Print this page
Saturday, 01 July 2017 14:57

“የፓስፊክ” ኢንዱስትሪ ከየት ወዴት?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

 · ባለቤቱ በሰራተኞች የቀረበውን ውንጀላ “ሀሰተኛ ሴራ ነው” ብለዋል
                     · “መንግስት ባለበት አገር እንዴት እንዲህ አይነት በደል ይፈፀማል?”
                           ቤተሰባቸው ፋብሪካ ነበራቸው - የሳሙና፣ የቅባትና የሰንደል ፋብሪካዎች፡፡ ተማሪ እያሉ በትርፍ ሰዓታቸው በፋብሪካዎቹ ውስጥ እየሰሩ ያግዙ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት የፋብሪካ ስራ መውደድ ብቻ ሳይሆን ዝንባሌውም እንዳደረባቸው ይናገራሉ፡፡
በ1980 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ አካባቢ የመጀመሪያውን የሳሙና ፋብሪካ ከፈቱ። በዓመቱ ደግሞ የጭማቂ ፋብሪካ፡፡ ከዚያም የውሃና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ባለቤት ለመሆን ቻሉ፡፡ የሳሙና ፋብሪካውን ሰርተው የሰጧቸው ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ ሥራ የጀመሩት በ25 ሺህ ብር ካፒታል ነበር፡፡ አሁን የአራቱ ፋብሪካዎች ካፒታል 150 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ይናገራሉ - የፋብሪካዎቹ ባለቤት አቶ መፍቱህ አብዱልጋፋር፡፡
አቶ መፍቱህ በሐረርጌ ክ/ሀገር በሂርና ከተማ በ1962 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱባት ከተማ በሂርና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ ጥቁር አንበሳ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታተሉ። ከዚያም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በንግድ ስራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) በማታው ክፍለ ጊዜ የሂሳብ ስራ ትምህርት (አካውንቲንግ) ለሁለት ዓመት እንደተከታተሉ አቶ መፍቱህ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ሦስት ዓይነት የልብስ ሳሙናዎች (ሰርሃ፣ ክርስቲና ማሩቲ) አብዛኛው ጥሬ ዕቃቸው (80 በመቶ) ከሀገር ውስጥ ከቄራዎች ድርጅት የሚገኝ ሞራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከውጭ አገር የሚገቡት ጥሬ ዕቃዎች አር ቢዲ ፓልም ሰትሪምና ኬኤፍኤዲ መሆናቸውን የፋብሪካው ባለቤት ገልጸዋል፡፡
“እኔ ከዛሬ 29 ዓመት በፊት የሳሙና ንግድ ስጀምር የሕዝብ ቁጥር እንዳሁኑ አልነበረም፡፡ የሳሙና አምራቾችም እንደ አሁኑ በዝተው የንግድ ፉክክሩ ጠንካራ ስላልነበር ንግዱ ጥሩ ነበር፡፡ አሁን አምራቹ ቢበዛም የዛኑ ያህል ፈላጊም ስላለው እያደገና እየሰፋ በመምጣቱ ንግዱ ጥሩ ነው” ብለዋል አቶ መፍቱህ፡፡
ከሳሙና ፋብሪካው ጋር በተቀራራቢ ጊዜ በ50 ሺህ ብር ካፒታል በትንሽ ቦታና በአነስተኛ መሳሪያ ሥራ የጀመረው የጁስ ፋብሪካው ነበር። በአሁኑ ወቅት ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ እንዲመረት በተደረገው ጥረት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ራሱን የቻለ ዘመናዊ ፋብሪካ ተሰርቶና ዘመናዊ መሳሪያዎች ተገጥመውለት ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው፤ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነው ከአራቱም ፋብሪካዎች ካፒታል ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ይኼው የጁስ ፋብሪካ እንደሆነ የፋብሪካው ባለቤት ተናግረዋል፡፡
