Print this page
Sunday, 02 July 2017 00:00

የሕንዱ አፓሎ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ቅርንጫች የመክፈት ዕቅድ አለው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

 በየዓመቱ ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን በሆስፒታሉ ይታከማሉ
            በህንድ አገር የሚገኘው አፓሎ ሆስፒታል ከበርካታ የምዕራብና የምስራቅ አፍሪካ አገራት አጋሮቹ ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ከሆስፒታሉ ጋር የመስራት ፍላጎት ያላቸው ጥሩ አጋሮች ከተገኙ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የመክፈት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ፡፡
የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎችና የህክምና ባለሙያዎች ሰሞኑን በኦሮሚያ ሆቴል በተዘጋጀው የሆስፒታሉ ታካሚዎችና ሀኪሞቻቸው የእርስ በርስ ውይይት ላይ እንደተገለፀው፤ ከኢትዮጵያ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን ለማግኘት በየዓመቱ ከ500 በላይ ታካሚዎች ወደ ህንድ ይጓዛሉ፡፡ ሆስፒታሉ ከባድ ለሚባሉ የጤና ችግሮች ህክምናና የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት የሆስፒታሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ራዲ ሞሃን፤ ከታካሚዎቹ 98 በመቶ የሚሆኑት ከህመማቸው ፈውስን እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡
ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ታካሚዎች ወደ ህንዱ ኦፓሎ ሆስፒታል እየሄዱ መታከማቸውን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ሆስፒታሉ ለልብ ለካንሰር ክትትል፣ ለከባድ የቀዶ ህክምና፣ ለኩላሊት ንቅለ ተከላና ለጭንቅላት ቀዶ ህክምና አገልግሎቱን እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡
በሆስፒታሉ ከበሽታቸው ተፈውሰው፣ ወደ አገራቸው ከተመለሱ ህሙማን መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዘመረ ጀማነህ፤ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ በልባቸው ላይ ደርሶባቸው የነበረውን የደምስር መዘጋት ችግር ያለምንም ቀዶ ህክምና ታክመው መዳናቸውንና ለህክምናው የከፈሉት ገንዘብም ከታይላንድና ሌሎች አገራት ጋር ሲተያይ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በጭንቅላቷ ውስጥ የወጣውን የጭንቅላት እጢ በሆስፒታሉ አስወጥታ ወደ አገሯ የተመለሰችው የአስራ አንድ ዓመቷ ታዳጊ ዳግማዊት ባይሳ በበኩሏ፤ በሽታው የእይታ ችግር ፈጥሮባት እንደነበርና ህክምናውን ካገኘች በኋላ ጤናዋ ሙሉ በሙሉ እደተመለሰላት ገልፃለች፡፡ የታዳጊዋ ወላጅ አባት ዋና ኢንስፔክተር ባይሳ ማሞ ለልጁ በተደረገላት ህክምና መደሰቱንና አሁን ልጁ ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር በሰላም ስትጫወት ማየቱ ለእሱ በቃላት ሊገለፅ የማይችል መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሆስፒታሉ ለህሙማን ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያን በማስከፈል የህክምና አገልግሎትን እንደሚሰጥ የገለፁት የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች፤ “አንዳንድ ሰዎች የውጪ ህክምና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ፈፅሞ የማይቻል መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ የአብዛኛውን ሰው አቅም ያገናዘበ ክፍያ በማስከፈል አገልግሎቱን ይሰጣል” ብለዋል፡፡ 

Read 4573 times