Sunday, 02 July 2017 00:00

የ13 ወር የፀሐይ ፀጋ ባላት አገር የተገነባው የሶላር ኢነርጂ ፋብሪካ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 - አሁን የምናመርተው እስራኤል 70 ኣመት ከተጠበበችበት ምርት ይበልጣል
                 - እኛ ፋብሪካ ውስጥ ፈተና ወድቆ መምጣት ነውር ነው
                 - ፋብሪካው ትንሽ ገቢ ሲያገኝ ለሰራተኞችም ጭማሪ ይደረጋል

          በ1978 ዓ.ም ነው አራት ህፃናት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ እስራኤል የተሻገሩት፡፡ የሄዱበት ምክንያት ደግሞ ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ነበር፡፡ ደሴ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉት አቶ አሰፋ አስናቀ መንገሻ፤ በወጣትነት እድሜያቸው በአየር ኃይል፣ በግብርና ሚኒስቴርና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሰሩ ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ የህብረት ስራ ማህበራት አደራጆች አንደኛው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በጠቅላላው ወደ 10 ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላ በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ አሰፋ፤ በዓመቱ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው፣ አራት ህፃናት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ እስራኤል መጓዛቸውን ይገልፃሉ፡፡ በእስራኤልም “ሰርቲፋይድ አካውንቲንግ” ካጠኑ በኋላ በአካውንታንትነት ሙያ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከቅጥር ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት በመክፈት ለተለያዩ ኩባንያዎች የአካውንቲንግ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር የሚናገሩት አቶ አሰፋ፤ ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን “አፍሮ አምክሰላር ኢነርጂ ቴክ” የተሰኘ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ የውሃ ጋኖችንና የፀሐይ ሀይል የሚሰበስቡ ፓኔሎችን የሚያመርት ፋብሪካ አቋቁመው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ አሰፋ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

    ከኢትዮጵያ ከወጡ ከ22 ዓመታት በኋላ እንዴት ነው ወደ አገርዎ የተመለሱት?
ከኢትዮጵያ ከወጣሁ በኋላ በአንድ ወቅት አንድ ሁለት ጊዜ መጥቼ ነበር፡፡ ብቅ ብዬ ነው የተመለስኩት። በመጣሁበት ወቅት ገና ለውጥ መጀመሩ ነበር፤ የመጣሁትም አባቴ አርፎ ለለቅሶ ነበር፡፡ ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ ገና ልማት አልተጀመረም ነበር፡፡ ወደ እስራኤል ተመልሼ ከሄድኩ በኋላ ለ22 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ አልመጣሁም፡፡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጣ ያበረታታችኝ ባለቤቴ ናት፡፡
እንዴት?
ባለቤቴ በእስራኤል አገር የትምህርት ዲቪዥን ኃላፊ ናት፡፡ በአንድ ወቅት ከእስራኤል አገር ለስራ ትልልቅ እንግዶችን ይዛ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ የተወለድንበትን አካባቢ ጎብኝታ፣ የተለያዩ አካባቢዎችን አይታ፣ ያለውን ለውጥ እንድመለከት ነገረችኝ፡፡ ከዚያም አብረን መጥተን፣ ሁሉንም ተዘዋውረን አየን፡፡ እንደገና ተመልሼ ብቻዬን መጣሁና ሁሉን ነገር በሚገባ ተመለከትኩኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ ከአዲስ አበባ እስከ ገጠር ስለሰራሁ፣ ያን ጊዜ የነበረውን የመሰረተ ልማት ችግሮች አውቅ ነበር፡፡ አሁን እነዚያ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በጥሩ ሁኔታ ተለውጠው አየሁኝ፡፡ ይህን ስመለከት እኔስ እዚህ መጥቼ ለአገሬ ምን ላድርግ፣ የሚለውን ጥያቄ ራሴን ጠየኩኝ፡፡ ይህን ያሰብኩት እ.ኤ.አ በ2011 ነበር፡፡ ከዚያም እስራኤል የምሰራውን ስራ ትቼ ወደ ኢንዱስትሪ ለመግባት ወሰንኩ፡፡ የተለያዩ ቢዝነሶችንም ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ እውነት ለመናገር እኔ ለአገሬ ቀናተኛ ሰው ነኝ፡፡ እዚያ የለሙ ነገሮችን ሳይ፣ የሆነ ነገር ተለውጦ ስመለከት፣ ምን ነበር አገሬ ላይ ቢሆን እላለሁ፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው ሳጠና የሶላር ኢነርጂው ጉዳይ የመጣልኝ፡፡
