Saturday, 22 July 2017 15:33

አወዛጋቢው የገቢ ግምት - አስተያየቶችና ሙያዊ ምክሮች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 (መንግስት-ታክስ - የግል ዘርፉ)

                     አነስተኛ ነጋዴዎች በቀን የሚያገኙትን ገቢ በግምት በማስቀመጥ ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑን ተከትሎ በርካቶች ጉዳዩን መነጋገሪያ አድርገውታል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችም በጉዩ ላይ የራሳቸውን ምልከታ እያስቀመጡ ሲሆን አዲስ አድማስ ጋዜጣም እነዚህን ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ አነጋግራለች፡፡ የባለሙያዎቹንና ፖለቲከኞችን አስተያየትና ሀሳብ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

                               “አብዛኛው ነጋዴ ስጋት ውስጥ ወድቋል”
                                  አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

      ይህ የግብር አሰባሰብ ሁለት ችግሮች እንዳለበት ይታየኛል፡፡ በአንድ በኩል በቂ መረጃ ሳይሰበሰብ በትንሽ በትልቁ ላይ ዝም ብሎ ግብር ይጫናል። ሳይንሳዊ በሆነ ሂደት የሚሰራ ሳይሆን በዘመቻ ነው የሚሰራው፡፡ ስለዚህ በመንግስት በኩል በቂ ጥናት ተደርጎ፣ ሁሉም ሰው የሚጠቀምበት ስርአት አልተዘረጋም፡፡ ሁልጊዜ በየዓመቱ ዘመቻ ነው ሲካሄድ የምናየው፡፡ ሰዎችም ለእንግልት ሲዳረጉ ነው የምንታዘበው፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ደግሞ ለሙስናም በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህ አንዱ ችግር ያለው በሳይንሳዊ ጥናት ሰዎች ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን ተገቢ የሆነ ግብር እንዲከፍሉ የሚያስችል ስርአት ገና አለመዘርጋቱ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በዘመቻ ነው፡፡ በዘመቻ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር ሊሳካ አይችልም፡፡
ሁለተኛው ችግር ያለው ደግሞ በራሱ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል ነው፡፡ ከነበረን አጠቃላይ ባህል አንፃር፣ ግብርን በአግባቡ የመክፈል ልማድ የለም፡፡ የሚከፍለውን ግብር እንደተነጠቀ አድርጎ የማሰብ ነገር አለ፡፡ ይሄም ራሱን የቻለ ችግር ነው። ዜጎቹ ግብር እስካልከፈሉ ድረስ መንግስት  ሀገር ማስተዳደር አይችልም፡፡ ስለዚህ የመሰረተ ልማት፣ የማህበራዊ ጉዳይና የኢኮኖሚ ፍላጎታችን በሙሉ ሊሟላ የሚችለው ዜጎች ግብር ሲከፍሉ ብቻ ነው። ይሄ ችግር እንዲፈታ ደግሞ መንግስት መጀመሪያ ግንዛቤ መፍጠርና የግብር ከፋዩ አቅም እንዲጎለብት ማድረግ አለበት፡፡ ዘንድሮ የተጨመረው ጭማሪ መቶ ፐርሰንት ወይም ሁለት መቶ ፐርሰንት አይደለም፤ በአብዛኛው ከአንድ ሺህ ፐርሰንት በላይ ነው፡፡ ለምንድን ነው በአንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ጭማሪ የመጣው? ሳይንሳዊ ነው? ይሄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ የግብር ጭማሬ ሲያስፈልግ ተገቢውን ጥናት ተከትሎ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይሄ ህብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ ጫና መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ወጥ የሆነ የተጠና አሰራር ያስፈልጋል፡፡
