Sunday, 02 July 2017 00:00

የመሪዎች ህልምና ጉዞ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)


       “መሪነት ከእናት ማህፀን ተይዞ የሚመጣ ሳይሆን፣ ከአካባቢያችን መሪዎች የሚጋባብን በጎ ተፅዕኖ ነው” የሚለው አስተሳሰብ በስነ አመራር ሊቃውንት ሰፈር የደመቀ ነው፡፡ … ስ፤ዚህ ይህንን ዲስፕሊን እንደ ትምህርት የወሰዱ ሰዎች ሁሉ ይህንን የክብሪት እሳት ልሰው፣ ሻማ ሆነው ወደ አካባቢያቸው የሚያንፀባርቁት እርሱ ኑ - ነው፡፡
ግን ደግሞ እንደ እኔ ዐይነቱ ሰው፤ ሀሳቡ የእውነት ልቡ ካልገባ፣ … ነፍሱ ጨው ጨው ካላላት፣ ዐይን ውስጥ እንደገባ ጉድፍ ይቆረቁረውና “ለምን?” ሊል ይችላል፡፡ ይሁንና እንደ ጆንሲ ማክስዌል አይነቶቹ የዘርፉ ምሁራን፤ አሁንም ደግመው የሚሉት፣ 85% ያህሉ መሪ የሚገኘው፣ ከሌሎች መሪዎች ተፅዕኖ ነው፡፡
እኔ በግሌ ሳይንሱን ከተጨባጭ ሀቅ ጋር ለማስታረቅ፤ ይህንን በጎ ተፅዕኖ ከልጅነት ጋር አያይዤ፣ ከዚያ ጋር አብሮ ያደገ ይሆናል! ወደሚል ሀሳብ ጎራ እላለሁ፡፡ ለምሳሌ የፔሬስትሮይካ አባት የሆኑት የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ፕሬዚደንት ሚካኤል ጎርባቾቭን እንያቸው፡፡ እኒህ ሰው በልጅነታቸው የሶቪየት ምድር ከላይ አበባ ለብሶ ውስጡ የበሰበሰ፣ አደባባዩ በሳቅ የተሞሉ መስለው ጓዳዎቻቸው እንባ ያረገዙ እንደነበሩ ያዩት፣ በገዛ ወገኖቻቸው ነው፡፡ ለፍተው ጥረውና ግረው ያገኙትን ሀብት እንደ ወንጀለኛ እያሳደዱ ሲነጥቋቸው፣ ታታሪ ገበሬዎችን “ኩላክ” እያሉ ሲረሽኗቸው፣ በልጅ ልባቸው፣ ይህ አስተዳደር መቀየር አለበት የሚል ፅንስ ፀንሰው ነበር፡፡ ምናልባትም አጠገባቸው ሆነው፣ የሚቆሙትን መሪዎች አስተውለው ነበር፡፡ እንግዲህ ያ ሀዘን፣ ያ ሥርዐት የለሽ ግፈኝነት እየጎፈነናቸው አድገው፣ ጊዜው ሲደርስ በልባቸው ያሰመሩትን መስመር ወደ ክዋኔ ያመጡት ይመስለኛል፡፡
ከወደ አሜሪካ ደግሞ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ተመሳሳይም ባይሆን በልጅነታቸው በውስጣቸው የምትንተከተክ ተሰጥዖ ቢጤ ነበረቻቸው፡፡ ራሳቸው ከፃፉት ግለታሪክ እንደተረዳሁት፤ … ጓደኞቻቸውን ሁሉ አንጋግተው፣ መምራትና ማዘዝ ይችሉ ነበር። በዕድሜ የሚያንሱዋቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የሚበልጡዋቸውንም። ታዲያ ይሄኔ ነው ግርታዬ! … እኒህና እኒያ ሰውዬ ከልጅነታቸው ይዘውት የመጡትን መሪነት ነው እንዴ ምሁራኑ፣ ካደጉ በኋላ ከታላላቅ መሪዎች እንደተጋባባቸው የሚቆጥሩት … እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ … የሚገርመው ግን ከየቱም የስነ አመራር መምህር ጋር ተወያዩ፣ አሊያም ተከራከሩ፤ ሙግታችሁን እየሰማ “አንገቴን ለካራ!” ይላችኋል፡፡
