Sunday, 16 July 2017 00:00

ሚክሎል የአባ ስበር - ልጅ

Written by  ከወንድዬ ዓሊ
Rate this item
(1 Vote)

ማንደርደሪያ (1)
ሁለት ዓመት ቢሆነው ነው፤ በካያን አዳም አዝማችነት የፌስቡክ ሠራዊት፣ ዱካው ጠፍቶ የከረመውን ሥዩም ገብረሕይወትን አሥሦ እንግሊዝ አገር አገኘው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ በኢሜይል ቃለ ምልልስ አድርጎለት ድምጹን አሰማን፡፡ በስንት ምጥ ተሠርቶ፤ መቅደላ አፋፍ ላይ ተጠምዶ፣ አንዴ ብቻ ተኩሶ እንደ ፈነዳው የአጤ ቴዎድሮስ መድፍ፣ አንዴ ታትሞ በዚያ መቅረቱ ለአሳሰበን ወዳጆቹ፣ አድናቂዎቹ በሕይወት መኖሩን ማወቃችን ብቻ እውነትም የምሥራች ነበር፡፡
ሥዩምና ባለቤቱ ወይዘሮ መብራት አቦራ፤አራት ልጆች አለን ይላሉ፡፡ ሦስቱ የአብራካቸው ክፋይ ሲሆኑ፣ አራተኛው ‹‹ሚክሎል›› ነው፡፡ ሚክሎል ተፀንሶ የተወለደው በሥዩም ‹‹ውስጠ-ነፍስ›› ሲሆን አዋላጇ መብራት መሆኗ ነው፡፡ ደግ አዋላጅ እኮ አብሮ ያምጣል!
* * *  
ሥዩም ‹‹ተገለጠ› አይደል! አድናቂዎቹ ውትወታ ሲያበዙበት እነሆ ሚክሎልን እንደገና አባዝቶ ሊያስነብብ አዲስ አበባ ከመጣ ሁለት ወራት ሆነው።
ማንደርደሪያ (2)
በተሰጠኝ ቁጥር ስልክ መትቼ ቀጠሮ አስያዝኩት፡፡ በአካል ስንገናኝ የመጀመሪያችን ነበር፡፡ በጋራ ዘመዳችን ኃይለመለኮት ቤት የወይዘሮ ቴሬዛን ‹‹አቲካላ›› ቡና እየጠጣን ሦስት ዙር አወጋን፡፡
ከአባ ስበር ዑመር ዓሊ ልጅ ጋር በግል ተገናኝቶ ማውራት፣ በሕይወት ዘመን ደጋግም የማያገኙት ፋሲካ-ነገር-ነው፡፡ ከሥዩም ጋር መጫወት፣ ሚክሎልን ራሱን ማንበብ ነው፡፡ እንደ ዘበት ከአንደበቱ የሚለቃቸው ቃላት የተዋቡ ናቸው፡፡ በዲያስፖራ አባዜ አልተኳሹም፡፡
እኒህ ሁሉ ተደማምረው እንደ ‹‹ወዶ-ገብ›› ጋዜጠኛ፤ በቃለ ምልልሳዊ- ትረካ መልክ ግርምቴን ለአዲስ አድማስ ቤተሰብ አካፍል ዘንድ ወደድኩ፡፡
መዳረሻ
‹‹ሥዩም፤ ሚክሎል ተፀንሶ እንደተወለደ በአጭሩ…›› ልለው ስል ‹‹እማማ ሕይወት›› ትዝ አሉኝ፤ ‹‹በምዕራፍ ምንም›› ያስተዋወቀን፡፡ እሳቸው መለሱልኝ፡፡ እማማ ሕይወት እብድ ከመሆን በስተቀር ሌላው የሕይወት ዘርፍ ያቃታቸው ናቸው። አንድ ቀን በእንቅልፍ ልቡ መጥተው ሥዩምን ‹‹አልተቻለም! አይቻልም!›› እያሉ በሰቅጣጭ ድምፅ፣ በዜማ ስልት ያንባርቁበታል፤ መግቢያና መፈትለኪያ ቀዳዳ እስከሚያጣ ድረስ፡፡
‹‹መልኳ ቢያስደነግጠኝም ልሸሻት ግን አልቻልኩም። ጎባጣ፣ ገጣባ፣ ጠንጋራ፣ ወላቃ፣ ሸፋፋ፣ ድሪቷም፣ ንጣታም፣ቅጫማም፣ ጨብራራ ወዘት ናት›› ሲል ይገልጻቸዋል ሥዩም (ገፅ II)
የአገሪቱ ቆንጆ የነበሩትን እማማ ሕይወት፤ በዘጠኝ ዘግናኝ ሥዕላዊ ቃላት ከገለጻቸው በኋላ ‹‹ወዘተ››ን ማከሉ ከተወዘተባቸው ፍዳ በላይ ምን ሊጨምር እንዳሰበ የማያውቀው ሥዩም ብቻ ነው፤ እንደ እንክርት ምድጃ ዳር ቶፋ በለብታ ስታዛጋ የነበረችቱን ነፍሱን እንደ አመነሹበት ግን አያጠራጥርም፡፡
የሥዩም ደመነፍስና የእማማ ሕይወት  እብደት ከብዙ ንትርክ በኋላ መዳረሻ አገኘ፡፡ እማማ ሕይወት የልብ ወለድ የደራሲነት ምኞቱን ጎነጡበትና ከተለመደው የፀሐፍት የመሮጫ እመም (ትራክ) አስወጡት፡፡ እንዲህ በማለት፡-
‹‹ከእውነት ድርቅ መሐል ቆመህ ውሸት የቸገረህ የምናብ ደራሲ…በል ይሄውልህ፣ ልቦለድ ያልሆነውን ታሪካችሁን ተመልከተው፤ ልቦለድ ያልሆነውን ታሪካችሁን፣… ወጋችሁን፣… ባህላችሁን፣… ትውፊታችሁን… ልቦለድ ያልሆነው አስተዳደጋችሁ፣ አመለካከታችሁ… የሚፈለፈልበት ወርቅ ቅብ የድንቁርና ካዝናችሁም እዚህ ውስጥ አለልህ…ምናልባት ከተከፈተልህ የውስጡን ጉድጓድ ተመልከተው›› አለችኝ፡፡
እኔም ልቦለድ ስላልሆነው ሸፋፋ የሕይወት ሚዛን ለመጻፍ ቋመጥኩ፤ ሚዛኑ ነቅነቅ ሲል ማሳየት እንዳለብኝም ልብ አልኩ፡፡
የሁለቱ አተካራ የተቋጨው በእብዷ እማማ ሕይወት አሸናፊነት ነበር፡፡ ‹‹አሁኑኑ ነቅነቅ በል! የአእምሮህን እግር ንቀለውና ተገትሮ የቆየውን እራስህን ቅድመው!!›› የነፍስያውን ወለልታ ሰማ። ዕድሜው በሠላሣዎቹ መገባደጃ ላይ ደርሶ ነበር፤ ሁሉን እርግፍ አድርጎ ትቶ ነፍስ ከአወቀበት እስከ ሚክሎል ረቂቅ የመጨረሻ ገጽ ድረስ የነበረውን፣ በሕይወት ጉዞ አውቆም- ሳያውቅም የተጣበቀበትንና እንዲሁም ራሱ ፈቅዶ ወዶ፣ ከነፍሱ ጋር ያጣበቃቸውን ኹነቶች በሚክሎል ስም ዘረገፋቸው፡፡
የአባ ስበር ልጅ ሚክሎን ተመስሎ በዘመናት ዝንጋኤ ሳይጎረብጡን፣ ሳይሸቱን (እሽ! ሳይገሙን)፣ ሳይሰነፍጡን… ተከናንበን-አከናንበናቸው ስንተኛው የነበሩትን ገዝፈ-ጅል እውነቶቻችንን እንደ ጃፓን ስኒ (ይቅርታ! ድሮ ነበር ቀሽሙ የጃፓን ስኒ)፣ እንደረጋ ሠራሽ ሸክላ ይሰባብራቸዋል፡፡
እንዲያው በቀላሉ ከመክፈቻው ‹‹ምዕራፍ ምንም›› ብንጀምር፣ በአኬዳማ ደረጃ የተማርናቸውን ‹‹መግቢያ፣ መቅድም፣ ይድረስ…›› እነሱን እንኳን አልማራቸውም፡፡
‹‹ከታተማችሁበት የአመለካከት ሣጥን ውጡ›› ለማለት ራሱ በርግዶ ወጣ! ‹‹መግቢያ›› ከተባለ መውጫም አለና! በነገረ-አዙሪት ውስጥ ላለ ማሕበረሰብ መጻፍ ደግሞ እውነታን አደባባይ ከማስጣት ባለፈ እንደ ኪኒን የሚዋጡ ‹‹እንዴቶችን›› መሰንዘር ድፍረት ነው፡፡ ከነቀነቁት ራሱን ነቅንቆ፣ የራሱን ክኒና ይቀምማል ባይ ነው፡፡
