Sunday, 09 July 2017 00:00

‹‹የከተማው ዘላን››

Written by  ድርሰት - ኦ . ሄንሪ ትርጉም - ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(14 votes)

 ...አሁንም ነጻ ነው! አላሰሩትም! ወይ ጉዱ! ካሁን በኋላስ እስከ መቼ በነጻነት መከራውን እያየ ይኖር ይሆን!
ሶፒ፤ በማዲሰን አደባባይ ተጎልቶ ያለ እረፍት ይቁነጠነጣል፡፡ ክረምት መግባቱን የሚጠቁሙ ምልክቶች ይስተዋላሉ፡፡ አዕዋፍ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየከነፉ ነው፡፡ የቤት እመቤቶች ካፖርትና ወፍራም ሹራብ እንዲገዙላቸው ለባሎቻቸው ትሁት መሆን ጀምረዋል፡፡ ሶፒ ደሞ በመኖሪያ መናፈሻው ውስጥ ተቀምጦ ያለ እረፍት ይቁነጠነጣል፡፡ እነዚህም የክረምቱን መምጣት አመላካች ናቸው፡፡
ርጋፊ ቅጠል ሶፒ እግር ላይ ወደቀች፡፡ ይኼ ደግሞ ለሶፒ ክረምት መክተቱን የሚያረጋግጥበት ልዩ ምልክቱ ነበር፡፡ በአደባባዩ ዙሪያ ለሚኖሩትም ሁሉ የመዘጋጃቸው ጊዜ ነው፡፡
ሶፒ፤ ማድረግ የሚገባውን ማውጠንጠን ያዘ፡፡ ወቅቱ ደረሰ፡፡ ከክረምቱ ብርድና ቆፈን የሚከለልበት አንድ የሆነ መላ መዘየድ አለበት፡፡ ለዚህም ነው በተቀመጠበት እንዲህ መቁነጥነጡ፡፡
ሶፒ፤ በክረምቱ ወራት ሊኖረው የሚሻው ያን ያህል የተጋነነ ነገርም አይደለም፡፡ መቸም በመርከብ ተሳፍሮ ለመጓዝ አይዳዳውም፡፡ ወደ ደቡብ ወይም ኔፕልስ ሄዶ በጠራው ሰማይ ስር ክረምቱን ስለማሳለፍም ከቶም አይከጅልም፡፡ እሱ የሚጓጓለት አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ቢኖር፤ ሦስቱን ወራት በብላክ ዌል ደሴት በሚገኘው ወህኒ ቤት ማሳለፍን ብቻ ነው፡፡ ለሶስት ወራት በየቀኑ ትኩስ ምግብ እየታደለው፤ ሌሊቱን በጥሩ አልጋ ላይ የድሎት እንቅልፉን መለጠጥ፡፡ ሦስት ወራት ከሰሜኑ የክረምት ውርጭና ቁር እንዲሁም ከፖሊሶች ወከባ እርቆ መቆየት፡፡ ለሶፒ በአለም ላይ ሊኖረው የሚሻው እጅግ ላቅ ያለ ምኞቱ ይኸው ብቻ ነው፡፡
ላለፉት ቡዙ አመታት የብላክ ዌል ደሴት የክረምት ቤቱ ነበር፡፡ በየአመቱ የኒው ዮርክ ዲታዎች እንደየሀብታቸው መጠን ወደ ፍሎሪዳ ወይም ወደ ሜዴትራኒያን ባህር ዳርቻ ለመሄድ ሲያቅዱ፤ ሶፒም እንደ አቅሙ ወደ ደሴቲቱ ለመሄድ ያቅዳል፡፡
እነሆ ጊዜውም ደረሰ፡፡ ዛሬም በመናፈሻው ውስጥ ነው ያደረው፡፡ በሦስት ሰፋፊ ጋዜጦች ከኮቱ ስር ተጠቅልሎና የእግሮቹን ዙሪያም ተደግልሎም እንኳ በሌሊቱ ብርድ መንጠርጠር አልቀረለትም፡፡ ስለዚህ አሁን ደሴቲቱን ይቃትት ዘንድ ግድ ሆነበት።
