Sunday, 02 July 2017 00:00

የዲሞክራሲ ጉዞ ምን ተይዞ?

Written by  አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ (በሀርቫርድ ዩንቨርስቲ፣ የበርክማን ክላየን ሴንተር፣ ሪሰርች ፌሎው)
Rate this item
(2 votes)

“-- ጥያቄው ደግሞ ከኢትዮጵያ እንማራለን ብለው ከገመቱ፣ ነገር ግን እኛ ከነሱ በእጅጉ ባነሰ ሁኔታ ውስጥ
ካለነው የታንዛኒያ ጋዜጠኛ መነሳቱ ጭምር ነው፡፡ ያልተገመቱበት ቦታ እንደ ግለሰብ መገኘቱ ብዙም አይከፋ ይሆናል፡፡ እንደ አገር ያልተገመቱበት ቦታ ወርዶ መገኘት ግን የምሬት ስሜቱ በጣም የተለየ ነው፡፡ ጠንካራ አማራጭ የቲቪ
ሚዲያ በአገር ውስጥ አለመኖሩን ተናግሬ ሳበቃ፤ ምን ያህል የግል ዕለታዊ ጋዜጣ አላችሁ? የሚል ጥያቄ ተከተለ፤ ምላሹ ቀላል ነበር፡፡ ‹‹ምንም›› አልኳቸው---”
             አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ (በሀርቫርድ ዩንቨርስቲ፣ የበርክማን ክላየን ሴንተር፣ ሪሰርች ፌሎው)

      ባለፈው ሳምንት በጀርመኗ ቦን ከ2ሺ ያላነሱ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ባለቤቶች፣ ክልላዊ፣ አገር አቀፍ ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሥርጭት ያላቸው የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት ባለሥልጣናት በተገኙበት 10ኛው የዶቸ ቨሌ ዓለም አቀፍ የሚዲያ መድረክ ለሶስት ተከታታይ ቀናት (ከሰኔ 12 እስከ 14) ተካሄዶ ነበር። በዚህ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ጉባኤ ላይ ተገኝቼ ያስተዋልኩት እውነታ የዚህ መጣጥፍ መነሻ ሆኗል።አጭር ነገር ስለጉባኤው በማስቀደም ወደ ዋናው ሃሳቤ እሻገራለሁ።
የመገናኛ ብዙሃኑ መድረክ የተከናወነባት ቦን የበርሊን ግንብ ከመፍረሱ በፊት የቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን በተለይ ከጀርመን ውህደት በኋላ ጀርመኖቹ ከተማዋን ፌዴራል ሲቲ (የፌዴራል ከተማ) በማለት የአገሪቱ ሁለተኛ ከተማ መሆኗን ያወሳሉ፡፡ በርግጥ ከተማዋ ለስም ብቻ ሳይሆን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች መገኛ ከመሆንም አልፋ ከፌዴራል መንግስቱ ተቀጣሪዎች መካከል ከ10 ሺህ የማያንሱት መቀመጫቸው በዚህችው ከተማ መሆኑ ዛሬም ድረስ የጀርመን ፖለቲካ ትኩሳት ሌላኛዋ መገለጫ መሆኗን ለማረጋገጥ በቅታለች፡፡ ከዚህ ውጪም በርከት ያሉ የተባበሩት መንግስታት ተቋማት በጋራ የሚገኙባት በመሆኑም የጀርመን “ዩኤን ከተማ”እያሉ ከተማዋን መጥራቱ የተለመደ ይመስላል። ጎብኚዎችን ለመሳብ በተለይ ከተማዋ ራስዋን የታዋቂውና ስመ ጥሩው የሙዘቃ ቀማሪ ሉድዊግ ቫን፣ ቤቶቨን የትውልድ ሥፍራ መሆኗን በስፋት ታስተዋውቃለች፡፡ ቤቶቨን አዋቂ ሳለ መስማት የተሳነው (የማዳመጥ ችሎታውን ከጊዜ በኋላ ሙሉ በሙሉ ያጣ ቢሆንም) ዛሬም ድረስ የሚደነቅበትን ሥራዎቹን ከ230 ዓመታት በፊት በመተው ብዙ አድናቂ ያለው ብቻ ሳይሆን (ለጭቁኖች የወገነ) የመጀመሪያው የለውጥ አክቲቪስት(አራማጅ) መሆኑን በማውሳት፣ የዚህ ታላቅ የሙዚቃ ቀማሪ አድናቂዎች ከተማዋን እንዲጎበኙ የታዋቂውን ሰው ሙዚየምና ሌሎችንም የቱሪዝም መዳረሻዎች በበቂ አሰናድታ፣ ገቢዋን ማሳደግ ችላለች፡፡