በጁስ ምርት ከፍተኛው ግብአታችን ስኳር ነው ያሉት አቶ መፍቱህ፤ የተለያዩ ፍሌቨሮች፣ ለማቅለሚያ የተለያዩ ቀለሞችና እንደ ሶዲየም ቤንዞይትና ሲትሪክ አሲድ ያሉ ኬሚካሎች ለኅብረተሰቡ ጤና ተስማሚ መሆናቸው በደረጃ መዳቢ ባለስልጣን ተመስክሮ፣ በጉምሩክ በኩከል ገብተው፣ ምርቱ በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ ባሉ ወኪሎችና ባሉን ሱቆች አማካይነት ይከፋፈላል በማለት ገልጸዋል፡፡
ከ14 ኣመት በፊት በአነስተኛ ደረጃ የውሃ ምርት ጀምረው ነበር፡፡ አሁን ግን፣ ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነና በዘመናዊ መሳሪያ የተደራጀ፣ በተለያየ ደረጃ መኖር ያለበትን የጥራት ደረጃ እያዩ የሚያረጋግጡ በርካታ ባለሙያዎች ያሉት ፋብሪካ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ተሰርቶ ምርት ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። በፕላስቲክ ፋብሪካው ደግሞ ለራሳችን የውሃ ምርት መያዣ ጠርሙስና ለሌሎች የውሃ አምራች ድርጅቶችና ለጭማቂ አምራቾች በሚፈልጉት ሞዴል መሰረት የፕላስቲክ መያዣ ጠርሙሶች እናመርታለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከድርጅቱ በተለያየ ምክንያት የለቀቁ የቀድሞ ሰራተኞች፤ “በድርጅቱ ከፍተኛ በደል ይፈጸምብናል፣ ሽንት ቤት ለመሄድ ነፃነት የለንም፣ ስልክ ቢደወልልን ለማንሳት አይፈቀድልንም፣ አንስቶ የተገኘ ከ3-5 ቀን ደሞዝ ይቀጣል፣ የሰራተኛ ደሞዝ በሰበብ አስባቡ ይቆረጣል …” በማለት ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቡትን ቅሬታ አቶ መፍቱህ በፍፁም አይቀበሉትም፡፡ “ይኼ በእኛ ድርጅት ሊፈጸም ቀርቶ በፍፁም የማይታሰብ ነው። ሰራተኞቹ የእኔንና የድርጅቱን መልካም ስም ለማጉደፍ ሆን ብለው የፈጠሩት የሀሰት ውንጀላ ነው” ብለዋል፡፡
“ይህንን ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎች ምን ላይ ነበሩ? ምን ይሰሩ ነበር ብለን ብንመለከት በግልጽ የሚታይ ጥፋት በመፈጸማቸው መላው የድርጅቱ ሰራተኞች ያዘኑባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ወሬ የሚያናፍሱት ስራቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አቅቷቸው፣ ከድርጅቱ በሥነ-ምግባር ችግር የተሰናበቱ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ 340 ሰራተኞች ባሉበት ድርጅት ውስጥ ነፃነት የለም ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ሰራተኞቹን የማይንከባከብ ድርጅት ህልውና አይኖረውም፡፡ ሰራተኛው በድርጅቱ እየሰራ ያለው በብዙ መንገድ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው፡፡ አሁን የስም ማጥፋት ዘመቻ የተያያዙ ሰራተኞች ከድርጅቱ የለቀቁበትን ምክንያት እኛ ከምንነግራችሁ ከሰራተኛው ብትሰሙ ይሻላል፡፡
