Saturday, 08 July 2017 12:54

በማኅበራዊ ቢዝነስ ሥራ ፈጣሪ የሆኑት ዕድሮች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በሀዋሳ፣ የእኛው ለእኛ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላት በበዓላት ወቅት ዶሮም ሆነ በሬ አርደው አረጋውያን አብረዋቸው በልተውና ጠጥተው ተደስተው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ከእንብራ የማኅበር ሱቅ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣… ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ገዝተው ለአረጋውን ይሰጣሉ፡፡ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸውና በዝናብ ወቅት የሚያፈስ ቤት ክፍለ ከተማውን አስፈቅደው፣ ለጥገና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን የከተማው ባለፀጎች እንዲደግፏቸው ለምነው እነሱው አናጢ፣ እነሱው መራጊ፣ እነሱው ሁሉን ነገር ሆነው ቤታቸውን ይጠግኑላቸዋል፡፡
በየሳምንቱ እሁድ የአረጋውያን ቤት ይፀዳል፣ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሴት የማኅበሩ አባላት፤ እሁድ እሁድ ቡና አፍልተው በማጠጣት፣ ፀሐይ ሞቀውና ፈታ ብለው ወደ የቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ልብስ ከከተማው ማኅበረሰብ ሰብስበው (ለምነው) አረጋውያኑን ያለብሷቸዋል፡፡ የተሰበሰበው ልብስ ልካቸው ካልሆነ ተሽጦ በገንዘቡ በልካቸው ልብስ ይገዛላቸዋል፡፡ አንሶላ፣ ትራስ፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣… እየገዙ ለአረጋውያኑ እንደሚሰጡ ወጣት አገኘሁ ወርቁ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት ባለፈው ሳምንት የማኅበረሰብ ምሥርት ተቋማት የመልካም ተሞክሮ ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ ባከበረበት ወቅት ተናግሯል፡፡
በባህርዳርም ከተማም ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳለ፣ ለቀድሞ ባለውለታ አረጋውያን ክብር እየተሰጠ መሆኑን የባህርዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ተስፉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳኛቸው ከጥምረቱ ውጭ ፋና የሕፃናትና ማኅበረሰብ ልማት ማኅበር አስተባባሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን ለመደገፍ በከተማዋ ብዙ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ፋና ማኅበር፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው፣ መሥራት ለማይችሉ፣ አልጋ ላይ ለወደቁ፣ ወጥተው መለመን እንኳ ለማይችሉና ለተረሱ 98 አረጋውያን ክብር በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው  ጠቅሰው፣ በራሳቸው መፀዳዳት የማይችሉትን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር እንዲያፀዳዷቸውና ቤታቸውን በተራ እንዲያፀዱ፣ አረጋውያን ወደ ውጭ ወጥተው ፀሐይ የሚሞቁበት ተሸከርካሪ ወንበር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲለግሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢሕማልድ) የዛሬ 32 ዓመት በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ለመታደግ የተቋቋመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ናቸው፡፡
በድርቁ ወቅት ድርጅቱ 6 የሕፃናት ማሳደጊያ ከፍቶ፣ ከ1000 በላይ ሕፃናትን ከተለያዩ አካባቢዎች ሰብስቦ ሲያሳድግ እንደነበረ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ አንድ ሕፃን ኅብረተሰቡ ውስጥ አድጎ የኅብረተሰቡን እሴቶች ማወቅ፣ ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር ማግኘት ስላለበት ኅብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራ ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የልማት ሥራዎች ድርጅቱ ከዚያ ቢወጣ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? በማለት አንድ ማኅበር መስርተው 7 ዓመት አብረው ሰርተው ቢወጡም ምስርት ማኅበራትንና ዕድሮችን በማጎልበት ድርጅቱ ሲሰራ የነበረውን እነሱ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢሕማልድ በአሁኑ ወቅት እያከናውናቸው ያሉት 3 ፕሮግራሞች 1ኛ፡- በማኅበራዊ አገልግሎት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ከቤተሰብ ጋር እያሉ መደገፍ፣ 2ኛው፡- የኑሮ ማሻሻያና የአካባቢ ጥበቃ፣ 3ኛው፡- የምስርት ተቋማትን አቅም ማጎልበትና ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የውጭ እጅ ከማየት ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አገር ውስጥ ያለን ሀብት በመጠቀም፣ ሀብቱ ውጤት እንዲያመጣ እየሠራን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤በዚህ ረገድ አንድ የስብሰባና የማሠልጠኛ ተቋም በቢሾፍቱ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ማሠራታቸውንና ይህ አሠራር ወደ ምስርት ማኅበራትም እየወረደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕንፃናትን በተቋም ከማሳደግ ይልቅ ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ያለውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በመገንዘብ በ1996 ዓ.