Sunday, 02 July 2017 00:00

የህይወት ነጠላ ሠረዞች

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት (ከዋሺንግተን ዲሲ)
Rate this item
(4 votes)

  ‹እኔኮ እዚህ ሀገር መኖር አልቻልኩም፡፡ በቃ ዝም ብለው ደስ ያላቸውን ሁሉ ነው እንዴ የሚያወሩት፡፡ አሁን ከእነ እንትና ይኼ ይጠበቃል› እያለ በአራቱም አቅጣጫ መኪና እንደበዛበት የትራፊክ ፖሊስ፣ እጁን በላይና በታች፣ በግራና በቀኝ እያወናጨፈ ወደ ቤቱ ገባ፡፡
‹እኔኮ ምን ይሻለኛል? ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖር የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በቀደም እንደዚያ ሲሉ ቆዩ፣ አሁን ደግሞ እንደዚህ ይላሉ? ቆይ ግን እንዴት ሆኖ ነው ከሰው ጋር መኖር የሚቻለው?› ሶፋው ላይ ዘፍ አለበትና በመዳፉ እንደ ቡና ወቀጠው፡፡ ይህን ሲሰሙ አጎቱ ጋቢያቸውን እያጣፉ ከመኝታ ቤት ወጡ፡፡ በሰያፍ ተመለከቱት፡፡ ፊቱ የማረቆ በርበሬ መስሏል፡፡ ጉንጩ ታርዶ እንደወረደ ትኩስ ሥጋ ይንቀጠቀጣል፡፡ እጁ ገበያ እንደ ደራለት ሸማኔ ያለ ዕረፍት ይወራጫል፡፡ እግሩ ምት እንደሚያስጠብቅ ከበሮ መቺ መሬቱን ይጠቀጥቃል፡፡ የሚያወጣው ትንፋሽ ግለቱ ኖርዌይ ላይ ቢገኝ በጥር የማሞቂያ ዋጋ ያተርፋል፡፡
‹ምን ሆንክ› አሉት አጎቱ እንደ ፊልም ሲያዩት ቆይተው፡፡
‹ቆይ ግን ከሰው ጋር እንዴት ነው መኖር የሚቻለው› አላቸው፡፡ ዓይኖቹ ትከሻቸው ጋ ደርሰው ተመለሱ፡፡
ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ሆኖ
አህያ ሲጭኑ ሦስት ሆኖ - ይባላል፡፡ አጎቱ እየሳቁ ጎኑ ተቀመጡ፡፡
‹ሞኝኮ ሦስት ጊዜ ይሸወዳል፡፡ መጀመሪያ ሞኝ ሲሆን፣ ቀጥሎ ሰዎች ሞኝ መሆኑን ሲያውቁ፣ በመጨረሻም ሞኝ ነው ብለው ሲያሞኙት፡፡ አየህ ሞኝ ስትሆን ሁሉንም ታምናለህ፡፡ ያን ጊዜ ትሸወዳለህ፡፡ የምታምነው እንጂ የሚታመንልህ አይኖርማ፡፡
አያሌው ሞኙ
ሰው አማኙ
የተባለውኮ ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ሞኝ መሆንህን ሲደርሱበት ደግሞ ዋጋህን ከግማሽ በላይ ያወርዱታል፡፡ ‹አሞኘ› የሚባል እንጂ ‹ተሞኘ› የሚባል ስም ሰምተህ ታውቃለህ፡፡ ሞኝ መሆንህን ሲያውቁ በጣም የምትቀርባቸው ሰዎች ሳይቀሩ አንተን በማሞኘት ደስታን ይፈጥራሉ፡፡ ‹ሞኝ አይሙት እንዲያጫውት የተባለው ለዚህ ነው› ሞኝነትህን ለሌላ ሰው ብቻ ሳይሆን ላንተ ለራስህ ‹አይ ሞኙ› እያሉ ይነግሩሃል፡፡ እና እንዴት ነው ሞኝ ሁን የምትለኝ፡፡ ብልጥ ሆኜም አልቻልኩት›
‹አይ፣ ይኼን እንኳን ትንሽ ዘና እንድትል ብዬ ነው። እሳት ላይ እሳት ላለመጨመር፡፡ ያንን የንብረት ክፍፍል ወረቀት አምጣውማ› አሉት፤ ከቴሌቭዥኑ አጠገብ የሚገኝ ወረቀት እያመለከቱ፡፡ አንድ እግሩን ከነበረበት ሳይለቅ፣ አንድ እግሩን አሻግሮ ይዞላቸው መጣ፡፡
‹ይቺን የመጀመሪያዋን ዐረፍተ ነገር አንብብልኝ› አሉት ተቀበለና ወረቀቱን ከላይ ወደ ታች በዓይኑ ዋኘበት፡፡
‹የመጀመሪያውን ዐረፍተ ነገር ብቻ› አሉት፡፡
‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው፣ የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ፣ ወፍጮ ቤቱ፣ የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡› አለና ቀና ብሎ አያቸው፡፡
‹የተጻፈውን ሁሉ አንብበኸዋል› አሉት፡፡
‹አዎ፤ የመጀመሪያውን ዐረፍተ ነገር ነው አይደል ያልከኝ› አላቸው፡፡
‹አዎ›
ወረቀቱን ለመቀበል እጃቸውን ዘረጉለት፡፡
