Sunday, 02 July 2017 00:00

ንባብ ለምን … ንባብ ለምኔ?

Written by  በታደሰ ለገሰ (ሀዋሳ)
Rate this item
(14 votes)

  ንባብ በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ሊኖረው የሚገባ መሰረታዊ ክህሎት ነው። የሰው ልጅ ሰብዕናውን የሚቀርፅበትና የማንነቱና የምንነቱ መገለጫ የሆኑትን ባህላዊ፣ ትረካዊና ሥነ ጥበባዊ ቅርሶቹና ዕሴቶቹ እንዳይጠፉ ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ የሚያቆይበት፣ የሚያስተላልፍበትም ዓይነተኛ መሳሪያም ነው፡፡ ማንበብ የማይችል ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ፤ አካባቢውን የማወቅና የመግለጽ ብቃቱ፣ በማየትና በመስማት ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ለማንኛውም የፈጠራም ሆነ የዕውነታ ጽሁፍ ዕውቀቶች እንግዳና ባይተዋር ይሆናል፡፡ ስለ ሕይወትና ስለ ተፈጥሮ … ስለ ከባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች ያለው ግንዛቤ ውሱንና የተዛባም ይሆናል፡፡
የዳበረ የንባብ ልምድ በቋንቋ የመጠቀም ብቃታችንን ከማሳደጉም በላይ ሂሳዊ አስተሳሰብና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ የዳበረ የንባብ ልምድ የሌሎችንም ሀሳብና ስሜት በቀላሉ ለመረዳትና ከማንኛውም አቅጣጫ ለሚሰነዘሩ አዎንታዊም ሆኑ አሉታዊ አስተያየቶች ምክኒያታዊና በሳል፤ ቁጥብና ገላጭ በሆኑ ቃላት ፈጣን ምላሽን መስጠት የሚያስችል ብቃትና ክህሎት ያስታጥቀናል። ንባብ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረትን ሰብስቦ የማሰብና የማሰላሰል ጠቃሚ ልምድና ብቃትን ያጎናጽፈናል። ታላላቅ ሳይንቲስቶችና ኢንጂነሮች፣ ስመ ጥር ደራሲያን፤ ጸሐፌ ተውኔቶች፤ ሰዓሊያን፤ ገጣሚያንና ባለቅኔዎች ወዘተ የሚፈጠሩት በዳበረ የንባብ ምናባዊ ዓለም ውስት ነው፡፡ ምናባዊ ወደ ሆነው የንባብ ዓለም ውስጥ ስንገባ፣ ግዑዙንና ገሀዱን ዓለም ጥለን፣ በታላቅ ጸጥታና ተመስጦ፣ በስፍራና በጊዜ በማይለካና በማይወሰን፣ ጥልቅና የትየለሌ ወደሆነው የዕውቀትና የጥበብ ዓለም ውስጥ እንገባለን፡፡
ከዚህ ምናባዊ የንባብ ዓለም ከምናገኘው ድንቅ የትኩረትና የተመስጦ ተመክሮ፤ በህይወት ጉዞአችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ተግዳሮቶችና ፈተናዎች እንዴት መወጣት እንደምንችል እንማራለን። ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ብቃታችንን እናሳድጋለን፡፡ ከንባብ ጋር የሚኖረን ጥብቅ ቁርኝትና ትሥሥር ለሕይወትና ለተፈጥሮ የምንሰጠውን ዋጋና ክብር በእጅጉ ይጨምራሉ፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ የዳበረ የንባብ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች፣ የንባብ ልምድ ከሌላቸው ግለሰቦች ይልቅ በሦስት እጥፍ የተፈጥሮ እንክብካቤና የበጎ አድራጎት (ሰብዓዊ) ድርጅቶች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ንቁ ተሳትፎ አንባቢያንን በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከማድረጉም በላይ ለግለሰቦችም ሆነ ማህበረሰቦች ደህንነት በእጅጉ ተቆርቋሪና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ንባብ ጭንቀትንና ውጥረትን በማስወገድ ዘና እንድንል ይረዳናል፡፡ በንባብ አውድ ዙሪያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች፤ ጭንቀትን እንደሚቀንስ ደርሰውበታል። ለስድስት ደቂቃ ጸጥ ብሎ ማንበብ የልብ ምትን ያረጋጋል፡፡ የተኮማተሩ የአካሎቻችን ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ ያደርጋል፡፡
