Print this page
Sunday, 02 July 2017 00:00

ህገ መንግስቱ ለውይይትና ለድርድር መቅረብ ይችላልን?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በፓርቲዎች ድርድር ኢህአዴግ፤ “ልደራደርባቸውም አልችልም” በሚል ውድቅ ካደረጋቸው አጀንዳዎች አንዱ የህገ መንግስቱ መሻሻል ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ህገ መንግስቱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር መቅረብ የሚችል አይደለም? ኢህአዴግ ለምን ለድርድርና ለውይይት እንዳይቀርብ ፈለገ? ህገ መንግስቱ ሲጸድቅ ተሳትፎ የነበራቸው አንጋፋ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ምሁራን አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ እንደተለመደው አጀንዳው ለውይይት ክፍት ነው፡፡
ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡

                “ህገ መንግስት ለምንድነው ለድርድር የማይቀርበው?”
               ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

      ህገ መንግስቱ ተግባር ላይ ከዋለ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ህገ መንግስቱ በወቅቱ በውይይት ነው የፀደቀው፡፡ በውይይት የፀደቀ ነገር በውይይት የማይሻሻልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት ለሚለው መነሻ ተደርገው ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል ለምሳሌ የፌደራል የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን፤“በአፍሪካ ብዙ ተናጋሪ ካላቸው ቋንቋዎች አንዱ ኦሮሚኛ ነው፤ በኢትዮጵያም ሰፊ ማህበረሰብ ቋንቋውን ተናጋሪ ነው፡፡” የሚሉ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ይሄን ለማስተናገድ እንግዲህ ህገ መንግስቱን ማሻሻል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
በርካታ ቋንቋዎችን ለስራ ቋንቋነት መጠቀም ደግሞ በሌላው አለምም የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ አስራ አንድ የስራ ቋንቋ ነው ያላት፡፡ በኛም ሀገር ይሄ ቢለመድ በግሌ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ የስራ ቋንቋ መጨመር ደግሞ ምንም የጎንዮሽ ጉዳት የለውም፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ በተቃውሞ ወቅት ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ካስፈለገ ህገ መንግስቱ መሻሻሉ የግድ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ በሚፀድቅበት ወቅት ያልታዩ፣ አሁን ግን ቢካተቱ ተብለው የሚቀርቡ ሀሳቦችን ለማካተት ድርድር ቢደረግ ምንድነው ችግሩ? ህገ መንግስቱ ለድርድር መቅረብ አለበት፡፡ የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት ከታሰበ ይሄን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ የትኛውም ህገ መንግስት ዘመን የሚጠይቃቸውንና የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች ለማሟላትና ለየወቅቱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መሻሻል ካለበት፣ ለውይይት ቀርቦ መሻሻል አለበት።
ለምሳሌ ህገ መንግስቱ ለግለሰቦች መብት ያለው ቦታ ትንሽ ነው፡፡ ለብሄርተኝነትና ለብሄር ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥ ህገ መንግስት ነው፡፡ ይሄ ብሄርተኝነት የህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት እየዳበረ ሲሄድ ተቀይሮ፣ ብሄርተኝነቱ እየላላ ሄዶ፣ ግለሰባዊ እሳቤና አንድነታዊ አስተሳሰብ ሊጎለብት ይችላል። ከቡድን መብት ወደ ግለሰብ መብት እየተቀየረ ይሄዳል፡፡ ይሄን ሂደት ለማስተናገድ ህገ መንግስቱ መፈተሽ አለበት፡፡
ሰዎች በውይይትና በድርድር ያፀደቁትን ነገር ለድርድር አይቀርብም ማለት ምን ማለት ነው? ይሄ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በቃ! ህገ መንግስቱ መሻሻል ካለበት ወይም ለውይይት መቅረብ ካለበት፣ መቅረብ አለበት፡፡ ጉዳዩን ዝግ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
ህገ መንግስቱ ከችግር የፀዳ፣ መሻሻል የማይችል ከሆነ፣ ያን መሆኑን የሚታወቀውም ለውይይትና ለድርድር መቅረብ ሲችል ብቻ ነው፡፡ የህገ መንግስቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከዚህ የተሻለ እድልም አይኖርም፡፡
ስለ ትክክለኝነቱ በተለያየ አውድ ከማስረዳት፣ በዚህ መንገድ መፈተሽ የተሻለ መፍትሄ ያመጣል። ከዚህ ውጪ ህገ መንግስቱ ለውይይት ይቅረብ እየተባለ አይቀርብም ማለት፣ “ህገ መንግስቱ ችግር አለበት፤ አዎ እንዳይቀየር የምንፈለገው ነገር አለ” እንደማለት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ለውይይትና ድርድር መቅረቡ በምንም መመዘኛ ችግር ሊሆን አይችልም፤ መቅረብ ይችላል፡፡ ሌሎች ህጎችና አዋጆች ላይ ተደራድሮ ህገ መንግስቱ ላይ አለመደራደር አንደምታው ምንድን ነው? ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡

