Sunday, 16 July 2017 00:00

ግዮናዊ ፍልስፍና ክፍል-፪

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

አንጋፋው የግሪክ ፈላስፋ አፍላጦን/Plato የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በዓለም ላይ በተነበበለት The Republic ድርሳኑ ውስጥ ያልነካካው ያላሰሰው ርዕሰ ጉዳይ የለም፤ ያ ሁሉ ድካሙ ደግሞ ፍትህን ፍለጋ ነበር። አፍላጦን ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንዴት ነው ልትኖረን የምትችለው? እያለ ሲመራመር የሰውን ነፍስ በሦስት እንደከፈላቸውና በኛ ማህበረሰብ ዘንድ ነፍስ ፍጹማዊ የሆነ አንድ ንጹህ ባህሪ ያላት ተደርጋ ስለምትቆጠር፤ የአፍላጦንን “ነፍስ” በእኛ ሃገር የ”ልቦና” እሳቤ እንደተካነው ባለፈው ሳምንት አይተናል። ስለዚህ ሦስቱን ዓይነት የአፍላጦንን ነፍስ፤ ሦስት ዓይነት ልቦና ብለናቸዋል። ልክ ሦስት ዓይነት ልቦናዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ብለናል። ሁላችንም እኩል አንድ አይነት ችሎታ የለንም፤ አንዳንዶቻችን ጥሩ ሠራተኞችነን                  /appetitic/ አንዳንዶቻችን ጠንካራ ጠባቂዎች              /auxiliary/ ወታደሮች /guardians/ ነን፤  ሌሎቻችን ደግሞ መልካም ተመራማሪዎች ነን /spirit/። ስለዚህ ፍትህ የሰፈነባትን ሃገር ለማግኘት ልጆቻችንን ይሄን ተረት እየነገርናቸው፣ ትምህርትም እንደየ አቅማቸው እንደየ ልቦናቸው ጠባይ እየተመጠነ ይሰጣቸው። ምርታማነትን፣ ክህሎትን፣ ፍላጎት ማመጣጠንን፣ ገበያ መፍጠርን ወዘተ ለብረታዊ ልቦች /the appetite/ እናሰልጥን። ዜጋንና ጠላትን መለየትን፣ ሃገርን ማስከበርን፣ ትእዛዝ ተቀባይነትን፣ ወኔን መቆጣጠርን ደግሞ ለብራዊ ልቦች /the auxiliaries/ እናስተምር። አለማዳላትን፣ ፍትሃዊነትን፣ ግለ ጥቅም አልባነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ አመራር ሰጭነትን፣ ተመራማሪነትን ደግሞ ለወርቃማ ልቦች /the spirit/ ስልጠና መስጠት ይኖርብናል፤ ተባብለን ብረታዊ/ መዳባዊ ልቦናዎች ምን ዓይነት ጠባይ እንዳላቸውና በምን ዓይነት የሥራ መስክ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ባለፈው ሳምንት አይተናል። ዛሬ ደግሞ እነሆ ብራዊ ልቦና፡-
ብራዊ ልብ፥ ይህ ልብ ወኔያም ደፋር ነው፤ ጦረኝነት /ጀብዱ ይወዳል፣ ቁጡ ነው፣ እንደ ብር ጠንካራ ነው፣ በራስ መተማመኑ ከፍተኛ ነው፣ አዳዲስ ነገሮችን ይደፍራል፣ ልዩ መሆንን ይመርጣል፣ አሸናፊነት ባህሪው ነው፣ አይንበረከክም። ሃገር ጠባቂ መሆን፣ ህዝብን ማስከበር፣ ኃያልነትን፣ ግዛት ማስፋትን ይወዳል። ይህ ልቦና እንደ አንበሳ ብርቱ ነው። ነገር ግን ኃይለኝነት የሚገዛው፤ ወኔውን መቆጣጠር የማይችል ነው።
ብራዊው ልብ ተከታታይና ጥንቃቄ የተሞላባቸውን ትምህርቶች መማር አለበት፤ በጠላትና በወዳጅ መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ ተረድቶ፣ ተገንዝቦ፣ አስተውሎ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድን መሰልጠን ይገባዋል። በዜጎችና በወራሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ ካልተገነዘበ፤ ለጠላት መጠቀም ያለበትን ኃይል ዜጎች ላይ ሊፈጽመው ይችላል እናም ማብቂያ የሌለው የውድመት ሰንሰለት ሊፈጥር ይችላል።
