Saturday, 22 July 2017 15:56

ዱባይና ኢትዮጵያ በቱሪዝም ትስስር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

   ለመዝናናት፤ ለመነገድና ለህክምና
                                                            
      የዱባይን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ አህጉር ጋር በላቀ ደረጃ ለማስተሳሰር ‹‹የ2017 የዱባይ ቱሪዝም ‹‹ሮድ ሾው››  በአዲስ አበባ ራዲሰን ብሉ ሆቴል ተካሂዶ ነበር። ይሄ ‹‹ሮድ ሾው›› በዱባይ ቱሪዝምና ንግድ ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት አማካኝነት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው  በቱሪዝሙ መስክ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትን የስራ ግንኙነት ለማጠናከር በታለመው በዚህ ልዩ መድረክ፤ በዱባይና በኢትዮጵያ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተለያየ መስክ የሚሰሩ ተቋማት ተገናኝተውበታል፡፡  ዱባይ ለአፍሪካ አገራት በተለይ በአቅራቢያ ለምትዋሰነው የምስራቅ አፍሪካ ክፍል በመዝናኛ፤ በንግድና በኢኮኖሚ የቱሪዝም መዳረሻነት ያሏትን አማራጮች የሚያጠናክሩ ሁኔታዎች መፈጠራቸው የተጠቆመ ሲሆን በህክምና፣ በትምህርትና በቱሪዝሙ መስክ አዳዲስ አቅጣጫዎች ተዋውቀዋል፡፡
የዘንድሮ ዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው በአፍሪካ፤  እንቅስቃሴውን የጀመረው በምእራቡ የአህጉሪቱ ክፍል ጋና እና ናይጄርያ በተለይ በጤናው ቱሪዝም ላይ በማተኮር ባካሄዳቸው ትርኢቶች ነበር፡፡ በምስራቅ አፍሪካ  ደግሞ አስቀድሞ በመዝናኛና በንግድ መስክ የተፈጠሩ ትስስሮችን በማጠናከር፣ በጤናው ቱሪዝም የትውውቅ እድሎች ተፈጥረዋል። ኬንያ፤ ታንዛኒያና ኢትዮጵያም የዝግጅቱ አካል ነበሩ። ከምስራቅ አፍሪካ በኋላ የዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው  በደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡  
የዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው ዋና ዓላማ፤ ከአፍሪካ ወደ ዱባይ የሚጓዙ  ቱሪስቶችን ማብዛት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ሁሉም አይነት ቱሪስቶች ወደ ዱባይ ከመጓዛቸው በፊት፤  በጉዟቸው፤ በቆይታቸውና በመመለሻቸው ላይ ሙሉ በሙሉ የሚረኩበትንና የሚተማመኑበትን ሁኔታ በመፍጠር ዓላማውን ለማሳካት ታስቧል። በዱባይ የሚያገኟቸውን ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ አገልግሎቶችና አማራጭ ሁኔታዎች በተመለከተ የተሟላ መረጃና ግንዛቤ የሚያገኙበትን አሰራር  ለመዘርጋት ጭምር ነው።  በአዲስ አበባው መድረክም በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚንቀሳቀሱ ከ100 በላይ አስጎብኝ ድርጅቶች፤ የጉዞ ወኪሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡  
በዱባይ ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን የአፍሪካ ዲያሬክተር ሚስስ ስቴላ ኦቢንዋ  ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ዋና ዓላማችን ከአፍሪካ አገራት ወደ ዱባይ  የሚጓዙ ቱሪስቶችን ብዛት ለማሳደግ ነው፡፡ ስለሆነም የዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው ስናዘጋጅ ባለድርሻ አካላቱ ተገናኝተው እንዲመክሩ አድርገናል፡፡  በመድረኩ የተፈጠሩ የጋራ መግባባቶችን አሳድጎ ለመንቀሳቀስና ለመስራት ያግዘናል፡፡ ወደ ዱባይ የሚጓዙ አፍሪካዊ  ቱሪስቶችን በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ቱሪስቶች ስለ ዱባይ ያላቸውን እውቀት በመጨመር ለማናቸውም የጉዞ ውሳኔያዎች ምቹ አሰራሮችን ለመፍጠርና ጅማሮዎችን ለማነቃቃት ነው።›› ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት በዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው ላይ ዱባይን በትንሹ ለማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ የየአገራቱን የቱሪዝም  ግንኙነት በማጠናከር፤ ባለድርሻ አካላት፣ በተሻለ መንገድ እንዲሰሩ ከማበረታታትም በላይ   አማራጭ የቱሪዝም አገልግሎቶችና የአሰራር አቅጣጫዎች የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡  
