Monday, 17 July 2017 13:26

ባህርዳር - ከቱሪዝም እስከ ጣና ሃይቅ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ከተቆረቆረች ስምንት አስርት ዓመታት ባስቆጠረችው የባህር ዳር ከተማ ባለፈው ሳምንት (ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2)
አምስተኛው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ለመታደም ባህር ዳር
የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በከተማዋ የቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም
ጣና ሃይቅ በተጋረጠበት አደጋ ዙሪያ ከከተማዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ጋር
ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

-  ባህር ዳር በተፈጥሮ ለነዋሪዎቿ የምትለግሰው በረከት ብዙ ነው
-  በወር አንድ ጊዜ ከንቲባው የሚሳተፉበት የህብረተሰብ የፅዳት ዘመቻ ይካሄዳል
-  ባህር ዳር ላይ የተከፈተ ዘመቻ አለ፤ ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ ናት
-  ለደራሲ አያልነህ ሙላቱ ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል


አምስተኛው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በከተማዋ መከበሩ ምን ፋይዳ አለው?
5ኛው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በከተማችን ባህርዳር ካለፈው አርብ እስከ እሁድ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ ከተማችን ባህርዳር በተለይም በከተማ አስተዳደሩ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጥያቄውን ለአስተዳደሩ አቀረበ፡፡ የከንቲባ ኮሚቴውም በዓሉ እዚህ መከበሩ ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢውን ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፋይዳውን በተመለከተ የሙዚቃ ቀኑ ሲከበር በተለያዩ ዝግጅቶች ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹የአማራ ክልል ሙዚቃ ከየት ወደየት›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት የአማራ ክልል ሙዚቃ የበፊቱም ሆነ አሁን ላይ ያለው ምን ያህል ከእነ ህልውናው ቀጥሏል፣ የአማራ ህዝብ ሙዚቃዊ ትውፊቶች ከእነ መሰረታቸው ቀጥለዋል ወይስ ተበርዘዋል የሚሉ ሁኔታዎች በስፋት ተዳስሰዋል፡፡ አምስተኛው የሙዚቃ ቀን እዚህ ሲከበር የከተማችንም ሆነ የክልላችን ወጣት ሙዚቀኞች፤ ስለ ባህላዊ ሙዚቃዎቻቸው የበለጠ ግንዛቤና መነቃቃትን ያገኛሉ፣ በሌላ በኩል ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ የሙዚቃ ድግስ ሲሆን ተዳሚው የከተማችን ህዝብ ነው፤ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣት ሙዚቀኞች አሉ፣ ወደፊት ሙዚቀኛ የመሆን ህልም ያላቸው አሉ፤ ሙዚቃውን ያቀረቡት ትልልቅ የአገራችን ሙዚቀኞች እንደመሆናቸው፣ ህዝቡ ከመዝናናት ባለፈ ወጣት አርቲስቶች ከእነዚህ አንጋፋዎች የሚወስዱት ልምድ ይኖራል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ትልልቅ ፋይዳዎች የተነሳ የሙዚቃ ቀኑ እዚህ እንዲከበር ፈቅደናል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የሙዚቃ ቀን በከተማዋ እንዲከበር ከመፍቀዱ ውጭ በገንዘብም ሆነ በሌላ መልኩ ያደረገው ድጋፍ አለ?
በዓሉ እዚህ እንዲከበር ከመፍቀድ ባሻገር አዘጋጁ አልባብ የሙዚቃና የቴአትር ፕሮሞሽን ባቀረበልን ጥያቄ መሰረት፤ የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በሌላ በኩል ዝግጅቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለእንግዶች የመኝታ፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ አገልግሎት አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉ አስተዳደራዊ ድጋፎች በማድረግ፣ ፕሮግራሙ ያለምንም እንከን ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከተማ አስተዳደራችን ከፍተኛ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በአገራችን ትልቁ ሀይቅ ጣና የአማራ ክልል ወይም የኢትዮጵያ ሀብት ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ለአደጋ መጋለጡ እየተነገረ ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ይህን ሀይቅ ለመታደግ ምን እየሰራ ነው?
