Saturday, 07 April 2012 07:44

የሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ የምንጊዜም ምርጥ ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለ57ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የሚደረገው ትንቅንቅ ለግማሽ ፍፃሜ ሲደርስ ለዋንጫ የሚያልፉትን ቡድኖች ለመገመት አስቸገረ፡፡ ከወር በኋላ የዋንጫው ጨዋታ በጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ ስታድዬም አሊያንዝ አሬና የሚደረግ ሲሆን በግማሽ ፍፃሜ ቼልሲ ከባርሴሎና እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከባየር ሙኒክ ይገናኛሉ፡፡ ከዛሬ 10 ቀናት በኋላ ግማሽ ፍፃሜው የእንግሊዙ ቼልሲ ከስፔኑ ባርሴሎና ታምፎርድ ብሪጅ እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ በአሊያንዝ አኔራ በሚያደርጓቸው የመጀመርያ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡ የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ  ከዛሬ 17 ቀናት በኋላ በሁለቱ የስፔን ትልልቅ ስታድዬሞች ኑካምፕና ሳንቲያጎ በርናባኦ ይካሄዳሉ፡፡ የዛሬ ወር ደግሞ ለፍፃሜ የሚገናኙት ሁለት ክለቦች ተለይተው በ2006 እኤአ የዓለም ዋንጫን የፍፃሜ ጨዋታ ባስተናገደው አሊያንዝ አሬና የሚፋለሙ ይሆናሉ፡፡

ለግማሽ ፍፃሜ የደረሱት አራት ክለቦች በውድድሩ ታሪክ ከቀረቡት 57 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች 17ቱን የወሰዱት ናቸው፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ በ57ዓመታት የውድድር ታሪኩ በ21 የተለያዩ ክለቦች የዋንጫ ድል የተመዘገበበት ሲሆን 12 ክለቦች የውድድሩን ዋንጫ ከ1 ግዜ በላይ ማንሳት እንደቻሉ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድል የሚያገኘው ክለብ በሽልማት ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 9 ሚሊዮን ዩሮ የሚታሰብለት ሲሆን በተጨማሪ  በተለያዩ የቦነስና የንግድ ገቢዎች እስከ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጨርሰው ክለብ ደግሞ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት 5.6 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን አጠቃላይ ገቢው እስከ 46 ሚሊዮን ፓውንድ ሊደርስ ይችላል፡፡ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሱት ሪያል ማድሪድ፤ ባየር ሙኒክ፤ ባርሴሎና እና ቼልሲ ለዚህ ምእራፍ በመድረሳቸው ብቻ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 2.85 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፈላቸዋል፡፡ በየውድድር ዘመኑ በ70 አገራት በ40የተለያዩቋንቋዎችበቴሌቭዥንየሚሰራጭላት የአውሮፓሻምፒዮንስ ሊግ ዘንድሮ የምንጊዜም ምርጥ የግማሽ ፍፃሜ ማስተናገዱ እየገለፀ ነው፡፡ የባለፈው ዓመት በሳንቲያጎ በርናባኦ ባርሴሎና 3ለ1 በሆነ ውጤት ማንችስተር ዩናይትድን ያሸነፈበት የዋንጫ ጨዋታ 178 ሚሊዮን ተመልካች በቲቪ እንደተከታተለው ይታወቃል፡፡በግማሽ ፍፃሜው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በሚመዘገቡ ውጤቶች ከወር በኋላ በአሊያንዝ አሬና ስታድዬም አራት ዓይነት የፍፃሜ ፍልሚያዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ በመጀመርያው በብዙዎች ግምት የተሰጠውና ጉጉት የፈጠረው የሪያል ማድሪድና የባርሴሎና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ኤልክላሲኮ ነው፡፡ 2ኛው 9 ግዜ ዋንጫውን ያነሳው ሪያል ማድሪድ በጆሴ ሞውሪንሆ አሰልጣኝነት ምንም ዋንጫ ያላገኘውን ቼልሲን ሊገጥምብት የሚችለው ነው፡፡ ሶስተኛው የፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ 4 ግዜ  እኩል ዋንጫውን በማንሳት  የውጤት ታሪክ ያላቸው የጀርመኑ ባየር ሙኒክ እና  የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና የሚገናኙበት ይሆናል፡፡ በመጨረሻ የአሊያንዝ አሬና የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ፍልሚያ ባለሜዳውን ባየር ሙኒክና የእንግሊዙን ቼልሲ ሊያገናኝ ይችላል፡፡

 

 

 

 

Read 3150 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 07:52