Sunday, 16 July 2017 00:00

የግጥም ጥግ

Written by  ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው
Rate this item
(28 votes)

“ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው”
ይህ ሰፊው ሕዝባችን፣ ማን ነው የበደለው
የት ነው የረገጥነው?
ማኅበር መሥርተን፣ በያጥሩ አደራጅተን
ሥራ እየሰጠነው፡፡
ሰፊው ግብሩ ረቆ፣ ሀገር እያስጠራ፣
ትውልዱን ማርኳል፤ “በአዳዲስ ፈጠራ …”
የመንደር መቀስ አፍ፣ መዐት እያወራ፣
ማኅበሩ እንዲረክስ፣ ግብሩ እንዳያፈራ፣
ሕዝቡን ቢመርዝም፣ “ሽብር” እያሶራ፤
ሰፊው ሕዝባችን ግን፣ ከቶ መች ቢገደው
ዕልፍ ጦስ ሲወራ፣
ጆሮና አፉን ስሎ፣ እርሱም ያሾረዋል፤
ለልማቱ ሥራ፡፡
ሰፊው ጠቢብ ሆኖ፣ በወጉ መትሮ
ዘመኑን ሲያድሰው፣
የልማቱን ግለት፣ ሚዲያው ተኩሶት
ወጣት ሲያዳርሰው፣
ሚልየንና ቢልየን፣ አንድ እየመሰሉት
ግርዱን ባወደሰው፣
ምርቱ ተመዝኖ፣ እድገቱ ይወራል
ሹሙ ባስደገሰው፡፡
ወሬው እንዲስፋፋ፣ ፈር እየተለመ
በቋንቋ አደራጅቶ፣
የልማቱን ውጤት፣ በየቤቱ አስገባው
በጣቃ አሰፍቶ፡፡
እውነትም ሰፊው ሕዝብ! በኢትዮጵያ
ምድር፣
ሥራ ሊያጣ አይችልም፤ መቼም
ጦም አያድር፡፡
ሀገር ሙሉ ቀዳጅ፣ ክልል ሙሉ ቅዳጅ፣
መንደሮቹ ጣቃ፣ ሠፈሮቹ ውራጅ!
ወንበሩም ጋሬጣ፣ ልብሳችንም ሰልባጅ፣
መሪው ኪስ በጫቂ፣ ተመሪው አስቀዳጅ፣
ሰዉ ሁሉ ቀዳዳ፣ በሆነበት ሀገር
በሆነበት ቦታ፣
ሰፊው ሕዝብ ታድሏል፤ መርፌውም
ቢጣመም መቼም ሥራ አይፈታ!

Read 5747 times