ንባብ እራሳችንን ለማስደሰትና ለማዝናናት ያስችለናል፡፡ በደራሲያን በጸሐፌ ተውኔቶችና በገጣሚያን የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ የምናገኛቸው ገጸ-ባህሪያት በተሳሉበት ምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚያደርጉት ልብ አንጠልጣይ እንቅስቃሴ፣ ለአእምሮአችን ምናባዊ ፍሰሀን ያጎናጽፈዋል፡፡ ንባብ ከማዝናናትም ባሻገር የህይወት ክህሎታችንን በማሳደግ ያስደንቀናል፡፡
ንባብ ከፊልምና ከቴሌቪዥን ከምናገኛቸው መረጃዎች ይልቅ የአስተሳሰባችንን አድማስ የማስፋትና ምናባዊ እይታችንን የማሳደግ ብቃት እንዳለው የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የሚያሳዝነው ግን አስቂኝ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረው ንባብ በብዙ ሰዎች ህይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገው ምክኒያት ሆነዋል፡፡ አንድ ሰው አዘውትሮ ቴሌቪዥን የሚመለከትና እምብዛም የማያነብ ከሆነ፣ የማንበብ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በትክክል የማሰብና የማመዛዘን እንዲሁም ሀሳቡን አቀነባብሮ የመግለጽ ችሎታው ሊቀንስ እንደሚችል በጥናት ተደርሶበታል። ማር ዎልፍ የተባሉ ጸሐፊ፤ “የአንባቢ አእምሮ ታሪክና ሳይንስ” (The Story and Science of the Reading Brain) በተሰኘ መፅሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፡- “ስታነብ ለማሰብ ወይም አንድን ነገር ለማሰላሰል ጊዜ ይኖርሃል፡፡ የማሰቢያ አፍታን ታገኛለህ፡፡ በሌላ በኩል ፊልም ወይም ቴሌቪዥን ስትመለከት አልያም ሬዲዮ ወይም ቴፕ ስታዳምጥ ወደ ውስጥህ የማየትና የማሰብ ጊዜን አታገኝም፡፡ ይህ የንባብ ሂደት ውስጥ የምታገኘው አፍታ፣ የማሰብና የማስታወስ ችሎታህን በእጅጉ ያዳብረዋል፡፡”
ለማጠቃለል በተፈጥሮ ሳይንስ፤ በማህበረሰብ ሳይንስ፤ በፍልስፍና ታሪክ፤ በስነ - ጥበብና በሌሎችም ዘርፎች ያለን ዕውቀት ሊሰፋና ሊያድግ የሚችለው በንባብ ነው፡፡ ንባብ በዕውቀትና በጥበብ የተካነ፣ ማንነቱንና ምንነቱን የተረዳ፣ ሁሉን ጠያቂና ተመራማሪ፣ በየተሰማራበት የሙያ መስክ ስኬታማ የሆነና እራሱንም ሆነ አገርና ወገኑን የሚጠቅምና የሚያሳድግ፣ ደስተኛና የተረጋጋ ሕይወት ያለው ዜጋ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡ ከታሪክ ሂደት መረዳት እንደምንችለው፤ መጪዎቹን ዘመንና ትውልድ መቆጣጠርና መምራት የሚችሉት በፈርጣማ ጡንቻዎቻቸው የሚያስቡ አምባገነኖች ሳይሆኑ በዳበረ የንባብ ልምድ የበለጸገ አዕምሮና ብሩህ አስተሳሰብ ያላቸው አንባቢ ማህበረሰቦች ስለመሆናቸው አንዳችም ጥርጥር ሆነ ብዥታ ሊኖረን አይገባም፡፡ እናም እናንብብ! እናንብብ! አሁንም እናንብብ! ግን እንዴትና ደግሞም ለምን?
