Monday, 17 July 2017 13:07

የይሁዳ ደብተር

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(16 votes)

አስክሬኑን ሳየው አሳዘነኝ፡፡ ኩርምት ብሎ ወድቋል። ከአይኑ ሥር ቁልቁል ወደ ጉንጮቹ የወረደው እንባ መስመር ሰርቷል፡፡ ዓይኖቹ ተከድነው፣ የታች ከንፈሩ ቆሥሏል፡፡ ምናልባት በሰራው ሥራ ቁጭት፣ ነክሶት ይሆናል፡፡ እግሮቹ አካባቢ በተለይ ተረከዙ፣ ተሰነጣጥቋል። ብርድና ቁር የተፈራረቀበት ዓይነት፡፡
መንገደኛው ሁሉ አገላብጦ አይቶ ትቶታል። አንድ ሰው እንኳ “ከመንገድ ዳር ፈቅ አድርገን እንቅበረው” ያለ የለም፡፡ የሰው ልጅ ጨካኝ እየሆነ ነው፤ አልኩ በልቤ፡፡
ከአንድ የኔ ቢጤ ስሜት ካደረበት ሰው ጋር ሆነን፣ ኪሱን ፈታተሽን፡፡ ጥቂት ገንዘብ ቀርቶታል። መሀረም፣ ስለት ቢጤና ትልቅ የማስታወሻ ደብተር ነገር አለው፡፡
“በቃ በዚህች ገንዘብ ላይ ጥቂት ከራሳችን ጨማምረን እናሥቀብረው!” አለኝ፤አብሮኝ ያለው ሰውዬ፡፡
እኔ ግን ልቤ ደብተሩ ላይ ነው፡፡ ውስጡ የተጻፈው ምን ይሆን? ብዬ፡፡
እኔ ለነገሩ፤ የአይሁዶችም የኢየሱስም ወገን አይደለሁም፡፡ ይልቅስ የግሪኩና የሮማው ፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ ቀልቤን ሰርቆኛል፡፡ መሪ አልሆንም እንጂ መሪ ብሆን፣ ኢየሱስም የራሱን፣ እነዚያም የራሳቸውን እያስተማሩ፣ አፈንጋጮቹም እየተፈላሰፉ፣ ይቀጥሉ ብዬ እፈቅድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እውነት የሆነው ያሸንፍ!
ሰዎች ግን አስቸጋሪ ነን፤ የራሳችንን እውነት ማስተማር ብቻ ሳይሆን መጋት፣ ካልሆነ የማንፈልገውን መግደል እንሻለን፡፡ ጎን ለጎን፣ ትይዩነት የለም፡፡ ስለዚህ አይሁድ፤ ኢየሱስ የሚባለውን መምህር ከወንበዴዎች ጋር ሰቀሉት። በእርሱ ጣጣ፣ ይህ ምስኪን ሰው ደግሞ ራሱን አጠፋ፡፡
ማስታወሻውን ከፈትኩት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ አሳብ ሰፍሯል፡፡ ጴጥሮስ ለዓሣ መግዣ የወሰደው፣ ዮሐንስ ለሙዝ፣ ፊሊጶስ ለእንጀራ … እያለ ይቀጥላል። እርሱ አላጓጓኝም፤ የይሁዳ ሕይወት ምን ይመስል ነበር? … የሚለውን ለማወቅ ነው የጓጓሁት፡፡ ሊፅፈውም ላይፅፈውም ይችላል፤ ግን ሕይወቱ ምስቅልቅልና እረፍት የለሽ ይሆን? ወይስ እንደ ኢየሱስ የተረጋጋ! … ባልንጀሮቹስ?
ወደ መጨረሻዎቹ ገፆች ዘለልኩ፡፡  እንዲህ ይላል፡-
ልክ ኢየሱስ ጉንጬን ሲስመኝ ስሜቴ ሁሉ በላብ ተጥለቀለቀ፡፡ ውስጤ ተረበሸ፡፡ በተለይ የፊጢኝ ሲያሥሩት ልቤ - ረገጠችኝ፤ ነፍሴ ተወራጨች። ኪሴ ውስጥ ያለው ብር፣ የከረጢቱ ሂሳብ ሁሉ ገፈታተረኝ። ዓይኔ በደም ሰከረ፣ … አይሁድ ይዘውት የመጡት ሰይፍ፣ ችንካር፣ መዶሻ፣ መጋዝ ሁሉ-- ሰውነቴን በየተራ ዘለዘሉት፣ ቆራረጡት፡፡
አሁን ወዴት ልሂድ! …. በፊት ያሰብኩት ሀሳብ ትክክል አልነበረም፡፡ አይሁድ አታልለውኛል፡፡ እኔም ስሜታዊ ሆኛለሁ፡፡ እኔ አሳልፌ ብሰጠውም ባልሰጠውም፣ ነገሩ የተቆረጠ ስለሆነ ኢየሱስን ማዳን አልችልም ብዬ ነው ብሩን የተቀበልኩት፡፡ … ቢቀርብኝ ይሻል ነበር፡፡ የእኔ እጅ ሳይገባበት ዓይኔ ሳያይ የወደዱትን ባደረጉት ኖሮ!