ሌላው እነዚህ አነስተኛ ነጋዴዎች በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ገቢ አላችሁ ተብሎ ሲገመትባቸው ወደ ከፍተኛ ግብር ከፋይነት እንዲገቡ ነው የሚገደዱት። ይሄን ለማድረግ የቫት ማሽን፤ ሰራተኛ መቅጠር አለባቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዴት ነው ይሄን ማድረግ የሚችሉት? ስለዚህ አቅሙ የሌለው ከንግዱ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ሽግግሩ በጥናት ላይ የተደገፈ፣ ትክክለኛ እድገትን ያገናዘበ መሆን አለበት። አድገዋል በሚባሉት ሀገራት ዝቅተኛው ህብረተሰብ ከታክስ ጫና ነፃ ነው፡፡ አነስተኛና ዝቅተኛ  ነጋዴዎችን በተመለከተ ዋናው የመንግስት ዓላማ መሆን ያለበት፣ ከእነሱ ከፍተኛ ግብር መሰብሰብ አይደለም። ዓላማው ስራ መፍጠር ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ግን መንግስት ትኩረቱ ግብር መሰብሰብ ላይ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይሄ ነጋዴዎቹን ከገበያ ያስወጣና የሥራ አጥ ቁጥሩን ይጨምረዋል። በየትኛውም ሀገር ዝቅተኛ ነጋዴዎች ከታክስ ነፃ ይደረጋሉ፤ እንደውም በመንግስት ይደገፋሉ፡፡ ምክንያቱም ዋናው አላማ ለዜጎች ስራ የመፍጠር ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ይሄ ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይመስለኝም፡፡ ኮሪደር ላይ ቡና አፍልተው የሚሸጡ ሁሉ መደበኛ ታክስ ከፋይ ይሁኑ ከተባለ  አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግስት በነዚህ ላይ ታክስ መጫን ሳይሆን ያለበት  የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንቱ እንዲሰፋ ምቹ ሁኔታ ነው መፍጠር ያለበት፡፡ ያኔ  የታክስ መሠረቱን ያስፋፋል፡፡
በየአመቱ የመንግስት በጀት እየጨመረ ነው፡፡ ይሄ በጀት ዝም ብሎ አይደለም መጨመር ያለበት። ከንግድ ህብረተሰቡ እድገትና ከሃገር ውስጥ ምርት ጋር ተያይዞ ነው መጨመር ያለበት፡፡ ዝም ብሎ በፖለቲካ ውሳኔ አመታዊ በጀትን ጨምሮ፣ ያንን በጀት ለማሟላት ካድሬዎችን በዘመቻ መልክ ይሄን ያህል ሰብስቡ ብሎ ኮታ መጣል ተገቢ አይደለም። እንዲህ አይነት አሠራር ቅሚያ ነው የሚሆነው። ስለዚህ መንግስት መጀመሪያ ቅደም ተከተሉን ማየት አለበት፡፡ ታክስ መሰብሰብ ያለበትም በዘመቻ አይደለም፡፡ ከህብረተሰቡ አቅም ጋር መገናዘብ አለበት፡፡ ሌላው ያየሁት ችግር፣ ማሽን አስገብተው 15 በመቶ ቫት የሚሰበስቡ ነጋዴዎች ሳይቀሩ ነው ይሄ ግምት የተጣለባቸው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ማሽኑ ያስፈለገው ቫት ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የነጋዴውን አቅም ለማወቅ ነው፡፡ የሚታወቅ አቅም ላይ እንዴት ግምት ይጣላል፡፡ ይሄ ስርአቱን ለተለያዩ ችግሮች መዳረግ ነው፡፡ ሰው ልኮ በነዚህ አካላት ላይ ማጣራትና መገመት አያስፈልግም፡፡ አሁን አብዛኛው ነጋዴ ስጋት ውስጥ ወድቋል፡፡ ይሄ ደግሞ አደገኛ ነው፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትም ይፈጥራል፡፡

----------------------------

                              “መንግስትና የግል ዘርፉ አጋር መሆን አለባቸው”
                                 አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ (የ”Fairfax Africa Fund” ሊቀመንበር)