በዘርፉ ለመሰማራት የመረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
የኖርኩባት አገር እስራኤል ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በፀሐይ ኃይል በኩል ከፍተኛ ተጠቃሚ ናት፡፡ በተለይ በፀሐይ ኀይል የምታለማው የመስኖ ስራ ከፍተኛ ነው፡፡ እኔም ሶስት አራት ዘርፎችን ግምት ውስጥ ካስገባሁ በኋላ በተለይ ዓለም በአሁኑ ሰዓት በኃይል እጥረት በተወጠረበትና የኢትዮጵያ መንግስት በታዳሽ ሀይልና በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ባደረገበት በዚህ ዘመን፣ የፀሐይ ሀይልን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ከማዳንና የኤሌክትሪክ ሀይል ብክነትን ከመታደግ እንዲሁም የስራ እድል ከመፍጠርም አኳያ አቻ የማይገኝለት ስራ ነው በሚል ነው “አፍሮ አምክሶላር ኢነርጂቴክ” የተሰኘውን ፋብሪካ በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የከፈትኩት፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ፀሐይ ሀይል ካለው ግንዛቤ፣ ዘርፉ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ አኳያ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙኝ ባውቅም ኃላፊነቱን ወስጄ ነው ያቋቋምኩት፡፡
ፋብሪካውን በማቋቋም ሂደት የገጠምዎት ተግዳሮቶች አሉ?
ፈተናው የጀመረው ሀሳቡን ለዘመድ ወዳጅ ማማከር በጀመርኩበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ እኔም ባለቤቴም በውጭ ስንኖር፣ በስራችን ባህሪ ምክንያት ከህዝቡ ጋር ብዙ ትውውቅና ቅርርብ ነበረን፡፡ ብዙ ፈረንጅ ጓደኞቻችን ሀሳቡን ስንነግራቸው፣ እንደ እብደት ነበር ያዩት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያውም ሶስተኛ ዓለም ላይ እንዴት ይህን ታስባለህ በማለት፣ እኔ እንዳልበረታታ ብዙ ግፊቶች ነበሩ፡፡ አንዱ ፈተና ይሄ ነበር፡፡ ያንን ፈተና ማለፍ ቻልኩኝ፡፡ ኢትዮጵያ በህዝቧ ጥረትና ብዛት፣ ባላት የተፈጥሮ ሀብትና ባለሙያዎች፣ ወደፊት ተስፋ ያላት አገር መሆኗን ስለማውቅ፣ ዛሬ ባይሳካ ነገ ይሳካል በሚል፣ የጓደኞቼን ምክርና ተግሳፅ ወደ ጎን ትቼ፣ በሀሳቤ ገፋሁ፡፡ በኋላ ደግሞ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ያሉ ዲፕሎማቶች ሀሳቤን ሲሰሙ፣ ከእኛ ጋር በአጋርነት ለምን አትሰራም የሚል አማላይ ሀሳብ አቀረቡና ትንሽ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ ይህንንም ከራሴ ጋር መክሬ ተውኩት፡፡ በምንም ሚዛን የአገሬን ያህል አይሆኑም፡፡
ይህን ካለፉ በኋላ የፋብሪካው ግንባታ ምን ይመስል ነበር?
እኔ በሀሳቤ ከፀናሁ በኋላ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ህላዌ ዮሴፍ በጉዳዩ ገብተውበት፣ የአቶ ታደሰ ኃይሌ ድጋፍ ተጨምሮበት፣ በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን በመረጥነው ቦታ ላይ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ወሰድኩኝ፡፡ ቦታውን ለማግኘት ብዙ አልተቸገርኩም። ከዚያ በኋላ በራሴ ገንዘብ ግንባታ ጀመርኩና ብድር ጥየቃ ወደ ባንክ ሄድኩኝ፣ ይሄ ቴክኖሎጂ በብዙ ዘርፍ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነውና ብድር ስጡኝ ስል፣ ገንዘብ የለንም አሉኝ፡፡ ቴክኖሎጂው ጠቃሚ ስለመሆኑ ሚኒስትሮቹና ባለሙያዎች እየመሰከሩ፣ እኔም ትልቅ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳለኝ ለማሳየት ከሚደግፉኝ ሰዎች ጋር ሆኜ፣ በራሴ ገንዘብ እየገነባሁ፣ ፈፅሞ ብድሩን ለማግኘት አልቻልኩም።
ከባንክ ምን ያህል ነበር የጠየቁት ብድር?