የዚያች ዓይነ-ትላልቅ ሴት-ፍቅርም የሆነ ነገር ፈጥሮብኛል፡፡ እርሷን ካገኘሁ በኋላ  ከጌታዬ መለየት፤ ቤት መሥራት፣ ጎጆ መቀለስ አምሮኛል፡፡ ጌታ እያስተማረ በነበረበት ሰፈር፣ በጆሮዬ መጥታ “ልቤ ወድዶሃል!” ካለችኝ በኋላ ስንቴ ተመላልሼ አግኝቻታለሁ፡፡ ምናልባት ኢየሱስም ሳያውቅብኝ አልቀረም፡፡ “ይሁን የሚወድደኝ ቢኖር መስቀሌን ይሸከም ያልኩትን ታስታውሣለህ? ብሎኛል ራት ስንበላ፡፡ ሳቅ ብዬ ዝም አልኩት፡፡
ከዚያች ልጅ በኋላ ሂሳብም ላይ እጄን አስገብቻለሁ። ኢየሱስ የተቀባው ሽቶ እንኳ የቆጨኝ በዚህ መንፈስ ሆኜ ነው፡፡ በፊት ለብር ብዙም አልነበርኩም፡፡ ይልቅ ኢየሱስ ወሬውም ትምህርቱም፣ ምሳሌውም ይመስጠኝ ነበር። ሌላው ችግር ትዳር ያለመመስረቴ፣ ከዘመዶቼ መለየቴ ነው። በፊት በፊትማ ሁላችንም ከኢየሱስ የምንጠብቀው ሥጦታና ሥልጣን ነበር፡፡ እኔም ጌታ አይሁድን ሲታደግ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። እርሱ ግን የማይሆን መሆኑ ከገባኝ ቆየ፡፡ በዚያ ላይ ኢየሱስ አንዳንዴ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ምስጢራዊ ወደሆነ ቦታ መሄዱ ይከነክነኝ ጀመር፡፡ አንዴ ወደ ተራራ … አንዴ ወደ ሌላ … “እኛስ ሃዋርያቱ አይደለ’ንዴ?” የሚል ቅናት ቢጤ ሳይሰማኝ አልቀረም፡፡ ማን ይሙት አሁን እኔ ከዚያ ከቀዥቃዣው ጴጥሮስ እብሳለሁ፡፡ … አሥሬ ሀሳቡን ከሚቀያይር ወፈፌ! ይህ ይህ ይናድደኛል፡፡
አሁን እረፍት አጣሁ፡፡ ይሄኔ ምን ያደርጉት ይሆን? … ጅራፍ ይዘዋል፤ ይገርፉታል፡፡ ሊሰቅሉትም ወስነዋል። እኔ ምን ነክቶኝ ነው ይህንን የፈፀምኩት? … ገንዘቡስ ምን ያደርግልኛል? እሺ መሬት ገዛሁበት፤ ከዚያስ? የኢየሱስ ሥቃይና መከራስ? … ምናልባት በተዐምር ራሱን ያስመልጥ ይሆን? ብዬም አስቤ ነበር፡፡ ቆይቶ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጡኝ፡፡ ተሰቅሏል፡፡
በቃ አሁን ከዚህ ሁሉ ጣጣ፣ ከዚህ ሁሉ እሳት፣ የሚገላግለኝን ገመድ ይዣለሁ፡፡ ትንሽ የሚቆጨኝ ተሰቅሎ ሳለ እንኳ ነፍሱ ሳትወጣ ይቅርታ ጠይቄው በነበር! … የወሰድኩትን ብር በፊቱ በትኜ፤ “ማረኝ” ብለው ኖሮ! … የይቅርታም ሰዓት ያልፋል ለካ! … የንስሃም በር ይዘጋል!