“እያንዳንዱ የመጋዘን ሰራተኛ ኃላፊነት ከጥበቃና ከሽያጭ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ጉድለት እየታየበት፣ ማጉደልንና ጥፋትን እንደ መብት ቆጥሮ፣ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ መስራት እጅግ ከባድ ስለሆነ የስነ-ምግባር ጉድለት እርምጃ ተወሰደባቸው፡፡ እነዚህ የተባረሩ ሰራተኞች ድርጅቱ በደል ፈጽሞባቸው ከሆነ፣ ወደ ሕግ ነው እንጂ ወደ ሚዲያ መሄድ አልነበረባቸውም፡፡ ወደ ሚዲያ የሄዱት ሆን ብለው በሀሰት ስም ለማጥፋት ነው፡፡
“ፋብሪካችን ነፃነት የሰፈነበት ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ የሚቀጠረው ለመስራት ነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነትና ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በአንዱ ፋብሪካ አምስት፣ በሌላው ደግሞ ስድስት መፀዳጃና መታጠቢያ የተሰራው ለሰራተኞቹ ነው እንጂ እኔ ልጠቀምበት አይደለም፡፡ ይኼ ባለበት ሁኔታ ሰራተኛውን አትታጠብ፣ አትፀዳዳ ማለት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ለምን ሰገድክ ተብሎ ተባሯል የተባለው፣ የማይመስልና እጅግ ከእውነት የራቀ ቅጥፈት ነው፡፡ ለመብላት፣ ለመስራት፣ ለመስገድ፣ ለመተኛት፣ … ለሁሉም ሰዓት አለው፡፡ እኔ ሙስሊም ነኝ፡፡ በሶላት ሰዓት ለምን ሰገድክ ብዬ እንዴት አባርራለሁ? ይኼ በፍፁም የማይመስል ውንጀላ ነው፡፡”
ሰራተኛው በየጊዜው እየተሰደበና እየተዋረደ ይባረራል፣ አንድ ሰራተኛ ከ3 ወር በላይ አይቆይም ለሚለው ቅሬታ አቶ መፍቱ ሲመልሱ፤ “እኔና ሰራተኞቼ ያለን የአባትና የልጅ ግንኙነት ነው፡፡ አባት ልጆቹን እንዴት እንደዚያ ያደርጋል? ቋሚ ቀርቶ ኮንትራት ሰራተኞችም ከዓመት በላይ የሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ችግሮችና የሥነ - ምግባር ጉድለቶች የተገኙባቸው ሰራተኞች ብቻ ናቸው ከወር ከአስራ አምስት ቀን እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ የተባረሩት እንጂ ሌሎች ዕድሜ ጠገብ ናቸው፡፡ እነዚህ የተባረሩ ሰራተኞች ቀድመውም ሲቀጠሩ የተለያዩ የጥፋት ተልዕኮ የነበራቸው ናቸው” ብለዋል፡፡
“አንድ ሰራተኛ ስልክ ሲያወራ ቢገኝ ከ3-5 ቀን ደሞዝ ይቀጣል፡፡ 30 ቀን ሰርቶ ደሞዝ በ1 ቢወጣና በዚያን ቀን ቀርቶ በ2 ቢመጣ ደሞዙ አይሰጠውም፣ ተመላሽ ይሆናል” በሚል ለቀረበው ቅሬታም፤ “ይኼ የውሸት ውንጀላ ነው፡፡ ይህ የ30 ዓመት ፋብሪካ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ በሰራተኛውና በአስተዳደሩ መካከል ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም ለማለት አይዳዳኝም፡፡ ግጭት ተፈጥሮ ይሆናል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ደሞዝ ተከለከልኩ፣ ደሞዜ ተመላሽ ሆነብኝ ብሎ ያመለከተ ወይም እኔ ጋ ቀርቦ የተናገረ አንድም ሰራተኛ አላውቅም። ወር ሰርቶ ደሞዝ ካልተከፈለው ምን በልቶ ነው በቀጣዩ ወር የሚሰራው? ይህ ኢ - ሰብአዊ ድርጊት ስለሆነ በእኛ ድርጅት ፈፅሞ የማይታሰብ ነው፡፡ እናንተ ጋ ከመጡ ሰራተኞች ሁለቱ ከ60-100 ሺህ ብር የሚበልጥ ጉድለት ተገኝቶባቸው ነው ስራ ያስቆምናቸው። በአንድ ወር ከ15 ቀን ተባረርኩ ያለችው ሰራተኛም የወጣችበትን ምክንያት አብዛኛው ሰራተኛ ያውቀዋል፡፡ እዚህ መግለጽ ፀያፍ ስለሆነ እተወዋለሁ፡፡ ሌላውም የተባረረው እዚህ መግለጽ በማልፈልገው የስነ - ምግባር ጉድለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሳይበላ ስለማይሰራ ክፍያ አይከለከልም፡፡” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ፋብሪካው ለጁስ ምርት የሚጠቀምበት ጥሬ ዕቃ ጊዜው ያለፈበት (ኤክስፓየር) ያደረገ ነው፡፡ “ቀምማችሁ ቆዩኝ” ይልና ሌሊት መጥቶ ኤክስፓየር ያደረገውን ፍሌቨር ጨምሮ ያመጣበትን ዕቃ ይዞ ይሄዳል በማለት ከፋብሪካው የለቀቁት ሰራተኞች ያቀረቡትን ቅሬታ አቶ መፍቱህ አይቀበሉትም፡፡ ሀሰተኛ ውንጀላ ነው ይላሉ፡፡