በከተማው ዙሪያ ምግብና ማደሪያ ቢጠይቃቸው የሚረዱት ሰዎች አሉ፡፡ በዚያ መልኩም ከአንዱ መኖሪያ አፓርታማ ወደ ሌላው እየተዟዟረ ክረምቱን ለማሳለፍ ይችል ይሆናል፡፡ እሱ ግን እዚያው ብላክ ዌል ደሴቱ ቢሄድ ይሻለዋል፡፡
ሶፒ ኩሩ ነው፡፡ እርዳታ ወደሚገኝባቸው ቦታዎች ቢሄድ ገንዘብ አይጠይቁት ይሆናል፤ ሆኖም ግን ከፈቃዱ ውጪ ገላውን ሙልጭ አድርጎ እንዲታጠብ ያስገድዱታል፤ በዚያም ላይ በጥያቄ መአት እያጣደፉ ስለ ህይወቱና ማንነቱ የጀርባ ታሪኩን ሁሉ ልቅም አድርገው ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡
ኧረ ወዲያ ይቅር! ከዚህስ ወህኒ ቤት በስንት ጣዕሙ፡፡ ወህኒ ቤቱ ሊያከብረው የሚገባውን ህግና ደንብ አስቀምጦለታል፤  ከዚያ በተረፈ በወህኒ ቤቱ ቅጽር የአንድ የተከበረ ሰው የግል ህይወት የእሱ የራሱ ገመና ብቻ ነው፡፡ በቃ!
ሶፒ፤ ወደ ደሴቲቱ ለመጓዝ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ወዲያውም ምኞቱን ለማሳካት ተንቀሳቀሰ፡፡
ወደ ስኬቱ ለመረማመድ የሚጠቅሙ በርካታ ዘዴዎች አሉ፡፡ የተሻለው መንገድ ግን፤ ወዳንድ ውድ ሬስቶራንት ገብቶ ጥሩ ራት አዝዞ መመገብ ነው፡፡ ከዚያም ‹የምከፍለው ገንዘብ የለኝም› ይላል፡፡ ፖሊስ ይጠራሉ፡፡ ሁሉም ነገር በፍጥነት ይኮቸማል። ፖሊሱ በቁጥጥር ስር ያውለዋል፡፡ወደ ፍርድ ቤት ይወስደዋል፡፡ ቀሪው የዳኛው ስራ ነው፡፡
ሶፒ፤ ከተቀመጠበት ተነስቶ በቀስታ እያዘገመ፤ ከማዲሰን አደባባይ አዋሳኝ ብሮድ ዌይን እና 15ኛውን ጎዳናን  ወደሚያገናኘው መንገድ አመራ፡፡ ሰፊውን አውራ ጎዳና አቋርጦም ወደ ብሮድዌይ በስተሰሜን አቅጣጫ አቀና፡፡ ከዚያም፤ በደማማቅ መብራቶች ከተንቆጠቆጠ አንድ ትልቅ ሬስቶራንት ፊት ለፊት ሲደርስ ቆም አለ፡፡ እጅ የሚያስቆረጥሙ ምግቦች የሚዘጋጁበትና በየምሽቱም በውድ አልባሳት በተሽቀረቀሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ጢም ብሎ የሚሞላ ታዋቂ ሬስቶራንት ነው፡፡
ሶፒ፤ እርሱም ቢሆን ከእግሩ በላይ በአለባበሱ ለክፉ እማይሰጥ መሆኑን ተማመነ፡፡ የለበሰው ጥሩ ኮት አያሳጣውም መቸም፡፡ ብቻ ባዶ ጠረጴዛ ያግኝ እንጂ ስኬት በእጁ ለመሆኗ ቅንጣት ታህል አልተጠራጠረም፡፡ ከላይ እሚታየው ገፁ አስተማማኝ ነዋ፡፡ አስተናጋጁ የሚያዝዘውን ሁሉ እያከታተለ ፊቱ ይደረድርለታል፡፡