ይኸንንም ራሱ በሳለው የመጽሐፉ የውጭ ሽፋን ‹‹ያለ ምክንያት መኖር ክልክል ነው›› ከሚለው በጨለማ ግርጌ ከለጠፉት መፈክር ሥር በቀጭን ክር ያስተሳሰራቸው እጅግ ፓራዶክሲካል ኹነቶች ነግሮናል፡፡ መቻል፣ማቃት፣ ብርሃን ጨለማ፣ መሆን አለመሆን፣ የነገረ ጨለማ፣ በጨለማው ውስጥ የብርሃን ነጠብጣቦች፤ በጨለማው ውስጥ የተጀበሩ፣ ወደ ተመለከቱት የብርሃን አድማስ ለመፍለስ የሚታትሩ፣ በዝቅጠትና በመቻል መካከል የማንነት ሚዛን ሲናጥ…!
* * *
ምነው በጥያቄ ሞላኸን  ሥዩም?
እህ! ሰው ከፍጥረቱ ጥያቄ ነው! አንተ እኮ ስትወለድ ጥያቄ ነህ፡፡ ነፍስ ከአወቅህ አንስቶ እኔ ማነኝ? ለምን ተፈጠርኩ? እንዴት ተፈበረኩ? ምን እያደረግኹ ነው? ወዴትስ እየተራመድኩ ነው? መጨረሻዬ ምንድነው? ወዘተ እንድትጠይቅ ነው የተፈጠርከው፡፡ ካልጠየቅህ፣ ጠይቀህም ራስህን ከአላገኘህ፣ እንግዲያውስ ‹‹ያቃተህ›› ሰው ነህ፡፡
ሰዎች ሁሉ ለዚህ የታደሉ ወይም የበቁ ናቸውን?
ሌጣ ሆኖ የተወለደ ምንም ፍጠረታዊ ሰው የለም፤ እያንዳንዱ ሰው፡- ከእነ አቅሙ፣ ከእነ-መንገዱ (ስልቱ) ነው የተፈጠረው፡፡ ሦስተኛ ነገር፤ ሁሌ ‹‹የሚቻል›› አንድ ነገር አለ፡፡ እንግዲህ መቻል (አቅም) ኢነርጂ ነው፤ ውስጣዊ ኢነርጂ፤ መቻል ከአለ - የሚቻልም ነገር አለ ማለት ነው። የማቃትን ቅርፊት እንደ ጫጩት ሰብረህ ለመውጣት፣ እንዲሁ ተፈጥሮ የሰጠህ መንገድ (መላ፣ ስልት፣ ብልሃት) አለ። እነዚህ ሦስቱ ሲገናኙ ነው በሕይወትህ ያሉት የማቃት (ያለ መሆን) አላባዎች እየተቀረፈቱ፣ የመቻል፣ የመከናወን አንተነትህ እየተሸለቀቀ የሚሄደው፡፡ ያኔ ነው ወደ ተለምከው የመሆን (የመቻል) ልዕልና የምትደርሰው።
ዋነኛው ገጸ ባህርይህ ጉግሣ በአገር ደረጃ ያለው ‹‹የማቃት›› አባዜ ያንገበግበዋል፡፡ እማማ ሕይወት ደግሞ ‹‹እኔ ብለህ ጀምር›› ይላሉ፤ ሁለቱን እንዴት እናስታርቃቸው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፤ እማማ ሕይወትና ጉግሣ አይጣረሱም፤ ለምን? ቤተሰብም፣ ማሕበረሰብም አገርም ‹‹እኔዎች›› - ግለሰቦች ሲጠራቀሙ የሚፈጥሩት ትልቅ ወንዝ ነው፡፡ ያቃታቸው ግለሰቦች በበዙ መጠን፣ ወንዙ ትልቅ ቢሆንም ‹‹ያቃተው›› ወንዝ ነው የሚሆነው፡፡
(ሥዩምን ለጥቂት ጊዜ ላናጥበውና፡- ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ይፋ ከመሆኑ በፊት የልጆች ዕድገት፣ ምርምርና የሥልጠና ማዕከል (ልዕሥምማ - በእንግሊዝኛው (CDTC) አባይን ተምሳሌታዊ አድርጎ፣ አንድ ቁጭት አዘል፣ የአሥራ ሁለት ደቂቃ ፊልም አሰናድቶ ነበር። ሥርጭቱን በተወሰኑ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች መወሰኑ እያሳዘነኝ፣ ከፊልሙ ትረካ ጥቂት ስንኞች ብቻ ልጥቀስላችሁ፡፡ ተራኪው ታዋቂው ሥዩም ተፈራ ከአንጀቱ ነበር ያነበነበው፡፡ እንዲህ ይላል፡-)
አባይ!
