንድ ተማሪ የሠራው ሥዕልም ተበርክቶላቸዋል፡፡

Read 3103 times
Administrator

Latest from Administrator