ሀሮልድ ብሩም የተባሉ ጸሐፊ “ለምንና እንዴት ማንበብ አለብን?” (How to read and why) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ እንዴት ማንበብ እንዳለብን ሲያብራሩ፤ “ስታነብ ለምታነበው ጽሁፍ ልብህ ክፍት ይሁን፤ የምታነባቸውን ፊደላት በፍቅር፤ በእርጋታና በጽሞና በውስጠኛው ጆሮህ እያደመጥክ በጸጥታ አንብብ፡፡” ስናነብ ትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል፡፡ ስናነብ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ከሌለን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን። ስናነብ እራሳችንን በባለታሪኮቹ ውስጥ አድርገን ስሜታቸውን ለመጋራት እንችል ዘንድ በፍቅርና በወዳጅነት መንፈስ ሆነን እናንብብ። ጸሀፊው ለምን ማንበብ እንዳለብን ሲገልጹም፤ የምናነበው ምክኒያታዊነታችንን ለማሳደግ እንዲያም ሲል አጠቃላዩን ንቃተ - ህሊናችንን ለማዳበር እናም ደግሞ ከህመማችን ለመፈወስ መሆን አለበት። ማንነታችንን ካላገኘንና እራሳችንን መሆን ካልቻልን፣ ለሌላው ምን መሆን እንችላለን? ሲሉም ይጠይቃሉ። ምክራቸውን እንስማ፤ ጥያቄያቸውንም ለመመለስ እንዘጋጅ፡፡
አመለካከት ማንኛውንም ድርጊት ለማድረግም ሆነ ላለማድረግ የመገፋፋት ሀይል አለው፡፡ ለአንድ ድርጊት የሚኖረን አዎንታዊ አመለካከት፤ ለድርጊት የሚያነሳሳን ሲሆን አሉታዊ … አመለካከት ደግሞ ያንን ድርጊት በንቃት እንዳናከናውን ተነሳሽነታችንን እንደሚቀንሰው በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። በዚህ ሀሳብ መነሻነትም … ለንባብ ያለንን ተነሳሽነት የሚወሰነው ለንባብ ባለን አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በዘርፉ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች፤ በልጆች የማንበብ ልምድ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖን ከመፍጠር አንጻር ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወቱት ወላጆችና መምህራን መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን የንባብ ልምድ ከማዳበር አንጻር ሁለት ወሳኝ ሚናዎችን ይጫወታሉ፡፡ አንድም “ድርጊት ከብዙ ቃላት ይልቅ ይናገራል” (action speaks louder than words) እንዲሉ የዳበረ የንባብ ልምድ ያላቸው ወላጆች መኖሪያ፤ በተለያዩ ጋዜጦች፤ መጽሄቶችና መጽሐፍት የተሞላ እንደመሆኑ፣ የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ ለህፃናት ግልጽ መልዕክትን (ያለምንም ንግግርና ገለጻ) ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ወጣቶች የንባብ ባህልን ከቤተሰቦቻቸው ይወርሳሉ ማለት ነው፡፡፡ እናም ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ለመከታተል፤ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ወይም ለመዝናናት ከሌሎች ዘዴዎች ይልቅ ንባብን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ በሌላም በኩል ወላጆች በካበቱት የንባብ ልምዳቸው አማካኝነት ለልጆቻቸው አዝናኝና አስተማሪ ድርሳናትን በማንበብ፣ በልጆቻቸው የንባብ አመለካከት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖን ማሳደር ይችላሉ፡፤