በራዲሰን ሆቴል መድረክ ላይ ዱባይ ቱሪዝም፣  ከዱባይ የጤና ጥበቃ ባለስልጣን፤ ከዱባይ የቱሪዝም ኮሌጅ፤ ከዱባይ ኢሚግሬሽን፤ ከኤመሬትስ አየር መንገድ፤ ከፍላይ ዱባይ፤ ከሌመሪዲያን ሆቴሎችና ሪዞርቶች፤ ከሸራተን ሆቴልና ሪዞርቶች፤ ከግሎባል ቪሌጅ፤ ከራያን፣ኖርዝ አስጎብኝ ድርጅቶች፤ ከግዙፍ የህክምና ተቋማትና  ሆስፒታሎች የመጡ ልዑካኖች ነበሩ፡፡ እነዚህ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን፤ አቅማቸውን፤ ልዩ ቅናሾች፤ ማበረታታቻዎችና አሰራራቸውን አስተዋውቀዋል፡፡
ሚስስ ስቴላ ኦቢንዋ እንደሚናገሩት፤ በሮድ ሾው ለዱባይ እና ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎች መነቃቃት መፈጠሩ የማይቀር ነው። የቱሪስቶች ብዛት በመጨመር፤ በአገልግሎት እርካታ በማግኘትና ተጠቃሚ በመሆን ውጤታማ አሰራሮች የሚዘረጉበትን እድል ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የሚገኙ የአስጎብኝ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች በዱባይ ከተማ አብረው ከሚሰሯቸው ኩባንያዎች ጋር በሚኖሯቸው ቀጥታ የስራ ግንኙነቶች ስኬታማ መሆናቸው በተዘዋወሪ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የሚችሉ ቱሪስቶች ብዛትንም ስለሚያሣድግ ነው፡፡
በተለይ በዱባይ ከሚገኙ ከ26 በላይ ዘመናዊ ሆስፒታሎችና ከፍተኛ ህክምና ተቋማት ጋር በዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው  ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወኑት ስራዎች አበረታች ጅማሮ ሆነው ይገለፃሉ፡፡  
በ2016 ተመሳሳይ የዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው በኡጋንዳ፤ በታንዛኒያና በኬንያ ተካሂዶ እንደነበር ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ውይይት ያስታወሱት ሚስስ ስቴላ፤ ዘንድሮ በኡጋንዳ ምትክ ኢትዮጵያ የገባችበትን ዋንኛው ምክንያት ሲያስረዱ፤ ወደ ዱባይ በየዓመቱ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን እየበዙ በመምጣታቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ይህን ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከር ታስቦ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለመዝናናት፤ ለንግድና ለህክምና ወደ ዱባይ የሚያደርጓቸው ጉዞዎች መጨመራቸው ዱባይን ወደ ኢትዮጵያ የበለጠ ያቀርባታል፤ ይህም የሁለቱ አገራት የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎች በስፋት የሚተሳሰሩባቸውን እድሎች ያጠናክራቸዋል›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የዱባይ ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን የአፍሪካ ዳይሬክተር ፡፡
ባለፈው ዓመት  ላይ ከመላው ዓለም ዱባይን የጎበኙ ቱሪስቶች ብዛት ከ14.9 ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ  የአፍሪካውያን ብዛት 1 ሚሊዮን ነበር፡፡ በተለይ የናይጄርያ ቱሪስቶች ብዛት ከአህጉሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ቢሆኑም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቱሪስቶች ጉብኝትም በሚቀጥሉት 3 ዓመታት እያደገ እንደሚሄድ ተገምቷል፡፡
በዱባይ ለአፍሪካውያን ቱሪስቶች  ምቹ እና የተሟላ አገልግሎት የሰጠባቸው መስኮች እየበዙ ነው። ለሰርግና ለክብረ በዓላትና ተመሳሳይ ዝግጅቶች፣ ለቤተሰብ ጉዞ፤ ለስብሰባ፤ ለፍቅር ጓደኞች የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ በአጠቃላይ ለሙሉ ቤተሰብ የሚሆኑ ዘመናዊ የመዝናኛ መሰረተ ልማቶች፤ የቱሪስት መዳረሻዎችና አገልግሎቶች በከተማዋ ተሟልተው ይገኛሉ፡፡ ለመዝናናት እና ለመነገድ ወደ ዱባይ የሚጓዙ አፍሪካውያን፤ አሁን ደግሞ ለህክምናና ለትምህርት እንዲመርጧት የሚያስችሏት ሁኔታዎች እያመቻቸች ነው ተብሏል ዱባይ፡፡
የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ዋና ከተማ የሆነችው ዱባይ ለመላው የዓለም ህዝቦች የምትመችና እንግዶቿን እንደ ቤተሰብ የምታስተናግድበትን ሁኔታዎችን አሟልታ የያዘች ናት፡፡ ዱባይ ከተማ ለቱሪስቶች ውድ እንደሆነች በተደጋጋሚ የሚገለፀው አግባብነት የለውም ይላሉ- ሚስስ ስቴላ ኦቢንዋ፡፡ በዱባይ ከተማ የሚገኘው ግሎባል ቪሌጅ ለአንድ ሰው መግቢያ 4 ዶላር እንደሚከፈልበት፤ የሁሉም ዓለም አገራት ባህልና ምግብ የሚገኝበት እንዲሁም ተመጣጣኝ ንግድና ግብይት ማከናወን የሚቻልበት  እንደ ሆነም በማስረዳት፡፡ በተጨማሪ በዱባይ አንዳንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ለአንድ ምሽት 16 ዶላር የሚያስከፍሉ ሲሆን በከተማዋ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የሆቴል አፓርትመንቶች ለሙሉ ቤተሰብ አገልግሎት እንደሚሰጡ በተለይ በረመዳን የፆም ወቅት ና በክረምት ወራት ብዙ ርካሽ አገልግሎቶች ከተማዋ እንደምታቀርብ ይጠቁማሉ፡፡
የዱባይ ሄልዝ ቱሪዝም ካውንስል ዲያሬክተር  ዶክተር ለይላ መሃመድ አልመርዙኪ በበኩላቸው፤ ‹‹ዱባይ ለኢትዮጵያውያን ቱሪስቶች ዋንኛ መዳረሻ እየሆነች በመምጣቷ እየተበረታታን ነው። ለመዝናኛና ለንግድ ምቹ እየሆንን መምጣታችን ለማጠናከር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ ጎን ለጎን ትኩረት ሰጥተን መስራት የጀመርነው በጤና ቱሪዝም ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መዋቅር መዘርጋት ነው፡፡ የዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው ይህን አቅጣጫ ለማስተዋወቅ የምንሰራበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ እና በዱባይ ከተሞች መካከል የበረራው ርቀት 4 ሰዓታት ብቻ የሚፈጅ ሲሆን ሁለቱን ከተሞች በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት በዋናነት የሚንቀሳቀሱት ሶስት አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በዱባይ መንግስት የሚተዳደረው ፍላይ ዱባይ እና ኤመሬትስ ኤርላይንስ ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ ታዋቂው ኤመርትስ ኤርላይንስ፤ በየቀኑ ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የሚበር ሲሆን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይ ዱባይ ሁለተኛዋ ዋንኛ የበረራ መዳረሻ መሆኗ ተጠቁሟል የዱባይ መንግስት ለሚያስተዳድረው ፍላይ ዱባይ፤ በኢትዮጵያ፤ በሶማሊላንድና በጅቡቲ ኮሜርሻል ማናጀር ሆነው የሚያገለግሉት አቶ ስራው በውቀቱ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ‹‹በዱባይ ቱሪዝም ሮድ ሾው ተሳትፏቸው አየር መንገዳቸው በበረራ አገልግሎት ተመራጭ የሚሆንባቸውን እድሎች ለመፍጠር አመቺ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ላለፉት  ስድስት ዓመታት በሳምንት ለ3 ቀናት ወደ አዲስ አበባ ቀጥታ በረራዎች እያደረግን በመሆኑ፣ ይህን አገልግሎት ለማስተዋወቅና አዳዲስ አሰራሮችን ለባለድርሻ አካላት ለመጠቆም ችለናል፣›› ብለዋል፡፡
‹‹በክረምት ወራት ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ በኋላ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ዱባይ ለእረፍት የሚጓዙ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ አስገብተን በፍላይ ዱባይ በኩል ለሚቀጥሉት ወራት በሚቆይ ልዩ የበረራ አገልግሎት ለአንድ ሰው ቪዛን ጨምሮ 299 ዶላር (እስከ 6ሺ ብር) በማስከፈል አገልግሎት እየሰጠን ነው፣›› ይላሉ፤ የፍላይ ዱባይ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ሰረቀ በውቀቱ፤ ወደ ዱባይ ለእረፍት፤ ለመዝናናትና ለመነገድ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቱሪስቶች ብዛት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን አቶ ሰረቀ ጠቁመው፤ በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ወራት በሚካሄደው ዓመታዊው የዱባይ ሾፒንግ ፌስቲቫል ላይ ላለፉት 4 ዓመታት ከአምስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መጓዛቸውን ይናገራሉ፡፡
ፍላይ ዱባይ በዱባይ ቱሪዝም የሮድ ሾው ተሳትፎው ከኢትዮጵያ የአስጎብኝ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች ጋር በቅርበት በመገናኘት አዳዲስ የአሰራር አቅጣጫዎችን እንዳስተዋወቀ የገለፁት ማርኬቲንግ ማናጀሩ፤ በተለይ በ2017 የጀመርነውን የፍላይ ዱባይ ደንበኞች የሆስፒታሊቲ ፓኬጅ ማለትም የበረራ ትኬት ከሆቴል መስተንግዶ ጋር ያቀናጀ አገልግሎትን በማቅረብ የምንሰራባቸውን ሁኔታዎች የምናጠናክርበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

Read 1947 times