Sunday, 09 July 2017 00:00

የዲሞክራሲ ጉዞ ምን ተይዞ?

Written by  አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ (በሀርቫርድ ዩንቨርስቲ፣ የበርክማን ክላየን ሴንተር፣ ሪሰርች ፌሎው)
Rate this item
(2 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
የሚዲያ (መገናኛ ብዙኃን) ብዝኃነትን በተመለከተ በዲሞክራሲ የተሻለ ልምድ ካላቸው የአፍሪካ አገራት ቀርቶ ታዳጊ ዲሞክራሲን እየገነቡ ነው ከሚባሉት አገራት አንፃር እንኳ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ  ስለሚገኘው የአገራችን የሚዲያ ነባራዊ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት የተወሰኑ ነጥቦችን አውስቼ ነበር፡፡ ከዛው ሐሳብ በመቀጠል በአጭሩ በግል መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ በፕሬሱ አሁንም ድረስ ዕለታዊ የሚባል አንድም ጋዜጣ የሌለን መሆኑን፣ በቲቪው ዘርፍም ቢሆን የአገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችንም መሰል መሰረታዊ ነገሮችን የተመለከተ የምርመራ ሆነ ሰፋ ያለ የዜና ዘገባ የሚቀርብበት የቲቪ ጣቢያ ከ25 ዓመታት በኋላም ያልታዳልንበትን ጉዞ ወደ ኋላ በመፈተሽ፣ ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃር  እንደ አንድ ማገር ስለሚቆጠረው ሚዲያ እና ተያያዥ መሰረታዊ የመናገር ነፃነት መብቶች መሸራረፍ ቅፅበታዊና ዘላቂ ጉዳቱን በተመለከተ የተወሰኑ ነገሮችን ለማለት ወድጄያለሁ፡፡
ያለፈው ጊዜ የትም አልሄደም
(the past didn’t go anywhere)
የተለያዩ መዛግብት እንደሚጠቁሙት፤ በኢትዮጵያ ከመናገር ነፃነት ጋር በተያያዘ በሕግ እውቅና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ተሻሽሎ በወጣው የ1948ቱ ህገ መንግስት ነው፡፡ በዚህ ህገ መንግሥት አንቀፅ 41 ስር፤ “በመላው የንጉሰ ነገስት ግዛት ውስጥ በህገ መሰረት የንግግር እና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው።” በሚል ተደንግጎ ነበር። በተጨማሪም የኤርትራ ህገ መንግስት በአንቀፅ 12/d/ ስር ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን እና የፌደራል መንግስት ይህን መብት የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በደርግ ዘመነ መንግስትም ማክተሚያው ገደማ ማለትም መስከረም 1 ቀን1980 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አዋጅ በአንቀፅ 47/1/ ስር፤ ኢትዮጵያዊያን የንግግር፣ የፅሁፍ፣ የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በአጭሩ በቅድመ ኢህአዴግ አገሪቱ በወረቀት ደረጃ ለመናገር ነፃነት እውቅና ብትሰጥም በተግባር ግን ሕጉ የመገናኛ ብዙኃን በሌሎች አገራት የሚጫወቱትን ሚና ለመጫወት አልቻሉም፡፡
ከእርስ በርስ ጦርነቱ ማግስት በኋላ በርግጥ የሽግግር ወቅት ቻርተር በክፍል 1 አንቀፅ (1) (ሀ) ስር የእምነት እና ሀሳብን የመግለፅ መብቶች ስለመጠበቃቸው እንዲሁም በ1987 ዓ.