Sunday, 02 July 2017 00:00

‘የተሳሳተ ጥሪ’

Written by 
Rate this item
(12 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ ስልክ ይደወልለታል። በዛ ሰዓት ይደውልልኛል ብሎ የሚያስበው ሰው ስላልነበር፣ የልብ ምቱ ትንሽ ፈጠን ይላል፡፡
“ሄሎ፣ ማን ልበል!” ይላል፡፡
በምላሹ “ሄሎ፣ እከሌ ነኝ፣” የለ፣ “ናፍቀኸኝ ነው” የለ፣ “ድንገት ትዝ ብለኸኝ ነው፣” የለ… “ፖለቲከኛው አለቃህ አሁንም ነክሶህ እንደያዘህ ነው ወይ!” ...ብቻ የሆነች ሴት ድምጽ በአንድ ሴከንድ ስድሳ ያህል ቃላት ታርከፈክፍበታለች፣ የስድብ ቃላት። በእሷ ዐይን ኤልሱን በጣም ጭምት፣ እንደ ኤሊ እየተንቀረፈፈች የምትናገር ነች፡፡ ቂ…ቂ...ቂ… ኧረ እሱ ላይ የደረሰው ነገር አያስቅም፡፡ ሊያስበው የሚችለውንና፣ የማይችለውን የስድብ አይነት ላይ በላይ ትዘረግፍበታለች፡፡ ስድቦቹ አይደለም በዚህ ዘመን በድሮው የ‘ሬድ ላይት’ ሰፈሮች እንኳን የተረሱ ናቸው፡፡ ከእሱ ጋር ቤተሰቦቹ አልቀሩ፣ ጓደኞቹ አልቀሩ፣ ሁሉም ‘የድርሻቸው’ ተሰጣቸው። ወላ ነጠላ ሰረዝ፣ ወላ አራት ነጥብ የሌለው አጥንት ሰባሪ ዘለፋ ታወርድበታለች፡፡ ቢቸግረው ስልኩን ይጠረቅመዋል፡፡ እንደገና ስትደውል አያነሳም፡፡ ደጋግማ  ስትደውል ለክፉም ለደጉም ብሎ ያነሳዋል።
“አንተ ማን አባክ ሆንክና ነው የምትዘጋብኝ!…” ብላ የአዲስ አበባን ቀለበት መንገድ ሦስት እጥፍ የሚረዝም የስድብ መአት ትደረድርለታለች። “ምን አለች በለኝ…” ብላ ታላላቅ ባለስልጣኖች እንደምታውቅ፡ ልቡ እስኪጠፋ እንደምታስጠበጥበው ፎከራ… “አንተን ልክ ካላስገባሁ ከምላሴ ጸጉር!” ምናምን ብላ ትዘጋበታለች፡፡
እኔ የምለው መጀመሪያ ስም አይቀድምም እንዴ!  “አንተን ማን ልበል፣” ምናምን አይነት ማረጋገጫ!
በማግስቱ በጊዜ ይደወላል ያው ቁጥር፡፡ አያነሳውም። ደጋግሞ ከተደወለ በኋላ “እባክህ ስልኩን አንሳልኝ፣” የሚል የጽሁፍ መልእክት ይደርሰዋል፡፡ ቀጥሎ ሲደወል ይነሳል፡ እያለቀሰች ይቅርታ ትጠይቀዋለች፡፡ ለካስ የገዛ ጓደኛዋን ይዞ የፈነገላት ‘ቦይፍሬንዷ’ መስሏት ነው፡፡ አሀ… ‘ቦይፍሬንድ’ስ ቢሆን ይሄን ያህል መሰደብ አለበት እንዴ! ማንኛውም ጨረታ ላይ እኮ “ድርጅቱ የተሻለ መንገድ ካገኘ ጨረታውን ማስተላለፍም ሆነ መሰረዝ ይችላል…” ምናምን የሚባል ነገር አለው (ሴትዮዋ ከሰማችን ሁለተኛው ዙር ለእኛ ነው፡፡)
በተለይ ደግሞ ከመሸ በኋላና በሌሊት የሚደውሉ የተሳሳቱ ጥሪዎች የምር አስቸጋሪ ናቸው፡፡
ይቺን ስሙኝማ፡፡ የቴሌፎን ኩባንያው ፕሬዝደንት ሌሊት እንቅልፉን ይለጥጣል፡  ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ስልኩ ሲጮህ ይነቃል፡፡
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ የቴሌፎን ኩባንያው ፕሬዝደንት ነህ?”
“አዎ ነኝ፣  ምን ልርዳዎ?”
“እስቲ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በተሳሳተ ጥሪ ከሚጣፍጥ እንቅልፍህ መቀስቀስ ምን እንደሚመስል አሁን ንገረኝ!” አለውና አረፈው፡፡
እናማ ‘የተሳሳተ ጥሪ’ ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡
እናማ…ይሄ ‘የተሳሳተ ጥሪ’ ነገር የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ የምር አሁን፣ አሁን የማትጠየቁት የሰው አይነት፣ የመሥሪያ ቤት አይነት የለም፡፡ አሁን እኔ ምኔ ‘እንትን ጋራዥ’ን ይመስላል! ቂ…ቂ…ቂ…  እናማ… ጥሪው ‘ከመሳሳቱ’ ሌላ የደዋዮቹ ባህሪይ ከአገር ሊያሰወጣን ምንም አልቀረው…  ከአገር የሚያስወጡ ነገሮች ያልበዙብን ይመስል!