በወቅቱ ፋብሪካውን ለማቋቋም ከ16 ሚ. ብር በላይ ያስፈልግ ነበር፡፡ እኔም የጠየኩት 16 ሚ. ብር ነው። ነገር ግን ይህን ብድር ለማግኘት ከ2 ዓመት በላይ ተጉላልቻለሁ፡፡ ሆኖም ግንባታው ቀጥሎ ነበር፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ብድር ፈቃጆች የፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ ግንዛቤ ስላልነበራቸው አልፈርድባቸውም፡፡ ሆኖም ጉዳዩን ከልብ አዳምጠው መረዳት ይችሉ ነበር፤ ግን ትኩረት አልሰጡትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትልልቆቹ ኃላፊዎች ጉዳዩን ጠንቅቀው ያውቁት ነበር፡፡ በኋላ ከስር ያሉት ሰዎች፤ “ይሄ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ፕሮጀክት አይደለም” የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡
ከዚያስ?
ያንን ውሳኔ ሲወስኑ የኢነርጂ ሚኒስትር ወደነበሩት ወደ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ሄድኩና የተከለከልኩበትን ደብዳቤ ሰጠኋቸው፡፡ በወቅቱ ተበሳጩ፡፡ ስልክ ደውለው ይሄን ቴክኖሎጂ እንዴት ትገፋላችሁ ብለው ተናገሩ። ከዚያ እንደገና ጉዳዩ ይታይ ተባለና፣ በባለስልጣኖቹ ድጋፍ ከሞላ ጎደል ብደሩ ተፈቀደ፡፡
ከሞላ ጎደል ሲሉ ከጠየቁት ብድር ምን ያህሉን አገኙ?
አልወሰኑም እንዳይባሉ ከጠየኩት 16 ሚ. ብር 11 ሚ. ብር ፈቀዱ፡፡ ትንሽ ቆዩና ፕሮጀክቱን በተግባር ሲመለከቱ እንደገና 1.3 ሚ. ፈቀዱና ብድሩ በጠቅላላ 12.3 ሚሊዮን ብር ሆነ፤ ያንን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ፈጀ፤ ያንን አልፈን ምርት ተጀመረ፡፡
መቼ ነው ማምረት የጀመራችሁት?
ባለፈው ዓመት ነሀሴ ላይ ማምረት ጀመርን። አሁን በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴሎች፣ በሻወር ቤቶች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ምርታችን በተፈለገበት ቦታ እየሄድን እንገጥማለን፡፡ በብዙ ኮንቴይነር ከሌላ ቦታ የሚገባውንና ለዚያ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ችለናል፡፡ ያለማጋነን ምርታችን እስራኤል አገር ካሉ ምርቶች በጥራት ይበልጣል፤ ይሄንን እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡
በፀሐይ ሃይል ውሃ ለማሞቅ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ምን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይልስ ይቆጥባል?
