Thursday, 05 April 2012 13:05

አዲካ የአመቱን ምርጥ ኮንሰርት ሊያዘጋጅ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

10ሺ ሰዎች ይገኙበታል ተብሎ ይታሰባል

የናቲና የአቤል አልበሞች በድጋሚ ሊመረቁ ነው

አዲካ የኰሚዩኒኬሽንና ኢቭንት አዘጋጅ ድርጅት የአመቱ ምርጥ የተባለውን ኮንሰርት ሊያዘጋጅ ነው፡፡ በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርትም ከአስር ሺህ በላይ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ድርጅቱ ለዝግጅት ክፍሉ የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው የፊታችን ሚያዝያ 13/2004 ዓ.ም በላፍቶ ሞል በሚዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ድምፃዊ ናትናኤል አያሌው /ናቲ ማን/ በዋነኛነት ሥራዎቹን የሚያቀርብ ሲሆን ፀደኒያ ገብረማርቆስ፣ ጆሲ ገብሬና ቤቲ ሙዚቃዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ አዲካ በቀጣይነትም የአቤል ሙሉጌታ፣ የሺ ደመላሽንና ትርሀስ ታረቀኝን ኮንሰርቶች እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል፡፡

አዲካ በቅርቡ ከወጣቶቹ ድምፃውያን ናትናኤል አያሌውና አቤል ሙሉጌታ ጋር ባደረገው የሥራ ስምምነትና ፊርማ መሰረትም የሁለቱን ወጣቶች የሙዚቃ አልበሞች በክለብ ዘ20 መጋቢት 27/2004 ዓ.ም በድጋሚ ለማስመረቅ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡ “አምሮኝ” በተሰኘው የመጀመርያ ነጠላ ዜማው ተወዳጅነትን ያገኘው ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በያዝነው አመት ለአድማጭ ጆሮ ያበቃውና “ማን” የተባለው አልበሙ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታል፡፡ በዚህ አልበሙ ላይ ስድስት የሚደርሱ አዳዲስ ሥራዎችን በመጨመር፣ በድጋሚ ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ የሚገኘው ናትናኤል (ናቲ ማን) ከአዲካ ጋር በአጠቃላይ የሙዚቃ ሥራዎቹን አስመልክቶ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው የ28 ዓመቱ ወጣት ድምፃዊ አቤል ሙሉጌታ፤ በቅርቡ የለቀቀውና “ተገርሜ” የሚል ስያሜ የሰጠው አልበሙ ከ50ሺህ በላይ ኮፒዎች ተሸጧል፡፡ ይህ አልበሙ ከፍተኛ ተቀባይነትን አስገኝቶለታል፡፡ አቤል ከአዲካ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ይህንኑ አልበም “ወዶ አይስቅም ጥርሴ” እና “የልቤን አውቃ” የተሰኙ ሁለት አዳዲስ ዘፈኖችን በማካተት መጋቢት 27/2004 ዓ.ም በክለብ ዘ20 በድጋሚ ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ታውቋል፡፡ አቤል ከአዲካ ጋር ያደረገው ስምምነት አልበሙን በድጋሚ ከማስመረቅ ጀምሮ ሌሎቹ የማስተዋወቅ ሥራዎችንና በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ኮንሰርቶችን ማቅረብንም ሥራንም እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡ በቅርቡ “ሸኮሪና” የተሰኘ ነጠላ ዜማዋን የለቀቀችውና በመጪው ሰኔ ወር ሙሉ አልበሟን ታወጣለች ተብላ የምትጠበቀውም ድምፃዊት አበባ ላቀው /አቢ ላቀው/፤ ከአዲሱ አልበሟ መለቀቅ በፊት ከአዲካ ጋር እንደምትፈራረምም ታውቋል፡፡ታዋቂ ድምፃውያንን በማስተዋወቅና ኮንሰርቶችን በማዘጋጀት እንዲሁም ሥራዎቻቸውን በማሰራጨት ሥራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው አዲካ ከዚህ ቀደም የሃይሌ ሩትስ፣ ትርሀስ ታረቀኝ /ኮበሌና/ የየሺ ደመላሽን ሥራዎች በማስተዋወቅ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

 

 

Read 1654 times Last modified on Thursday, 05 April 2012 13:08