Sunday, 09 July 2017 00:00

በሠብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ከ97 በፊት ከ100 የማያንሱት ድርጅቶች፤ አሁን ከ5 አይበልጡም ተብሏል
   በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብትና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ህልውናቸው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ወቀት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱት ከ5 የማይበልጡ ደካማ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ከሽግግር መንግስቱ ጀምሮ እስከ 97 ምርጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሰብአዊ መብትና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደነበሩ ያመለከተው ሰሞኑን ለውይይት የቀረበ አንድ ጥናት፤ “የእነዚህ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የሚገድበው የበጎ አድራጎትና ማህበራዊ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ በአሁን ወቅት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ቀርተዋል፤ እነሱም በእጅጉ ደካማ ሆነዋል፤ ጨርሶ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል” ብሏል፡፡  መንግስት የእነዚህን ድርጅቶች እንቅስቃሴ የሚገድብ አዲስ አዋጅ እንዲያወጣ ያስገደደው የምርጫ 97 አጋጣሚ መሆኑም ተወስቷል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል ያቀረቡት መለስተኛ ጥናት፤ ከ97 በኋላ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ መስራት በመንግስት እንደ ፖለቲካ ስራ ተደርጎ መወሰዱ የችግሮቹ ሁሉ መነሻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ “የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያ በሌለበት ስርአት ውስጥ ስለ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ልንነጋገር አንችልም” ያሉት አቶ ደበበ፤ “ከ97 በኋላ በእነዚህ ሶስት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መንግስት ቀድሞ የነበረውን አቋም ለውጦ፣ በሶስቱም ጉዳዮች የህግ ማሻሻያዎችን ማድረጉ አጣብቂኝ ሁኔታዎችን ማስከተሉን አብራርተዋል፡፡
ከሽግግሩ መንግስት እስከ 97 የነበረው ጊዜ በተለይ በሰብአዊ መብት ላይ ለሚሰሩ የበጎ አድራጎት ማህበራት አሁን ካለው በአንፃራዊነት የተሻለ ወቅት እንደነበር የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው፤ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራ የፖለቲካ ስራ በመሆኑ ይሄ ሊሰራ የሚገባው በዜጎች እንጂ በውጭ  እርዳታ ሊሰራ አይገባም በሚል አቋም የገንዘብ ምንጭ ላይ ገደብ የሚጥለው አዋጅ መውጣቱ፣ የድርጅቶቹን ህልውና እንደተፈታተነ አስረድተዋል፡፡
ከ97 በፊት በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ላይ ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶች በምርጫ፣ በፖሊሲ ጉዳዮችና በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ለማህበረሰቡ በራሳቸው ተነሳሽነት ግንዛቤ ያስጨብጡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደበበ፤ ለፖሊስ፣ ለአቃቤ ህጎችና ለዳኞች ጭምር በህግ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናም ይሰጡ ነበር ብለዋል- በአሁኑ ወቅት ይህን ተግባር የሚፈፅሙ ድርጅቶችን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በመግለፅ፡፡
“የሰብአዊ መብት ሥራ ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ አይደለም ያሉት” የህግ ባለሙያው፤ የገንዘብ ምንጭ ላይ ገደብ መቀመጡ አግባብ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ አዋጅ የተነሳም በየዓመቱ ከአንድ መቶ ያላነሱ ድርጅቶች እንደሚዘጉና እስካሁንም ከ1 ሺህ በላይ እንደተዘጉ አቶ ደበበ በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡
በ“ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ” አስተናባሪነት በተዘጋጀው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተወካይ በበኩላቸው፤ ባለፉት 8 ዓመታት 400 ያህል የበጎ አድራጎት ማህበራት እንደተሰረዙ ጠቅሰው፤ በየዓመቱ መቶ ይሰረዛሉ የተባለው የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው እየጠፉ ያሉት ድርጅቶች እንዲያገግሙ ከተፈለገ በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ መሻሻል እንዳለበት እንዲሁም በሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን መንግስት ሊደግፋቸው እንደሚገባ አስረድተዋል- የጋና መንግስት ለመሰል ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ጭምር እንደሚያደርግላቸው በመጥቀስ፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ የሰማያዊ፣ የመኢአድ፣ የኢራፓ እና የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን የፓርላማ ተወካይና የመንግስት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው፤ የበጎ አድራጎት ማህበራት ችግርና አሁን ያሉበት ሁኔታ በገለልተኛ አካል ተጠንቶ ከቀረበ አዋጁን ለማሻሻል መንግስት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁን ወቅት በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ 3 ሺህ 185 ያህል ድርጅቶች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ከ97 በፊት ወደ 4700 የሚጠጉ እንደነበሩ ታውቋል፡፡    


Read 3625 times