ም በፀደቀው በአገሪቱ ህገ መንግስት አንቀፅ 29 ስር፤ ሀሳብን የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት ስለመረጋገጡ ይደነግጋል። ከዚህ ውጪም በተባበሩት መንግስታት የፀደቀው የሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights)፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን (International Convenant on Civil & Political Rights)፣ የአፍሪካ የግለሰብና የቡድን መብቶች ቻርተርን ጨምሮ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ሆነ በአህጉራዊ ደረጃ ያፀደቀቻቸው ስምምነቶች የህገ መንግስቱ አካል ስለመሆናቸው ተደንግጓል፡፡  የሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሮች ላይ ተፈፃሚነት ያለው የሰብአዊ መብት መግለጫ ሲሆን ለምሳሌም በአንቀፅ 19 ስር፤ “ማንም ሰው አስተያየት የመስጠት ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እና መብት አለው። ይህ መብት እንያንዳንዱ ሰዉ ያለምንም ተፅዕኖ አስተያየት እንዲኖረዉና እና ጠረፍ ሳይወስነዉ በማናቸዉም ዓይነት መሳሪያ መረጃዎችን ወይም አሳቦችን የመፈለግ የመቀበልና የማስተላለፍ ነፃነትን ይጨምራል” በማለት ሰዎች ነፃ የሆነ ሀሳብን የመግለፅ እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ዋናው ጉዳይ ያለው እዚሁ ላይ ነው። አንድ መንግስት ዲሞክራሲያዊ ነኝ ካለ፣ ዋናው የሚጠበቅበት ማንኛውም ዜጋም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመናገር ነፃነቱ ሳይሸራረፍ ሐሳቡን ለማሰራጨት ይቻለው ዘንድ የሕግ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግን በራሱ ቋንቋ ለማነጋገር ትልቁ ጥያቄ ከላይ የተወሱትን መብቶች በወረቀት ማስፈሩ ሳይሆን ዋናው ጉዳይ እነዚህ መሰረታዊ ሰው በመሆን የሚገኙ መብቶች  በተግባር ላይ ይውሉ ዘንድ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ጥበቃ ተደርጎላቸዋል? የሚለው ነው፡፡ ‹‹ስለ ምን?›› ቢሉ እንኳን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት እገነባለሁ በሚል መንግስት ቀርቶ በአምባገነኖች ሥርዓት ዘንድ ሳይቀር የመናገር መብት ሰው በመሆን የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ሰው በመሆን ብቻ የሚገኝን መብት ደግሞ መጠበቅ እንጂ ሰጠሁ ማለት አይቻልም፡፡
እንደ ሌሎች አፋኝ ስርዓቶች ሁሉ ለመንጠቅ መሞከር ግን ይቻላል። ኢህአዴግም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህንኑ እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን የመናገር ነፃነት ልክ እንደ አይን ሆነ ጆሮ ስንወለድ የሚኖረን በመሆኑ፣ ዛሬ ከቃሊቲ እስከ ዝዋይ ዋጋ የሚከፍሉ ወገኖችም አታህ ፊሊፕስ እንዳለው፤” በመናገር ሰብዓዊ መብቴ አልደራደርም” በማለታቸው የሚከፍሉት መስዋዕትነት ለነፃነት የሚሰጡት ዋጋ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከዲሞክራሲያዊ መሰረታዊ መስፈርቶች አንዱ በሆነው የሚዲያው ነባራዊ ሁናቴ አገራችን ያለችበት ሁኔታን ስንገመግም ያለፈው ጊዜ የትም አልሄደም (the past didn’t go anywhere) የሚያሰኘው፡፡
‹‹የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመገናኛ ብዙኃን››
የኢህአዴግ የተለያዩ ዶክመንቶች በግል ሚዲያው ላይ የሚያዘንቡት አቤቱታ ማጠንጠኛ፣ ፓርቲው የመናገር መብትን በሕገ መንግስቱ በማስፈሩ እንደ ውለታ እንዲቆጠርለት ለማስመር  በመጣር፣ የግል ሚዲያው እንደ መንግስት ሚዲያው ሁሉ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ  የተባለውን መስመር ካልተከተለ ባይ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ማስረጃ የምጠቅሰው ‹‹የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና ስትራቴጂ›› አዲስ ረቂቅ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ስለማስታወቁ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨውን ዜና ነው፡፡ ማንኛውም አገር የሚዲያ ፖሊሲ እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው መንግስትም የሚዲያ ፖሊሲ ማውጣቱ ባይገርምም ከዚህ ቀደም ብዙ ሲወራለት ከነበረውና ምንም ሳይፈይድ ከተዘነጋው የሚዲያ ፖሊሲ በስም የተለየውን በግልፅ ግን ‹‹የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመገናኛ ብዙኃን›› በማለት የተሰየመው ይኸው ፖሊሲ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በሂልተን ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃንና ለኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ለውይይት በቀረበበት ወቅት ለረቂቅ ፖሊሲው መዘጋጀት እንደ ምክንያትነት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የህዝብ፣ የግልም ሆነ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን የሚመሩበት ራሱን የቻለ የተጠቃለለ ሀገራዊ የፖሊሲ ሰነድ አለመኖር በዋናነት በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በወቅቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዴኤታው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ እውነቱ ብላታ፤ ‹‹ፖሊሲው የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሽን፣ በልማታዊና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ የልማት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የህልውና ጉዳይ አድርጎ እንዲሰራ ያደርጋል›› ብለው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይሄ ከመጠሪያው ጀምሮ ችግር ያልተለየው ፖሊሲና ‹‹በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ›› የተባለለት ‹‹የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና ስትራቴጂ አዲስ ረቂቅ ፖሊሲ›› በርካታ ውይይቶች ከተደረጉበት በኋላ በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጀመሪያ ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን በወቅቱ የተነገረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ፖሊሲው ያለበት አይታወቅም፡፡ ከዚህ በይበልጥ የሚገርመው ደግሞ በአገሪቱ ብዙ በተባለለት የሁለተኛው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ‹‹በርግጥ የግል ሚድያን አቅም ለማጠናከር መንግስት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመመካከር የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡›› ከማለት ውጪ ምንም አይነት ዘርፉን ለማሳደግ ስለሚከናወኑ ነገሮች አለመጠቀሱ ነው፡፡ ያም ሆኖ የነፃ ፕሬሱን ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን የተመለከተው ፖሊሲ በተለይ ‹የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመገናኛ ብዙኃን›› በሚል የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃንን በፓርቲው አይዲዮሎጂ በአንድ ማቀፍ የመጥራቱ አዝማሚያ ፓርቲው የተዘፈቀበትን የፓርቲ እና መንግስት ሚና ያለመለየት አባዜ በግልፅ ያሳያል። በተለይ እንደ ማንኛውም ገዢ ፓርቲ የራሱን አይዲዮሎጂ የማራመድ መብት ቢኖረውም የአገሪቱን ሚዲያ በሙሉ የእኔን አይዲዮሎጂ ተከትላችሁ ተንቀሳቀሱ ማለቱ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል›› የሚለውን ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ኢህአዴግ ‹‹ልማት›› እያለ በሚያወሳው ሀሳብ ላይ እንኳ ሰዎች የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ይታወቃል። ስለሆነም ሚዲያውን የማዳከሙ ብቻ ሳይሆን የወደፊት አቅጣጫውን ጭምር በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት የሚለው የፓርቲው ሀሳብ እንኳን ለነፃ ሚዲያው ቀርቶ ለመንግስት ሚዲያው እንኳ የማይበጅ ነው። የህገ መንግስቱም (አንቀጽ 29/ለ/5) በርግጥ ‹‹በመንግስት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል›› ይላል። በመሆኑም ፓርቲው የራሱን ልሳኖች በፈለገው አይዲዮሎጂ ማሽከርከር ቢችልም ከህዝብ በሚሰበስበው ገንዘብ  የቆመው የመንግስት (የሕዝብ) ሚዲያ ግን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ እንዲችሉ ሆነው መመራት እንደሚኖርባቸው ህገ መንግስቱ ያዛል፡፡ ነገር ግን የራሱ ድርሻ የሆነውን ህግ ለማክበር ገዢው ፓርቲ ባለመፈለጉ፣ ከዚህም ባለፈ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት አስከባሪ ነፃ የፍትህ አካል በመጥፋቱ “የሕዝብ” የሚል ካባ የተደረበለት የመንግሥት ሚዲያው፣ አልፈዋል እንደተባሉት የቀድሞ ሥርዓቶች መገናኛ ብዙኃን ሁሉ የመንግሥቱ አፈ ቀላጤ ከመሆን ዛሬም  ፈቀቅ አላለም። ይባስኑ ብሎ ጭራሽኑ ለፓርላማው ዘገባ እንኳ ያነሰ ሆኖ ተገኘ። ‹‹ኢቢሲ የፓርላማውን ጉዳዮች ለምን በአግባቡ እንደማይዘግብ የሚያስረዳ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ስለመታዘዙ›› በዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቅርቡ መዘገቡ የሚታወስ ነው። የዚህ ሁሉ መንስኤው የታዳጊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት የሆኑት አገራት በተጓዙበት መንገድ ሚዲያው እንዳይሄድ መደረጉ ነው። የአንድ ፓርቲን ሥርዓት አገሪቷ በምትከተልበት የደርግ ዘመን  የኢሰፓ አባላት የተቋሙ ሰራተኞች እንደነበሩት ሁሉ የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት እየገነባን ነው በሚባልበት በዚህ ዘመን ዋንኛ ሹሞቹ ብቻ ሳይሆኑ ከላይ እስከ ታች ያሉ የተቋሙ ሰራተኞች  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፓርቲ አባልነቱ ወደ ዕድገት መንገድ መሸጋገሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሁሉም የመንግስት ሚዲያ ሰራተኞች የኢህአዴግ አባል ባይሆኑም በተቋም ደረጃ ግን የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ባህል አልተፈጠረም፡፡ የትላንቱ ዘመን ኢቲቪ ገዢውን መንግስት አወዳሽ እንደመሆኑ ያሁኑም ከዚሁ አፋኝ ባህል አልተላቀቀም፡፡ የብዙኃን ሐሳብ የማስተናገድ ህገ መንግስታዊ ግዴታውን ካለማክበሩ ባለፈ ጭራሽኑ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት ጨፍልቆ፣ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት አላግባብ ዜጎች ላይ ሲፈርድባቸው  ተስተውሏል፡፡
“በኒዮ ሊበራል አሳቦ…”