አንተና ትውልድ ሐበሻ- በቅኔ ሕብር
የተሰራችሁ፣
የሰሙ ጥፍጥፍ- የወርቁ ልቃቂት ናችሁ፤…
አባይ!
አንተ እኮ ለእኛ ቅኔ ነህ፣
ቅኔ ነህ የሰምና ወርቅ፤
አንድም-የባከነ ወንዝ፣
አንድም የትውልድ ዚቅ፡፡…
….ድምበር ማዶ ገና ከድንበር፣
እንደ ወላድ ነፍሰጡር፣
መድረሻህን ቀን አሰልተው፣
መንገድህን አበጅተው፣
መከተሪያህን ደልድለው፣
እንደስለት ልጅ- በስስት ዓይን
ተቀብለውህ በእልልታ ሲቃ፣
አካፋ-ዶማ ሰብስበው
እያጫወቱህ ‹‹ዕቃ ዕቃ››
በመሐንዲስ እሽሩሩ…. በጥበባቸው እያዋዙ፣
የአረጉህን ሆንክላቸው…ሶብህን ተቀብተው
ወዙ፡፡…
…እኛ ግን፡-
የታሪክ እውነት፣ የታሪክ ስላቅ፣ ሆነብንና
ውራጃቸውን ረጠቡን፣ ስንዴ ላኩልን በልመና
መቼም ከሰነፍ ደጅ፣ ሞፈር ይቆረጣልና፡፡
የነገደ ጎልጎለው አርቲሎ መሰለኝ “ድንቁርና ሲከማች የአደባባይ ቆሻሻ ይሆናል›› ያለው፣ ለምን እንዲህ አለ?
ሮሃ አያህ! ድንቁርና በአጭሩ ‹‹ማቃት›› ነው። ሲቻለን - ሳለ አለመቻልን መምረጥ ነው፤ በአንድ በኩል። በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለው በጎ የመሆን ማቃት ሲጠራቀም፤ በተገላቢጦሹ ደግሞ ያልሆነውን ነገር የማድረግ ዝንባሌአችን ሲጎለምስ - ሕይወት ትጠለሻለች።
ለምሣሌ!፡- በየግላችን ነውርን የመጠየፍ አቅም ከአጣን፡- ሌብነት ከኪስ አውላቂነት ወይንም ከመንደር ወሮ በላ ባህርይ አልፎ በአገር ደረጃ በአሁኑ ቋንቋ ‹‹ሙስና›› ይሆናል፡፡ ሙስና ግን ምትሃታዊ፣ አፍዝ - አደንግዝ አይደለም፤ ቁሻሻ ሥነ ምግባርን ለመጠየፍ ያቃተን የየግላችን አመለካከት ውጤት ነው፡፡ እየጎለበተ ሲሄድ የማሕበረሰብም፣ የአገርም የአደባባይ መጠሪያ ይሆናል፡፡
(ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዚህ ረገድ ለአገራችን የሰጧትን መለኪያ ልብ ይሏል፡፡)
ከብዙ ዓመት በኋላ ወደ አገርህ ስለተመለስክ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የተከማቸው የቆሻሻ ክምር ዘግንኖህ ብዬ?