ይሄ በጣም ጥሩና አስፈላጊ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከውጭ አገር የሚገቡት በፀሐይ ኃይል ውሃ የሚያሞቁ በርሜሎች አብዛኞቹ 200 ሊትር ናቸው፡፡ እኛ ግን አማራጮችን አስቀምጠናል፡፡ ለምሳሌ ባልና ሚስት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ከሆነ፣ 200 ሊትር ውሃ ምን ያደርግላቸዋል? 80 ሊትር በቂ ነው፡፡ ወጥ ቤትም ውስጥ ሙቅ ውሃ መጠቀም እፈልጋለሁ ካልሽ፣ 150 ሊትር ከበቂ በላይ ነው፤ የግድ 200 ሊትር ስላለ ብቻ ሰውን ያንን ግጠም ብሎ ማስገደድ አግባብ አይደለም። አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው በፀሐይ ኃይል ለመሞቅ የሚወስደው ጊዜ እንደየወቅቱና አካባቢው ቢለያይም፣ በአማካይ ግን የሁለት ሰዓት የፀሐይ ሙቀት 200 ሊትር ውሃ በደንብ ያሞቃል፡፡ በ80 እና በ150 ሊትር ግን በበርሜል ውስጥ የፈላ ውሃ ታገኛለሽ፡፡ እኛ አገር በጣም ክረምት በሚባለው በሐምሌና ነሐሴ ወር እንኳን ዝናብ ከመዝነቡ ከአንድና ሁለት ሰዓት በፊት ፀሐይ ይወጣል፤ ያኔ ሙቅ ውሃ አለ፤ ፀሐይ ጭራሹኑ በማይኖር ጊዜ ማሞቂያችን በኤሌክትሪክ ሲስተምም ስለሚሰራ፣ ያኔ ግድ ከሆነ ኤሌክትሪክ መጠቀም ይቻላል፡፡ የኛ የፀሐይ ኃይል ሲስተም ከፍተኛ ኢንሱሌሽን ያለው ነው፤ አንዴ ከሞቀ ለረጅም ጊዜ ሙቀት አፍኖ የመያዝ አቅም ስላለው ቶሎ አለመቀዝቀዙ ከሌላው ይለየናል፡፡
ምን ያህል የኤሌክትሪክ ሀይል ይቆጥባል የሚለውን አልመለሱልኝም …
በጣም ጥሩ! በእያንዳንዱ 200 ሊትር የፀሐይ ኃይል ውሃ የሚያሞቅ በርሜል 7 ኪሎ ዋት ኢነርጂ እንቆጥባለን። በ150 ሊትርም ቢሆን 7 ኪሎ ዋት ትቆጥቢያለሽ፡፡ ይሄን ሀይል መንግስት ለሌላ በርካታ ስራ ያውለዋል፡፡ እኛ ይህንን የምንለው በኪሎ ካሎሪ ነው፤ ያንን ወደ ኢነርጂ ስንለውጠው የምንቆጥበውን ኃይል እናውቀዋለን፡፡ ይሄ የእስራኤል ሳይንቲስቶች ቀመርና የ70 ዓመት ልምድ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ከፍ አድርገን እንመልከተው፡፡ ለምሳሌ እኛ 1 ሺህ ማሞቂያዎችን ብንገጥም፣ ከ7 እስከ 10 ሜጋ ዋት ኃይል በቀን ለመንግስት ይቆጠብለታል፡፡ ይሄ ማለት የቆቃ ሀይል ማለት ነው፡፡ ቆቃ እስከ 90 ሜጋ ዋት ነው ያመርታል የሚባለው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ክቡር አለማየሁ ተገኑ ፋብሪካውን መጥተው ጎብኝተው፤ “መቼ ነው ማስፋፊያ የምትጀምረው?” ብለው ጠይቀውኛል። ከስራቸውም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ እርሳቸው ባይደግፉኝ ህልሜ እውን አይሆንም ነበር፡፡ “ይህንን ስራ አስፋፍተህ የአዲስ አበባን የኤሌክትሪክ ውሃ ማሞቂያ ጠራርገህ አውጣልኝ” ነው ያሉት፡፡ ይሄ የሚያመለክተው መንግስት ምን ያህል የኃይል እጥረት እንዳለበትና ተጨማሪ አጋዥ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀን ወደ 400 ሜጋ ዋት ሀይል ያስፈልግ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 700 ሜጋ ዋት አድጓል። እኛ እድሉንና ድጋፉን ካገኘን ይህንን ሀይል መቆጠብ እንችላለን፡፡ ይህን የምናደርገው የህዝቡን ግንዛቤ አሳድገን፣ ፋብሪካችን ተስፋፍቶና ገበያውን ሰብረን ስንገባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁንም ከመንግስት ብዙ ድጋፍ እንፈልጋለን፡፡
በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ እየተስፋፋ ከመጣው የፋብሪካ ብዛትና የኃይል አቅርቦት አለመመጣጠን አንፃር ከውሃ ማሞቂያ ይልቅ የሚያስፈልገው መብራት ይመስለኛል፡፡ መንግስትም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከውጭ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ መብራቶችን ቢያስገባም፣ አብዛኞቹ ለብልሽት እንደተዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እርስዎ ከመብራት ይልቅ እንዴት ለውሃ ማሞቂያዎች ቅድሚያ ሰጡ? ወደፊትስ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ መብራቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ያሰቡት ነገር የለም?