      በእድገት ላይ ባለ ሀገር፤ በስራ ፈጠራም ሆነ የታክስ ገቢ በማመንጨት የሚመራው የግል ዘርፉ ነው፡፡ ከ25 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ ነው። ታክስ የሚሰበሰበውም ከመንግስት ሰራተኛ ደመወዝና ትንሽ ትርፋማ ከነበሩ የመንግስት ድርጅቶች ነው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተቀየረ መጥቷል። ለወደፊት ደግሞ በጣም ይቀየራል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  የግል ዘርፉ ከሆነ የሚመራው፣ ይህ የግል ዘርፍ ከመንግስት ሊደረግለት የሚጠብቀው እስካለ ድረስ (ለምሳሌ መሰረተ ልማት) ታክስ መክፈል እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ሌላ የገንዘብ ምንጭ የለውም፤ ግብር ነው አንዱ ምንጭ፡፡ ለወደፊትም ቢሆን በዚህ የእድገት ግስጋሴ ከሄድን ግብር የሚሰበሰበው ከግል ዘርፍ ነው፡፡ ይሄ እስከሆነ ድረስ መንግስትና የግል ዘርፉ አጋር መሆን አለባቸው። በአጋርነት መንፈስ ነው መጓዝ ያለባቸው፡፡ መንግስት መጀመሪያ ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር አለበት፡፡ የግል ዘርፉም ይሄ ሁሉ ግድብ የሚሰራው፤ ባቡር፣ መንገድ፣ ጤና ጣቢያዎች የሚስፋፉት  በግብር መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል። መጀመሪያ ይሄ አይነት መንፈስ  መፈጠር አለበት፡፡
ከሰሞኑ አነጋጋሪ የሆነው  የታክስ ጉዳይ በጥሩ መንፈስ ይፈታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ መተማመንና መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ አንዱ ግብር ከፋይ ሆኖ፣ ሌላው ግብር ሳይከፍል የሚኖረን ኢኮኖሚ ጤናማ አይሆንም። ሁሉም መክፈል አለበት፡፡ ግብር የማይከፍለው ግብር ከፋዩን እንዳይጨቁን፣ ሁሉም ወደ ግብር ከፋይነት መምጣት አለበት፡፡ ይሄ ግን በመነጋገርና በመግባባት የሚመጣ ነው፡፡ መንግስት ይሄን አስቀድሞ በአግባቡ ማስረዳት አለበት፡፡ በዓለም የኢኮኖሚ እድገት ቀዳሚ ሆናለች የተባለች ሀገር ደግሞ የታክስ ስርአቷን ማዘመን አለባት፡፡ ይሄ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በአሁን ወቅት እንኳ ኢትዮጵያ ታክስ በመሰብሰብ ከአፍሪካ ሀገራት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለችው፡፡ ኢትዮጵያ የታክስ ገቢዋ ከአጠቃላይ 13 በመቶ ገደማ ነው፤ኬንያ 18 በመቶ ደርሳለች፡፡ ስለዚህ ጀማሪ የግል ዘርፎችን በስርአቱ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤ ሳይሰጥ የሚተመን ታክስ አለመግባባትን ነው የሚፈጥረው፡፡ መንግስትም በተሰበሰበው ታክስ በሚገባ ስራ ሰርቶ በተከታታይ ማሳየት አለበት፡፡ ከተማ ውስጥ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት የመሳሰሉትን የማሟላትና የማስተካከል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ይሄ ከተደረገ ነው ሁለቱ አካላት ተጋግዘው ወደፊት ሊጓዙ የሚችሉት።   

------------------------

                                     “የታክስ ስርአቱ ከግምት አሰራር መውጣት አለበት”
                                        አቶ አቢስ ጌታቸው (በኢኮኖሚክስ የፒኤችዲ ተማሪ)

