Sunday, 16 July 2017 00:00

“አማሌሌ እና ሌሎችም”ን በጨረፍታ

Written by  ወግደረሰኝ መርሻዬ
Rate this item
(5 votes)

ከሰሞኑ አንድ መፅሐፍ እጄ ገባና አነበብኩት። እጄ ከመግባቱ ቀደም ብሎ ባሉት ጥቂት ቀናት በሬድዮና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ሲወራለት ሰምቼ ነበር፡፡ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይም ዜናዎችን ማንበቤ መፅሐፉ ትኩረቴን እንዲስብ አስገድዶኛል፡፡ የበለጠ ያጓጓኝ ግን የደራሲ አዳም ረታ አጭር ልብ-ወለድ በመድበሉ ውስጥ መካተቱ ነበር፡፡
ካልተሳሳትኩ ደራሲ አዳም ረታ ከአንባቢ ጋር የተዋወቀው በስብስብ ስራዎች ውስጥ በተካተቱለት ታሪኮቹ ነበር፡፡ “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” በሚል ርዕስ በወጣ መድበል ወደ ሥነ-ፅሑፍ አደባባይ የተቀላቀለው አዳም፤ “ድብድብ” እና “ዕብዱ ሺበሺ”ን ጨምሮ አራት ልብ-ወለዶችን አዋጥቶ ነበር፡፡ በ1977 ዓ.ም በታተመው በዚህ ስራ ላይ “አባ ደፋር” የተባለው  ፊት-አውራሪ ርዕስ ባለቤትነቱ የወቅቱ ገናና ደራሲ የአበራ ለማ ነበር። በርግጥ በ1990 ዓ.ም “ጭጋግ እና ጠል” በተሰኘ መሰል የስብስብ ስራ ላይም “ዘላን” የምትል አጭር ታሪክ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ረዥም አመታት በግሉ ሙሉ መፅሐፍ እያመረተ ንባብ ለተጠማ የሥራ-ፅሑፍ አድናቂ ሲያበረክት ቢቆይም፣ አሁን “አማሌሌ እና ሌሎችም” በሚል የቡድን መድበል ብቅ ብሏል፡፡ ታድያ ጥያቄ የፈጠረብኝ፣ ከዚሁ ሁሉ የብቸኝነት ዓመታት በኋላ እንዴት ወደ ቀድሞው የስብስብ ልማዱ ተመለሰ? በአጋጣሚ ወይስ አቅዶበት? ምናልባት የወጣትነቱን ትዝታ ሊመልስበት ይሆን ይሆናል፤ ወይም ላይሆንም ይችላል፡፡ የአዳም ሥነ-ፅሑፋዊ እድገት ማረጋገጫ የሆነልኝ አንድ ነጥብ ግን አግኝቻለሁ፡፡ ደራሲ አበራ ለማ “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” ላይ ቀዳሚው ተጠሪ የነበረ ሲሆን አዳም ረታ ደግሞ “አማሌሌ” በተባለ ታሪኩ በአዳዲስና ነባር ፀሐፊያን ታጅቦ መምጣቱ ደራሲው የሚገኝበትን የብቃት ደረጃ ማሳያ ሆኖኛል፡፡ ለማንኛውም፣ ከዓመታት በኋላ በዚህ መድበል ውሥጥ ከተካተቱት መካከል ነጥሮ የሚወጣ ፀሐፊ እንደሚኖረን ተስፋ እናድርግ። ነጥቤን ትቼ ይህን ያህል አንባቢን በማድከሜ ይቅርታ ልጠይቅና ወደ ጉዳዬ ልለፍ፡፡