‹ተሳስተሃል፤ ያላነበብከው ነገር አለ› አሉና መልሰው ሰጡት፡፡ ወረቀቱን ጠጋ አድርጎ መነጠረው፡፡ ምንም ነገር የሳተው የለም፡፡ ፊደሉን ቆጠረው፡፡ ያው ነው፡፡ ‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው፣ የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ፣ ወፍጮ ቤቱ፣ የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡ አይደለም እንዴ የሚለው›
ወረቀቱን ተቀበሉትና በጣታቸው መጠቆም ጀመሩ፡፡ ‹እስኪ መኪናው በሚለውና የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ በሚለው መካከል ምን ይታይሃል? በሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑና በወፍጮ ቤቱ መካከል ምንም ነገር የለም? በወፍጮ ቤቱና በትራክተሩ መካከልስ ቦታው ባዶ ነው?› ቅድም አጎቱ እንዳሉት ሞኝ የሆነ መሰለው፡፡
‹የሚታየኝ ነጠላ ሠረዝ ብቻ ነው›
‹አ - ዎ፤ ታድያ ለምን አላነበብከውም? ‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው (ነጠላ ሰረዝ) የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ (ነጠላ ሠረዝ) ወፍጮ ቤቱ (ነጠላ ሠረዝ) የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡ ብለህ ለምን አላነበብክም? ለምን ዘለልከው?›
‹እንዴ አጎቴ፤ ነጠላ ሠረዝ ይነበባል እንዴ?›
‹ካልተነበበ ታድያ ለምን ገባ?›
‹ለአነባበቡ ይመስለኛል›
‹እንዴት?›
‹በቃ፣ በየመሐሉ ፋታ እየሰጡ ለማንበብ›
‹ስታነብ ግን ነጠላ ሠረዙን ታየዋለህ አታየውም›
‹አየዋለሁ እንጂ›
‹ግን አታነበውም› ነገር ዓለሙን ረስቶ ሳቀ፡፡
‹በሕይወትም ውስጥ እንደዚህ ነው፡፡ ብዙ ነጠላ ሠረዞች አሉ፡፡ የሚታዩ እንጂ የማይነበቡ፡፡ የሚሰሙ እንጂ የማይደመጡ፣ የአንተ ችግር ነጠላ ሠረዙን ሁሉ ስለምታነብ ነው፡፡ ነጠላ ሠረዝ - ሰዎች፣ ነጠላ ሠረዝ ሐሳቦች፣ ነጠላ ሠረዝ - ድርጊቶች፣ ነጠላ ሠረዝ - ክስተቶች፣ ነጠላ ሠረዝ - ችግሮች ሞልተዋል፡፡ ሁሉም ግን ይታያሉ እንጂ አይነበቡም። ትዘላቸዋለህ፡፡ ቢበዛ - ገታ - ያደርጉህና ፋታ ትወስድባቸዋለህ፡፡
ከዚያ በላይ ግን ቦታ አትሰጣቸውም፡፡ ትሻገራቸዋለህ፡፡ ነጠላ ሠረዞቹ ግን ለአነባበብህ ያስፈልጉሃል፤ በሕይወትህ ውስጥ ያሉ ነጠላ ሠረዞችም የአኗኗርህን መንገድ ለማስተካከል ያስፈልጉሃል፡፡ ግን አይነበቡም፡፡ በሕይወትህ ውስጥ ነጠላ ሠረዙን ሁሉ እያስገባህ የምታነብ ከሆን ምን እንደምትሆን ታውቃለህ?› ዝም ብሎ አያቸው፡፡
‹እንካ የቅድሙን ጽሑፍ ነጠላ ሠረዙን እያስገባህ አንብበው›
‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው (ነጠላ ሰረዝ) የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ (ነጠላ ሠረዝ) ወፍጮ ቤቱ (ነጠላ ሠረዝ) የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡›
‹ዐረፍተ ነገሩ - አንድም ትርጉም አጣ፣ አንድም ቸከ፡፡ ሕይወትህም አንድም ትርጉም ያጣል፣ አንድም ይቸካል፡፡ አንተ አሁን እንዲህ አሉኝ፣ እንዲህ አደረጉኝ፣ እንዲህ ሆኑ፣ እንዲህ ሠሩ የምትላቸው ሁሉ ነጠላ ሠረዞች ናቸው፡፡ አታንባቸው፡፡ ዝለላቸው፡፡ ትርጉም ወደሚሰጠው ነገር ሂድ፣ ይዘሃቸው አትጓዝ፡፡ ነጠላ ሠረዞቹን እዚያው ወረቀቱ ላይ ተዋቸው፡፡
‹ነጠላ ሠረዞች› አለ፤ ሰማ ሰማና
‹መልሰህ አነበብካቸው‘ኮ› አሉት እየሳቁ፡፡

Read 2294 times