ከጥያቄሽ በመነሳት ሁለት ነገሮችን ልመልስ … ሰው በሀይል እጥረት መብራት ይቆራረጥበታል፤ አዎ እውነት ነው፡፡ ግን በተወሰነ የሰዓት ገደብ መብራት ያገኛል። መታጠቢያን ስትመለከቺ፣ አብዛኛው ሰው በሙቅ ውሃ የመታጠብ እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይሄን ከኢኮኖሚ አለማደግ ጋር እናያይዘዋለን፡፡ ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ኃይል እንጀራ ለመጋገር፣ ውሃ አሙቆ ለመታጠብ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው የማይፈቅድ ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ ግን አንዴ ማሞቂያ ፓኔሉን ካስገቡ በነፃ ነው የሚጠቀሙት። ቆጣሪ የለውም፤ ክፍያ የለውም፤ ተፈጥሮን ብቻ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ሁለተኛው ነገር ወደ ገጠሩ ወጣ ብለን እንዳየነው ከሆነ፤ አሁን አሁን ሰዎች ሻወር ቤት እየገነቡ፣ በፀሐይ ሀይል ውሃ የሚያሞቅ በርሜልና ፓኔል እየገጠምንላቸው፣ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጡና እነሱም እየተጠቀሙ ነው፡፡ በሀይል ቁጠባም በኩል ካየሽው፣ ከመብራት (ከአምፖል ይልቅ) የውሃ ማሞቂያው ብዙ ሀይል ስለሚፈጅ፣ ለውሃ ማሞቂያው ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡ የውጭ ምንዛሬንም ማስቀረት ችለናል፡፡
ይሁን እንጂ በፀሐይ ሀይል ብርሃን የሚሰጥ መብራት የመስራትም እቅድ አለን ግን አሁንም ከፍተኛ ገንዘብ፣ ትልቅ ፋብሪካ ይፈልጋል፡፡ እኛ መንግስት ድጋፍ ካደረገልን፣ በዚህም በኩል ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ምርት የማምረት እውቀቱም ብቃቱም አለን፡፡ ከተማውንም ሆነ ገጠሩን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን፡፡ መንግስት ፋይናንሱን ከሰጠን ከ6-8 ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት እንችላለን። በሰራተኞቻችን እውቀትና የስልጠና አቀባበልም እንተማመናለን፡፡
በፀሐይ ኃይል የሚሰራ መብራት ለማምረት ብድር ጠይቃችሁ ነበር?
ሁልጊዜ እንጠይቃለን፤ ከውጭ አይምጣ፤ ጥራት ያለው የፀሐይ መሰብሰቢያና ለመብራት የሚውል እቃ ላምርት ብዬ ብዙ ጊዜ ብጠይቅም ፋይናንስ የለም ነው መልሳቸው፡፡ በቃ በዚህኛው ተገድቤ እየሰራሁ ነው፡፡
እስኪ በፋብሪካችሁ ስለሚሰሩ ሰራተኞቻችሁ ይንገሩኝ፡፡ የትምህርት ደረጃቸው እንዴት ነው? የሠራተኛ አያያዛችሁ ምን ይመስላል?