የኢህአዴግ የሚዲያ ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ሰፍሮ ያለው ሌላው አስገራሚ ነጥብ  የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የግል ሆኖ በኒዮ ሊበራል ሃይሎች የሚመራ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ እነዚህን ኒዮ ሊበራሎች እንዲዋጋ ሆኖ መስራት አለበት የሚለውን ሐሳብ እንደ ማጠንጠኛ ማውሳቱ ነው፡፡ የሚገርመው ‹‹ላሞኛችሁ ዝም በሉ›› ከሚል አንድ ተራ ካድሬ ካልሆነ በቀር እንዲህ አይነት መከራከሪያ በዚህ ዘመን ያውም በሚዲያ ፖሊሲ ላይ ማንሳቱ አሳፋሪ ነው፡፡ አንደኛ ምንም እንኳ በአሜሪካ ሆነ  በምዕራቡ ዓለም ሊበራሊዝም ፍልስፍና መሰረት ግዙፉ የግል ሚዲያ ተቋማት መኖራቸው እሙን ቢሆንም ሚዲያው በሙሉ ግን በግል ዘርፉ ብቻ የታጠረ ወይም ኢህአዴግ እንደሚለው “በኒዮ ሊበራሎች” ብቻ የሚመራ አይደለም፡፡ በአሜሪካ ብቻ ከ14,000 በላይ ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ የሚደጎሙ የራዲዮ መገናኛ ብዙኃን፣ ከ350 በላይ የቲቪ ቻናሎች ያሉ ሲሆን የአውሮፓ ትልቁ ሚዲያ ተቋም ቢቢሲም እንደዚሁ በሕዝብ በተገኘ ገንዘብ የሚደጎም ነው፡፡ ሌላኛው ከአውሮፓ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጀርመኑ ዜድኤፍን ጨምሮ በዓለም ላይ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አተገባበር ከአንድ እስከ አስር አራት ያሉ የምዕራብ አገራት በሙሉ በመንግስት የሚደጎም የሚዲያ ተቋም አላቸው።  ይሄን በቀላሉ የተለያዩ ጥናቶችን በማገላበጥ ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን ፓርቲው ራሱን አገሪቷን ሊበዘብዙዋት ከሚመጡባት ኒዮ ሊበራሎች ለማዳን የተቀመጠ አዳኝ አድርጎ አይዲዮሎጂውን የሚተነትንበት መንገድ ልክ እንደ ቀድሞው ዘመን የሶሻሊስት ፍልስፍና አገሪቷ ካንድ ፓርቲ በላይ አይዲዮሎጂ እንዳይኖራት ከማለም የተለየ አይደለም። የመገናኛ ብዙኃን እንደ አራተኛው የመንግስት አካል (The Fourt Estate) ተደርገው የሚታዩ እንደመሆናቸው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የላቀው  የሚድያ አንዱ ተግባሩ መንግስትን መቆጣጠር ነው፣ በመሆኑም መንግስት እመራበታለሁ የሚለው አይዲዮሎጂ እና መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩበት ፍልስፍና የተከለለ መስመር ሊኖረው ግድ ነው፡፡  እዚህ ላይ በመንግስትና  አገር  መካከል ሊኖር ስለሚገባው ልዩነት አሜሪካ ካፈራቻቸው ድንቅ ጸሃፍት መካካል የሚመደበው እውቁ ደራሲ ማርክ ትዌይን፤ “Loyalty to country always. Loyalty to government, when it deserves it.” (ለሃገር መታመን ሁልጊዜም፣ ለመንግስት ግን መታመን ሲገባው) በማለት ያወሳውን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡
የምዕራቡ ዓለም የመንግስት ሚዲያ ከኛው አገር መሰል ተቋማት የሚለዩት፣ ሚዲያዎቹ ለህዝቡ ጥቅም የቆሙና የገዢውን ፓርቲ ማንኛውም ብልሹ አሰራር ከማጋለጥ ወደ ኋላ የማይሉ በመሆናቸው ነው፡፡ የፓርቲው አፈቀላጤ ሆኖ የሚሰራውን የአገሪቱን የመንግስት ሚዲያ፣ የህዝብ ስለማድረግ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል። በጀርመን የሚገኘውና ከቢቢሲ ቀጥሎ በግዙፉነት ከአውሮፓ በሁለተኛነት ደረጃ የሚወሳው የሚዲያ ተቋም ዜድኤፍ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን የህዝብ ሚዲያ ተልዕኮውን ለመወጣት ይጠቀማል። ቀዳሚው የሚዲያ ቦርዱ አመራሮች ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት አመራሮችና ከሌሎችም በአገሪቱ ውስጥ ድርሻ ካላቸው አካላት የተወከሉ ሰዎችን ያቀፈ ነው። በመሆኑም በተቻለ አቅም ሚዲያው ህዝቡን እንጂ ለገዢው ፓርቲ ሆነ ስልጣኑ ላይ ላለ ማንኛውም