የዚህች ከተማ ሌላው መታወቂያዋ የጀርመን ድምፅ ዶቸ ቨሌ መገኛ መሆኑዋ ነው፡፡ 10ኛው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መድረክ የተካሄደውም አማርኛን ጨምሮ በ30 ቋንቋዎች የሚዘጋጁት የዶቸ ቨሌ ፕሮግራም ማዘጋጃ ጣቢያ ከሚገኝበት በቅርብ ርቀት ከሚገኘው የቦኑ ታሪካዊ አዳራሽ ውስጥ ነው። የሲቪል ማህበራት፣ ጦማሪያን፣ ደራሲያን፣ የነፃነት አራማጆች፣ ከኩባ እስከ ፓኪስታን፣ ከአውስትራሊያ እስከ ዚምባብዌ በተለያዩ መንገዶች የሚሰሩ የሚዲያ ሙያተኞች በአንድ መድረክ ለመሳተፍ ችለዋል። በዓለም አቀፍ የሚዲያ መድረክ ላይ ከ40 በላይ ውይይቶች፣ የልምድ ልውውጦች፣ ወርክሾፖች፣ ቀርበዋል። ከሲኤንኤን፣ ከዶቸ ቨሌ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከሌሎችም ተቋማት በርካታ ጋዜጠኞች፣ የኮሙኒኬሽን ኤክስፐርቶችና የሚዲያ ሙያተኞች ተገኝተው ልምዳቸውን በማካፈል፣ እነሱም ከሌሎች ይጠቅመናል ያሉትን ወስደዋል። በተለይ በዘንድሮ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መድረኩ የኋይት ሃውስ ዘጋቢዎች ማህበር ተሸላሚ መሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡ በእርግጥ ሽልማቱ ለሕዝብ ጠላት ተሰጠ ብለው ትራምፕን የሸነቆጡ አልጠፉም። የሆነው ሆኖ “ብዝሃነት እና ማንነት” በሚል መሪ ቃል ለ10ኛ  ጊዜ የተከናወነው ኮንፈረንሱ፤ መገናኛ ብዙሃን የገጠማቸው ተግዳሮት፣ የሃሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት፣ የድህረ እውነት ጋዜጠኝነት፣ የአዲሱ ሚዲያ (ኒውሚዲያ) ለመገናኛ ብዙኃን የፈጠረው ዕድልና ስጋትን ጨምሮ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መድረክ ከተካሄደባቸው ንዑስ አዳራሾች መካከል አንደኛው በአዘጋጆቹ “አዲስ አበባ” ተሰኝቶ እንደነበር ሳልጠቅስ ማለፉን አልወደድኩትም።
የሃሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት፣ የድህረ እውነት ጋዜጠኝነት፣ የአዲሱ ሚዲያ (ኒውሚዲያ) ለመገናኛ ብዙኃን የፈጠረው ዕድል እና ስጋትን ጨምሮ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መድረክ ከተካሄደባቸው ንዑስ አዳራሾች መካከል አንደኛው በአዘጋጆቹ አዲስ አበባ ተሰኝቶ እንደነበር ሳልጠቅስ ማለፉን አልወደድኩትም።
የአፍሪካ ሚዲያ ገፅታና ተግዳሮቱ
በዓለም አቀፉ የሚዲያ መድረክ ላይ ከተካሄዱት የጎንዮሽ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ በአፍሪካ ሚዲያ ገፅታና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረው ይገኝበታል። የአፍሪካ ሚዲያ ገፅታን በተመለከተ የተካሄደው ውይይት ላይ የነበረው የአፍሪካ አገራት የቲቪ ስርጭት ልምድ የሚደንቅ ነበር። የውይይቱ ተሳታፊ አገሮች የግል ቲቪ ጣቢያዎች ዋንኛ ችግር ከመንግስት የሚደርስባቸው ተፅዕኖ ሳይሆን የማስታወቂያ ገቢ ወደ አዲሱ ሚዲያ /ኒው ሚዲያ/ በማጋደሉ ይህንኑ የገቢ መቀነስ በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ያሰምሩበት ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ካለ አገር ለመጣው እንደ እኔ አይነቱ ተሳታፊ፤ ቴሌቪዥን ለድራማና ሙዚቃ ካልሆነ በቀር ከሞላ ጎደል አሁንም ድረስ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የቲቪ ስርጭት አማራጭ የሌለበት አገር መኖር፣ ከየት ወዴት እየሄድን ነው? የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀሬ ነው፡፡