     ታክስ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ነው፡፡ ግዴታም ነው፡፡ አሁን ጥያቄው በምን አይነት መልኩ ታክስ ይሰብሰብ የሚለው ነው፡፡ በኛ ሀገር ያለውን ስናይ፣ ከንግድ ማህበረሰብ የሚሰበሰበው ግብር ከተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚሰበሰበው ያነሰ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሄ የሚያሳየው የሀገሪቱ የግብር ጫና ሰራተኛው ላይ እንደተጫነ ነው፡፡ ግብር መክፈል ያለባቸው ነጋዴዎች መክፈል አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ገና በጀማሪና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሁኔታ ያሉ ነጋዴዎች ላይ ግብር መቆለል አይደለም። የትኛውም የሥነ- ምጣኔ ሀብት አስተምህሮ፤ በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ የሚፈጠርን የግብር ጫና አይደግፈውም፡፡
በአጠቃላይ የታክስ ስርአታችንን ስናይ፤ግብር ከፋዩን የሚያበረታታና የሚያሳድግ ሳይሆን የሚያስደነብር ፖሊሲ ነው ያለው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ትንሽ ገቢ ሲያገኝ፣ ያችን ያገኛትን ትርፍ ተጨማሪ ንግድ ለማስፋፋት እንዲያውለው ሳይሆን ቋጥሮ እንዲያስቀምጥ የሚያደርግ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደውም እምነት ከማጣት የተነሳ ገንዘቡን ወደ ውጪ ሀገር ገንዘብ  መንዝሮ የመያዝ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ ይሄ አንዱ የታክስ ስርአታችን የፈጠረው ችግር ነው፡፡ አነስተኛ ነጋዴዎች ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ሲደረግ፣ መጀመሪያ መጠየቅ ያለበት እንዲቋቋሙና እንዲጠናከሩ ምን ያህል ድጋፍ ተደርጎላቸዋል የሚለው ነው፡፡ ማበረታቻ ወይም ድጋፍ ሲባል አንዱ የግብር አስተያየት ነው። ይሄም ብቻ አይደለም፤የኢኮኖሚ መረጋጋት ተፈጥሮለታል? የሚለውን ማረጋገጥም አንዱ ማበረታቻ ነው፡፡ መሰረተ ልማትም እንዲሁ፡፡ የኢንተርኔትና መብራት አገልግሎት መቆራረጥ ትልቅ ባህል በሆነበት በአሁኑ ወቅት  ሰው ከልቡ ኢንቨስት አድርጎ ይሰራል ማለት የዋህነት ነው፡፡ የፈለገውን አይነት ማበረታቻ ቢሰጠው እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች እስከሌሉ ድረስ ዋጋ የለውም፡፡ በዚህ መነሻነት በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ብንመለከት፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቻቸ ነገር አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡
በሌላ በኩል ግብርን በግምት መስራት አሳማኝ ውጤት አይሰጥም፡፡ ስለዚህ የታክስ ስርአቱ ከዚህ አሰራር መውጣት አለበት፡፡ አሁን ላይ ቢዝነሶችን የመደገፍና የማሳደግ ጉዳይ ተዘንግቷል ማለት ይቻላል፡፡ መጀመሪያ ቢዝነሶችን የሚያበረታታ ስልት መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ በእርግጠኝነት ገንዘቡን አውጥቶ እንዲሰራ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አሁን በተያዘው መንገድ ግን መተማመን መፍጠር አይቻልም፡፡ ይሄ በግምት የሚሰራው አሰራርም መፈተሽ አለበት። በኢትዮጵያ የአመት ሽያጩ 500 ሺ ብር የሆነ ነጋዴ የቫት ተመዝጋቢ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ የተጣለው የቀን ገቢ ግምት ደግሞ አብዛኞቹን ወደዚህ መስመር የሚያስገባ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ነጋዴዎቹ የቫት ተመዝጋቢ ስለሚሆኑ 15 በመቶ ጭማሪ ወደ ሸማቹ ወይም አገልግሎት ፈላጊው ይጫናል፡፡ ቀድሞ የሚያገኘው ትርፍ እንዳይጓደልበት በመስጋትም ነጋዴው ሸክሙን ለሸማቹ ሊያጋራም ይችላል - ዋጋ በመጨመር፡፡ በዚህም ሁኔታ  የገበያ አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ የሚሆነው ግን በዚህ የተነሣ የንግዱ ማህበረሰብ በስራው ላይ መተማመን ካጣ ነው፡፡ መተማመን ካጣ ሸቀጥን ወደ መደበቅ ይገባል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ የገበያ ቀውስ ይፈጥራል፡፡

--------------------------

                                “ግመታው በሳይንሳዊ ጥናት መፈተሽ ነበረበት”
                                    ዶ/ር አንዷለም (በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር የማይክሮ ኢኮኖሚ ዲፓርትመንት ኃላፊ)