ያቺስ ሴት? … እርሷም እኔን ትዳር አ’ርጋ አብረን ልንኖር እየጠበቀች ነው፡፡ ቁንጅናና ፀባይ አላነሳት! … አብረን ብንኖር፣ ሰላም ቢሆን ደስ ባለኝ! … ግን ፀፀቱ! … ኢየሱስ እሾህ ነስንሶብኝ ሄደ፡፡
ምናልባት በዚህ መሬት ላይ የሕፃናት ማሳደጊያ ሰርቼ፣ የድሆችን ልጆች ባስተምርስ? እርም ነው ደግሞ! … ብሩ የደም ነው፡፡ የንፁህ ሰው ደም! ምናለበት መሞቴ ካልቀረ ከጌታ ጋር ብሰቀል! … ከእነ በደሌ ከምሞት በይቅርታ መንፈስ በንፅህና ብሰናበት?
ዮሐንስ አይሸሽም፡፡ ጴጥሮስ እርግጠኛ ነኝ ሀገር ለቅቆ ይጠፋል፡፡ ያዕቆብስ? … ጉዳቸው ፈላ። ወዴት ነው የሚሄዱት? … አንዲት ቅርስ የላቸው። ሥራቸውን አቁመዋል፡፡ ዓሣ አጥማጆቹ እንኳ ዓሣ ሊያሰግሩ ቢሄዱ፣ ቦታቸው ላይ ሌሎች ሰዎች ተተክተው አያሰሯቸውም፡፡ ኢየሱስ ግን ምን ማለቱ ነው? ሰውን ከየእንጀራው ነቅሎ ነቅሎ ሲያበቃ፣ በትኖዋቸው የሚሞተው? … ግን ለሞቱ የኔም እጅ አለበት፡፡ አሁን ቀጣዩ ነገር ምን ይሆናል? ሀገራችን መላዋ ምንድነው? … ጉዳችን ፈላ! እኔ እንኳ ጉዴ አሁን ብቻ ነው! ጓደኞቼስ?
ዝም ብዬ ከዚህች ቆንጆ ጆኮረዳ ጋር ብኖርስ? … እሷ እቅፍ ውስጥ ሆኜ አመልጣለሁ? ወይስ ፀፀት ከብብትዋ ሥር ቆፍሮ ያወጣኛል? አሁን በጊዜ ራሴን ማሸሽ አለብኝ። ከዚህ ሁሉ ጣጣ መውጣት ይጠበቅብኛል፡፡ ለሶስት ዓመታት ያበላኝና ያጠጣኝን ጌታዬ ሸጫለሁ፡፡ አሁን የህዝቡ ነቀፋ እንዴት ያኖረኛል? መዘባበቻ መሆኔ ነው?
እንባዬ አቃጠለኝ፣ ጉንጬ ብቻ አይደለም፤ ዓይኖቼን!... ምህረት ከማን መቀበል እችላለሁ? … ኢየሱስ እንደሆን አለፈ፡፡ ወይኔ ይሁዳ! … የተረገዝክ ቀን በእናትህ ማህፀን ውሃ ሆነህ በቀረህ ጥሩ ነበር፡፡ አማራጭ የለኝም፡፡ ራሴን ማስወገድ አለብኝ፡፡ ሰዎች ይሁዳ ጨካኝ ነው እንደሚሉኝ አውቃለሁ፡፡ ጨካኝ ግን አይደለሁም! … ራሴን የምገርፍ ጅራፍ ነኝ! .. ዕድለ ቢስ ነኝ! .. እንደኔ ላለው ማን ያዝንለታል? … ባገኘው የሚያዝንልኝና የሚረዳኝ ያው ራሱ ኢየሱስ ነበር፡፡ ግን እርሱንም አስወገዱት፡፡ የሰው ልጅ ከመነጋገር ይልቅ ባላንጣውን በማስወገድ ለምን ያምናል? … ኢየሱስ ወጣት ነው፣ አይሁድ ጠና ያሉ ናቸው፡፡ ለምንድነው የወጣት ሀሳብ የሚያንገፈግፋቸው? … የበለጠ ልምድ አለን ካሉ፤ ለምን ተከራክረው አያሳምኑትም? ለነገሩ መነጋገር መቻል ቀላል ነው እንዴ?