ምን መመገብ እንዳለበት ያማርጥ ጀመር። የምግብ አይነት ፊቱ ተከምሮ ታየው፡፡ ሂሳቡ ያን ያህል ብዙም ላይሆን ይችላል፡፡ ምንም ቢሆን ባለሃብቶቹን ለኪሳራ ሊዳርጋቸውና ምርር ብለው እንዲናደዱበትም አይፈልግም፡፡ የሆነ ሆኖ የሚመገበው ራት ምርጥ የሆነና ወደ ክረምት ቤቱ የሚሸኝበት የስንብት ማእዱ ቢሆን ይሻል፡፡
ግን ምን ያደርጋል፤ ሶፒ ገና የምግብ ቤቱን በር አለፍ እንዳለ፤ የአስተናጋጆቹ ኃላፊ ሸፋፋ ጫማዎቹንና ጨምዳዳ ሱሪውን አየ፡፡ ለዚሁ መሰል ተግባር ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ ግድንግድና እንደ ብረት የጠነከሩ እጆች በወገቡ ዙሪያ ተጠምጥመው ወደመጣበት እያጣደፉ መለሱት፡፡
ሶፒ የብሮድዌይን አካባቢ ለቅቆ ወጣ፡፡ ሲያስበው ቀላል የነበረው ወደ ደሴቲቱ የመጓዝ ታላቅ ምኞቱ አልሰመረለትም፡፡ በየትኛውም መንገድ ካሰበው ለመድረስ የሆነ ሌላ መላ ማመንጨት አለበት፡፡
በስድስተኛው ጎዳና አንድ ጥግ ላይ የአምፖሎቹ ብርሀን የሚያንጸባርቅ ሰፊ የመስተዋት መስኮት ያለው ሱቅ አየ፡፡ ሶፒ ትልቅ ድንጋይ አነሳና ወደ መስተዋቱ ወረወረ፡፡ ሰዎች ከየአቅጣጫው እየወጡ ተሰባበሰቡ፡፡ ቀድመው ከደረሱት መካከል አንዱም ፖሊስ ነበር፡፡ ሶፒ ከቆመበት ንቅንቅ ሳይል መጠባበቅ ጀመረ፤ፖሊሱን ሲያይ ደግሞ ፈገግ አለ፡፡
‹‹ማነው ይህን ያደረገው?›› ጠየቀ ፖሊሱ፡፡
‹‹እኔ ልሆን እንደምችል እርግጠኛ መሆን አትችልም?›› አለ ሶፒ፤ በአኳኋኑ ልክ እንደሚተዋወቀው ወዳጅ ፍንክንክ እያለ፡፡ የሚፈልገው ነገር ከች ብሎለታላ፡፡
ችግሩ፤ ፖሊሱ ሶፒ ይሆናል ብሎ በፍፁም አለመጠርጠሩ ነው፡፡ መስተዋት ያደቀቀ ሰው እንዲህ ፊት ለፊት ቆሞ ከፖሊስ ጋ አይገዳደርማ፡፡ በተቻለው መጠን እግሬ አውጪኝ ብሎ እብስ ይላል እንጂ፡፡ ፖሊሱ ቀና ሲል፤ ከመንገዱ ባሻገር የሚሮጥ ሰው አየና እርሱን አባርሮ ለመያዝ ተፈተለከ፡፡ ሶፒ ልቡ ሲዝልበት ተሰማው፤ እናማ በእርጋታ እያዘገመ ሄደ፡፡
አሁንም በዚያው መንገድ ላይ ሌላ ምግብ ቤት አገኘ፡፡ ይኼኛው በእርግጥ ቅድም በብሮድዌይ እንዳየው ያለ ድንቅ የሚባልለት አይነት አልነበረም፡፡ ደንበኞቹም ሀብታም የሚባሉ አይደሉም፡፡ ምግቡም ያን ያህል አይነገርለትም፡፡ ለዚህኛው ሙከራ ሶፒ ቆልማማ ጫማዎቹን እና ከላይ የደረበውን መናኛ ልብሱን ሸሽጎ ሰተት አለ፤ ማንም ያስቆመውም  አልነበረም፡፡ ወዲያውም አንድ ጠረጴዛ ያዘና በገፍ ያዘዘውን ራት ይሰለቅጠው ጀመር፡፡ሆዱን ከሞላ በኋላም፤ እሱና ገንዘብ እንደማይተዋወቁ አይኑን ‹በጨው አጥቦ› ነገራቸው፡፡