በነገራችን ላይ እኔ መንግስትን ከማደንቅበት አንዱ የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶችን አስፋፍቶ፣ ወጣቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሰልጥነው፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቀደም ሲልም እንደነ ፖሊቴክኒክ፣ ተግባረ ዕድ ያሉ የስልጠና ተቋማት ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ ነው ስልጠና የሚሰጡት። አሁን መንግስት ያስፋፋቸው የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶች በርካታ ዕድል ላላገኙ ወጣቶች እድል ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ እድል ያላገኙ የነበሩት ደግሞ በጣም ጥሩ ጥሩ ጭንቅላት ያላቸው ልጆች ናቸው፡፡ የእኛን ፋብሪካ ቀጥ አድርገው የያዙትም ከትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች በኤሌክትሪካል ወይም በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የተመረቁ እንዳይመስሉሽ፤ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የመጡ ብቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከፍተኛ ስልጠና እንዲያገኙ ከውጭ አገር ኤክስፐርቶችን ለሳምንት ለ10 ቀን እናመጣለን። እነሱ በ3 ቀን ስልጠና ሁሉን አውቀው ያጠናቅቁና በቃ ፈረንጁን ወደ አገሩ መልሰው ይላሉ፡፡ አሁን እየሰሩ ያሉት በትልቅ ብቃት ነው፡፡ አያያዝንና እንክብካቤን በተመለከተ፣ እኔ ከምናገር እነሱ ቢጠየቁ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ውጤታማ ስራ ለመስራት ከፈለገ፣ ሰራተኞቹን መንከባከብ፣ እንደ ቤተሰብ ቀርቦ ችግራቸውን መረዳት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ እውቀታቸው እንዲያድግ፣ ጥሩ የስራ ከባቢ እንዲኖራቸው ማድረግ የግድ ይመስለኛል፡፡ እኛ ይህን እናደርጋለን፡፡ እኛ ጋ እየሰሩ የትምህርት ደረጃቸውን እያሳደጉ የሚገኙ አሉ። የፈተናና የጥናት ሰዓታቸው ይከበራል፡፡ እኛ ፋብሪካ ውስጥ ፈተና ወድቆ መምጣት ነውር ነው፡፡ በጣም ታማኝና ቅን ሰራተኞች ናቸው፡፡ ነገ በስራቸው ሌሎችን አሰልጥነው ተክተው፤ እነሱ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ የማድረግ እቅድ አለኝ፡፡ በሌላው ፋብሪካ እንደምታዘበው፣ ለስልጠናና ለአቅም ግንባታ ሰራተኞቻቸው ላይ ብዙ ብር አፍስሰው ሲያበቁ ጥለዋቸው ይሄዳሉ፡፡ እኔን እስካሁን ጥሎኝ የሄደ ሰራተኛ የለም፤ ቢሄዱም ከኔ የተሻለ እንክብካቤና ደሞዝ አግኝተው ከሆነ ቅር ሊለኝ አይገባም፡፡ እስካሁን ያለው ይሄን ይመስላል፡፡ እኛ አሁን ከሌቭል አንድ የወሰድናቸው ነበሩ፡፡ እዚህ እየሰሩ ሌቭል ሁለትና ሶስትን ተምረው፣ ሲኦሲ አልፈው፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት የሚያስቡ አሉ፡፡ ክፍያን በተመለከተ ተመጣጣኝ ክፍያ እንከፍላለን፡፡ ፋብሪካው ትንሽ ገቢ ሲያገኝ ለእነሱም ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ከደሞዛቸው ውጭም ሲስተም ለመትከል ስንሄድ የሚያገኙት ገንዘብ አለ፤ ለተከሉበት ማለት ነው፡፡ እኔም ሲስተም እንዲገጥሙ ስወስዳቸው የውሎ አበል እከፍላለሁ፡፡ ሁሉም የተሻለ ክፍያ እንደምከፍላቸው ያውቃል፡፡ አንድ ስራ ከያዙና ካልጨረሱ ምሳ ለመብላት እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እንዲህ ዓይነት ታማኝና ጠንካራ ሰራተኞች አለመንከባከብ ውድቀት ነው፡፡ እነዚህ ልጆች ከቴክኒክና ሙያ ነው የመጡት፤ ግን ሰውን መፍጠር ይቻላል፡፡
የውሃ ማሞቂያዎችን በምን ያህል ዋጋ ነው የምትሸጡት? ሲስተሙን ለመግጠም ተጨማሪ ክፍያ ትጠይቃላችሁ?
ዋጋን በተመለከተ 80 ሊትሩን የውሃ ማሞቂያ ቫትን ጨምሮ በ13, ሺህ 500 ብር፣ 150 ሊትር ቫትን ጨምሮ በ17 ሺህ ብር፣ 200 ሊትሩን ደግሞ 22 ሺህ 500 ብር እንሸጣለን፡፡ ሄደን በምንገጥምበት ጊዜ ለባለሙያዎች 700 ብር ገዢው ይከፍላል፤ ያ 700 ብር ወደ እኛ አይመጣም፤ ወደ ገጣሚዎቹ ነው የሚሄደው፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅሙ ምን ያህል ነው? የፈላጊውስ መጠን?
