Sunday, 02 July 2017 00:00

የሳኡዲ መንግስት የምህረት ጊዜ አዋጁን ለአንድ ወር አራዘመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 “ህገ ወጦች በ90 ቀን ውስጥ ከሀገሬ ውጡልኝ” ሲል የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ ለተጨማሪ አንድ ወር ማራዘሙ ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሳውዲ መንግስት ቀነ ገደቡ እንዲራዘም የሚጠይቅ የተማፅኖ ደብዳቤ መፃፋቸው የተገለፀ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ቀነ ገደቡ በሚራዘምበት ጉዳይ ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ሲያካሂዱ እንደነበር ታውቋል፡፡
ቀነ ገደቡ የተራዘመው በ90 ቀናቱ በተለያዩ ምክንያቶች መውጣት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ተረጋግተው እንዲወጡ በማሰብ መሆኑን የሳኡዲ የፓስፖርት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል መግለፁ ታውቋል፡፡ ቀኑ ታሳቢ የሚደረገውም ከእሁድ ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
እስከ ትናንት ድረስ 111ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ሲሆን ከ46 ሺህ በላይ ደግሞ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አቶ መለስ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከሳውዲ የማስወጣት ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል” ያሉት አቶ መለስ፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድም ትርፍ በማያገኝበት ሁኔታ ራሱን ለኪሳራ አጋልጦ ዜጎቹን እያመላለሰ ነው” ብለዋል፡፡  

Read 3700 times