ግን ይሁን ብለን እንተወውና፤ መሪነት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ሚና ይኖረዋል? የትኛውስ የአመራር ዓይነት ለህዝቦች ህይወትና ኑሮ የተሻለ ውጤት ያመጣል? በዓለማችን ለሀገራቸው ጥሩ መሪ የነበሩት እነማን ናቸው? የሚለውን ለማየት እንሞክር፡፡
ወደ ጥሩ አመራር ሥርዓት ዓይናችንን ባቀናን ቁጥር የአሜሪካው ፕሬዚደንት ቶማስ ጀፈርሰን ላይ እናርፋለን። ጀፈርሰን ምን ዓይነት መሪ ነበረ? ካልን ደግሞ ያለምንም ማወላወል “ዲሞክራሲያዊ” መሪ መሆኑን የሚመሰክሩልን ብዙ እማኞች እናገኛለን፡፡
ጀፈርሰን የአሜሪካ ነፃነት ደራሲ፣ የስልጣኔዋ ጎዳና ደልዳይ ነበር፡፡ ሰውየው ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ካልን ደግሞ ከጀርባው የምናየው ሥዕል እጅጉን አንባቢ፣ መጻሕፍት መርማሪ መሆኑን ነው። ንባቡም የዲሲፕሊን ምርጫ እንኳን ያልነበረውና የዕድሜውን ብዙ ጊዜ የወሰደበት ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ዓለም ላይ ባለ ብዙ ተሰጥኦና ክህሎት ባለቤት ከሆነው ሌዎናርዶ ዳቪንቺ ጋር ጎን ለጎን የሚታይ ነው፡፡ ሳይንቲስት ገበሬ፣ አርክቴክት፣ ደራሲ፣ ጥሩ ፖለቲከኛ … ብዙ - ብዙ ነገር!
በዚህ ሞያው ደግሞ አሜሪካንን በሚገባ መምራት ችሏል፡፡ ሰውየው የአሜሪካ ሦስተኛ ፕሬዚዳንት በሆነበት ጊዜ የሀገሪቷን ቀጣይ ሥዕል አስቀምጧል። የሕዝቦች መብት፣ ማለትም ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በገቢር ፈፅሟል፡፡ ያውም እነ አውሮፓ በጨቋኝ ገዢዎች ይማቅቁ በነበረበት ውቅት! … ብዙዎቹ የስነ አመራር ምሁራን የሚስማሙበት አንድ ነገር ደስ ይለኛል፡፡ “አንድ መሪ በቅድሚያ ራዕይ ሊኖረው ይገባል!” የሚለው፡፡ ራዕይ የምንደርስበት ግብ ነው፡፡ ይህ ግብ ደግሞ ገና መሰረት ሳይቆፈርና ሳይጀመር፣ በውስጣችን ያለው የህንፃው የመጨረሻ መልክ አይነት ነው፡፡ የራሱ ራዕይ የሌለው መሪ፤ መሪ አይደለም፡፡
ጀፈርሰን የፕሬስ ነፃነትን ለመትከል ታግሏል። የሃይማኖት እኩልነት እንዲኖር ከፍተኛ ተጋድሎ ፈፅሟል። ለዚያውም ነገሩ ገና ውል ባልያዘበት ዘመን፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም መርሁን ተከትለው እንዲሄዱ፣ ሕገ መንግስት በመቅረፅ፤ ቀጣዩን የሀገሪቱን ዕድል አመቻችቷል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበሩት ስመጥር ፕሬዚደንቶችም ያንን ድርሰት ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ አሌክሳንድር ሀሚልተን ከጀፈርሰን ጋር ያንድ ዘመን መሪ ነበር። የጆርጅ ዋሽንግተን ፀሐፊ ሆኖም ሰርቷል፡፡ ግን ደግሞ ወደ ጦረኝነቱ ያመዝናል፡፡ አሟሟቱም አሜሪካንን ነፃ በማውጣት ፍልሚያ ውስጥ ነበር። እጅግ በጣም ብዙ ነገሮችን አኑሯል፡፡ በተለይ በሀገራዊ መሰረት መጣያው ወቅት!
የአሜሪካ መስራች መሪዎች ያደረጉት ዋናው ነገር፣ ተስፋ ማሳየት፣ ሥዕል መፍጠር ነበር፡፡ የአሁኗን በእንግሊዝ እጅ የወደቀችውን ምስኪን ሀገር ሳይን ታላቅ ሀገር!