በእርግጥ የአገራችንን የብዙሃን ሚዲያ ምን አልባት ከደቡብ አፍሪካ ጋር ማወዳደሩ አይመስልም ይሆናል። ነገር ግን ከኛው አገር ብዙም ባልራቀ ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አልፈው ዛሬ ለአብነት የሚጠቀስ የነፃ (ግል) ሚዲያ ተቋማትን መገንባት ከቻሉ አገራ እንኳ ሳይቀር በጣም ያነሰ ደረጃ ላይ መገኘታችን አንገት ያስደፋል ከሚሉትም ይከፋል፡፡ ይሄን ያሰኘኝ ስንት የግል ቲቪ ጣቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ? የሚለው ጥያቄ ነበር። ጥያቄው ደግሞ ከኢትዮጵያ እንማራለን ብለው ከገመቱ፣ ነገር ግን እኛ ከነሱ በእጅጉ ባነሰ ሁኔታ ውስጥ ካለነው የታንዛኒያ ጋዜጠኛ መነሳቱ ጭምር ነው፡፡ ያልተገመቱበት ቦታ እንደ ግለሰብ መገኘቱ ብዙም አይከፋ ይሆናል፡፡ እንደ አገር ያልተገመቱበት ቦታ ወርዶ መገኘት ግን የምሬት ስሜቱ በጣም የተለየ ነው፡፡ ጠንካራ አማራጭ የቲቪ ሚዲያ በአገር ውስጥ አለመኖሩን ተናግሬ ሳበቃ፤ ምን ያህል የግል ዕለታዊ ጋዜጣ አላችሁ? የሚል ጥያቄ ተከተለ፤ ምላሹ ቀላል ነበር፡፡ ‹‹ምንም›› አልኳቸው፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ሆነ ከሌሎች የአፍሪካ ክልሎች ለመጡት ጋዜጠኞች ነገሩ ሁሉ በጭራሽ የማይታመን መስሎ ነበር የታያቸው፡፡ ‹‹እንዴት ሆኖ ነው? ቢያንስ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ባለበት አገር አንድ ዕለታዊ ጋዜጣ ወይም የዜና ቲቪ ጣቢያ እማይኖራችሁ?›› ነገሩን በዝርዝር ለማስረዳት በሞከርኩ ቁጥር፣ ‹‹ዋት ካይንድ ኦቭ ፖሊሲ ዩ ቶክን አቦውት›› /ስለምን አይነት ፖሊሲ ነው እምታወራው/ እያሉ በኢትዮጵያ ያለው መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ብዬ ያቀረብኩትን ማብራሪያ ‹‹በጭራሽ ስሜት የማይሰጥ›› ሲሉ ውድቅ ካደረጉት በኋላ፣ ከታንዛኒያ ታዳሚ የነበረው ጋዜጠኛ ድንገት ተነስቶ፤ ‹‹አሁንም የሶሻሊስት ስርዓት ውስጥ ነው እንዴ ያላችሁት?›› የሚል ጥያቄውን አከለ፡፡
ይህ ጥያቄው በተለይ የዚህ ጽሁፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሚዲያ ጨምሮ ለሌሎች በቀጣይነት ለማነሳቸው ሐሳቦች መኮርኮሪያ መሆኑ አልቀረም። የሆነው ሆኖ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ በአገራችን ያለው የሚዲያ ብዝሃነት ሲታሰብ በአንድ በኩል የጎረቤታችን ኬኒያን ጠቅላላ የሚዲያ ሁኔታ ከእነ ጉድለቱም ቢሆን እንደ ምዕራቡ ዓለም ደረጃ እንዲናፈቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በዕለታዊ፣ ሳምንታዊ ጋዜጣቸው ሆነ የምርመራ ጋዜጠኝነት የታከለበት የቴሌቪዥን አማራጫቸው ከኬኒያውያን ጋር ማነፃፀሩ ምን አልባት አይገባ ይሆናል፡፡ አንዳንዶች የኬኒያ ሚዲያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የወሰዳቸው ነገሮች አለ ስለሚሉ ማለቴ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስቲ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ሆነ በሌሎች ታሪካዊ ክስተቶች ስለምትመስለን ታንዛኒያ እናንሳ፡፡