ከአገር የመውጣት ነገር ካነሳን፣ ከዚህ በፊት አንስተናት ልትሆን የምትችል ነገር ላውራችሁማ። ‘በዛኛው ዘመን’ የሆነ ነው፡፡ ውጪ ተምሮ የመጣ ሰው ነው፡ ለምርምር ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ይላካል። ታዲያላችሁ… “ይህ ሰውዬ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ሳይኖረው አይቀርም ተብሎ  እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በወታደር ይጠበቃል፡፡ ታዲያ ጧት፣ ጧት እየተነሳ ይሮጣል፣ ወታደሮችም ይከተሉታል። ይሀ ነገር ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥልና ከወታደሮቹ ይላመድና በራሱ እየሮጠ መመለስ ይጀምራል። ታዲያ አንድ ቀን በወጣበት ይቀራል፡፡ በሳምንቱ ገደማ… “ሩጫ ስለፈቀዳችሁልኝ አመሰግናለሁ፣” የሚል የስልክ ጥሪ ይደርሳል...ከኖርዌይ። (ሩጫ በሸታና እድሜን ማባረሪያ ብቻ ሳይሆን ‘መብረሪያ’ ሊሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው።)
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ ማን ልበል?”
“ሄለንን አቅርብልኝ፡፡”  ጥያቄ ሳይሆን ትእዛዝ፡፡
“ጌታዬ ተሳስተዋል፡ ሄለን የሚባል ሰው የለም፡፡”
“አታቀርብልኝም፣ ማለት ነው?”
“ጌታዬ እንደዛ የሚባል ሰው የለም አልኩዎት እኮ!”
“በአንተ ቤት ማታለልህ ነው! ደግሞ ንገራት፣ እናትሽ ሆድ ብትገቢ አታመልጪኝም በላት፡፡ ይሄ የምትኩራሪበትን መልክሽን የህጻናት ማስፈራሪያ ባላደርገው እኔ አይደለሁም ብሏል በላት!”  ጥርቅም!
ሰውየው ይደውልና…
“ይሄ ቁጥር ስንት ነው?” ይላል፡፡ በወዲያኛው ጫፍ ያለው ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “አንተ ንገረኝ እንጂ፣ አንተ አይደለህ እንዴ የደወልከው?” አሪፍ መልስ አይደል!
እኔ እኮ ይሄ ሞባይል የሚሉት ነገር…ፎካሪው መብዛቱ! “ተሳስተዋል፣” “ሌላ ቁጥር ነው የደወሉት፣” እያላችሁት ያለ ጋሻና ጦር ቀረርቶውን ይለቅባችኋል። ሄለን የለችም ማለት፣ “ሄለን የለችም” ማለት አይደለም እንዴ!
ሀሳብ አለን…የተሳሳተ ቁጥር በደወሉ ጊዜ ምን ማለት እንደሚገባዎ የሁለት ወር ልዩ የክረምት ስልጠና ምናምን ይዘጋጅልን፡፡ አሀ..እነሱ በተጣሉት፣ እነሱ በተፈነጋገሉት፣ እነሱ በተካካዱት…እኛ ስድቡን የመሸከም ውል ተዋውለናል እንዴ!
“ሄሎ!”
“ሄሎ!”
“እስቲ ባንጃውን አቅርብልኝ…” ቁጣ፡፡
“ይቅርታ፣ ተሳስተዋል፡፡”
“ስማ፣ ሄደህ የምታሾፍበት ላይ አሹፍ፡፡ አሁን ባንጃውን ታቀርብልኛለህ፣ አታቀርብልኝም!”
ባንጃው ምንም ያድርግ ምን ጦሱ ወደ እናንተ ይመጣል፡፡ (ስሙ ግን ብዙ ነገር ማድረግ የሚችል ያስመስለዋል፣ ቂ…ቂ..ቂ…)
“ጌታዬ ምናልባት ሲደውሉ ቁጥር ተሳስተው ይሆናል፡፡”
ጆሯችሁ ላይ ጥርቅም!
ለነገሩ ዘንድሮ የባህሪይ ነገር፣ የስነ ምግባር ነገር ግራ እየገባን “ሰውረነ ከመአቱ…” አይነት የሚያስብል ሆኗል። ስልክ ደግሞ ሳይታዩ እንደልብ ለመሆን ስለሚያመች ይኸው እንግዲህ የተነጠቀውም፣ የተፈነገለውም፣ የተጭበረበረውም…እኛ ላይ ንዴቱን ይወጣል፡፡
ለመሳሳቱ እናንተ ምክንያት የሆናችሁ ይመስላል። ከተናደደ ቴሌ ጆሮ ላይ አይጠረቅመውም እንዴ!
እንግዲህ ባንጃው ማን ይሁን፣ ምን ይሁን የሚያውቅ ይወቀው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው በኦፕሬተር በኩል ይደውላል፡፡  
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ እንዴት ይዞሀል?”
“ደህና ነኝ፡፡ ስማ ትንሽ ብር ስለቸገረኝ መቶ ብር ያህል በባንክ ላክልኝ፡፡”
ድምጹ ይለወጣል፡፡ “ስልኩ ይንኮሻኮሻል…የምትለው አይሰማኝም፡፡”
“መቶ ብር በባንክ ላክልኝ ነው ያልኩህ…”
“ምን አይነት ስልክ ነው… የምትለው ምንም አይሰማኝም!”
ይሄኔ ኦፕሬተራ ጣልቃ ትገባና “እኔ የሚለው ይሰማኛል፣” ትላለች፡፡ ይሄኔ አጅሬው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እንግዲያው መቶ ብሩን አንቺ ላኪለት፡፡”
ደህና ሰንብቱልኝማ!  


Read 6121 times