ሮሃ እሱም ቀላል አይደለም! ሚክሎልን ስጽፍ በነበርኩበት ጊዜና አሁንም እኔን የሚያስ
ጨንቀኝ ከቁሳዊ ቆሻሻ ይልቅ በአገር ደረጃ አየሩ ላይ የጋገረው - ህሊናዊ ቆሻሻ ነው፡፡ ቆሻሻን ማስወገድ የሚቻለው ቀድሞ ነገር አመለካከታችን ንጹህ ሲሆን ነው፡፡
ማለት?
ማለትም! እያንዳንዱ ቆሻሻ ባለቤት አለው፡፡ የማስቲካ፣ የማስቲካ ወረቀት፣ ሶፍት ባለቤት አለው። ያንን ሁሉ ዝርክርክ ብዙ ሺህ ሠራተኞች ብታሰማራ እንኳን መሰብሰብ ያዳግታል፤ በየቀኑ - ያው ነውና! ከዚያም አልፎ በጠራ ጠሐይ፣ በአውላላው አውራ ጎዳና ሽንትና-ምናምናቸውን ሲፀዳዱ ምንም ደንታ የሌላቸው ስንቶች ናቸው? ለምን መሰለህ? ህሊናቸው ስለ ቁሻሻነት ያለው ግንዛቤ ዜሮ/ምንም ስለሆነ ነው፡፡ እንጂ ሰው እንዴት እንደ እንስሳ ነውሩን በአደባባይ ይገልጣል?
እንግዲህ ክቡር የሆነው ሰብዓዊ ፍጡር በህሊናው ሙት፣ በቁሳዊውም ነሮ ቆርቁዞ በድህነትና በጉስቁልና የሚኖረው በተፈጥሮ የተለገሠውን ሁለንተናዊ የመቻል አቅም ላለመጠቀም ሲደነዝዝ ነው፡፡ ጉግሣ ኢትዮጵያን ሲያስብ የሚያንገበግበው ይህን መሰል “የመሆን ክሽፈት ሰለባ” ስለሆነችበት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ስሜትህ አየል፣ ከረርም ያለ ይመስላል ልበል?...ማለት “ኢትዮጵኝነት”
ሮሃ ባይሆን ነበር የሚገርመኝ! አሁን ጊዜውንና መድረኩን በማላስታወሰው ቦታ ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቄ ነበር፡፡ በአጭሩ እንዲያውም ‹‹ኢትዮጵያዊነት ራሱ እኔ ነኝ›› ነበር የመለስኩላቸው፡፡ አዎ! ኢትዮጵያን በጣም እወዳለሁ፤ አገሬ ድሪቶ የሰማይዋን ጣራ ጥሳ፣ ሌላ ንጹህና ትልቅ ሰማይ እንድታይ እመኛለሁ፡፡ በሚክሎል ያስተላለፍኩትም ዋና መልእክት ይኼው ነው፡፡
ጀውጃው ጉግሣ፡- በአርቲሎ በጣም የተሞገተ ይመስለኛል፤ የሁለቱም ፈጣሪ አንተ ነህ፤ አርቲሎ፡- ‹‹የመሆን አለመሆን ጥያቄ ለዚች ምድር ይከብዳታል…›› ሲል ምን ማለቱ ነው?
አርቲሎ የከሸፈበት የጥበብ (የአርት) ሰው ነው፤ ዕድሜውም ‹ቃ› ያለ ነው፡፡ ጉግሣ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው፡፡ ጉግሣ ‹‹ማቃትን›› በመቻል መለወጥ ይቻላል ባይ ነው፡፡ አርቲሎ ግን ‹‹ወስፋቱን›› ማስታገሥ የማይችል ማሕበረሰብ፤ዳቦ ሳይጠግብ ስለ ነገ መቻል/መከናወን-ማሰብ አይችልም ይለዋል፡፡ አገራችን የመሆን-አለመሆንን- ጉዳይ ለማንሳት ማሕበረ-ሥነልቡናዋ አይፈቅድላትም ማለቱ ነው! ከቶ መጀመሪያ ወስፋቷን መቼ አሥታገሰችና! በአጠቃላይ የወል የሆነው ማሕበራዊ ንቃት፣ ‹‹የመሆን አለመሆንን›› ጥያቄ ለማንሳት አይቻላትም፡፡ ለምን? የወስፋቱ ጩኸት፣ የነፍሱን የመሻት ኡኡታ ትውጥበታለችና፡፡