 ፋብሪካው አሁን ባለበት ሁኔታ በወር 3 ሺህ በርሜሎችንና የፀሐይ ኃይል የሚሰበስቡ ፓኔሎችን የማምረት አቅም አለው፡፡ ፈላጊው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ሆቴሎች፣ ግለሰቦች፣ ባለ ሻወር ቤቶችች፣ ጤና ጣቢያዎች እየጠየቁን፣ በክልልም በአዲስ አበባም ምርታችንን እያቀረብን እንገኛለን፡፡ አሁን ህዝቡ ግንዛቤ እያገኘ ነው፡፡ ወደፊት ገበያውን ሰብረን እንገባለን፤ ያኔ አሁን ከምናቀርብበት ዋጋ በጣም ባነሰ ለማቅረብ ያስችለናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ባመረትንና በሸጥን ቁጥር ከውጭ የሚመጡ መሳሪያዎችን እዚህ ማምረት እንጀምራለን፡፡ በተጨማሪም ከውጭ በተዘዋዋሪ የምናስገባቸውን የፋብሪካ ግብአቶች ቀጥታ ከአምራቾች የምንረካከብበትን ሁኔታ የመፍጠር አቅም ይኖረናል፣ ይሄ ይሄ ወጪያችንን ስለሚቀንስልን አሁን ከምናቀርብበት ዋጋ በጣም በመቀነስ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
ምን ያህል ሰራተኞች አሏችሁ?
በአሁኑ ወቅት ከ19 እስከ 22 የሚደርሱ ሰራተኞች አሉን፡፡ ስንጀምር የፋብሪካው መነሻ ካፒታል 16 ሚ. ብር ነበር፤ ሲሆን አሁን ከ30 ሚ. ብር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳል፡፡
የወደፊት ዕቅድዎ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ኖሮት፣ መንግስትም ዋነኛ አጋዥ ኃይል መሆኑን በመገንዘብ ይበልጥ አግዞን፣ ሁሉም ህብረተሰብ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው አላማዬ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ህዝቡም አውቆት የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሎ፣ ካደግን በአጎራባች አገሮች ያለውን ገበያ መያዝና የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ ኢትዮጵያ በሶላር ኢነርጂ ከሌላው ዓለም የተሻለች መሆኗን ማሳየት ሌላውና ትልቁ አላማችን ነው፡፡ ምክንያቱም 13 ወር ሙሉ የፀሐይ ፀጋ ያላት በተፈጥሮ የታደለች አገር ናት፡፡ ሌላው ለውጭ ገበያ ደረጃውን የጠበቀ የዘርፉን ምርቶች ማቅረብና ሁሉንም መስራት እንደምንችል ለሌላው ዓለም ማሳየትም የአፍሮአምክ ሌላው ራዕይ ነው ይህን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁንም የምናመርታቸው ምርቶች እስራኤል 70 ዓመት ከተጠበበችበት ምርት ይበልጣል፡፤
ከዚያ ቀጥሎ ዋናው ዓላማችን የኤሌክትሪክ መፍጠሪያውን መሳሪያ አገራችን ላይ አምርተን ማሳየት ነው፡፡ ይሄ እንደውም በቅርቡ ቢሆን ትልቅ ምኞት አለን፡፡ ለዚህ ዋና እንቅፋት የሆነብን ፋይናንስ እንጂ እውቀትና ብቃት አለን፡፡ ቢሮክራሲው እስከለቀቀንና ፋይናንስ እስካገኘን ድረስ መስራት እንችላለን፡፡ ፈረንጅ ላይ ጥገኛ መሆን አያስፈልገንም፡፡ በቃ በአገራችን ልጆች እውቀት እንመን፤ መልዕክቴ ነው፡፡ በተረፈ እዚህ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙኝም ያንን እንዳልፍ የረዱኝን ቤተሰቦቼን፣ የመንግስት ኃላፊዎችንና ጓደኞቼን እንዲሁም ዓላማዬን ራዕዬን ተረድታችሁ፣ ፍላጎቴንና ስራዬን ለህብረተሰቡ እንድናገር እድል የሰጣችሁኝን የጋዜጣችሁን ዝግጅት ክፍል ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 2991 times