‹‹ቶሎ በሉ ፖሊስ ጠሩ›› አለ ሶፒ፤ ‹‹የተከበረ ደንበኛችሁን ማጉላላት አይገባምኮ!››
‹‹ላንተማ ፖሊስ አያስፈልገንም›› አለና አስተናጋጁ፣ ሌላ አስተናጋጅ ጠራ፡፡
ሁለቱ አስተናጋጆችም ግራና ቀኝ ይዘው እየጎተቱ ወደ ውጪ ወስደው፤ ኮሮኮንች መንገዱ ላይ በግራ ጆሮ ግንዱ ለጠፉት፡፡ እንደምንም እጅና እግሮቹን ተራ በተራ በቀስታ እየጎተተ ከወደቀበት ተነስቶ ቆመና አቧራውን አራገፈ፡፡ ወህኒ የመወረዱ ጉዳይ የቀን ህልም፤ የደሴቲቱ ተስፋ የማይደረስበት ሩ....ቅ  ሆነ፡፡ በአካባቢው የተመደበ ቆሞ የነበረ ፖሊስ ሳቅ እያለ አልፎት ሄደ፡፡
ሶፒ፤ ሌላ ሙከራ ከማድረጉ በፊት ግማሽ ማይል ያህል ያለማቋረጥ ገሰገሰ፡፡ በቀጣዩ ሙከራው እንደሚሳካለትም ፍጹም እርግጠኛ ሆነ፡፡ ሽክ ያለች ወጣት አንድ ሱቅ በረንዳ ላይ ቆማ በመስተዋቱ ውስጥ የተደረደሩትን እቃዎች ታያለች፡፡ ከእሷ ፈንጠር ብሎ  ደግሞ ፖሊስ ቆሟል፡፡
ሶፒ ልጅቱን ‹ለክፎ› ለማበሳጨት ነው ያሰበው። ማንም የማታውቀው ሰው ደፍሮ እንዲያናግራት የምትፈልግ አይነት አለመሆኗን ሁኔታዋን አይቶ ብቻ መገመት ይቻላል፡፡ ፖሊስ መጥራቷም አይቀርም፡፡የፖሊሱ እጆች ክንዱን አፈፍ ሲያደርጉት ተሰማውና ሀሴት አደረገ ሶፒ፡፡ ወደ ደሴቲቱ ማቅናቱ ነው በቃ።
ልጅቱን አፍንጫዋ ድረስ ቀርቦ ተጠጋት፡፡ ፖሊሱ የሚሆነውን በርቀት እየተከታተለ መሆኑንም አውቋል። ልጅቱ ከቆመችበት ወደ ኋላዋ ሸሸት አለች። ሶፒ ተከተላት፡፡ እናም ጎኗ ቆሞ ‹‹እንደምን አመሸሽ ቤዲሊያ! አብረን ፈታ ብንልስ ምን ይመስልሻል?››
ፖሊሱ አሁንም እያየው ነው፡፡ ልጅቱ እንደማመናጨቅ ብላ አንዴ ብቻ እጇን ወንጨፍ ታድርግ እንጂ፤ ሶፒ ወደተመኘው ስፍራ ሄደ ማለት ነው፡፡ የማረፊያ ቤቱ መኝታ ሙቀቱ ካሁኑ ይሰማው ጀመር፡፡
ወጣቷ ግን በወዳጅነት መንፈስ ወደሱ ቀረብ አለች። እጆቿንም ዘርግታ ክንዷን በክንዶቹ መሀል አቆላልፋ ያዘችውና ‹‹በደስታ ማይክዬ!›› አለች እየፈነጠዘች ‹‹መጠጥ እምታጋብዘኝ ከሆነ ነው ታዲያ፡፡ እኔ ራሴ ገና እንዳየውህ ላናግርህ ፈልጌ ነበር፤ ፖሊሱን ፈርቼ ነው እንጂ!›› አለችው፡፡
ሶፒ፤ በልጅቱ ክንዱን እንደተሸበበ ፖሊሱን አልፈውት ሄዱ፡፡ በሀዘን ተሰበረ፡፡ አሁንም ነጻ ነው! አላሰሩትም! ወይ ጉዱ! ካሁን በኋላስ እስከ መቼ በነጻነት መከራውን እያየ ይኖር ይሆን!