*   *   *
አባ ስበር
አባ ስበር ዑመር የሃድራው አገር የባቲ (ወሔ) ተወላጅ ናቸው፤ እስከ አፍለኛ ዕድሜአቸውም የኖሩት እዝያ ነበር፡፡ ‹‹ከወንዝ ወዲህ ማዶ - ከወንዝ ወዲያ ማዶ›› በመባባል ወጣቶቹ ጉርምስናቸውን ለማስመስከር ያህል (ይመስላል) በሚፈጥሩት ድብድብ ውስጥ ዋነኛ ሆኑ፤ እኩዮቻቸው ጀግንነታቸውን በማድነቅ ‹‹አባ ስበር›› የሚል ቅጽል ስም አወጡላቸው፡፡
አባታቸው ሸህ ዓሊ ግን በዚህ ደስተኛ አልነበሩም፤ የቁርዓን ዓሊምና የአካባቢው ማሕበራዊ መሪ (Opinion Leader እንዲሉ) ስለነበሩ፣ የልጃቸው ጀብደኝነት አላማራቸውም፡፡ “ተው! ልጄ!... ዶረኛነት ይቅርብህ ልጄ! አለዚያ እረግምሃለሁ›› ሲሉ አስጠነቀቋቸው፡፡
አባ ስብር የአባታቸውን ምክር አዘል ተግሣፅ በይሁንታ ከማስተናገድ ይልቅ ወደ አሥመራ ተሰደዱ። (በነገራችን ላይ የእኔም አባት የንግሥጽ ዘውዲቱ ወንበር (ዳኛ ማለት ነው) ከሆኑት አባቱ ጋር አፍለኛነት ስታኳርፈው፣ የአባቱን ሁለት በሬዎች ሰርቆ፣ በአራት ጠገራ ብር ሽጦ፣ አሥመራ ተሰዶ ነበር፤ የአፍላነት ጀብዱ ያረገፉበትን ጥርሶቹን በወርቅና በነጫጭ አርቴፊሻል ጥርሶች አስተክሎ ተመለሰ፡፡)
 አባ ስበር ዑመር ዓሊና የእኔው ዓሊ ሐምዛ እንግዲህ ያን ጊዜ በኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ሥር ወደ ኤርትራ የተሰደዱት ከሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ማለትም ከማይጨው ጦርነት በፊት መሆኑ ነው፡፡
ወደ አባ ስበር እንመለስ፡- የተስተካከለ ረዥም ቁመና፣ ንቃትና ኩራት የታደሉት አባ ስበር፤ ከኤርትራ በሊቢያና በሌሎች ቅኝ ግዛቶቻቸውን ለማስከበር የሚያገለግሏቸውን ወታደሮች በሚመለምሉ የጣልያን መኮንንኖች ዓይን ገቡ፡፡ በውትድርና ሰልጥነው ወደ ትሪፖሊ (ሊቢያ) ሄዱ፡፡ (“ሸጋው ትሪቦሊ” የሚባለውን ዘፈን ያስታውሷል፡፡)
አባ ስበር፡- በአሥመራና በትሪፖሊ ቆይታቸው፣ ከመሐል አገር የተለየ የዘመናዊ አኗኗር ስልት መቅሰማቸው አልቀረም፡፡ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ለቀሪው ሕይወታቸው የሚጠቅማቸውን ሙያ የተማሩት ግን በውጊያ እግራቸው ጣቶች አካባቢ በጥይት ተመተው “ቦርድ” ከወጡ በኋላ ነበር፡፡ ጣሊያኖች በአትክልት ልማት ሙያ አሰለጠኗቸው፡፡ ዘመናዊነትን ከቋንቋ (ጣሊያንኛ) እና ከአዲስ ሙያ ጋር ደብለው፣ ከትሪፖሊ አሥመራ፣ ከዚያም መቀሌ ደረሱ፡፡