ይህንን ህልም ፕሬዚደንት ቢንደን ሊ. ጆንሰን፤ አንዴ በንግግራቸው ጠቅሰውታል፡፡ በልጅነታቸው የቀድው የሀገራቸው ፕሬዚደንት የሆኑት ፍራንክሊን ሩዝቬልት፤ በሚቀጥለው ዘመን አሜሪካውያን ስላላቸው ተስፋ ሲናገሩ፣ ሰምተው፣ ልባቸው በደስታ እንደነደደ ያስታውሳሉ፡፡ እውነትም እስከ ጫማ ጠራጊነት ሥራ የሰሩት ጆንሰን፤ በዚያችው ጫማ በጠረጉባት ምድር፣ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ … መሪ … ራዕይ ጠንሳሽ እንጂ ህልም አኮላሽ ሊሆን አይገባውም፡፡ ጆን ሲ ማክስዌል ለሰዎች ተስፋ መስጠትና ተጨባጭ ህልም ማስጨበጥ ለአመራር ስኬታማነት ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡
ሌላው የመሪ ትልቁ ችሎታና ብቃት፤ የተግባቦት ክህሎት ወይም አቅሙ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰዎችን የሚቀርብበት መንገድ፣ ለህዝቡ የሚያደርገው ንግግር ተከታዮቹ ወይም ህዝቡ፣ ሀሳቡን እንዳይቀበሉት ልባቸውን ሊዘጋው ይችላል፡፡
ለዚህም እንደማስረጃ የሚሆነን የአሜሪካ የሥራ አመራር አባት የሚባሉት ፒተር ድራከር በአሀዝ ያስቀመጡት መረጃ ነው፡፡ በእርሳቸው አባባል፤ 60% የሚሆነው የአስተዳደር ችግር የሚፈጠረው በተግባቦት ብልሽት ነው፡፡ የወንጀል ጥናት ሊቃውንት ደግሞ ከ90% በላይ የሚሆኑት ወንጀለኞች፤ የችግራቸው መነሾ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው የተግባቦት ድክመት ነው፤ ይላሉ፡፡
ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ፍራንክሊን ሩዝቬልት፤ ያገኙዋቸውን ሰዎች ስም ወዲያው በመያዝና ሰዎችን በማግባባት ይታወቃሉ፡፡ … ከሁሉ የተሻለ የተግባቦት ችሎታ ነበራቸው የሚባሉት ግን ከፊልሙ ዓለም የመጡት ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ናቸው፡፡ ጆን ሲ ማክስዌል ሲገልፁዋቸው፤ ሰዎችን የማዝናናትና የማነሳሳት አቅም ነበራቸው ይላሉ። በዚህ አንፃር ጆን ኤፍ ኬኔዲም ሰዎችን የማቅረብ ተሰጥኦ ወይም አቅም ነበራቸው፡፡ ምናልባት፣ እርሳቸውም በሞያቸው ጋዜጠኛ መሆናቸው ሳይረዳቸው አልቀረም፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ባለስልጣኖች፣ የጦር መሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ መሪዎች ያለቅጥ መከበር ጀምረው ነበር። ቀድሞ ጀፈርሰን ይፀየፈው የነበረ፣ የጨቋኞች አስተዳደር እየተፈጠረ ነበር፤ ይሁንና የቀደመው ሥዕልና ህዝባዊ የሆነው ህገ መንግስታዊ መርህ ስለነበር ወደዚያው ተመልሰዋል፡፡
አሁን ወዳለንበት ዘመን ስንመጣ ደግሞ ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የሚለውን እናገኛለን። ይህ የአመራር ዘዬ እጅግ የተሻለና አሳታፊ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ መሪ ከማኔጀር የሚለይባቸውን ነገሮች ማወቅም ያስፈልጋል። መሪ ማለት ትኩረቱ በሰዎች ላይ የሆነና ለሰዎች ቅድሚያ ሰጥቶ፣ በሰዎች ላይ የሚሰራ ሲሆን፣ ትኩረቱና ዝንባሌው ሀብትና ቁሳቁስ ላይ ብቻ አይሆንም፡፡ እርሱ የማኔጀሩ ስራ ነው፡፡ መሪ ግን እንደ ንብ ንግስት፣ ተከታዮቹን አስከትሎ ያለመው ላይ ለመድረስ የሚተጋና የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ሰው ከተሰራ፣ ያ ሰው ሀብቱን ይሰራዋል፡፡
