Sunday, 09 July 2017 00:00

ግዮናዊ ፍልስፍና ክፍል-፩

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@yahoo.com
Rate this item
(7 votes)

  “-- እነዚህን ሁ ሉ የኑሮ ዘዬዎች በ አንክሮ ብንመረምራቸው፣ የኢትዮጵያዊያን ህያው ታታሪ ልቦናን ፍንትው አ ድርገው ያሳዩናል። በጉልበቱና በክህሎቱ ለዘላለም ምስክርነት የተከላቸው ውቅርና ትክል ድንጋዮችም የታታሪነቱ ምስክር ናቸው---”
           
       ‹‹አንድም ሦስትም ልቦና›› እና ‹‹ግዮን እንደ ፍልስፍና›› በሚሉ ርዕሶች ተያያዥነት ያላቸዉ ፅሑፎችን ከዚህ በፊት አቅርቤ ነበር፡፡ ከአንዳንድ ወዳጆቼ በተሰጠኝ ምክር መሰረት፤ የታጨቁ ሃሳቦችን ለማብራራት ያህል፤ ‹‹አንድም ሦስትም ልቦና›› በሚል የቀረበውን ፅሑፍ በሦስት ከፍለን እንመለከታለን። የግሪኩ አንጋፋ ፈላስፋ አፍላጦን    /Plato/ ፍትህ ምን ማለት እንደ ሆነ በሚተነትንበት ድርሳኑ /the Republic/ ውስጥ ሁለት ዓለማት መኖራቸውን፤ እነርሱም ዓለመ አምሳያ  እና ዓለመ ህላዌ መሆናቸውን፤ ዓለመ ኅላዌ እውነት፣ ውበት፣ ፍትህ፣ እውቀት መገኛ መሆኑንና ዓለመ አምሳያ ደግሞ የዓለመ ኅላዌ ቅጅ፣ ጥላ፣ ግልባጭ፣ አምሳያ መሆኑን እና አንድ ሰው ፈላስፋ፣ ጥበበኛ፣ ደቂቀ መለኮት የሚባለው ሁለቱንም ዓለማት ጠንቅቆ የመረመረ እንደሆነ መሆኑን ያስረዳል።
በዚህ ጽሑፍ የምናየው ጥበበኛው/ፈላስፋው ለምን እና እንዴት መሪ መሆን እንዳለበት አፍላጦን የሰውን ነፍስ መዋቅርና የአንድን ሃገር ሰዎች መዋቅር በንጽጽር ያስረዳበትን ነው። የነፍስን መዋቅር ሲመረምር ሦስት ዓይነት ነፍሳት አሉ ይለናል። አንደኛው ነፍስ ከወርቅ የተሰራ ነው፤ሁለተኛው ነፍስ ከብር የተሰራ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ከብረት የተሰራ ነው ይለናል አፍላጦን።
 በኛ ማህበረሰብ ዘንድ ነፍስ ፍጹማዊ የሆነ አንድ ንጹህ ባህሪ ያላት ተደርጋ ስለምትቆጠር፤ የአፍላጦንን “ነፍስ” በእኛ ሃገር የ”ልቦና” እሳቤ እንተካው፤ ምክንያቱም ለኢትዮጵያዊያን ነፍስ ተናጋሪ፣ አሳቢ እና ኅያዊት ናት፤ አንደኛ ሁለተኛ ሦስተኛ ደረጃ የላትም። ስለዚህ ሦስቱን ዓይነት የአፍላጦንን ነፍስ፤ ሦስት ዓይነት ልቦና እንበላቸው። አንዳንድ ልቦች ከወርቅ፤ አንዳንዶች ከብር፤ ሌሎች ደግሞ ከብረት/መዳብ የተሰሩ ናቸው እንበል፤ ሃሳቡን በቀላሉ እንድንጨብጠው።