ያኔ፡- ትግራይን ከንጉሥ እኩያ የሚያስተዳደሩት የዓፄ ዮሐንስ ልጅ፣ ልዑል ራስ መንገሻ ዮሐንስ ነበሩ፡፡ የሆነ “ጠጉረ ልውጥ” ሰው ከተማቸው እንደመጣ ሰሙ። አለባበሱ፣ አነጋገሩ፣ ጥዱነቱ ያሳጣው የባቲ ልጅ፡፡ ቤተ መንግስታቸው አስጠርተው፥ ከአነጋገሯቸው በኋላ “አንተንማ አለቅህም! በአስተርጓሚነት ታገለግለኛለህ›› አሏቸው፡፡ ክርስትና አንስተውም ገብረሕይወት አሏቸው። የባላምባራስነት ማዕረግም ሰጧቸው፡፡ አባ ስበር ዑመር፤ ባለምባራስ ገብረሕይወት ሆኑ፡፡
በዚህ ማስታወሻ ከቶም ሊገለጽ የማይችል የሕይወት ጉዞ አሳልፈው፣ ትውልድ መንደራቸው ባቲ ደርሰው አንዲት የአምባሰል ቆንጆ አግብተው፣ በጉልምስና ማምሻ ላይ የወለዱትን ልጅ “ሥዩም” አሉት፡፡ የራስ መንገሻ ልጅ ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ እንደሆኑ ያስታውሷል። ይወዷቸው ነበር ማለት ነው፡፡
* * *
የባላምባራስ ሥዩም አዲስ የትዳር ሕይወት እንደአሰቡት አልተሳካም፤ የስዩም እናት ሕመምተኛ ሆኑ፤ ለተሻለ እንክብካቤ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመለሱ፡፡ ከስምንት ወሩ አንስቶ እንደ እናት እንደ አባትም ሆነው ያሳደጉት አባቱ ናቸው፡፡
ሥዩም አባቱ የጨቅላነቱን ዘመን እንደነገሩት ልክ እንዲህ ነግሮኛል፡- “አባቴ አትክልትና ፍራፍሬ በሚያለማበት ማሣ ይወስደኝና፣ ከዋርካ ሥር ጥላ ያስቀምጠኝና ትኩስ የፍየል ወተት በጡጦ ያረግልኝና ወደ ሥራው ይመለሳል፤ በእናት ጡት ሳይሆን በፍየል ወተት ነው ያደግኹት”
ሥዩም ነፍስ አውቆ ቤት ያፈራውን መመገብ ከጀመረም በኋላ አባቱ በጥብቅ ይከታተሉት ነበር፡፡ ፍየል አርደው የሚጠቡት (የሚገፉት) ራሳቸው ነበሩ፡፡ ሆድ ዕቃውን ከፍተው መጀመሪያ የሃሞት ከረጢቷን ያወጡና ‹‹የኔ አንበሳ! ና ጠጣት” ይሉታል፡፡ የጨቅላ ልቡን በአንበሳነት ሞልተውታልና፣ የሃሞት ከረጢቷን እንቦሳ ጥጃ የናቱን ጡት እንደሚልግ መጥምጦ ይጨልጣታል፡፡ እንዲህ አደገ ሥዩም- “በወተትና በሃሞትም››፡፡
 የልጆች ዕድገት ባለሙያዎች እንደሚነግሩን፤ የሰብዓዊ ፍጡራን ሰብዕና (ማንነት፣ ምንነት)፣ በሌላ አነጋገር የአመለካከትና የአደራረግ ዝመት፣ ድልዳል የሚይዘው ከጨቅላነት እስከ ስምንት ዓመት ዕድሜአቸው ድረስ ነው፤ ሆኖም ያለፉባቸውና ያሳለፉባቸው የሕይወት መስመሮች በጥቂቱ በትምህርትና በተሞክሮ ሊሞረዱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ማን ነበሩ “ልጅህን እስከ ስምንት ዓመቱ ስጠኝ፤ ለዘላለሙ የእኔ አደርገዋለሁ” ያሉት መንፈሳዊ አባት!?