ወዳጁን በቀላሉ በማየት ብቻ መለየት እንዲችል ሆኖ መሰልጠን ይኖርበታል፤ ጠላቱንም እንደ አዳኝ አውሬ በቅጽበት እይታ ለይቶ ጉሮሮ ለጉሮሮ የሚተናነቅ ሰብዕና ሊኖረው ይገባል። ለጠላቱ መውሰድ ያለበትን እርምጃ ለወዳጆቹም አደረገ ማለት ሌላ ጠላት ሳይገባባቸው እርስ በእርስ የሚተላለቁ ማህበረሰቦች ሆኑ ማለት ነው። ስለሆነም በከፍተኛ ወጭ እጅግ የሰለጠኑ አሰልጣኞች ተመድበውለት፣ ትክክለኛውን የብርማ ልቦና እንዲላበስ መደረግ ይኖርበታል። አንበሳ ልጆቹንና ሚስቱን ብሎም ተወላጅ ቤተሰቦቹን የሚንከባከብበት ጠባይና ለቤተሰቡ ምግብ የምትሆነውን አጋዝን የሚያንቅበት ጠባይ እጅግ የተራራቁና የማይመሳሰሉ ጠባዮች ናቸው፤ ነገር ግን እነዚህን እጅግ የሚቃረኑ ጠባዮቹን ያው እራሱ አንበሳ በውስጡ አስታርቆ ያስተዳድራቸዋል እንጅ የገዛ ሚስቱን እንደ አጋዝኗ አንቄ ካልገደልኩሽ አይልም፤ ካልታመመ በስተቀር።
የብራዊ ልቦና ጀብዱ የሚጠቅመው ከጠላት ጋር በሚያደርገው ግብግብ እንጅ ከዜጎች ጋር በሚያደርገው መስተጋብር የቤት ጠባቂ ውሻ ያህል ጭራውን እየቆላ መቅለስለስ ይጠበቅበታል፤ ጠንካራው ክንዱ ጠላትን ለመጠርመስ መዋል አለበት እንጅ ከቤተሰቡ ጋር ሲሆን መጎራረስ ይጠበቅበታል፤ አለመንበርከክ የሚገባው ለሃገሩ ጠላት ነው እንጅ ከልጆቹ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ሁሉ ተሸናፊ ሆኖ መጫወትን ሊከለክለው አይገባም። እነዚህን ባህሪዮቹን ማቻቻል ካልቻለ የራሱ አረር አውዳሚ፣ ለራሱ ቤተሰብ አፍራሽ፣ እራሱን በራሱ የሚያቆረቁዝ ከመሆን አይድንም። ስለ ፍትህ፣ ስለ እውቀት፣ ስለ ስነምግባር፣ ስለ ኅላዌ መመራመርና መፈላሰፍን መለማመድ አለበት። ትክክለኛውን የእውቀት አስገኝ የሆነውን ብርሃን ለማግኘትም የሚታትር መሆን ይጠበቅበታል፤ በጥላና በእሳቱ ውጋገን የሚፈጠሩ ብዥታዎችን እየተከተለ የሚባዝን መሆን የለበትም። ኮሽታዎችና ድንፋታዎች የሚያስደነብሩት ድንባዣም መሆን የለበትም። ይህንን ድንባዣም ባህሪውን በትምህርትና በልምምድ ካላሻሻለ እራሱም ወድሞ ሃገርም ያወድማል።
የአንበሳን ጠባይ በእጅጉ ሊዋሃደው ይገባል ይህ ልቦና፤ አንበሳ ለጠላቶቹ እጅግ ቂመኛ ከመሆኑ የተነሳ አዳኞች ካቆሰሉትና ከተረፈ ጠረናቸውን በማሽተት እየተከተለ ያቆሰሉት አዳኞች የሚኖሩበት መንደር ድረስ በመሄድ ይበቀላል። አባቶቻችን እንዲህ ይላሉ፡-  ‹‹የመንገዱን ዳርዳር በሙሉ ለሃጩን እያዝረበረበ በለሃጩ ይለቀልቅና ወደ ገደል አፋፍ የምትወስደውን መንገድ ብቻ ይተዋታል፤ ከዚያ በኋላ ከዳገት አፋፍ ላይ ይወጣና በከባድ ድምጽ ያገሳል/ይጮኻል፤ የዚያን ጊዜ በዚያ መንደር ያሉ ከብቶች ይደነግጡና ከየበረታቸውና ከታሰሩበት ገመድ እየዘለሉና እየበጠሱ ከግቢያቸው ይወጣሉ፤ የሚጠብቃቸው ግን የአንበሳው ለሃጭ ስለሆነ አንበሳውን የሸሹ እየመሰላቸው በተሳሳተ መንገድ ሄደው ገደል ውስጥ እየገቡ ተሰባብረው ይሞታሉ››