እንግዲህ  ‹‹አባይ መቀነቷ ጣና ነው ደረቷ›› የሚባልላት ከተማ ናት፤ ባህርዳር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አባይ ከተማዋን መሀል ለመሀል ሰንጥቆ ስለሚያልፍና ጣና ደግሞ የከተማዋን ግማሽ አካል ስለሚሸፍን ነው፡፡ ለባህርዳር ከተማ መመስረት ብቻ ሳይሆን ለእድገቷ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉት አባይና ጣና ናቸው፡፡ አንቺም እንዳልሺው ጣና ላይ እየደረሱ ያሉ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትና ለመከላከል ብዙ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከብክለት ጋር በተያያዘ ከተማው እያደገና እየተስፋፋ ሲሄድ ወደ ሀይቁ የሚገቡ የተለያዩ ፍሳሾች፣ በሀይቁ ላይ ደለል የመስራት ሀይል ስላላቸው፣ ይህን ለመከላከል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በምን መልኩ ነው የመከላከል ሥራው እየተሰራ ያለው?
እነዚህን የመከላከል ስራዎች የምንሰራው ከከተማ አስተዳደሩ የብዝሀ ህይወት ድርጅትና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ሀይቁ የሚገባውን ደለል ለመከላከል የተለያዩ የሳር ዝርያዎችን ለምሳሌ ቀድሞም ይሁን አሁን ባህርዳር የምትታወቅበት ደንገል (ፓፒረስ) የተባለ ሳር በብዛት በመትከል፣ ወደ ሀይቁ ንፁህ ብቻ ፍሳሽ እንዲገባ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ በጎርፍ የታጠበ አፈርም ቢሆን በሳሩ ስር ይያዝና ውሃው ብቻ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል በከተማ አስተዳደሩ ይሁንታ በጣና ዙሪያ የሚገነቡ ቱሪስት መጥን ሆቴሎች፣ ሎጆች የመዝናኛ ማዕከላት ይገኛሉ። እነዚህ ማዕከላት የሚያመነጩትን ቆሻሻ ወደ ሀይቁ እንዳይለቁ የቁጥጥር ስራ ይሰራል፡፡
እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት?
የመጀመሪያው ሆቴሎቹም ሆኑ ሎጆቹ ገና ሲገነቡ ዲዛይናቸው ይጠናል፡፡ የሀይቁን ደህንነት ይጎዳሉ አይጎዱም የሚለው ይታያል፡፡ ከተሰሩም በኋላ ፍሳሽ ቆሻሻ እንዳይለቁ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል። በቀጣይም ጣናን እንዴት ከጉዳት ጠብቀን እናስቀጥለው ለሚለው ስትራቴጂ ተቀርፆለት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በሀይቁ ላይ ስለዘመተው ‹‹እምቦጭ›› የተባለ አረም ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ምርምር እየሰራ ነው፤ ሰርቶ ያገኘውም ውጤት አለ፡፡ ይህን አረም ለማጥፋት ምን ምን ያስፈልጋል በሚለው ላይ ከተማ አስተዳደሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመምከር ላይ ይገኛል፡፡
ባህርዳርን የሚያዋስኑ በጣና ደሴቶች ላይ የሚገኙ ገዳማት፣ ሙዚየሞችና በርካታ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች ይበልጥ ሳቢ ለማድረግ ከመሰረተ ልማት፣ ለህዝብ ግንዛቤ ከማስጨበጥና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን እየሰራችሁ ነው?
ባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተብሎ የሚጠራው ይህ መሀል ያለው ከተማ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው የሚገኙ ሳተላይት ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎችንም ይጨምራል፡፡ በተለይ ዘጌ ባህረ ገብ መሬት ነው፤ ግን ሙሉ በሙሉ ውሃ ሳይሆን በአንድ ጎን የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ አለው። ክብራን አለ፤ እንጦሮስ አለ፤ ደብረ ማሪያምም አለ፡፡ እራቅ እያልሽ ስትሄጂ ደጋ እስጢፋኖስ፣ ናርጋ ስላሴና ጣና ቂርቆስ የሚባሉ ገደማትም አሉ። እኛም ከባህር ዳር ሀገረ-ስብከት ጋር በመነጋገር፣ እነዚህ ገዳማት በተለይ እንጦሮስ ኢየሱስ፣ ክብራን ገብርኤልና ዘጌ ፔንሱላ ያሉ ሁሉም ማለትም ዘጌ ጊዮርጊስ፣ በትረ-ማሪያም፣ አዝዋ ማሪያም፣ ኡራ ኪዳነ-ምህረት፣ ይጋንዳ ተክለሀይማይኖት ይገኛሉ፡፡ በነዚህ ገዳማት ውስጥ ደግሞ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ስር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተፈጥሮአዊ ሀብቶችና ገዳማት ለከተማዋ የቱሪዝም መስፋፋት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሀብቶች እንዴት ይበልጥ ተደራሽ እናድርጋቸው፣ በእነዚህ ገዳማት ዙሪያ ያሉ ህዝቦች በምን መልኩ ተጠቃሚ ይሁኑ የሚባለው ተጠንቶ፣ ‹‹ናቡ›› ከተባለ ድርጅት ጋር እየሰራ ነው፡፡ ስራው ይበልጥ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ቅድም እንዳልሽው፣ የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግና ይበልጥ በማስተዋወቅ ከተማዋም ክልሉም ሆነ አገሪቱና ህዝቧ ከዚህ ጥቅም የሚያገኙበት ስራ እየተሰራ ነው፡፡
ከእነዚህ ገደማት የትኛው ነው ይበልጥ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስበው?
በተለይ ዘጌ ፔንሱላ ነው የቱሪስት መናኸሪያ የሆነው፡፡ በነገራችን ላይ ከነዚህ ገዳማትና አድባራት ባለፈ የተለያዩ አዕዋፋትና የዱር አራዊት ዝርያዎች በጣና ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ አዕዋፋትና አራዊት ቁጥር እንዲጨምር የማድረግ ስራም እየተሰራ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየገዳማቱ ያለው ነዋሪ ህዝብ፣ የተለያዩ ባህላዊ ጌጣጌጥ፣ አልበሳት፣ የእጅ ስራ ውጤቶችንና ከገዳማት የሚገኙ ፍራፍሬና የጫካ ቡና ለጎብኚዎች በማቅረብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ነው፡፡ ግን ተጠቃሚነቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ፣ ህዝቡን የማዘመን ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሁሉም በሂደት ላይ ነው፤ ውጤቱ በቅርቡ ይታያል፡፡ በየገዳማቱ የቱሪስት አስጎብኚ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አሉ፡፡ እነዚህ ማህበራት ወጣቶች ተደራጅተው የሚሰሯቸው ናቸው፡፡ አስጎብኚ ድርጅቶች የትርጉም አገልግሎት በመስጠት፤ ለሽያጭ የሚቀርቡ እቃዎችን ለጎብኚው እይታ ምቹ በማድረግ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ባህርዳር ከተማ በተፈጥሮ ለነዋሪዎቿ የምትለግሰው በረከት ነው፡፡ ነገር ግን ያለንን ሀብት ከዚህ በላይ ለመጠቀም ብዙ መስራት አለብን፤ ይሄ የቤት ስራችን ይሆናል፡፡
ባህርዳርን ቀድሞ ሳውቃት በጣም ንፁህና ሰላም የምትሰጥ ከተማ ነበረች፡፡ ህዝቡ እሁድ እሁድ መጥረጊያ ይዞ የፅዳት ዘመቻ ይወጣ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሰሞኑን በከተማዋ ስዘዋወር በተለይ ገበያው አካባቢ ቆሽሾ ነበር፤ መጥፎ ሽታም ነበረው፡፡ ምንድን ነው ችግሩ?