-----------

                     “በሀገሪቱ የተነሱ ውዝግቦች ከህገ መንግስቱ ጋር የተገናኙ ናቸው”
                   ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛ)

     ህገ መንግስቱ ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች ይነሱበታል፡፡ ዘመንና ጊዜም አዳዲስ ነገሮችን ያመጣል፡፡ በህገ መንግስቱ ተፅፈው ወደ ተግባር ተሟልተው ያልወረዱ ጉዳዮችም አሉ። አዳዲስ አስተሳሰቦችም መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የምርጫ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት መንገድ መኖር እንዳለበትና ሊታሰብበት እንደሚገባ ያቀረብኩት ሃሳብ ነበር፡፡ ይህ ሀሳብ አሁንም ቢጤን መልካም ነው፡፡
በሀገሪቱ የተነሱ ውዝግቦች ህገ መንግስቱን ይመለከታሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በኮንሶ---በሌሎችም የተነሱ ተቃውሞና ግጭቶች ማጠንጠኛቸው ህገ መንግስቱ ላይ ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ቢሆንም አብላጫው ህገ መንግስታዊ ነው፡፡ “ህገ መንግስቱ በትክክል ተግባራዊ አልተደረገም፤ ህገ መንግስቱ እንደገና መታየት አለበት” የሚሉ ሀሳቦች ሁሉ ሲቀርቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ልዩ ጥቅም ጉዳይ፣ እንዲሁም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ጉዳይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በተቃውሞ ወቅት ሲንፀባረቁ የነበሩ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ህገ መንግስቱን በድጋሚ መፈተሹ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ እንዴት ይሻሻል ወይም እንዴት ውይይት ሊደረግበት ይችላል የሚለው በዚያው በህገ መንግስቱ የሰፈረ ጉዳይ ነው፡፡ ማሻሻያ ሀሳቡን ግለሰቦችም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ አካላት የሚቀርቡ የማሻሻያ ሀሳቦች በረቂቅ ደረጃ ከተዘጋጁ በኋላ ለህዝብ ውይይትና ለህዝብ ውሳኔ ይቀርባሉ፡፡ ይሄ ነው ሂደቱ፡፡
ከዚህ በፊት ህገ መንግስቱን ስናፀድቅ ህዝቡ በቀጥታ አልወሰነበትም፡፡ በተወካዮች በኩል ነው የወሰነው፡፡ አሁንም መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የማሻሻያ ረቂቅ ሀሳብ ከተዘጋጀ በኋላ ለህዝብ ውሳኔና ውይይት ነው የሚቀርበው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተናጥላዊ ድርድር ብቻ ህገ መንግስት አይሻሻልም፡፡ ሊወያይበት የሚገባውም ህዝቡ ነው። ህገ መንግስቱ ይሻሻል አይሻሻል የሚለው ሀሳብ በራሱ፣ ለህዝበ ውሳኔ መቅረብ አለበት፡፡

------------

                         “ህገ መንግስቱን ለማሻሻል ህዝቡን ማወያየት ያስፈልጋል”
                         ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ (ፖለቲከኛ)

