Sunday, 02 July 2017 00:00

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚደነግገው አዋጅ ለህዝብ ውይይት ሊቀርብ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

 “አዋጁ ለትውልድ የጭቅጭቅ በር የሚከፍት ነው” የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች
                          
       የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ቢሆንም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመፅደቁ በፊት በስፋት ለህዝብ ውይይት እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡
ረቂቅ አዋጁ ጥያቄያችንን ያሟላ አይደለም ያሉት የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ አዋጁ ግልፅነት ይጎድለዋል ሲሉም ተችተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ አባላቱ የተወያዩበት ሲሆን የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩበት ወቅት ረቂቁ መቅረቡ አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ ከአባላቱ ተሰንዝሯል፡፡ የም/ቤቱ አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ለም/ቤቱ አባላት ቅሬታ በሰጡት ምላሽ፤ በረቂቁ ላይ በፍጥነትና በአጭር ጊዜ የመወሰን አካሄድ አይኖርም ብለዋል፡፡
ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ በቀረው የም/ቤቱ የስራ ዘመን ይፀድቃል ተብሎ እንደማይጠበቅም አፈጉባኤው አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት በየደረጃው ላሉ አካላትና ለህዝብ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ይደረግበታል ብሏል እንደሚደረግበት አስታውቋል፡፡
የረቂቅ አዋጁን ይፋ መደረግ ተከትሎ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ ያወጡ ሲሆን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ “አዋጁ በዚህ መልኩ መውጣቱ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ሳይሆን ለትውልድ የጭቅጭቅ በር የሚከፍት ነው” ብሏል፡፡
“ዋናው ጥያቄ አዲስ አበባ የኦሮሞ አካልነቷ ይረጋገጥ፣ የኦሮሚያ አካል ትሁን” የሚል ነው ያሉት የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ አሁን የወጣው ረቂቅ አዋጅ በርካታ ክፍተቶች ያሉበትና ለወደፊት ትውልድን የሚያጨቃጭቅ ነው ብለዋል፡፡
አዳማ፣ ጅማ፣ ነቀምት የመሳሰሉት ከተሞች ውስጥ የኦሮሞ ተወላጆችን ጨምሮ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ ያወሱት አቶ ሙላቱ፤ “አዲስ አበባም የሁሉም ብሄረሰቦች መኖሪያነቷ ተረጋግጦ፣ የኦሮሚያ አካል መሆን ይገባታል” የሚል አቋም ፓርቲያቸው እንደሚያራምድ አስታውቀዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የተጠቀሱ የቋንቋ፣ የትራስፖርት አገልግሎት፣ የውሃ አቅርቦት የመሳሰሉት ጉዳዮች ልዩ ጥቅም ሊባሉ የማይችሉ የመንግስት ግዴታዎች ናቸው ያሉት አቶ ሙላቱ፤ በአዲስ አበባ ላይ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የሚቻለው፣ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ የኦሮሚያ አንድ ከተማ እንድትሆን በማድረግ ነው” ብለዋል - የፓርቲያቸው መሆኑን በመጠቆም፡፡
የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ መሞከሩና ረቂቅ አዋጁ መውጣቱ መልካም መሆኑን የገለፁት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ይሁን እንጂ አዋጁ ጥያቄያችንን በሙሉ የሚመልስ አይደለም ብለዋል፡፡ “አዲስ አበባ በተፈጥሮ አቀማመጧ የኦሮሚያ አካል በመሆኗም ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል ስር እንድትተዳደር ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡
ቋንቋን በተመለከተም የኦሮሚያ ቋንቋ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በፌደራል ደረጃም የስራ ቋንቋ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው በአዋጁ ላይ አርሶ አደሮችን አሳምኖ ለልማት እንዲነሱ ማድረጉ ይቀጥላል መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል - ማንም መፈናቀል የለበትም በማለት፡፡
“የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ ላይ ያለው የፖለቲካ ጥቅምና የሀገር ባለቤትነት ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ልዩ ጥቅም ሊከበር አይችልም፤ ረቂቅ አዋጁም ውሃ የሚቋጥር አይሆንም” የሚሉት ደግሞ የመላ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦዴፓ) ም/ሊቀመንበር አቶ ተከለ አዱኛ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት ሳይሆን ለኦሮሚያ መሆን አለበት ማለት ነው ያሉት ም/ሊቀመንበሩ፤ ከአዲስ አበባ የሚሰበሰብ ታክስና ግብርም ለኦሮሚያ ተጠሪ መሆን አለበት ብለዋል፡፡   ሐሙስ ለፓርላማው ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ረቂቅ አዋጅ በአራት ክፍሎት የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቁ ከተካተቱት መካከል በከተማዋ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ ሙዚየሞች የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ወግ የሚያንፀባርቁ ቅርሶችና መፅሐፎች እንዲሟሉና እንዲኖሩ ይደረጋል፣ በከተማዋ በመንግስት የሚሰራጩ መገናኛ ብዙኃን በአፋን ኦሮሞ ጭምር የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዲኖር ይደረጋል የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩና የኦሮሞ ክልል የጋራ ምክር ቤትም እንደሚቋቋም፤ ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግስቱ እንደሚሆን የሚገልፀውየምክር ቤቱ አላማም “ልዩ ጥቅሞቹ” ተግባራዊ መደረጋቸውን መከታተልና መገምገም ይሆናል ተብሏል፡፡  የምክር ቤቱ አባላትም ከአስተዳደሩና ከክልሉ በኩል በቁጥር ይወከላሉ ይላል - ረቂቅ አዋጁ፡፡

Read 9324 times