ትራንስፎርሜሽናል ሊደር ደግሞ ተከታዮቹን ለዓላማ የሚያነሳሳ፣ በክህሎት የሚያስታጥቅ፣ ዲሞክራቲክ፣ በመነጋገርና ሰዎች የራሳቸውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን መንገድ የሚያመቻች፣ ለፈጠራ በር የሚከፍት ሰው ነው፡፡ ማነሳሳትና ማሰራት ብቻ ሳይሆን ስላደረጉት አስተዋፅኦ ማበረታቻና ሽልማት በመስጠት፣ ትጉሀንን የበለጠ ማትጋት የሚችል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር ምናልባት በቡድንና በማደራጀት በሚያምነው መንግስታችን ዘንድ ቦታ የሚኖረው አይመስልም። ምክንያቱም ለጥፋትም ለልማትም ድርጅትን እንጂ ግለሰብን አይመለከትም፡፡ ይህንን ጉዳይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም አንደበት ሰምተነዋል፤ ተተኪውም ይህንኑ ደግመውታል፡፡ “ፓርቲዬ ቢልከኝ ወረዳም ቢሆን…” አይነት ሀሳብ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የዚህ የትራንስፎርሜሽን ሊደርሺፕ መሪ የሆነ ሰው፤ የራሱ የሆኑ በጎ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ከነዚህም አንዱ ቀደም ሲል የጠቀስኩት ጥርት ያለ ራዕይ (Clear vision) ነው፡፡ በተጨማሪም ሁልጊዜ ውስጡ የተነቃቃና የበረታ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ ባለፈ ህዝቡን መምራት የሚችለው ህዝቡን ሲያውቅ ነው፤ ህዝቡን ማወቅ ያልቻለ መሪ የሚያስብበት ቦታ መድረስ አይቻለውም፡፡
መሪነት በጎ ተፅዕኖ መፍጠር ከሆነ፣ ውሳኔ መስጠትና በአቋም ያለማወላወል ይጠበቃል። ችግሮች በሚፈጠሩ ጊዜ አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨት ስትራቴጂ መቀየስም የመሪው ኃላፊነት ነው፡፡” አንዴ የያዙትን ሙጢኝ ብሎ መሞትና መግደል የትራንስፎሜሽናል ሊደር ጠባይ አይደለም። ሌላው ወሳኝ ነገር መሪዎች ለእውቀት በራቸው ክፍት መሆን አለበት፡፡ ለትምህርት ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ሌት ተቀን መስራት አለባቸው። ሁልጊዜ ያወቀና የሚተጋ ህዝብ ያላት ሀገር አትወድቅምና! …. ከዚያ ውጭ ግን ሀገርን ለተለያዩ ርካሽ ሸቀጦች ማራገፊያ፣ ለወደቁ ሥነ ምግባራት መጠጊያ ያደረገ መሪ፤ ሀገሩን ከማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ይከታታል የሚለው ስጋት ሁላችንንም ያስማማናል፡፡
ጊልበርት ሃይጌት የተባሉ ፀሐፊ በዓለማችን ላይ ለዕውቀት በራቸውን የከፈቱ ሀገራትንና መሪዎችን አደንቃለሁ ሲሉ እንዲህ አስፍረዋል፡-
“That we admire republican Athens, Augustine Rome, Renaissance Italy, and French, England and Germany of nineteen century…”
እኛ ኢትዮጵያዊያን የዚህ ዓይነት መሪዎች ነበሩን? ወደ ኋላ ስናይ ዲሞክራሲያዊነት ዕጣ ክፍላችን አይመስልም። እንኳን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን የሚያመቻቹልን ቀርቶ፣ ሰብዓዊ መብታችንንም ተነፍገናል፡፡ ጆሮ እያለን እንዳንሰማ፣ ዐይን እያየን እንዳናይ ታግደናል! … የዚህ ሁሉ ግብ ግን ለኛም፣ ለሀገራችንም፣ ለመሪዎቻችንም አይጠቅምም፡፡
ገጣሚ አሌክስ አብረሃም፤ “እጆቿን ወደ እግዜር መዘርጋቷን ትታ፣
ትጀነን ይዛለች - ቀዳዳ ኪሶች ውስጥ ባዶ እጆቿን ከትታ” ብሏል፡፡
ለመሪዎቻችን ልብ ይስጥልን!!   

Read 3287 times