“ይኼ ዓይን ያወጣ የተቀነባበረ የውሸት ውንጀላ ነው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር እንዴት እንዲህ ዓይነት በደል ይፈጸማል? የሚሉት ነገር ተፈጽሞ ከሆነ፣ በአገር ላይ የተሰራ ትልቅ በደል ነው፡፡ አንድ ፋብሪካ ሲቋቋም ጥቅሙ ለህብረተሰብና ለመንግስት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ነው ባለቤቱ የሚጠቀመው፡፡
“ይኼ 30 ዓመት ገደማ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ፋብሪካ ነው፡፡ ጁሱ ለሕዝብ ምግብነት የሚቀርብ ስለሆነ አቀማመሙን ለሰራተኞች ማስተማር፣ መከታተልና መቆጣጠር የእኔ ኃላፊነት ነው። በእርግጥ ክትትሌ ጠበቅ ያለ ነው፡፡ ይኼን የማደርገው ቀን ነው እንጂ ሌሊት ሄጄ አይደለም፡፡ በዚህ ፋብሪካ ውስጥ ዘጠኝ ወይም 10 ኬሚስቶችና ማክሮባዮሎጂስት ባለሙያዎች አሉ። እንዴት እነሱን አልፎ የተበላሸ ግብአት የተጨመረበት ምርት ለገበያ ይቀርባል? ለኅብረተሰብ የሚቀርብ ምርት በጥራት መስራት ከምንም በፊት የህሊና ጉዳይ ነው፡፡ ለአገር፣ ለህብረተሰብ ጥቅም የሚውል ኢንቨስትመንት፣ ልጆቻችን የፈረንጅ አሽከር እንዳይሆኑ፣ ለአገራችን ዕድገት ፈር ቀዳጅ የሚሆን ፋብሪካ ከፍተን ስንሰራ እንዲህ ያለ ነገር መፈጠሩ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡
“ለውሃ ማጣሪያ የምንጠቀምበት ክሎሪን በዘጠኝ ባለሙያዎች እይታ ስር ነው የሚያልፈው። እነሱን ዘልዬ እኔ የተበላሸ ክሎሪን እንዲጠቀሙ የማዝበት ሁኔታ የለም፡፡ በፋብሪካው ውስጥ የተደራጀ ላቦራቶሪ አለ። ባለሙያው የተበላሸ ነገር ከተጠቀምን ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያስከትል ያውቃል፡፡ ይኼ ሁሉ ጥንቃቄ በሚደረግበት ስፍራ “የተበላሸ ጥሬ ዕቃ ይጠቀማሉ” ያለችው፤ በጣም የቆዩ ነገሮች እንዲወገዱ የተቀመጡበት ክፍል ውስጥ የተቀመጠ የተበላሸ ክሎሪን አይታ ነው፡፡ እኔ ስለዚህ ክፍል ብዙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ሰዎች ሲቀያየሩ ሳይወገድ ብዙ ጊዜ የቆየ ክሎሪን ነው እንጂ በምንም ዓይነት መስፈርት ቢሆን ያንን ክሎሪን ተጠቀሙ የሚል ትዕዛዝ አልሰጥም፡፡
ለምርት ጥቅም ከውጭ አገር የምናስገባቸው ኬሚካሎች አሉ፡፡ እየተጠቀምንባቸው እያለ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ሊያልፍ ይችላል፡፡ ያኔ ከሚመለከተው አካል ጋር ሆነን እናስወግደዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ጥቃቅን ነገሮች እኛው ራሳችን እናስወግዳቸዋለን፡፡ አሰራሩ ይህን ይመስላል፡፡ ልጅቷ ያለችው ነገር ግን እጅግ የተሳሳተ ነው፡፡ “በቆጠራ ወቅት 20 ዓመት የሆነው 40 ጀሪካን ፍሌቨር አገኘሁ” ያለችውም ቢሆን ተጠቅመንባቸው የተቀመጡ ባዶ ጀሪካኖች ናቸው እንጂ እኛ ጊዜው ያለፈበት ነገር በፍፁም አንጠቀምም” በማለት አስረድተዋል አቶ መፍቱህ አብደልጋፋር፡፡

Read 2090 times