እነዚህ ሦስቱ የተለያዩ ነገር ግን እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ጠባዮች ያሏቸው ልቦናዎች ናቸው። አፍላጦን ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንዴት ነው ልትኖረን የምትችለው እያለ ሲመራመር ልክ ሦስት ዓይነት ልቦናዎች እንዳሉ ሁሉ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ይለናል። ሁላችንም እኩል አንድ አይነት ችሎታ የለንም ይለናል። አንዳንዶቻችን ጥሩ ሠራተኞች ነን /appetitic/ አንዳንዶቻችን  ጠንካራ ወታደሮች ነን /auxiliary/ ሌሎቻችን ደግሞ መልካም ተመራማሪዎች ነን /spirit/። ስለዚህ ፍትህ የሰፈነባትን ሃገር ለማግኘት ልጆቻችንን ይሄን ተረት እንንገራቸው ይላል አፍላጦን።
እስኪ ሦስቱንም አንድ በአንድ እየዘረዘርን እንመልከታቸው። ለዛሬው ግን ብረታዊ/መዳባዊ ልብን ብቻ እንያት፡-
ብረታዊ/መዳባዊ ልብ፥ ብረታዊ ባህሪ የሚያደላበት ልቦና ታታሪነት፣ መብል፣ መጠጥ፣ መዝናናት፣ ማምረት፣ መጋር… ወዘተ ቅብጥብጥ ዓይነት እና ቀለል ያለ ስሜትን የሚወድ ዓይነት ልብ ነው። ይህ ልብ ዕለታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፤ ቀለል ያሉ ዘልማዳዊ ስራዎችን የሚያዘወትር፤ የሚታወቁና የተለመዱ ስራዎች ላይ መጠመድ የሚስማማውና ምቾት የሚሰጠው ነው። እንደ ጉንዳን ታታሪ ልቦና ነው ይህ ልቦና። ነገር ግን ፍላጎት/ስሜት ብቻ የሚመራው፤ ፍላጎቱን ማሸነፍ የማይችል ነው፤ ቅብጥብጥነት ያጠቃዋል። ግብረ ጉንዳን እንደ አፍላጦን የብረት ነፍሳት ያሉ ናቸው። ታታሪዎች፣ ለፍቶ አደሮች፣ ሁሌም የሚጎትቱት የሚሸከሙት ነገር አያጡም ጉንዳኖች፤ እናም ታታሪውን፣ አራሹን፣ አምራቹን፣ ሰራተኛውን ኢትዮጵያዊ ልቦና ቀደም ብለን የብረት ልብ ያልነውን ግብረ ጉንዳን ብንለው የሚወክለው ይመስለኛል።
አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክል ልቦና ነው፤ ይህ ብረታዊ ልብ፤ ማምረት፣ መልፋት፣ መስራት፣ መታተር፣ መድከም… የላብን፣ የወዝን ለመብላት የሚደክመውን ማህበረሰብን ይመስላል። ሰርቶ አደሩ፣ ወዛደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ሸክለኛው፣ ሸማኔው፣ ቀጥቃጩ፣ አንጥረኛው፣… ጥሮ ግሮ አዳሪው በሙሉ በአፍላጦን ፍልስፍና መሰረት ከዚህኛው የልብ መደብ የሚመደብ ነው። ገበያውን፣ መንገዱን፣ አውራ ጎዳናውን፣ አደባባዩን ሞልቶት የምናገኘው ይህ ልቦና ነው፤ በአንድ ሃገር መዋቅር ውስጥ ብዙውን ክፍል ይሸፍናል፤ ብዙውን ሃገራዊ ሸክም ይሸከማል።
በዘልማድ ከአባቶቹ በወረሰው እውቀት ያመረተውን ምርት አሳምሮ፣ አስውቦ ወደ ገበያ ለመውሰድ ይታትራል እንጅ፤ የእውቀት ምንጮችን፣ የውበት አይነቶችን፣ የስነ ምግባር መነሻዎችን እናም ኅላዌን የመመርመር ጠባይ የለውም። እንደው ዝም ብሎ ያመርታል፤ ያመረተውንም ወደ ገበያ ይዞ ይወጣል፤ የሸጠውን ሸጦ ባገኘው ገንዘብ ደግሞ እንደ እርሱ ካሉት መዳባዊ ልብ ያመረቱትን የሚፈልገውን ያህል ገዝቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ይህ የመዳባዊያን ልቦናዎች ጥበብ እና እውቀት እንዲሁም ስነ ምግባር ነው።