ሥዩምን ቀረብ ብሎ ላጠናው ሰው፤ የአባ ስበር “ወተትና ሃሞት” ውጤት እንደሆነ ማስተዋል ይቻለዋል። መጽሐፉን ላነበበ ደግሞ በየመስመሪቱ መሐል የአባ ስበር ወተትና ሃሞት በሥዩም ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደተንሰላሰሉ በረቂቁ ይገነዘባል፡፡
ወተትነቱ
በእኔ ግምት የሥዩም ወተቴነት፤በአብዛኛው ከቋንቋና ከአተራረክ ክህሎቱ የሚቀዳ ይመስለኛል፡፡ ሚክሎል እኮ በዝርው ተጻፈ እንጂ ግጥም ነው፤ ቅኔ ነው፤ ወይራ ነው፡፡ ዜማ አለው፤ ቃለ ኃይሉ አንኳሪ ነው፡፡ እያባበለ ይነዳል፡፡ እኒህ ጉልበቶቹ የመነጩት ከሁለት አንጓዎች ይመስለኛል። አንዱ “ቃሉዬ” መሆኑ ነው፤ ቃሉዎች “ቃል ያነጥራሉ” ይባልላቸዋል፡፡
የዜማ፣ የግጥም፣ የሥነ ቃል አገር ነው - ቃሉ። የቃሉዎች አማርኛ ከኦሮምኛ፣ ከአፋርኛ፣ ከአረቢኛ፣ ከግዕዝ፣ ከትግሪኛ ተወስዶ ፥ እዚያው ሲነብር በልጥጎ “ቃሉኛ” አማርኛ ሆኗል፡፡ ያንን ሐብት ነው - የአባ ስበር ልጅ በዝብዞ ሚክሎል ላይ የዘረገፈው፡፡
ሁለተኛም፡- ሥዩም ከለጋ ወጣትነቱ አንስቶ ገብጋባ አንባቢ መሆኑ ነው - ገብጋባ!! ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ አብይ የሚባሉ ዘመን ተሻጋሪ መጻሕፍትን ያነበበ ሰው ነው፡፡ ከአገራችን ደራሲዎች እንደ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የሚያደንቀው የለም፡፡ በተለይማ “ኦቴሎ፣ ሐምሌት፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ የከርሞ ሰው…” ነፍሱን እንደ አሰገሩለት ይናገራል፡፡
እንዲያውም በአንድ ወቅት የጸጋዬን ቃለ-ልቀት ከአጣጣመ በኋላ ሌሎች የአማርኛ ድርሰቶችን ለማጣጣም በጣም እንደተቸገረ ይገልጻል፡፡ ጠቅልሎ አይጣለው እንጂ ሥዩም ለአቅመ - አቃቂር በደረሰበት ዓመታት ማለትም በደርግ አፍለኛ ዘመን፣ በሥነ ጽሑፍ መጠበብ እየከሰመ የሄደበት ወቅት ነበርና - አልፈርድበትም፡፡
“ሃሞትነቱ”
ትንሽ ልቡን አንዴ በአንበሳነት ሞልተውታልና እየጎመዘዘውም ቢሆን እንኳን እንቦሳ ጥጃ የእናቱን ጡት እንደሚልግ መጥምጦ ይጨልጣታል፡፡ እንዲህ አደገ ሥዩም- በወተትና በሃሞት፡፡
ሥዩምን ወይንም ሥራውን ቀረብ ብሎ ላጠና ሰው፣ የሥዩምን “ወተትና - ሃሞትነት” በንግግሩና በመጽሐፉ የመስመር መሐል ንባቦች ያገኘዋል፡፡ ዝንተ ዓለም ተከናንበን የተጋደምንባቸውን ጅላጅል ልማዶች፣ አመለካከቶችና ወጎችን እየነቀሰ ሲያነኩራቸው ለአፍታ ያህል አያመቻምችም፡፡ እንደ ሃሞት የመረሩ ገጸ ባህርያትን እንድንዳስሳቸው፣ እንድንጨብጣቸው አርጎ በመሳል፡- አይነኬዎች ሆነው የዘለቁ ሃይማኖትን፣ ራሱንም እግዚአብሔርን ጭምር፣ ይሞግታል፡፡ ቤተ መቅደሱንም፣ ቤተ መንግስቱንም በሊጨኛ ሲላጫቸው “ለነገ” አይልም። እንዲያውም ሚክሎልን በጻፈበት ወቅት ጭራሽ “ነገ” የሚባለው ዑደት የቆመ ሳይመስለው አልቀረም፡፡ በመራር እውነቶች ያለ ስስት ክፉኛም ጠቅጥቆታልና፡፡
የሚክሎልን መጠቅጠቅ ሳስብ ታዲያ እንዲህ ለማለት ይቃጣኛል፡- አገር ያህል ምሬቶች፣ እሬቶችም፣ ጥያቄዎችና በአነጠራቸውም መሪር ሐቆች የተሰባበሩ የማቃት (ያለመሆን) ጋግርት ስብርባሪዎች መዘክር ነው! ሚክሎል- የሥዩም አባ ስበር የበኩር ሥራ!



Read 2798 times