ወገን እንዳይወግን የቦርዱ አመራር አባላት ስብጥር የራሱ ሚናን ይጫወታል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ በጣቢያው ውስጥ የሚስተናገዱ ዜናዎችን በሶስት ምዕራፍ በመክፈል የማለዳ፣ የእኩለ ቀን እና የምሽት ዜናዎችን የሚያስተናግዱ የተለያዩ ዜና ክፍሎችን በማዋቀር የዜና ክፍሎቹ እርስ በርስ ተፎካካሪና የየራሳቸው የተለየ የኤዲቶሪያል ስብሰባ እንዲኖራቸው ማድረጉ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ተመልካቹ አንድን ጉዳይ ከጠዋት እስከ ማታ በተመሳሳይ ሁኔታ ከመስማትና ማድመጥ ከመዳኑ ባለፈ የዜና ክፍሎቹ የተለየን መረጃ ለማቅረብ በሚያደርጉት የእርስ በርስ ፉክክር፣ የተለያዩ ጉዳዮችን በተለየ አንግል ለመስራትና የኢዲቶሪያል ነፃነታቸው ካላስፈላጊ ተፅዕኖ እንዲጠበቅ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ በሌላም በኩል በዲሞክራሲ የዳበሩ አገራትን የህዝብ ሚዲያ ተሞክሮ ያጠኑት የኒው ዮርክ ዩንቨርስቲዎቹ ሮድኒ ቤንሰን እና ማቲው ፓወርስ ‘’PUBLIC MEDIA AND POLITICAL INDEPENDENCE’’ በተሰኘው ጥናታቸው፤  በመንግስት (ገዢው ፓርቲ) እና በሕዝብ ሚዲያው መካከል የተሰመረ ልዩነትን ለማኖር በማሰብ አገራት የትኛውም ተመራጭ ፓርቲ ስልጣን እንደያዘ በሕዝብ ሚዲያ ተቋሙ ውስጥ ያሉ ሃላፊዎችን ሆነ ሰራተኞችን ከመሾም ከመሻር በህግ ስለመገደባቸው፣ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ተደራራቢ ያልሆነ የቁጥጥር ሥርዓቶችን ስለመዘርጋታቸው ከሌሎች አብነቶችም ጋር በስፋት ያትታሉ፤ በአጭሩ ግን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በገነቡት አገራት ያለው ተሞክሮ ተመሳሳይ ሲሆን ለብዝሃ ሀሳብ መስተናገድ ሲባል ለህዝብ መገናኛ ብዙኃኑ አመቺ የህግ ማዕቀፍ ከማውጣቱ ባለፈ አስፈፃሚው የመንግስት አካል ሆነ ተቆጣጣሪው በጭራሽ የህዝብ ሚዲያው ሊሰራ ስላቀደው ስራ የሚያውቁት ነገር አይኖርም፡፡  ይሄ ልማድ ለኤሌክትሮኒክስ ብቻ ሳይሆን በመንግስት ለሚደጎሙ የዲሞክራሲ አገራት ፕሬሶች ጭምር  የሚያገለግል ነው፡፡ በመሆኑም በስዊዲን፣ በኖርዌይ እና በፈረንሳይ የሚገኙ በመንግስት የሚደጎሙ ፕሬሶች ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡ በመሆኑም እንኳን በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ ፓርቲዎች ቀርቶ በፓርላማው እንኳ ከወቀሳ ያላመለጠውን ተቋም፣ በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠው መሰረት የሁሉንም ሐሳብ በተወሰነም መንገድ ቢሆን የሚያንሸራሽርበትን መሰረት የሚያሰፋበትን ዕድል ለመፍጠር የሚቻልበትን ሐሳብ ማቅረብ ይቻላል። ይሄን በማድረግ የዲሞክራሲ ባሕልን ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ በሚዲያው ዘርፍ ለማስረፅ ማስቻል ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ፓርቲ ወጋኝ ነው የሚባለውን የግሉን ሚዲያ ማሳጣት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ገዢው ፓርቲ ሌሎቹን የሚያስፈራራበትን ራሱ ግን እንዳሻው የሚሸራርፈውን ህገ መንግስት በማክበር፣ ህግን አክብሮ በማስከበር የዲሞክራሲያዊ ባህልን መሰረት በጣለ ነበር፡፡
