Saturday, 22 July 2017 15:23

አዲስ አበባ በኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ቀዳሚነቱን ይዛለች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

የኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ መጠን መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን አገሪቱ በበሽታው ወረርሽኝ ውስጥ እንደምትገኝ ተጠቆመ፡፡
የፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው ስልጠና ላይ እንደተገለፀው፤ ዘንድሮ (በ2009) አገሪቱ የሚታየው አጠቃላይ የስርጭቱ ምጣኔ 1.18% ደርሷል፡፡
በዓለም አቀፍ የኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝ ስርጭት መለኪያ መሰረት፤ የስርጭት መጠኑ ከ1% በላይ ከሆነ አገሪቱ በወረርሽኝ ውስጥ እንዳለች እንደሚያመለክትና ኢትዮጵያም ከዓለም አቀፍ መለኪያ በላይ የስርጭት ምጣኔ ውስጥ ስለምትገኝ በኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝ ውስጥ እንደምትገኝ ተገልጿል፡፡
በአገሪ ከፍተኛው የኤችአይቪ ስርጭት ከሚታይባቸው አካባቢዎች ዋንኛው አዲስ አበባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከተማው ስርጭቱ 4.9 መድረሱን፣ ባለፉት ዓመታት በጋምቤላ ክልል ይታይ የነበረውን የአራት በመቶ ስርጭት በመብለጥ አዲስ አበባ ቀዳሚነቱን መያዟ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ 718 ሺ 500 ሰዎች በበሽታው መያዛውን ከእነዚህ መካከል 204 ሺ 481 የሚሆኑት በአማራ ክልል፣ 185 ሺ516 የሚሆኑት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል፣ 127 ሺ 619 የሚደርሱት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙና 68 ሺ 971 የሚሆኑት በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በሦስቱ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙት የኤችአይቪ ኤድስ ህሙማን በአገሪቱ የሚገኙትን አጠቃላይ የኤችአይቪ ኤድስ ታማሚዎች 82% እንደሚይዝም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡ የስርጭት ምጣኔውን በተመለከተም አዲስ አበባ በ4.9% ከፍተኛውን ደረጃ ሲይዝ፣ ጋምቤላ ክልል በ4% ይከተለዋል፡፡ አነስተኛ የስርጭት ምጣኔ የሚታየውም በደቡብ ክልል መሆኑ ተገልጿል፡፡   
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች በሽታው በከፍተኛ መጠን እንደተገኘባቸውና 25% የሚሆኑት ወይም ከአራት ሴተኛ አዳሪዎች መካከል አንዷ የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ መታወቁም ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት በበኩሉ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከትናንት በስቲያ በፓናሮማ ሆቴል አዘጋጅቶት በነበረው አውደጥናት ላይ እንደተገለፀው፤ በከተማው የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሄዷል፡፡ አቃቂ ቃሊቲና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍና በሴተኛ አዳሪዎች ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የስርጭት ምጣኔ ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት ተነድፎ ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የ9.5 ሚ. ብር የገንዘብ ድጋፍ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የበሽታውን ስርጭት በ2030 የማቆም ራዕይ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን እስከ አሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ከ39 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ህይወታቸውን በኤችአይቪ ማጣታቸው ተገልጿል፡፡

Read 7420 times