የመንገዱ ጫፍ መታጠፊው ጋ ሲደርሱ፤ ክንዶቿ ውስጥ የተሸጎጠ ክንዱን መንጭቆ አውጥቶ  የነፍስ አውጪኝ ሮጠ፡፡
ሮጦ ሮጦ ሮጦ አረፍ ሲል፤ በርካታ ቴአትር ቤቶች ያሉበት አካባቢ ራሱን አገኘው፡፡ የዙሪያው መንገድ መብራቶች  ሞቅ ደመቅ ያሉበትና ከሌሎቹ የከተማዋ ሰፈሮች በተለየ አሽኮለሌ የሚገንንበት ቦታ ነው፡፡ ወይዛዝርቶችና ባለ ሀብቶች የደረቧቸውን ሞቃት ልብሶች የክረምቱ ጤዛ ላይ በቄንጥ ሽር ብትን እያደረጉ ወዲያ ወዲህ እሚሉበት ስፍራ፡፡
ድንገት አንዳች ስጋት ይንጠው ጀመር ሶፒ። አንድም ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው አልቻለማ።
ከቴአትር ቤቶቹ በአንዱ በራፍ ላይ የቆመ ፖሊስ አጠገብ ደረሰ፡፡ አሁንም ሌላ እሚሞክረውን ነገር ማሰላሰል ቀጠለ፡፡
አለቅጥ መጠጥ ተግቶ እንደተንበጫበጨ ሰካራም ሆኖ ጩኸቱን ያቀልጠው ጀመር፡፡ ማውጣት የቻለውን ድምጽ ሁሉ አሟጥጦ ነው ያወጣው፡፡ ጭፈራውን እያስነካ ቀወጠው፡፡
ፖሊሱ ግን ለሶፒ ጀርባውን ሰጠው፡፡ በጎኑ ለሚያልፍ መንገደኛም ‹‹የኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡ ማንም ላይ ጉዳት አያደርስም፡፡ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ፤ እንዳንነካቸው ትእዛዝ ተላልፎልናል፡፡›› አለው፡፡
ሶፒ ድርቅ ብሎ ቀረ፡፡ አንድም ፖሊስ ጫፉን ሊነካው አልቻለም ማለት ነው? ደሴቲቱ የመንግስተ ሰማይ ያህል ስትርቀው ታወቀው፡፡ ብን ብላ አልቃ የነተበች ኮቱን ከግራ ቀኝ ሰበሰበ፤ ብርዱ ሰውነትን ያቆራምዳል፡፡
ከዚያም አንድ ሱቅ ውስጥ ጋዜጣ የሚገዛ ሰው አየ፡፡ ሰውየው ዣንጥላውን የሱቁ በራፍ ላይ አስደግፎታል፡፡ ሶፒ ወደ ሱቁ ገብቶ ዣንጥላውን አንስቶ ወጣና ተረጋግቶ መራመድ ጀመረ፡፡ ሰውየውም ቀልጠፍ ብሎ ከኋላው ተከተለው፡፡
‹‹ዣንጥላዬን!›› አለ ሰውየው፡፡
‹‹ኧረ! ተው እንጂ! ያንተ ዣንጥላ ነው?›› አለው ሶፒ። ‹‹ከፈለግክ ፖሊስ ጣራ፡፡ በቃ ወሰድኩት! ዣንጥላህን ውስድ አደረግኩብህ! እና ለምን ቶሎ ፖሊስ አትጠራም?! ያው እዚህ መታጠፊያው ጋ የቆመ ፖሊስ አለልህኮ!››
የሚከተለው ሰውዬ እርምጃውን ገታ አደረገ። ሶፒም ወደ ፊት መሄዱን ትቶ ቆም አለ፡፡ አሁንም ላይሳካለት እንደሚችል በውስጡ ጥርጣሬ አደረበት። ፖሊሱ ካለበት ሆኖ ወደ ሁለቱም አተኩሮ እያየ ነው፡፡
‹‹እኔም...›› አለ ባለዣንጥላው ሰውዬ ‹‹...ማለት ያው...ይገባሀል አይደል....ያው የኔ ወንድም መቸም... ማለት እንዲህ አይነት ግጥምጥሞሽ  ያጋጥማል  አይደል...እና ያንተ ከሆነማ ውሰደው... በጣም ይቅርታ...እኔም ያው እንዳልኩህ ባጋጣሚ ነው ዛሬ ጠዋት ቁርስ የበላሁበት ምግብ ቤት ውስጥ ያገኘሁት...እና ንብረትህ ከሆነማ ውሰደው እንጂ...መቸም እንደማትቀየመኝ ተስፋ አደርጋለሁ...እ?...”