ታንዛኒያ እንደኛው የምስራቅ አፍሪካና የብዙ ብሔሮች አገር ከመሆኗ ባሻገር በተለይ ደግሞ ከፈላጭ ቆራጭ የሶሻሊስት ስርአት ወደ ታዳጊ ዲሞክራሲ የተሸጋገረችው በቅርቡ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ታንዛኒያ ከእነ ችግሮቿም ቢሆን፣ በሚዲያ ብዝሃነት ለአብነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች። በበርካታ የፕሬስ ሆነ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የግል ሚዲያው የሚጫወተው ሚና ሰፊ ከመሆኑ አልፎ አብዛኛው ማሕበረሰብ ከመንግስት ሚዲያ ይልቅ የግሉን የሚከታተል ነው፡፡ በመሆኑም ይህች አገር በአሁኑ ወቅት የመንግስት ተቋማት ከግል ሚዲያው በክፍያ ማስታወቂያና  ሌሎችም አስፈላጊ ነው ያሉትን ነገሮች እሚያስተላልፉባት ናት። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በፕሬስ ሆነ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የዳበረ ልምድ ያላት አገር ለመሰኘት የበቃች ሆናለች። ታንዛኒያ ከኛ በግማሽ ያነሰ ህዝብ ቁጥር ይዛ በሚዲያ ብዝሃነት ግን በእጅጉ ትልቀናለች። ታንዛኒያን ልዩ የሚያደርጋት ሌላው ነገር በደርዘን ከሚቆጠሩ የነፃ ራዲዮ ጣቢያዎቿ ባሻገር፣ የአገሪቱ ቲቪ ሥርጭትን በተመለከተ ከ10 በላይ ቻናሎችን ለህብረተሰቡ በአማራጭነት ማቅረብ መቻሏ ነው:: እንደ ስቲድማን ጥናት ከሆነ፤ 31 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ አዋቂዎች ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ጋዜጣ ያነባሉ። 42 በስፋት በአገሪቱ ከአንድ ክልል በላይ የሚሰራጩ ዕለታዊና ሳምንታዊ ጋዜጣዎች ያሉ ሲሆን በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዘርፍም የኢትዮጵያ መንግስት ገና ያልጀመረውን ነገር ግን ቃል ከተገባለት ብዙ ጊዜ ያለፈበትን የዲጂታል ማይግሬሽን (የዲጂታል ስርጭት ሽግግርን) እውን ለማድረግ ችላለች፡፡
የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ጄኔቫ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፤ አገራት አንደ ጎርጎሳውያኑ የዘመን ቀመር ጁላይ 17, 2015 ከማለፉ በፊት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርጭት ሽግግር ለማድረግ ቃል መግባታቸው  ይታወቃል። ያደጉት አገራት ከሞላ ጎደል ከአስር አመታት በፊት ሽግግራቸውን ያገባደዱ ሲሆን እንደ ታንዛኒያ ያሉ አገራት በቅርቡ ሽግግራቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የዲጂታል ሽግግሩን በ2016 መጨረሻ እውን ለማድረግ መታቀዱ ቢነገርም እስካሁን በተግባር የታየ ነገር የለም፡፡ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማይግሬሽን ቀነ ገደብ ካለፈ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በይፋ ዲጂታል ስርጭት ሽግግሩ መቼ ተጀምሮ እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም፡፡
ሌላው በምሳሌነት ከአፍሪካ መወሳት የሚገባት ናይጄሪያ ናት፡፡ ናይጄሪያ ከእርስ በርስ ጦርነትና ከተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስት ተላቃ፣ ታዳጊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ከጀመረች ገና 15 ዓመት ያልሞላት ቢሆንም በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ተወዳዳሪ የሆነን ሚዲያ እውን ለማድረግ አልተሳናትም። ቦን በተካሄደው የመገናኛ ብዙሃን ጉባኤ ላይም የተገኙትና ልምዳቸውን ያካፈሉት የቻናል ሚዲያ ግሩፕ ዋና ስራ አሰፈጻሚ ጆን ሞሞህ ምስክርነት፣ የአገሪቷን የሚዲያ ብዝሃነት አንዱ ማሳያ ነው። የእሳቸው ተቋም ብቻ የ24 ሰዓት ዜና ማሰራጫውን ጨምሮ ከአራት ያላነሱ ቻናሎችና ከ30 በላይ አካባቢያዊ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አሉት። እንደ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን ላሉት ታላላቅ የውጭ ሚዲያዎች ሳይቀር በዋንኛነት በዜና ዘገባ ምንጭነት ለመጠቀስ የበቃው የሚዲያ ተቋሙ፣  20 ሚሊዮን የሚደርሱ አድማጭ/ተመልካቾች ያለው ሲሆን ከተመሰረተም 22 ዓመት አልፎታል። የሚዲያ ተቋሙ በርካታ ችግሮች ቢገጥሙትም ከተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ዋና ፀኃፊ ባን ኪ-ሙን ጋር ለመፈራረም ከመቻሉ ባለፈ በአፍሪካ አህጉራዊ ደረጃ ሆነ የናይጄሪያ ሚዲያ ሜሪት አዋርድ ትረስት ለ10 ጊዜ ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ነው። ከዚህ ባለፈ የቲቪ ቻናሎች በጥቅሉ ከ50 በላይ ሲሆኑ ሳምንታዊው ስርጭታቸው ሚሊዮኖችን የሚሻገሩ ጋዜጣና መጽሔቶች፣ የናይጄሪያ የታዳጊ ዲሞክራሲ ውጤቶች ናቸው።
በኛ አገር ውስጥ እየተገነባ ነው በተባለው ዲሞክራሲ እንኳን ይህን ያህል ጥንካሬ ያላቸው በርካታ የሚዲያ ተቋማት ይቅርና አንድም የግል የቲቪ ዜና ሚዲያ እንደሌለ ማስረዳቱ፣ ለአፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንኳ ለማመን የሚከብድ ቢሆንባቸውም እንደ አገር ግን ከመሰል የአፍሪካ አገራት አንፃር እንኳ ያለንበት ርቀት አስከፊ መሆኑ ሊያሳስበን የሚገባ ነው፡፡ ሥርዓቱ በፈጠረው አፈና የተነሳ በአገራችን ያለው ነባራዊ የሚዲያ ሁናቴ የተሽመደመደ በመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን የጋራ መድረክ ላይ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ለመወያየት ለሚያበቃ ለተገደበ ሚዲያ ብዝሃነት ያልታደልን እያደረገን ነው፡፡
የታንዛኒያው ጋዜጠኛ እንደ ቀልድ፤ ‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፍሪካ ዲሞክራሲ እየጎለበተ ነው። አገራችሁ በዚህ ረገድ መሻሻልን ካላሳየች የአፍሪካ መዲና የመሆን የሞራል ልዕልናዋን ማጣቷ አይቀርም›› ሲል የተናገረኝን በውስጤ ሳወጣ ሳወርድ፣ አህጉር ዓቀፍ ሚና መጫወቱ ቀርቶ በውስጥ ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ ተዋስዖ (National Dialogues) ሊደረጉባቸው ከሚገባቸው ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል አንዱ በሚገባን መጠን ስለሌለንና አደጋ ውስጥ ስላለው መገናኛ ብዙኃን መሆን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ይህን መሰረታዊ ጉዳይ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማዕዘን ነው ብሎ ተገቢው አትኩሮት እንዲቸረው የሚሰራ ተቋም ወይም ወገን የለም፡፡ ሚዲያው ይጠቃል፤ ጋዜጠኛው ይታሰራል አሊያም ይሰደዳል፡፡ ነገር ግን ለምን? ግን እስከ መቼ? የሚል ያገባኛል ባይ አይሰማም፡፡  
ሩብ ምዕተ ዓመታት ስለ ዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ሲነገረን ቢያልፉም በእርግጥ አሁን ላይ ምን አይነት ነፃ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት አሉን? የዲሞክራሲ ሂደቱን ኦዲት ለማድረግ ብንሞክር ከየት ወደ የት እየሄድን እንደሆነ መሬት ላይ ያሉት እውነታዎች ምን ይነግሩናል? በጥቅሉስ የዲሞክራሲ ጉዞ ምን ተይዞ? በሚሉት ሐሳቦች ዙሪያም ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በማከል ሣምንት እመለስበታለሁ።

Read 2596 times