አጭር ልብ-ወለድ የሚባለው የሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ በባሕሪው ቁጥብና አይቀሬ ጉዳዮችን ብቻ መርጦ የሚይዝ ነው፡፡ እንዲያውም፣ በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች “የተዋጣለት አጭር ልብ-ወለድ አንዲት መስመር እንኳን በዘፈቀደ ያልተጨመረበት ነው” ሲሉ ይደመድማሉ፡፡ በዚህ የሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ ቅርፃዊና ይዞታዊ ክልል ውስጥ ሊካተት የማይችል ነገር ማንሳት፣ የኪነ-ጥበቡን ቀለም እንደማደብዘዝ ይቆጠራል፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑ ዝርዝር ነገሮችን በአጭር ታሪኮች ውስጥ ለመሙላት መሞከር የተበላሸ ውጤት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ እስኪ ለጥቂት ሰከንዶች አስቡት፤ “ኦሮማይ”ን ወይም የ”ፍቅር እስከ መቃብር” ታሪኮችንና ገፀ-ባህሪዎችን አንድም ሳይቀሩ አሰጣጥሮ ወደ አጭር ልብ-ወለድነት መቀየር ይቻል ይሆን? ወይ አይቻልም፤ ወይም ከተቻለም ደግሞ ሥነ-ፅሑፋዊ ቀውስ መፈጠሩ የማይቀር እውነታ ይሆናል፡፡
“አማሌሌ እና ሌሎችም” ውስጥ ከተካተቱት ታሪኮች መካከል ከላይ ለጠቀስነው መርህ ተገዢ የሆኑትን እያብራራሁ ለመጥቀስ ገፅ ይገድበኛል። የመፅሃፉን ግማሽ አካል ከያዙት 12 አጫጭር ልብ-ወለዶች ውስጥ ምናልባትም ሁሉም ለማለት በሚያስችል ድፍረት የተካኑ ናቸው፡፡ የታሪክ ፍሰትን ወይም የቋንቋ አጠቃቀም ክሕሎትን እንደ መስፈርት ከወሰድን አንዱ ፀሐፊ ከሌላኛው ያለው መላቅና መራቀቅ የሚታይ ሥለመሆኑ የሚካድ ባይሆንም፣ እያንዳንዱ ታሪክ የሚናገረው ግን የሥነ-ፅሑፍ መርህን አለመሳቱን ነው፡፡ ሁሉም ደራሲያን በታሪኮቻቸው ውስጥ የተስፋፋ የገፀ-ባሕሪ ወይም የሕይወት ታሪክ አላካተቱም፡፡ ልብ-ወለዶቹ ቁጥብነትን ብሎም ዘርፉ የሚፈልገውን  ፈጣንነትን የጠበቁ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የመፅሐፉ ገፆችም በጥንቃቄ የተመረጡ አረፍተ ነገሮች የሞሉበት ነው፡፡ ተደጋጋሚነትን፣ አሰልቺነትን ወይም የታሪክ መወሳሰብን ያራቀ ስብስብ መሆኑን ጀማሪ አንባቢ እንኳን በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ በተለይ በሌሊሳ ግርማ የተፃፈው “መዓተኛው ተሳፋሪ” እና በሰለሞን አበበ ቸኮል የተደረሰው “ጉጉት ኣምላክ ነበር”፣ በአጭር ልብ-ወለድ ሥራ ላይ የሚፈለገውን የቦታና የጊዜ ውሥንነትን አጣምሮ በመያዝ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የአለማየሁ ንጉሴ “የምን ትዝታ?” ደግሞ በተመረጡ ቃላትና በሚያማልሉ ዐረፍተ ነገሮች መደርጀቱ ከሌሎቹ ሥብስቦች አቻ-የለሽ እንድንል ያስገድደናል፡፡