‹‹የኔ ነው--- እእእእእ!!!›› ሶፒ በሀይለኛ ቁጣ አምባረቀ፡፡
ባለ ዣንጥላው ሰውዬ ፈረጠጠ፡፡ ፖሊሱ አንዲት መንገድ እምታቋርጥ ሴት አይቶ እሷን ለመርዳት ተንቀሳቀሰ፡፡ ሶፒም ወደ ምስራቅ አቅጣጫ አመራ። ባለ በሌለ ሀይሉ ዣንጥላውን አሽቀንጥሮ ወዲያ አርቆ ወረወረው፡፡ ስለ ፖሊሶች እሱ እስከ ዛሬ ያስበው የነበረውንና አሁን እየሆነ ያለውን ነጣጥሎ ማውጠንጠን ጀመረ፡፡ ምክንያቱም፤ እሱ በቁጥጥር ስር መዋል ይፈልጋል፤ እነርሱ ግን ደርሶ አንዳችም እክል እንዳልፈጸመ፣ ልክ እንደ ንጉሥ አክብረው፣ እንዳላየ ሆነው ያልፉታል፡፡
በመጨረሻም ሶፒ፤ ከከተማዋ በስተምስራቅ ራቅ ብሎ ከሚገኘውና ከሌሎቹ ስፍራዎች በተለየ ፀጥታ ከነገሰበት ስፍራ ደረሰ፡፡ በአንድ መታጠፊያ በኩል አድርጎም ወደመጣበት ወደ ማዲሰን አደባባይ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ወደ ቤቱ እየገባ መሆኑ ነው እንግዲህ፤ እልፍኙም ያችው በመናፈሻው ውስጥ ተኮራምቶ የሚውል እሚያድርባት ቦታ ናት፡፡
ሆንም ግን አሁን ሶፒ፤ አንድ መንገድ ጥግ ላይ ሲደርስ ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ በአቅራቢያው አንድ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በግርግዳው መሀል ባለው ቀለሙ ማራኪ መስኮቱ በኩል የሚፈነጥቅ ለስላሳ ብርሀን ይታያል፡፡ ኩልል ብሎ የሚወርድ ጥኡም ዜማ ወደ ሶፒ ጆሮ ደረሰ እናም ካለበት እንዳይነቃነቅ አደረገው፡፡ ከበላዩ በሰማዩ ላይ የጨረቃዋ ሰላማዊ ደማቅ ብርሀን። ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው በመንገዱ ላይ ሲተላለፉ የሚታዩትም።
እነሆ ከቤተ ክርስቲያኑ የሚመጣው የቅዳሴ ድምጽ፤ ሶፒን ገትሮ አስቀረው፡፡ ረዥም ጊዜ ሆኖታል ይህን ድምጽ ከሰማ፡፡ በነዚያ ወርቃማ ጊዜያትም በውስጡ ታትሞ የቀረው የምእመን እናቶች ምስል፣ የአበቦች ውበት፣ ‹የእጣንና የጠፋ ጧፍ ጢስ ሽታ›፣ ብዙ ብዙ የተስፋ ከፍታዎች እና ብዙ ወዳጆች ዙሪያውን እናም ያልተበረዙ ንፁህ ሀሳቦች፣ ያልቆሸሹ ፅዱ ልብሶች . . . የመሳሰሉ የህይወቱ እፁብ ድንቅ ትዝታ ምስሎች ተፈራረቁበት፡፡