አንበሳ  ደፋር፣ ኃይለኛ፣ ጠንካራ ነው እና የብር ልብ ያልነውን ኢትዮጵያዊ አንበሳ ይወክልናል ይመስለኛል። አንበሳ ለጠላቶቹ እንደዚህ የከፋ ጉዳትን ማድረስን በተፈጥሮው ተጠብቦ፣ ተውቦ፣ ተዋህዶታል። ብራዊ ልቦና ለጠላት እጅግ ክፉ፣ ለወዳጅ እጅግ ፍቅር ሰጭ መሆን ይጠበቅበታል። መዳባዊ ልቦናዎች የሚሰሩትን እያንዳንዱን ጥቃቅን ድርጊት በጥንቃቄ የለየና የተማረ መሆንም ይጠበቅበታል፤ የራሱ አምራች ዜጎች የሚሰሩትንና የሚያመርቱትን በጥንቃቄ መለየቱ ጠላቶቹ ከሚሰሩትና ከሚያመርቱት ሁሉ ለይቶና አግልሎ እንዲያውቅ ያስችለዋል። መንፈሰ ጠንካራነቱና አዳዲስ ነገር ደፋሪነቱ ለሃገሩ በሚጠቅም በማናቸውም መንገዶች ሁሉ እንዲሳተፍ የሚያስችሉት ጠባዮች ሆነው ከራሱ ጋር ሊዋሃዱት ይገባል። አስተዋይና ተመራማሪ መሆን አለበት።
ግዮን ብራዊም ነው፤ ጀግንነትና ጀብዱ ባህሪው ነው። በአምስቱ አመት የአርበኝነት ዘመን ለኢትዮጵያ አርበኞች መሸሸጊያ ዋሻ ሆኖ አገልግሏል። ጥላ፣ጎጆ ሆኗቸዋል፤ ሲደክማቸው ብርታት፣ ሲጨንቃቸው ተስፋ ሆኗቸዋል። ‹‹ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው፥ ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው›› የሚለው እንጉርጉሮ የአባይንና አካባቢውን አርበኝነት፣ አልገዛም ባይነት የሚያስታውሰን ነው (ሶማ በረሃ የአባይ ድንበርተኛ በረሃ ነውና)። ኃይለኝነቱን በጠባይ መያዝ ላወቀበት ግዮን የኃይል ምንጭ ነው። በአልገዛም ባይነቱና ባሸናፊነቱ የኢትዮጵያን ተራሮች አቋርጦ፣ የሱዳን በረሃ ሳያመነምነው፣ የግብጽ አሸዋ ሳይመጠው፣ ሁሉንም ድል አድርጎ ሜድትራኒያን ባህር ይቀላቀላል።  ኃይለኝነት ባህሪው ነው። በፍቅር ሲጠጡት ነው ጤና የሚሰጥ እንጅ ክፋት ይዘው ቢጠጡት ጤና ይነሳል፤ እንደ ስካር አናት ላይ ወጥቶ ቋንቋ ይደበላልቃል። ነብዩ ሙሴ ከአባይና ከአባይ መንፈስ ጋር በመስማማቱና በመጣጣሙ፣ ከካህኑ ዮቶር ቤት ሳይርቅ፣ በለምለም ተክል ላይ እሳት እየተንቦለቦለ ተዋህደው አየ፤ እሳትና ነበልባል ከሐመልማልና ልምላሜ ጋራ በአንድነት አንዲት ተክል ላይ ተዋህደው ማየት ቻለ። ግዮን ለሚራቀቁበት ረቂቅ ጥበብን ይገልጣል፤ ቁጡነትንም ትኁትነትንም ያቀዳጃል።
ብራዊው ባህሪ ገናና ሆኖ ጉልበተኛና አውዳሚ እንዳይሆን፤ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላባቸው ስልጠናዎችን እስኪጨርስ ድረስ ወደ መሪነት ወንበር መጠጋት የለበትም ይለናል አፍላጦን። ምክንያቱም ፍትህ የሰፈነባት ሃገር ለማግኘት አያስችልምና። ዜጋንና ጠላትን መለየትን፣ ሃገርን ማስከበርን፣ ትእዛዝ ተቀባይነትን፣ ወኔን መቆጣጠርን ለብራዊ ልቦች /the auxiliaries/ እናስተምር፤ ኃይለኝነቱን በምክንያታዊነ ት/አመክንዮ/ ማሸነፍ ይለማመድ። እንደ ግዮን የተራሮች ድንፋታውን በሱዳኖችና በግብጽ የአሸዋ ሜዳ ሳይፈጽም ለሜዳው እንደ ባህሪው በስክነት፣ ለተራራው እንደ ባህሪው በፍጥነት መጓዝን ከተለማመደ ያለ ምንም ችግር ከታላቁ ባህር ከሜድትራኒያን ይቀላቀላል፤ ያለ ውድመት፣ ያለ ጥፋት።
ኢትዮጵያዊ ከጥንትም ጀምሮ አሁንም ድረስ ዳር ድንበሩን ማስከበር፤ አልገዛም ባይነት፤ጀግንነት ባህሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊን በዚህ የሚጠረጥረው ማንም የለም፥ ካለም የጁን ያገኛል። ዛሬም ድረስ የአካባቢውን ሰላምና የአለምን ደህንነት ለማስከበር ደፋ ቀና ከማለት አልቦዘነም፤ ኢትዮጵያዊ። ኃይለኝነትና ጀብዱ እንደ ባህሪ ተዋህደውታል። ጦሩን ሰብቆ ጋሻውን ነጥቆ አፈር ከድሜ ያበላቸው ጠላቶቹ፤ ለኢትዮጵያዊ ደፋር ልቦና ምስክር ናቸው (ግብጾችና ጣልያንን ያስታውሱ)።






Read 1576 times