ም ከማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በሙከራ የተጀመረው የልማት ሥራ፤በአሁኑ ወቅት አድጎ በ22 የተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከ142 ማኅበራትና  ዕድሮች ጋር ዘላቂ የልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት የኢሕማልድ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው፤ቀደም ሲል አባላትን በማስተዛዘን ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደው የነበሩ ዕድሮች የአሰራር ስልታቸውን በመቀየር ሕዝቡ የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት ኅብረተሰብ አቀፍ ልማት ውስጥ መግባታቸው ምርጥ ተሞክሮና ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ከተማ ከኢሕልማድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተው የእንብራ ራስ አገዝ ማኅበር ወጣት ቡድን አባል የሆነው አገኘሁ ወርቁ፣ አባቱን በሞት የተነጠቀው በኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ከእሱ ጋር የ3 ልጆች እናት የሆነችው እናቱ፤ምንም የሌላት የቤት እመቤት ነበረች። እቤት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው አገኘሁ ወደ ጎዳና ወጣ፡፡ እየለመነና ትንንሽ ዕቃዎች በመሸከም የሚያገኘው መጠነኛ ገቢ፣ ጎዳና ከወጣ በኋላ ለለመደው ሱስ አልበቃ አለው፡፡ ስለዚህ እሱና ጓደኞቹ ጨለማን ተገን አድርገው ሞባይል መቀማትና ኪስ መበርበር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እሱ ከሌሎች ጓደኞቹ ፈርጠም ያለ ስለነበር ሰዎችን አንቆ ሲይዝ፣ ሌሎቹ ኪስ ገብተው ይበረብሩ ነበር፡፡ አሁን የእሱና የጓደኞቹ ሕይወት ተለውጧል፡፡
እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር አቅርቧቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርና ስልጠና ሰጣቸው፡፡ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶላቸው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ከቤት ወጥተው እንዲሰሩ አደረጋቸው፡፡ ፎቶ ኮፒ፣ መጠረዣና ማሸጊያ መሳሪያ ገዝቶ የሥራ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ከአገኘሁ ጋር ሲቀሙ ከነበሩት ጓደኞቹ አንደኛው አሁን 5ኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ፣ ወላይታ ሶዶ ውስጥ ሲኖትራክ እያሽከረከረ መሆኑን፣ አገኘሁ ደግሞ ሐዋሳ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ 2ኛ ዓመት ተማሪ መሆኑን ገልጾ፣ ሕይወቱ እንዲለወጥ ያደረገውን ኢሕማልድን ከልቡ አመስግኗል፡፡
በማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ምርጥ ተሞክሮ ቀን የተገኙ በርካታ ማኅበራትና ዕድሮች ኢሕማልድ ቢወጣ የራሳቸው ገቢ ማግኛ ፕሮጀክት ስላላቸው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንደማያቋርጡ ተናግረዋል፡፡  
የባህር ዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ሰይፉ ቤትና መጋዘን ሰርቶ በማከራየት፣ ሥጋ ቤት ከፍቶ በመነገድ፣ … በአጠቃላይ በተለያዩ የገቢ ማግኛ ፕሮጀክቶች በመሰማራት በዓመት ከ650 ሺህ ብር በላይ ስለሚያገኙ፣ ወላጅ አልባና የቤተሰባቸው የገቢ አቅም አነስተኛ የሆኑትን ሕፃናት አስፈላጊ ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ት/ቤት ልከው እያስተማሩ መሆኑን፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ብድር በመስጠት የገቢ አቅም እንደፈጠሩላቸው፣ ለአረጋውያን የፈረሰባቸውን ቤት በመጠገን፣ በዓመት በዓል ጊዜ ከብት አርደው በማብላትና የተወሰነውን ወደ ቤታቸው ይዘው እንዲሄዱ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የተለያየ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳና አካባቢው (ሻሸመኔና አቼቡራን ያጠቃልላል) ምስርት ማኅበራት ጥምረት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ከበደ የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ጥምረታቸው 41 ዕድሮችና ማኅበራትን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሕማልድ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ ቢያቋርጥ ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን ማህበራዊ አገልግሎት ላለማቋረጥና ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ በ3,170,200 ብር ካፒታል አቋቁመው፣ 1,869,621 ብር ትርፍ ማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡
ባገኙት ትርፍ፣ በማኅበሩ ውስጥ ላሉና ለሌሎች ችግረኛ ሕፃናት ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት እያኮበኮቡ እያሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው፣ ለወጣቶች 2500 ብር ተዘዋዋሪ ብድር በመስጠት የተለያየ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ለችግረኛ ልጆች ቤተሰቦች 4000 ብር ብድር በመስጠት ነግደው የብድሩን 60 በመቶ ለራሳቸው ተጠቅመው፣ 40 በመቶውን እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለገቢ ማግኛ በዕድሮችና ማኅበራት የሚተዳደሩ 15 ባጃጆች አሉ፡፡ እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር 3፣ የዕድሮች ኅብረት 4፣ 03 ቀበሌ መረዳጃ ማኅበር ዕድር 2፣ ሐረር ሰፈር መረዳጃ ዕድር 4 ባጃጆች፣ እንዳሏቸው የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ባጃጆቹ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ሲሠሩ ቆይተው ሌሊት ለሕሙማን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡   

Read 1153 times