ከወላጆች ቀጥሎ የህፃናትንና የወጣቶችን የንባብ ባህል በማሳደግ ረገድ ጉልህና የማይተካ ሚና መጫወት የሚችሉት መምህራንና ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ተማሪችን እንዲያነቡ የሚያበረታቱ መምህራንና በባለሙያ የሚታገዙና በአግባቡ የተደራጁ ቤተ-መጽሐፍት ያላቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ወጣቶች፣ ከሌሎች ይልቅ በእጅጉ የተሻለ የንባብ ልምድ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡
ይሁንና እስካሁን ድረስ የወጣቶቻችንን የንባብ ልምድ በተመለከተ ሰፊና የተቀናጀ አገር አቀፍ ጥናቶች መደረጉን እርግጠኛ ባልሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚገልጹት ከሆነ፤ ወጣቶቻችን ለንባብ ያላቸው አጠቃላይ አመለካከት በአብዛኛው አሉታዊ እንደሆነ አመላካች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር አለም እሸቴ በቅርቡ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ያካሄዱት የጥናት ውጤት ይሄንኑ እውነት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ፕሮፌሰሩ ወጣቶች ለምን እንደማያነቡ ላቀረቡላቸው ጥያቄ፣ ከሰጧቸው ሰበቦች መካከል እስቲ ጥቂቱን ለአብነት ያህል እንመልከተው፡-    
ንባብን ከቤተሰቤ አልለመድኩትም፡፡ በአካባቢዬ ብዙ ቤተ - መጻሕፍት ቤት ስለሌለ አንብብ፤ አንብብ አይለኝም፡፡
ይሄ የአውሮፓ እግር ኳስ እያለ በየት በኩል ላንብብ?
ትላልቅ መጽሐፍትን ሳይ ተስፋ ስለሚያስቆርጡኝ አላነብም፡፡
አንብቦ ለመረዳት ችግር ስላለብኝ ሳነብ አይገባኝም፡፡
የሚሰለቹ መጽሐፍት በመብዛታቸው ምክኒያት አላነብም፡፡
በጊዜ ማጣት ምክኒያት አላነብም፡፡
ለምን እንደማላነብ ራሴም ምክኒያቱን አላውቅም፡፡
መጽሐፍ የማላነበው ለዓይኔ ስለምፈራ ነው፡፡
ወጣቶቹ ላለማንበባቸው የጠቀሷቸውን ሰበቦች ጠቅለል አድርገን ስንቃኛቸው፣ ለወጣቶቻችን የንባብ ችግር ዋነኛው ምክኒያት፣ የንባብ ፍላጎት ማጣት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህም ከወጣቶች የንባብ ልምድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የጥናት ድርሳናት እንደምክኒያትነት የሚጠቀሰው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ጫና፤ (እዚህ ላይ የእነ ቃና፤ የእነ ዲኤስ ቲቪ፣ የእነ ኤምቢሲ፤ የእነ ኤምቲቪ ወዘተ … ቻናሎች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡) በተጨማሪም በሉላዊነት ሳቢያ፣ ገደብ ያልተበጀላቸውና ከምዕራቡ ዓለም በብርሃን ፍጥነት እየተሰራጩ ያሉ የአሉታዊና መጤ ጎጂ ልማዶች መስፋፋትና ወረራ፤ እንዲያም ሲል ወላጆች፣ መምህራንና ትምህርት ቤቶች የንባብን ባህል ከማዳበር አንጻር መጫወት የሚገባቸውን ሚና በአግባቡ መጫወት አለመቻላቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በተለይ ህፃናቱንና ወጣቶችን ወደ ንባብ ባህልና ልምድ ለማምጣት ሁላችንም የድርሻችንን ማድረግ እንደሚገባን መዘንጋት የለብንም፡፡ እናንብብ! እናንብብ!

Read 7784 times