በርግጥ ገዢው ፓርቲ ለዚህ የለውጥ ቁመና የተዘጋጀ አለመሆኑ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው በሚዲያ ጭምር ቀርበው ተቃዋሚዎችን የመረጠ የሀገራችን ህዝብ በመኖሩና የዚህ ህዝብ ድምፅ መሰማት ስላለበትም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር አካሂዳለሁ፣ ለዚህም የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ፣ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብተው ነበር፡፡ የሚገርመው ይህን ካሉ ከዓመት በኋላ ከተቃዋሚዎች ጋር ይካሄዳል በተባለው ድርድር በጭራሽ ሕገ መንግስቱን ስለማሻሻል አልደራደርም ብሎ፣ የቀደመውን ሳይጠየቅ የገባውን ቃል እንደተለመደው ማጠፉ ነው፡፡
ቶማስ ጀፈርሰን ብለውታል እንደሚባለው መረጃ የዲሞክራሲ መገበያያ ነው፡፡ (“Information is the currency of democracy”) ያለ አማራጭ ሐሳብን የማንሸራሸሪያ መንገድ ዲሞክራሲ ሊገነባ አይችልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ለግሉ ሚዲያ አስፈላጊውን ጥበቃና ማበረታቺያ ማድረግ የመንግስቱን ሚዲያ ከቁም እስረኛነት ማላቀቁ ግድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለዲሞክራሲ ሥርዓት መሰረት የሆነው ሚዲያ ሚናውን እንዳይወጣ መንግስት ጥበቃ በማድረግ ፋንታ ጥቃት አድራሽ ሆኖ የላቀ ደረጃ እንዳይደርስ ብቻ ሳይሆን አገሪቷን የሚጠቅሙ ሐሳቦች በሚገባ እንዳይንሸራሸሩ ጋሬጣ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ሆኖ የሚወሳው ለአራት ዓመታት ያህል ብዙ ሲያወዛግብ የቆየውና የብዙዎች ሐሳብ ሳይካተትበት በፓርላማ የፀደቀው ስለመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 540/2000 ነው። በጊዜው አዋጁ በተለይ የግል ሚዲያውን ለማጥቃት ይውላል፣ ህገ መንግስቱ ላይ ያለውን መብትም ይሸራርፋል በሚል ብዙ አከራካሪ አንቀፆቹ ቢያንስ እንዲወጡ  አሊያ እንዲለወጡ ቢጠየቅም በእምቢታ የፀናው ገዢው ፓርቲ  አዋጁ ‹‹ሀሳብን ለመግለፅ ነፃነት ዋስትና የሚሰጥ ነው›› ሲል የብዙዎችን ትችት ውድቅ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈው ምርጫ ዋዜማ ብዙዎች እንደፈሩት፣ መንግሥት ሕጉን እንደ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም የተለያዩ የነፃው ፕሬስ ልሳኖች በአንድ ምሽት ፀጥ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ የነፃው ፕሬስ እንከን አልባ ነው የሚል እምነት ባይኖረኝም ሕጉን ሆን ብሎ ለማጥቂያነት እያዋለ በሚገኝ የአፈና ሥርዓት ውስጥ ሌላው ዓለም የደረሰበት ለመድረስ ፕሬሱ ብዙ ድጋፍ ሊደረግለት በተገባ ነበር የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን በእግሩ ሳይቆም በሚቃጣበት ጥቃት የነፃ ሚዲያ ልሳናት እየተዘጉ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሃሳቦች መንሸራሸሪያዎች እየተገደቡ ነው፡፡
ሐሳብን በመገደቡ ፀጥ ማሰኘት ቢቻል ኖሮ፣ ሚዲያው ዝም እንዲል በተደረገበት፣ ገዢው ፓርቲ ከእነ አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ የፓርላማውን ወንበር በተቆጣጠረ ማግስት የህዝብ አመጽና ተቃውሞ ባልተነሳ ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ዳግም የዜጎች ንጹህ ሕይወት እንዳይቀጠፍ በቁርጠኝነት ስሜት ለለውጥ መዘጋጀት በተገባ ነበር፡፡ ይሄ ግን አልሆነም! ሃሳቤን የምቋጨው በአልበርት አንስታየን አባባል ነው፣ “Insanity: doing the same thing over and over again and expecting different results.” አገሪቱ ለገጠማት ተደጋጋሚ ችግር ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ የእሳት ማጥፋት እርምጃዎች በመውሰድ ብቻ የተለየ ውጤት መጠበቁ አንስታየን፣እንዳለው ከእብደት አሊያም ከአዕምሮ ንክነት የተለየ አይሆንም።






Read 1557 times