የባህርዳር ከተማን ፅዳትና ውበት በተመለከተ፣ የከተማ አስተዳደራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ከተማዋ በፊትም ሆነ አሁን በጣም ንፁህ ናት፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል የነበራት ስፋት አለ፤ አሁን ያላት ስፋት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በበፊቱ የከተማዋ ስፋት ልክ የሚያፀዱ የፅዳት ሰራተኞች አሉት፡፡ የከተማዋ ስፋት ግን በጣም ጨምሯል፡፡ ከተማው እያደገ በመጣ ቁጥር ከዚያ ጋር የሚመጣጠን የፅዳት አገልግሎት መስጠት ስለሚገባን፣ አንድም መንግስት በጀት መድቦ የሚሰራው ስራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፅዳት ስራውን አውትሶርስ በማድረግ ወጣቶች በየክፍለ ከተማው ተደራጅተው በደንብ እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ ቀደም ሲል “ድሪምላይት” የተባለ ማህበር ብቻ ነው የነበረው፡፡ አሁን በሁሉም ክ/ከተማ የፅዳት ማህበራት አሉ፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ ነው፡፡ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ከከተማ አስተዳደሩ የሩዋንዳን ዋና ከተማ የኪጋሊን ተሞክሮ የሚቀምር አንድ ቡድን ወደ ኪጋሊ ሄዶ ነበር። እንደሚታወቀው ኪጋሊ በአፍሪካ ደረጃ በፅዳት በኩል ሞዴል ናት። ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት፣ በወር አንድ ጊዜ የከተማ መስተዳድሩም ከንቲባውም የሚሳተፉበት የህብረተሰብ የፅዳት ዘመቻ ይካሄዳል፡፡
ለዚህ ዘመቻ የተመረጠ ቀን አለ ወይስ በዘፈቀደ በወር አንድ ጊዜ ነው የሚደረገው?
በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ሁሌም ወር በገባ በ27ኛው ቀን የፅዳት ዘመቻው ይካሄዳል፡፡ ሁሌም በ27 ፅዳት አለ፡፡ ይህ አሰራር ገና አዲስ ነው፤ ግን ላለፉት 3 ወራት ተካሂዷል፤ ውጤታማ ነው ይቀጥላል፡፡ የመሪዎቹ ሚና የህብረተሰቡን ተነሳሽነት ለመጨመር ስለሆነ በዘመቻው ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ገበያው አካባቢ የሚታየው የመቆሸሽ ሁኔታ ጊዜያዊ ነው፡፡ እውነት ነው እዚያ አካባቢ በርካታ ግብይት የሚካሄድበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከተማዋ ከአንድና ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጥ የገበያ ማዕከል ይኖራታል። ምክኒያቱም የነበረው የገበያ ቦታ በሙሉ ፈርሶ በዘመናዊ መንገድ እየተሰራ ነው፡፡ በፈጣን ሁኔታ እየተሰራ በመሆኑ አንዳንዶቹ ተጠናቅቀው ውጭ ላይ ይነግዱ የነበሩት ወደ ህንፃ እየነገቡ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ሁሉም ቦታ ቦታውን ይይዛል፡፡ አሁን የሚታየው መጠነኛ የመቆሸሽ ሁኔታ ያን ጊዜ አይኖርም፡፡
በከተማዋ ላይ የፀጥታ ችግር እንዳለ በሰፊው ይወራል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ ናት፡፡ ህዝቡ በሰላም የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያከናውናል፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያለምንም ችግር ስራዎቻቸውን ይሰራሉ፡፡ ወደ ከተማችን ለመዝናናትም ሆነ ለስራ የሚመጡ እንግዶች በሰላማዊ መንገድ ተዝናንተውና ስራቸውን ሰርተው ይመለሳሉ። ነገር ግን ባህር ዳር ከተማ ላይ የተከፈተ ዘመቻ አለ። ዘመቻው ከማን፣ ለምን እና ከየት እንደተከፈተ አሁን ለጊዜው እንተወው። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቀው የበሬ ወለደ አይነት ወሬ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወይም ነሐሴ ገደማ በአካባቢውና በአጎራባች ቦታዎች አለመረጋጋቶች ነበሩ። እነዚህ አለመረጋጋቶች መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ፣ ስራዎች ተሰርተው መረጋጋት ተፈጥሯል። ሁሉም ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ ባህር ዳርም ወደቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች፡፡ ግን ውጭ ውጭውን የሚወራ አለ፡፡ ከአዲስ አበባና ከሌሎች ቦታዎች እየተደወለ “ከተማዋ ላይ ሰላም እንደሌለ ሰምተናል፤ ምንድን ነው” ይሉናል፡፡ እዚህ ፍፁም ሰላማዊ ነው፡፡
ታዲያ የወሬዎቹ መነሻዎች ምንድን ናቸው ይላሉ?