         አንድ መንግስት ምን ያህል ታክስ ነው መሰብሰብ ያለበት የሚለው መጀመሪያ መታየት ያበት፡፡ በበርካታ አገሮች  ታክስ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ ያለው አስተዋፅኦ ይለያያል፡፡ ባደጉት ሀገራት ማንኛውም የገንዘብ እንቅስቃሴ በዘመናዊ መንገድ ነው የሚያልፈው፡፡ መረጃ መደበቅም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እንደኛ ባለ ሀገር ግን የታክስ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ በስካንዲኔቪያን ሀገራት፤ ከሚሰበሰበው ታክስ ሁሉም በፍትሃዊነት ይጠቀማል የሚል እምነት ስላለ ሁሉም በፍቃደኝነት ነው ግብር የሚከፍሉት፡፡ ለመደበቅ ጥረት የማድረግ እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወደኛ ሀገር ስንመለከት፣ በሁሉም ሂደት ገና ብዙ ይቀረናል። ምክንያቱም አንደኛ የፋይናንስ መረጃ ስርአታችን እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ የመንግስት አካላት የመረጃ ዘዴያቸው እጅግ ደካማ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መንግስት ታክስ የማግኘቱ ምጣኔ ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል ታክስ ለመክፈል የማህበረሰቡ ፍላጎትም ዝቅተኛ ነው፤ ምክንያቱም ዘመናዊ አሰራር ተዘርግቶ መተማመን አልተፈጠረም፡፡
እኔ ሶስት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ይታዩኛል። አንደኛ፤ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የመፍትሄ መንገድ፣ አሁን ግብር ሰብሳቢው ከግምት ውጪ መስራት የሚያስችለው አቅም ስለሌለው፣ይሄ ደግሞ ብዙ ውስብስብ ችግር ስለሚፈጥር፣ መጀመሪያ ቢዝነሶች በስርአቱ ላይ መተማመን እንዲያዳብሩ መጣር ያስፈልጋል፡፡  ይሄን ግመታ ለመስራት ሲታቀድ፣ ከአማካሪ ድርጀቶች ጋር በሳይንሳዊ ጥናት መፈተሽ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሴቶች የውበት ሳሎን ሁልጊዜ ተመሳሳይ ገቢ አያገኙም፡፡ በሰርግ ወቅትና በሌላው ጊዜ አንድ አይሆንም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች በሳይንሳዊ መንገድ መጠናት አለባቸው፡፡ ዝም ብሎ ግመታ ማስቀመጥ መተማመንን ያሰጣል፤ ምክንያቱም አሰራሩ ግልፅ አይደለም፡፡ ይሄ አሁንም በድጋሚ መታሰብ አለበት።
በመካከለኛ እቅድ ደረጃ ደግሞ ከግምት ስርአት መውጣት ነው፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን ማስፋፋትና ስርአቱንም ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ጋ ያለው ችግር ማሽኑ ትክክለኛ መረጃ ለግብር ሰብሳቢው ቢልክም ያንን መረጃ በሚገባ የሚተነትን ብቁ ባለሙያ ያለመኖሩ ነው፡፡ ይሄን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ በርካታ የተማሩ ወጣቶች አሉ፤እነሱን አሰልጥኖ የሰው ኃይሉን ማዘመን ለምን አይቻልም? ለምሳሌ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመርቀው ስራ አጥ ሆነው የተቀመጡ ወጣቶች አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የግብር አስከፋዩ መስሪያ ቤት እና ባንኮች ተናበው መስራት አለባቸው፡፡ ያ አለመናበብ ብዙ ችግሮች ይፈጥራል፡፡ ይሄም የሚቀረፍበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡
በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ መገንዘብ ያለብን ሰዎች በተገቢው ታክስ ሊከፍሉ የሚችሉት በታክስ ስርአቱ ላይ እምነት ሲያሳድሩ ነው፡፡ የተሰበሰበው ገንዘብ መንግስት በአግባቡ እየተጠቀመበት ነው፤ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም እየከፈለ ነው፤የሚለውን ስሜት ወደ መፍጠሩ ነው መሄድ ያለብን፡፡ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መተማመን መፈጠር አለበት። 

Read 5052 times