ድግግሞሽ የሚበዛበት ህይወት የሚመራ እና የነበረውን እውቀት መርመሮ ለማወቅ የማይነሳሳ፣ መነሻ ምንጩን ለመመርመር የማይታትር፣ ዕለታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፤ ድካሙን ለመርሳት መዝናናትን እንደ መፍትሔ የሚወስድና፤ የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ የሚለብሰው እንዳይጎድልበት ሙሉ ሕይወቱን የሚደክም ልቦና ነው ብረታዊ ልቦና። ሲመሽ፣ ሲነጋ በሚያየውና፣ በሚሰማው፣ በሚያሸተው፣ በሚቀምሰው፣ በዳሰሰው የስሜት ህዋሳቶቹ የገበየውን ማንኛውንም ስሜታዊ እውቀት እንደ ፍጻሜ የሚቆጥር ነው።
በጥላ እና በአካላዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንኳ ለመመርመር ባለመታተሩ ጥላዎች ሁሉ አካላዊ ግዝፈት ያላቸው የሚመስለው ነው። አማናዊውን ዘላለማዊውን የእውቀት፣ የህይወት መነሻ የሆነውን ብርሃነ ፀሃይን አይቶ አያውቅም እና የእሳት ወጋገን ለእርሱ የሕይወት ሁሉ አስገኝ ኃይል ይመስለዋል። በእሳቱ ውጋገን የሚፈጠሩ የቁስ አካላት ጥላዎችን እንደ ተፈጥሯዊ አካላት በመውሰድ እውቀትን ከጥላዎች መገብየትን የሚቀናው፤ ከጥላዎች ባሻገር ያለውን እሳት እንኳ በአግባቡ የማይመረምር፤ ከእሳቱ ማዶ ያለውን አማናዊውን ብርሃን አስገኝ ፀሐይ የማያውቅ ልብ ነው።
ግዮን መዳባዊ ነው፤ ጸባዩን የተረዱት ያርሱበታል፤ አምርተው ቀለባቸውን ይሰፍራሉ። ከታች ወደ ግብጽ እና ከምንጩ እሰከላ ሥር ያሉት የሽንኩርት የካሮት መደባቸውን ያጠጣሉ፤ ፍራፍሬ ያመርቱበታል፤ ከብቶቻቸውን ያጠግባሉ። ታላቁ ነብይ ሙሴ ከግብጽ በተሰደደ ጊዜ የግዮንን ፈለግ መንገድ መሪ አድርጎ፣ ወንዙን ተከትሎ ወደ መነሻው ወደ ምንጩ ነበር የመጣው እናም ውኃ የሚያጠጡ እረኞችን ያገኘው። በኋላም የነብይነት ጥሪውን እስኪጀምር ድረስ የካህኑ ዮቶር እረኛ ሆኖ የኖረው እዚሁ ነው። ግዮን እንዲህ ነው፤ እረኝነትንም ያስተምራል።
የኢትዮጵያዊ ልቡ እንደ ግብረ ጉንዳን ታታሪ ነው። እርሻን ቀድመው ከጀመሩት የጥንት ስልጡኖች አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው። ምግብ አብስሎ መመገብ፤ እንስሳትን ማላመድና ማርባት፤ ልብሱን ከእጽዋት/ጥጥ/ አዘጋጅቶ መልበስ ከጀመሩት ሁሉ ቀዳሚ ነው ኢትዮጵያዊ። እነዚህን ሁሉ የኑሮ ዘዬዎች በአንክሮ ብንመረምራቸው፣ የኢትዮጵያዊያን ህያው ታታሪ ልቦናን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል። በጉልበቱና በክህሎቱ ለዘላለም ምስክርነት የተከላቸው ውቅርና ትክል ድንጋዮችም የታታሪነቱ ምስክር ናቸው (አክሱም፤ ላሊበላ፤ ጢያ ወዘተን ያስታውሱ)።

Read 2369 times