       በመጀመሪያ እየተደረገ ያለው ድርድር ላይ ኢህአዴግ በቀና መንገድ ገብቶበታል ብዬ አላምንም። “ሀገሪቱን ወደ አለመረጋጋት የከተታት ምንድን ነው?” ተብሎ ተጠንቶ፣ ምክኒያቶቹ ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው መቅረብ ነበረባቸው፡፡ ህገ መንግስቱን በተመለከተም መነጋገር የምንችለው ከዚህ በመነሳት ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ አሁን እየተኬደበት ያለው መንገድ የለብለብ ነው፡፡
ኢህአዴግ በድርድሩ “ይሄን ተቀብያለሁ፣ ያንን አጀንዳ አልተቀበልኩም” ብሎ ሲገልፅ የተቀበላቸው አጀንዳዎች ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አይደለም የተቀበላቸው፡፡ የፀረ ሽብር፣ የፕሬስ ህጎችን… የአፈፃፀም ጉዳይ ብቻ አድርጎ ነው የተመለከታቸው። እንዴት በአፈፃፀም ላይ ድርድር ይደረጋል፡፡ በአፈፃፀም ላይ ተደራድሮ ሀገሪቱን አቅጣጫ ማስያዝ አይቻልም፡፡ ህገ መንግስቱ መሻሻል ካለበት፣ አይነኬ አይደለም መሻሻል ይችላል፡፡ እንዴት ይሻሻላል የሚለው ደግሞ በራሱ በህገ መንግስቱ በግልፅ ተደንግጓል፡፡
ህገ መንግስቱን ለማሻሻል ህዝቡን ማወያየት ያስፈልጋል፡፡ እያወያዩ ሀሳቦችን እያሰባሰቡና ወደ መድረክ እያመጡ፣ ህዝብ በፈለገው መንገድ መኬድ አለበት፡፡ የህገ መንግስት መሻሻል ይቅርና ሀሳብን በነፃነት መግለፅ፣ መደራጀት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ራሱ ቅድሚያ ከህዝቡ ጋር ነፃ  ውይይት መደረግ አለበት፡፡ አስቸኳይ አዋጅ ባለበት ሁኔታ ድርድር ቢደረግም፣ ከህዝቡ ያልመነጨ ድርድር የትም አያደርስም፡፡
በኔ አተያይ የኢትዮጵያ ወቅታዊ አንገብጋቢ ችግር፣ በሀገሪቱ የህግ ልዕልና እየተጣሰ መሆኑ ነው፡፡ በርካታ ህጎችን ህገ መንግስቱ አካቷል፡፡ ግን አሁን ወቅቱ የሚጠይቀው ነገር ካለ፣ ህገ መንግስቱ ተፈትሾ ሊካተት ወይም ሊቀነስ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እንደ‘ኔ ግን ያሉትን የህግ ጥሰቶች ለማስተካከል ጥረት ቢደረግ፣ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ችግር ለመቅረፍ ብዙ ርቀት መሄድ ይቻል ነበር፡፡ ህገ መንግስት ማሻሻል ኋላ ላይ ሊመጣ ይችላል፡፡ የህገ መንግስት ማሻሻያ በአስቸኳይ ካልተደረገ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አይመጣም የሚል እምነት የለኝም፡፡ እምነቴ ህገ መንግስቱ ውስጥ ያሉ መብቶች፣ በትክክለኛ መንገድ ቢተገበሩ ኖሮ፣ ወደዚህ አለመረጋጋት አንገባም ነበር የሚል ነው፡፡

--------------------

                            “ከህዝቡ በስተቀር ማንም ህገ መንግስቱን መንካት አይችልም”
                          ዶ/ር ንጋት አስፋው (ፖለቲከኛ)

      ህገ መንግስቱን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ማቅረቡ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ህገ መንግስት ማለት ህዝብ ያወጣው ህግ ማለት ነው፡፡ የህዝብ ህግ ነው፡፡ በተወካዮች ም/ቤት የፀደቀ ህግ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የፖለቲካ ድርጅቶች በመጠየቃቸው ሳይሆን ህገ መንግስቱ ሊሻሻልባቸው የሚችሉ የራሱ አካሄድ አለው፡፡
ህዝቡ በሚያደርገው ውሳኔ ነው የህገ መንግስቱ ጉዳይ ሊታይ የሚገባው፡፡ ለድርድር ይቅረብ አይቅረብ የሚለውም ቢሆን በህዝበ ውሳኔ (Referendum) የሚወሰን መሆን አለበት፡፡ ሊሻሻልና ሊቀየር የሚችለውም በህዝበ ውሳኔ ነው፡፡ ባለቤቱ ህዝብ ነው፡፡
አንድ ህገ መንግስት፤ የሀገር ህግ ሊሆን የሚችለው፣ ከዳር እስከ ዳር የህዝብ ተወካዮች በሙሉ ያሉበትና በህግ ባለሙያዎች ተቀምሞና ተዘጋጅቶ፣ ህዝቡ በየደረጃው ተወያይቶበት የሚፀድቅ ሲሆን ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ደረጃ ያለውን ስናይ፣ ህግ የሚያወጣው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው። የሚያስፈፅመው መንግስት፣ ተርጓሚው የፍትህ አካላት ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የኔ ጥያቄ፤ አሁን በእርግጥ ትክክለኛ የህዝብ ተወካይ አለን ወይ የሚለው ነው። አለ! ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ሳይሆን የኢህአዴግ አባላት ተወካዮች ነው ያለው፣ የሚል እምነት አለኝ። መቶ በመቶ በዚህ ስርዓት የተያዘ ነው፡፡ ህግ የሚያወጣው፣ የሚያስፈፅመው፣ የሚተረጉመው ራሱ ስርአቱ ነው፡፡ በአንድ ሳንባ የሚተነፍስ የፖለቲካ ስርአት ነው ያለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ይህን ህገ መንግስት ከምልአተ ህዝቡ በስተቀር ማንም ተወካይ ሊነካው አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ከህዝቡ በስተቀር ማንም ሊነካው አይችልም፡፡ የህገ መንግስቱ ባለቤት ህዝቡ ነው፤ ሊነካው ሊያሻሽለው ሊያስተካክለው የሚችለው ባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ ከባለቤቱ ውጪ ማንም አውቅልሃለሁ የሚል ሊነካው አይችልም፡፡ ይህ ህገ መንግስት በአመዛኙ ከፌደራል ስርአቱ ጋር ተጣጥሞ የወጣ ነው፡፡ በዚህ መሃል አንዳንድ ግልፅ ጉድለቶች አሉ፡፡ ያሉትንም ጉድለቶች ቢሆን ማሻሻል የሚችለው ህዝቡ ነው፡፡  

