Thursday, 05 April 2012 13:07

ማንዴላን የሚተውነው ደቡብ አፍሪካዊ ብቻ ነው ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የነፃነት ታጋዩና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ በፃፉት “Long walk to Freedom” መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ በሚሰራው የህይወት ታሪካቸውን የሚያሳይ ፊልም ላይ ማንዴላንን ወክሎ የሚተውነው ደቡብ አፍሪካዊ ብቻ ነው በሚል የተወሰነውን ውሳኔ “ዘ ጋርዲያን” ጋዜጣ ተቸ፡፡

ሰሞኑን የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮች በሰጡት መግለጫ፤ ማንዴላን ለመተወን ከደቡብ አፍሪካዊ ውጭ ሌላ ተዋናይ አንፈልግም ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣው፤ የማያሳምን ውሳኔ በሚል  ነቅፎታል፡፡  የ”ጎልደን ግሎብ” ተሸላሚው ኢድሪስ ኤልባ በፊልሙ ላይ ማንዴላን ለመተወን ዋና እጩ እንደነበር የጠቀሰው “ዘ ጋርድያን”፤ የ39 ዓመቱ የፊልም ተዋናይ የደቡብ አፍሪካ ትውልድ ቢኖረውም በዜግነቱ እንግሊዛዊ በመሆኑ እድሉን እንዳጣ አመልክቷል፡፡ ፊልሙን በተሳካ መንገድ ለመስራት ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ተዋናዮች መወዳደር ነበረባቸው ያለው ጋዜጣው፤ በቂ ልምድ የሌላቸው የደቡብ አፍሪካ ተዋናዮች ይሰሩታል መባሉንም አጣጥሎታል፡፡ ከእስር ከተፈቱ 22 ዓመት በሆናቸው የ94 ዓመቱ ኔልሰን ማንዴላ ህይወት ዙሪያ የተለያዩ ፊልሞች የተሰሩ ሊሆን ማንዴላን በመተወን ትላልቅ የሆሊውድ ተዋናዮች መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ ከተዋናዮቹም መካከል ዳኒ ግሎቨር፤ ሲድኒ ፖይተርና ሞርጋን ፍሪማን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

 

 

 

Read 1060 times Last modified on Thursday, 05 April 2012 13:08