እሱ ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ አሁን በቅርቡ አንድ የሆነውን ነገር ልንገርሽ፡፡ አንድ እስረኛ ከእስር ቤት ሊያመለጥ ሞከረ፤ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ይሄ የሆነው ከ30 ደቂቃ ባልበለጠ እንቅስቃሴ ነው፤ ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ባህር ዳር በከፍተኛ የመሳሪያ ተኩስ እየተናወጠች እንደሆነ ተደርጎ ተወራ፤ በጣም ነው የገረመኝ፡፡
ምናልባት እስረኛውን ለመያዝ ተተኩሶ ይሆን?
በፍፁም! ምንም አይነት ተኩስ የለም፤ እስረኛው በቀላሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡ የሆነውና የተወራው ግን ምንም አይገናኝም፡፡ ይሄ እንግዲህ ሆን ተብሎ ከተማዋ ላይ የተከፈተ ዘመቻ ነው፡፡ የከተማው ህዝብ ስለ እስረኛው ማምለጥና መያዝ የሚሰማው ከአዲስ አበባ ተደውሎለት ነው። ከተማዋ ምን ሆና ነው ይላሉ። ነገር ግን እዚህ ከተማ ላይ የሚኖር ህዝብ አለ፡፡ ችግር ከተከሰተ ይመለከታል ይታዘባል፡፡ ለማንኛውም አሁንም አስረግጬ የምናገረው፤ ባህር ዳር ከተማ ፍፁም ሰላማዊና ምቹ ከተማ ነች፡፡ ሁሉም ሰው ወደ ውቢቷ ከተማችን ይምጣ፤ ይዝናና፤ ይስራ ይረፍ፡፡ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም፡፡ በጥሩ ሁኔታ በጥሩ መንፈስና መስተንግዶ ረክቶ ይመለሳል፡፡
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በነበረው አለመረጋጋት፣ የቱሪስት ፍሰቱ መቀዛቀዝ አሳይቶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ አለመረጋጋት የከተማዋን ቱሪዝም ምን ያህል ጎድቶታል? አሁን ያለውስ ሁኔታ ምን ይመስላል?
እንዳልሺው በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት እንደ ማንኛውም የአገሪቱ ከተሞች የቱሪዝም ፍሰቱ ላይ መቀዛቀዝ ነበረ፡፡ ይህም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢም መጉዳቱ አይቀርም፤ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ተስተካክሎ ወደቀደመ ሁኔታው ተመልሷል፤ ገቢውም በዚያው ልክ ያድጋል፡፡ ንፅፅሩን ከከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ማግኘት ይቻላል፡፡  
ደራሲ፣ ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በ2000 ዓ.ም ከከተማ አስተዳደሩ ባህር ዳር ላይ ቦታ ወስዶ አንድ ነገር እንዲሰራ በተጋበዘው መሰረት ቦታ መርጦ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ካርታ ቢወስድም ላለፉት ሰባት ዓመታት ቦታውን ሳያገኝ መቅረቱንና በዚህም ቅር መሰኘቱን ገልጿል፡፡ እርስዎ ይህን ጉዳይ ያውቁታል?