------------------

                         “ህገ መንግስቱ ለውይይትና ድርድር መቅረብ ይችላል”
                         አቶ ገብሩ አስራት (ፖለቲከኛ)

    በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለበት፣ የተቃዋሚ አመራሮችና ግለሰቦች በታሰሩበት የሚደረግ ድርድር እውነተኛ ነው፤ኢህአዴግም በአሁን ወቅት ለድርድር ዝግጁ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግ ሊያሻሽላቸው የሚፈልጋቸውን ነገሮች የፓርቲዎች ይሁንታ አለበት ለማለት እንጂ እውነተኛ ድርድር አይደለም፡፡ አጀንዳ አቀራረፁም ችግር አለበት፡፡ ኢህአዴግ የሚፈልጋቸው ብቻ ናቸው ለድርድሩ የቀረቡት፡፡
የህገ መንግስት ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም ብሎ ዋናውን ጉዳይ ዝግ አድርጎታል፡፡ የህገ መንግስት ጉዳይ ሁኔታው ከፈቀደ ለድርድር ሊቀርብ ይችላል፡፡ ራሱ ኢህአዴግ መጀመሪያ ላይ ወደዚህ ድርድር ሲገባ፣ “ካስፈለገ አንዳንድ የህገ መንግስት ማሻሻያዎችን አደርጋለሁ” ብሎ ነበር፡፡ ታዲያ ይሄ ቃል የት ገባ? ለምሳሌ የፓርላማ ውክልና ጉዳይ መሻሻል እንዳለበት ኢህአዴግ አስታውቆ ነበር፤ ይሄን ለማድረግ የህገ መንግስቱን መሻሻል ይጠይቃል፡፡
የህገ መንግስት ጉዳይ ላይ ከመሄዳችን በፊት ከህገ መንግስቱ በመለስ ያሉ ጉዳዮችን ሳይቀር ኢህአዴግ ሊያነሳቸው የፈለገ አይመስልም፡፡ እኛ ወሳኝ የምንለው የፖለቲካ ምህዳር ጉዳይ ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለበት ደግሞ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አይታሰብም፤ ይሄ ባለበት እንዴት ነው ድርድር ሊካሄድ የሚችለው? “በኢትዮጵያ ምንም የፖለቲካ እስረኞች የሉም” ብሎ ከሚያምን ጋር እንዴት ድርድር ሊካሄድ ይችላል? ከህገ መንግስቱ በፊት እነዚህን ጉዳዮች ኢህአዴግ መቀበል ነበረበት።
ህዝቡ ያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ህገ መንግስቱን ማሻሻል የሚያስፈልጉ ከሆነ፣ ህገ መንግስቱ ለምን አይሻሻልም? ፖለቲከኞች እኮ ህዝቡን ይወክላሉ፡፡ ስለሚወክሉም ነው የህገ መንግስት ድርድር የጠየቄት፡፡ ለምሳሌ አንቀፅ 39፣ የመገንጠል ጉዳይ አለ፡፡ ይሄ ችግር ያለበት አንቀፅ ነው፤ መገንጠል የሚለው አስፈላጊ አይደለም፤ የመገንጠል ጥያቄ የሚለው መሻሻል አለበት፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ይቀድማል፤ ከዚያም በህገ መንግስቱ ላይ መወያየትና መደራደር ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግስቱ ለድርድር መቅረብ ይችላል፡፡ መሬት የመንግስት ነው የሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ በራሱ ተቃውሞ  የሚቀርብበት ነው፡፡
የፖለቲካ ምህዳር ሲጠብ ፅንፈኝነትና ነውጥ ነው እያየለ የሚመጣው፡፡ እነዚህ ከተለወጡ በኋላ ህዝቡ ራሱ በሚፈልገው መንገድ ማሻሻል መለወጥ ይችላል፡፡

Read 2881 times