የሶፒ ልቦና በተፈጥሮው እንዲህ ላሉ ጉዳዮች ዝግጁ የሆነ ነው፡፡ እና አሁንም ወደ ቤተ ክርስቲያን በድንገት የመጣው በትክክለኛው ጊዜ ላይ መሆኑ ተሰማው። ባንዳች ያልተጠበቀና ፍፁም አስደናቂ በሆነ ሁኔታ መንፈሱ ተነቃቅቶና በአሳዛኝ የሚያርበደብድ ፍርሀት ውስጥ ሆኖ፤ ምንኛ ተንኮታኩቶ ወድቆ እንደነበር ለማስተዋል በቃ። ያባከናቸውን አመታት፣ አጉል ምኞቶቹን፣ ከንቱ ተስፋዎቹን፣ የላሸቀውን የአእምሮ ሀይልና አካላዊ ጉልበቱን፣ የተነጠለውን የመልካም ስነ ምግባራት ልእልናውን ሁሉ አንድ ባንድ እየመዘዘ አጤነ፡፡
በዚሁም ቅጽበት ልቡ የመንፈሱን መለወጥ አበሰረለት፡፡ ህይወቱን ለመለወጥ መታገል ይገባዋል፤ ከሰመጠበት የማጥ አዘቅት፤ ተዘፍቆ ከከረመበት አታካች ኑሮ ራሱን ጎትቶ ማውጣትና ወደ ላይ ከፍ ማድረግ አለበት፡፡ ራሱን ሆኖ የሚቆም ማንነት ይኖረው ዘንድ መትጋት ግድ ይለዋል፡፡
ደሞ እንዲያ ያሉ ወቅቶችንም  አሳልፏል ፤ አፍላ ወጣት ሳለ፡፡ ያንን መልካም ሰብእና መልሶ ማምጣት ያስፈልገዋል፡፡ እናም ያንን በጎ መርህ በመከተል መኖር መቀጠል፡፡ የሰማው ጥኡም ዜማ ሁለመናውን ነበር የለወጠው፡፡ ነገ ማለዳ ተነስቶ ስራ ማፈላለግ። ባንድ ወቅት አንድ ቅን ሰው ስራ ሊቀጥረው እሺ ብሎት ነበር፡፡ ያን ሰው ነገ በጠዋት ማግኘት። በአለም ላይ ራሱን ችሎ የቆመ ሰው መሆን፡፡ እንዲሁም ደግሞ...
ሶፒ አንድ እጅ ክንዱ ላይ ሲያርፍ ተሰማው፡፡ በፍጥነት ዞር ብሎም ሲያይ፤ ከአንድ ፊቱ ሰፊ ፖሊስ ጋር ተፋጠጠ፡፡
‹‹እዚህ አካባቢ ምን እያንጎዳጎድክ ነው በል?!›› ሲል ጠየቀው ፖሊሱ፡፡
‹‹ምንም!›› አለ ሶፒ፡፡
‹‹የምትለኝን እማምንህ ይመስልሀል?›› አለ ፖሊሱ፡፡
ሶፒ አዲስ በሰረፀበት ምሉእ ጥንካሬ ለፖሊሱ ለማስረዳት ያቅሙን ያህል ጥረት አደረገ፡፡ ችግሩ ከኒው ዮርክ ፖሊስ ጋር አታካራ መፍጠር የሚመከር አለመሆኑ ነበር፡፡
‹‹እሺ አሁን ቀጥል!›› ትእዛዝ አስተላለፈ ፖሊሱ።
‹‹ለሦስት ወር ወደ ደሴቲቱ ማረፊያ ቤት!!!›› አሉት ሶፒን በማግስቱ፤ ክቡር ዳኛው፡፡
ምንጭ - The Cop and the Anthem.
by  -  O HENRY
የትርጉም አርእስት ውሰት - በ195? ዓ.ም ከታተመው
የግራዝማች በትእዛዝ ወ/ዮሐንስ የግጥም መድበል ውስጥ
የከተማው ዘላን
‹‹ ...ወፍ እንቁላል ስትጥል በሰራችው ቤት
በጣም ያሳዝናል ያንተ መዋተት፡፡››

Read 3983 times