ያቺ ቆንጆ ፍቅረኛዬ፤ መሬቱን ልታይ ትመጣለች። ግን እኔ ከርሷ ጋር ከንፈር የምናጠቅበት ልብ የለኝም። ውስጤ ጭቅቅት ነው፡፡ ደሜ ቆሽሿል፡፡ ሳቅዋ አያጓጓኝም፤ ድምፅዋ እንደ ድሮ አያሰክረኝም። አካሄድዋ አይናፍቀኝም፡፡ “ምን ነበር ያለችኝን በቀደም?”፤ “በመጪው ዓመት ሙሽራዬ! ተብሎ እየተደለቀልን ቤታችን እንገባለን” ነበር ያለችኝ። ያጓጓል፡፡ ከርሷ ጋር መኖር ያጓጓል፤ ከኢየሱስም ጋር መኖር ደስ ይላል፡፡ ከእነ ገደባገደቡ! …
አሁን ግን ውስጤ ከድንኳን ኑሮ ወደ ጎጆ ምስረታ እያጋደለ ነበር፡፡ እርሱ ነው እዚህ ጣጣ ውስጥ ያስገባኝ። ፈጣሪ የፈጠራቸው ነገሮች መልሰው ለእኛ እንቅፋት ይሆናሉ! … የትራፊክ ምልክቶቹም ብዙ ናቸው፡፡ ቢሆንም እንኳን ከሙሴ ዘመን አመለጥኩ ብዬ አስብ ነበር፤ በድንጋይ መወገር ፈርቼ!
ግን የባሰው ቀን መጣ፣ … ገመዴን ቋጥሬ ልገላገል! … ድንቄም ግልግል! … ይሁዳ ጨካኝ ነው ቢሉኝም በራሴ ላይ ነው፡፡ ጨካኝ ብሆንና ደንደሳም ልብ ቢኖረኝ ጮማዬን እየቆረጥኩ፣ ይህቺን ሸበላ አቅፌ እኖር ነበር! … ዕድለ ቢስ ነኝ፡፡
እንባዬ በጉንጬ ሲወርድ እንድናስቀብረው ሀሳብ ያመጣው ሰውዬም አለቀሰ፡፡ ደብዳቤውን ሰጠሁት…
“ምናለ ራሱን ባያጠፋ!”
“ይሁዳ ሕሊና ያለው ሰው ነበረ”
ሺህ ሰው ገድለው፣ ሺህ ሰው አስገድለው የሚኖሩ ቱጃሮች ሞልተው የለ፡፡ መቃብር ገዛንለት፤ … ማስታወሻውን ያዝነው፡፡ መርፌና ሴንጢው አብሮት ተቀበረ፡፡ ወዲያው አንዲት ቆንጆ ልጅ መጣች፡፡
“ወይኔ ጉድ አደረግኸኝ! … አታለልከኝ?” እያለች ትጮሃለች፡፡
ልናረጋጋት ብንሞክርም አልቻልንም፡፡
“አንት ውሸታም! … አንት ከሀዲ!” ትላለች፡፡
“ሜዳ ላይ ጣልከኝ! … አሳፈርከኝ!”
“አይዞሽ” ብዬ እንደማቀፍ አደረኳት፡፡ ሆዴን አባባችው፡፡ … ሰውየው ቸኮለ ወይም ልቅሶው አሥጠላውና ጥሎን ሄደ፡፡
አብሬያት ዋልኩ፡፡ ብቸኝነትዋ ብቸኝነቴን አስታወሰኝ፡፡ የኔም ውስጥ ሰው ተርቧል፡፡ “ይሁዳ ዕድለኛ ነበር!” አልኩ፡፡ አመለጠው፡፡ ይህቺ ሴት፤ እንኳን የአንድን ሰው ነፍስ፣ ዓለምን ታስረሳለች፡፡ የራስዋ ፀሐይ፣ የራስዋ ከዋክብት አሏት፡፡
ተጠጋሁዋት፡፡ ዘመድ አደረኳት፡፡ ቀስ በቀስ እኔም እርስዋም የይሁዳን ሀዘን ረሳነው፡፡ ይሁዳም ትንሽ ቢቆይ የኢየሱስን ፀፀት ይረሳው ነበር፡፡
ግን እንኳን አልረሣ! … እንኳን ሞተ! … ይህቺን ውድ ሴት የት አገኝ ነበር? ለሰው ደግ ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ እዚህ መቃብር ቦታ፣ የህይወቴ ፀሐይ ወጣች! እሰይ! እንኳን ሞተ፡፡ የይሁዳ አበባ የኔ ሆነች!  

Read 5529 times