ጉዳዩን አውቀዋለሁ፡፡ ‹ባህር ዳር ፊት ነሳችኝ› ብሎ አዲስ አድማስ ላይ ያቀረቡት ቅሬታም አንብቤያለሁ። ጋዜጣው ላይ የወጣውን ቃለ ምልልስ የተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎችም ለጥፈውት ተመልክቻለሁ፡፡ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውም መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን የከተማችን አሁን ያለው አመራር፤ ጥያቄያቸውን በፅሁፍ አቅርበው ስለነበር ጉዳዩን ቁጭ ብለን መርምረናል፡፡ ቦታው ተሰጣቸው የተባለው በሚሊኒየም በዓል አካባቢ ነው፡፡ ቦታውም አባይ ዳር ላይ ነው ከድልድዩ ጎን። ነገር ግን ይህ ቦታ ከ3ኛ ወገን ነፃ አልነበረም። ያን ጊዜ አባይና ጣና ዙሪያ የተለያዩ የማልማት እንቅስቃሴዎችም ነበሩበት፡፡ ከዚያ በኋላ ቦታውን ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ቦታው ላይ ያሉ ሰዎች እንዴት ይነሱ? ለነዚህ ተነሺዎች ካሳ ማን ይከፍላል? የሚሉ አከራካሪ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ቅሬታቸውን ለክልል አመራሩና ለከተማ አስተዳደሩ አመለከቱ፤ ከዚያ በኋላ ጣናና አባይ ዙሪያ ላይ ምንም ዓይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ መመሪያ ተላለፈ፡፡ በዚያ ምክንያት ሌላ ተለዋጭ ቦታ ውሰዱ ሲባሉ በፍፁም አሉ። በቃ ከሰጣችሁኝ ያንኑ ቦታ ስጡኝ፤ ያለበለዚያ ተዉት አሉ፡፡
መጀመሪያውኑ ቦታው ከሶስተኛ ወገን ነፃ ሳይሆን ለምን ቦታውን ውሰዱ ተባሉ? ለምንስ ማዘጋጃ ቤቱ ካርታ ሰጠ?
እንግዲህ ይህንን ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው በወቅቱ የነበረው አመራር ነው፡፡ ሁለተኛ በዛን ወቅት ከሶስተኛ ወገን ነፃ ተደርጎ የሚሰጥበትና፣ ነፃ ሳይደረግ ለኢንቨስተሩ ተሰጥቶ ያንን ሶስተኛ ወገን ጥቅሙን አስጠብቆ የማስነሳት አካሄድ ነበር፡፡ ምትክ ቦታ በመስጠት ሊሆን ይችላል፤ ካሳ በመክፈል ሊሆን ይችላል ሶስተኛው ወገን የሚነሳው። አሁን ደግሞ ነፃ አድርጎ የመስጠት ሁኔታ አለ፡፡ ዞሮ ዞሮ እንዲህ ባለ መልኩ ስጉላላ ከረምኩ ብለው በፅሁፍ ቅሬታቸውን ለከተማው ከንቲባ አቅርበው፣ ከንቲባውም ለከንቲባ ኮሚቴ ጉዳዩን አቅርበዋል፡፡
ግን ጥያቄው ተገቢ ነው አይደለም?
ጥያቄያቸው ተገቢ ነው አይደለም በሚለው ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ይህንን ጉዳይ ከተማ አስተዳደሩ ብቻውን ስለማይጨርሰው፣ ቦታው ሲሰጥ የክልሉ ይሁንታም ስለነበረበት፣ አባይና ጣና ዙሪያ ቦታ መስጠትም ስለተከለከለ … ምን መሆን አለበት በሚለው ዙሪያ የከንቲባ ኮሚቴው የራሱን ውሳኔ ወስኖ ለክልል አቅርቧል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ይህ የሆነው እሳቸው ቅሬታቸውን አዲስ አድማስ ላይ ከማቅረባቸው በፊት ነው፡፡ እሳቸው ግን ጉዳያቸው እንደታየላቸው ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ እኛ እያየንላቸው ለምን ሚዲያ ላይ ቅሬታቸው አቀረቡም አንልም፤ መብታቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ እስከዛሬ ያልተስተናገዱት የእሳቸው ፕሮጀክት ስለማይጠቅም አይደለም፡፡ በእሳቸው ላይ ለመጥመም አይደለም፡፡ በጠቀስኩልሽ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች የተነሳ ብቻ ነው፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን መዘግየት አልነበረበትም በሚለው ላይ ሁላችንም እንስማማለን፡፡
Read 2030 times