Sunday, 16 July 2017 00:00

አቶ በቀለ ገርባ በሽብር ህጉ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

በሽብር ወንጀል ተከስሰው የነበሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ  ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ ክስ በቀረበባቸው የሽብር ህጉ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጣቸው በክስ መዝገቡ ከተካተቱት አምስቱ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ከትላንት በስቲያ በዋለው ችሎት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተከሳሾች በተካተቱበት መዝገብ ላይ የአቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መቅረብን ተከትሎ ብይን ሰጥቷል፡፡ ቀጥተኛ ሽብር በመፈፀም ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ፤ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው የማስረጃ ዝርዝር የሽብር ወንጀልን የሚያመለክት ባለመሆኑ ግዙፍ ባልሆነ መሰናዳትና መገፋፋት ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
በቀጥተኛ ሽብር ድርጊት ተሳትፈዋል ተብለው በመዝገቡ ከተካተቱት መካከል የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑትን አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች ክሳቸው “በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ” በሚል ተቀይሮ እንዲከላከሉ ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡
በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ክስ ተመስርቶባቸው ከነበሩት 13 ግለሰቦች መካል አምስቱ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን ቀሪዎቹ አስቀድሞ በተከሰሱበት እንዲከላከሉ ተበይኗል፡፡
በእለቱ አቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ በጠበቆቻቸው በኩል በቃል አውርበው የነበረ ሲሆን ፍ/ቤቱ በፅሑፍ አስገቡ ብሏቸዋል፡፡
ፍ/ቤቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮች ለማድመጥ ከነሐሴ 8-12 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡ 

Read 2119 times