አጭር ልብ-ወለድን መልካም ሊያሰኙት ከሚችሉ ነጥቦች አንዱ ገፀ-ባህርያትን በድርጊት ማሣየት መቻሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለምሣሌ አንድ ተሣዳቢ ገፀ-ባህሪ፣ በታሪኩ ውስጥ ሲሳደብ ብናየው ታሪኩን የበለጠ አሣማኝ ያደርገዋል፡፡ አንድን ሴሰኛ ስለ አመንዝራነቱ ብዙ ከመተረክ በድርጊት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ምስል ከሳች በሆነ ብዕር ማብራራት ልብ-ወለዱን የማይረሳ ያደርገዋል። በዚህ መንገድ የተሳሉ ተዓማኒነት ያላቸው ገፀ-ባህርያት ደግሞ ከአንባቢ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ ዕውኑን ዓለም የወከለ ትረካን ይስሉልናል፡፡ ኪናዊነት ማለት ይህ ነው፡፡ “አማሌሌ እና ሌሎችም” ላይ ይህን ብናይ መገረም የለብንም። መድበሉ ካቀፋቸው ታሪኮች ውስጥ በኢትኤል ዮናስ የተተረከው “አባትየውና የፋሲካ ዶሮ” በዘመኑ ቋንቋ የተፃፈና አብዛኞቻችን ያደግንበት  የልጅነት ሥነ-ልቦና አምሳያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጋሽ ሽፌ ሁሉም እንደሚፈራቸው በታሪክ መጀመርያ ግድም ይገለጽና ከቆይታ በኋላ ደግሞ ቤተሠባቸውንና የመንደሩን ህፃናት በቁጣ ሲያምሱት ይታያሉ፡፡ ልጃቸው ታሜም ላይ ደራሲው የተጠቀመው ስልት ተመሳሳይ ነው። ልጁ የዶሮ ቀበኛ መሆኑን ሰምተን ወዲያው ያንኑ የተነገረለትን ባህሪ በተግባር ሲፈፅመው እናያለን፡፡
በነገረችን ላይ፣ በደራሲነት ማዕረግ የሚጠራ ማንኛውንም ፀሐፊ በልብ-ወለድ ነፍስ ዘርተው እንዲንቀሳቀሱ የፈጠራቸውን ገፀ-ባሕርያት በሚገባ መረዳት አለበት፡፡ የጓደኛ ያህልም ሊያውቃቸው ይገባል፡፡ ይህ ሥራ ታድያ ታሪኩ መፃፍ ከመጀመሩ በፊት መጠናቀቅ ያለበት የደራሲው የቤት-ሥራ ነው፡፡ እስከማውቀው ወይም እስከተረዳሁት ድረስ፣ ከአዳም ረታ ታላላቅ ብቃቶች መካከል አንደኛው ይህ መሆኑን እኔን ጨምሮ አብዛኞቹን አድናቂዎቹን ያስማማል፡፡ የ“ግራጫ ቃጭሉን” መዝገቡን ማን ይዘነጋዋል? መፅሃፉ ለማንኛውም ደራሲ፤ ገፀ-ባሕሪውን ምን ያህል መረዳት ወይም ማወቅ እንዳለበት ትምህርት የሚሠጥ ነው፡፡ ለግምገማ በመረጥኩት መድበል ላይ የምናነበው ዘለግ ያለ አጭር ልብ-ወለድ “አማሌሌ” የተባለው የአዳም ታሪክ ነው፡፡ አንዳንዶች አጭር ልብ-ወለድ ከ10ሺ ቃላት መብለጥ የለበትም የሚሉትን ቀመር እንቀበል ብለን ብንነሳ “አማሌሌ” ከዚያም በላይ ቢሆንም፣ የተሳሉት ገፀ-ባሕርያት ግን ከደራሲው ጋር የወዳጅ ያህል ቀረቤታ እንዳላቸው በቀላሉ ማየት ይቻላል። በግሌ ይህንን መልክ በአንድ ጊዜ ንባብ ብቻ መረዳት ችያለሁ፡፡ በገፀ-ባሕርያቱም ላይ የሚታየው የሰብዕና ለውጦች ምክንያታዊነታቸውን በመድበሏ ላይ ለተካተቱትም ሆነ ሌሎችም ፀሐፊያን መማሪያ ሆኖ አልፏል፡፡ በአንፃሩ፣ “ለምለሚና” የተባለችው የዮናስ ብርሃኔ ድርሰት፣ ከአጭር ልብ-ወለድነት ይልቅ የአጭር አጭር ወደሚባለው የስነ-ፅሑፍ ዘርፍ ያደላች መሆኗን ተናግሬ ልለፍ፡፡ ስለ አጫጭር ታሪኮች ያለኝ ትኩረት፣ ጥቂትም ቢሆን ስለ አፃፃፍ ዘይቤው ለማወቅ እንድጥር ገፍቶኛል፡፡ አንዳንዴ “ድርሰት ሊፃፍበት የሚገባ ብቸኛ መንገድ ይህ ብቻ ነው” የሚሉ የሥነ-ፅሁፍ ተመራማሪዎችን ልክ ናቸው እስከምል ድረስ አስገድዶኝ ነበር፡፡ እንደውም “አማሌሌ”ን ጨምሮ ሌሎች ታሪኮችን ሳነብ፣ በእነዚህ የምርምር ቀመሮች እየተመራሁ ነበር፡፡ ፀሐፍያኑንም የምዳኘው ከዚህ አንጻር መሆኑ በዚህች አነስተኛ ጹሑፌ መረዳት ይቻላል፡፡
ይኽን ተጽዕኖ ከተረዱ የሥነ-ጽሑፍ አድናቂ ጓደኞቼ መካከል አንደኛው ይሕን በቀመር የሚለካ ዘይቤ የሚያፈራርስ አንድ መጽሐፍ ሰጥቶኝ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ የመጽሐፉን ርዕስ ብዘነጋውም ዋና ጭብጡ ግን ሥነ-ጽሑፍ በዚህ ወይም በዚያ ቅርፅ መፃፍ እንደሌለበት እና ለድርሰት አጥር ማበጀት ታሪኮች ላይ መፋለስ ይፈጥራል የሚል ድምዳሜን ያቀፈ ነበር፡፡ ለማንኛውም ይኽን የዘመናት ክርክር ለዘርፉ ተመራማሪዎች ልተውና ወደ መጨረሻው ነጥቤ ልለፍ፡፡
በረዣዥም ልብ-ወለድ ውስጥ ውጤት የሚባል ነገር አለ፡፡ ውጤት ማለት ድርሰቱ ሊተረክበት የበቃበት አብይ ሰበብ እና ሔዶ ሔዶ የሚርፍበት ግብ ነው፡፡ በረዥም ልብ-ወለድ ዘርፍ ቁጥራቸው የበዛ ውጤቶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ በአጫጭር ልብ-ወለድ ደግሞ ነጠላ ውጤት የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚኽ ዘርፍ ደግሞ ከመጀመሪያው ዓረፍተ-ነገር ጀምሮ የደራሲው ጥድፊያ ወደታቀደው ግብ ለመድረስ መሆን አለበት፡፡ ከገፀ-ባሕርያቱ እውቂያ እስከ ታሪካቸው ማለቂያ ድረስ የሚፈፀሙ ክንዋኔዎች እና ሁነቶች የታሪኩን ፈጣን ጉዞ የማይጎትቱ፣ አንባቢውን ለቅፅበት እንኳን ዓይኑን ከገፀ-ባሕርያቱ ላይ እንዳያነሳ የሚያደርጉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የአንድ ታሪክ ነጠላ ውጤቱም ይሕ ነው፤ ታሪኩም እዚሕ ላይ ያበቃል ማለት ነው። ወደዚህ የታሪክ አጥናፍ ከተደረሰ በኋላ ሌላ ነገር መጨመር ድርሰቱን መልክ አልባ ማድረግ ይሆናል። ተጓዳኝ ግብ የሚባል ነገር በአጭር ልብ ወለድ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ከዚሕ አንፃር “አማሌሌ እና ሌሎችም” የተሰኘው የአጫጭር ልብ-ወለዶች እና ወጎች መድብል ውስጥ የተካተተው የግርማ ታደሰ “አልመለስም!”ን  ከተመለከትነው በጥቂት ገፆች ብዙ ነገሮችን ለመናገር የሚሞክር መስሎ ይታያል። በቋንቋ አጠቃቀም ክሕሎቱ፣ በአተራረክ ዘይቤው እንዲሁም ምናባዊነቱ ግሩም ቢሆንም፣ በአንድ ጊዜ  ብዛት ያላቸው ተጓዳኝ ግቦችን ለማካተት ሲሞክር ይስተዋላል፡፡ ታሪኩን በጥድፊያ ለመቋጨት የሔደበት ችኮላ ለትችት በር ከፋች ነው፡፡
በአጠቃላይ “አማሌሌ እና ሌሎችም” ብዙ ሊደነቅና ሊወረፍ የሚችል መፅሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የመድበሏን ሁለተኛ ክፍል ማለትም የወጎቹን ስብስብ፣ ጊዜና የጋዜጣዋን አዘጋጆች መልካም ፈቃድ ካገኘሁ በዳሰሳ እንደምመለስበት ቃል እገባለሁ፡፡



Read 5679 times