Sunday, 25 June 2017 00:00

የተስፋ ብልጭታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ክፍል 3

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልን አስመልክቶ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያቀረብናቸው ዘገባዎች ነበሩ፡፡  በክፍል 1 የስፖርት መሰረተ ልማቱብ የግንባታ ሂደቶች በመጠኑ የዳሰስን ሲሆን በክፍል ሁለት ደግሞ የማሰልጠኛ ማዕከሉን ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶች፤ የአሰልጣኞችን የሙያ እና የብቃት ደረጃ  የሰልጣኞች ምልመላ እና ተያያዥ ሁኔታዎችን  ከመመልከት ባሻገር፤   የማሰልጠኛ ማዕከሉን ፍሬያማነት ፤ የሰልጣኞችን ተስፋና የአሰልጣኞችን የብቃት ደረጃን ማሻሻል አንስተን ነበር፡፡ በክፍል 3  ላይ የማዕከሉን አሳሳቢ ችግሮች በተወሰነ ደረጃ በማንሳት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ   የወደፊት አቅጣጫዎችን  በመጠቃቀስ  አቅርበናል፡፡
ማዕከሉን የሚያሳስቡ ዋና ዋና  ችግሮች
 የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ከከተማ ወጣ እና ራቅ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡ በማዕከሉ    ያለው የትራንስፖርት አገልግሎቱ ደካማ  ነው፡፡ ሰልጣኞች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች ሰራተኞች ወደ መስክ የልምምድ ስራዎች፤ ወደ ትምህርት ቤት እና ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓጓዙት 1 ሚኒባስ እና አውቶብስ ብቻ ናቸው፡፡ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችል ነው፡፡በአገር ውስጥ መኪኖችን የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች  በልዩ የስፖንሰርሺፕ ሁኔታ በመተሳሰር ችግሩን በቶሎ ለመፍታት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ማዕከሉ ለሰልጣኞች የትጥቅ አቅርቦቱን ለማሟላት አለመቻሉን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ምናልባት ይህ ችግር ከበጀት እጥረት ጋር ሊያያዝ ቢችልም የሰልጣኞቹን ተነሳሽነት፤ የልምምድ እና ሌሎች ሁኔታዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በመፍጠር መቀጠል የለበትም፡፡ ምናልባትም  በተመሳሳይ የማሰልጠኛ ማዕከሎች ያሉ አሰራሮችን ማጥናት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ያሉ ተመክሮዎችን ብንመለከት የትጥቅ አቅርቦት ችግሩን በቀላሉ ለመቀየር እንደሚቻል መረዳት አይሳንም ፡፡  በነገራችን ላይ ማዕከሉ ከምንም አይነት የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር የመሰረተው ግንኙነት ወይም የሚሰራበት አቅጣጫ አለመያዙን በጥናት ልዩ እቅድ አውጥቶ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ የትጥቅ አቅርቦቱን ከመንግስት በሚያገኘው ድጋፍ ይዞ መቀጠሉ ለወደፊቱ የማያዋጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የትጥቅ አቅርቦቶቹን በማሟላት ረገድ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጭዎች ጋር በአጋርነት የሚሰራበትን አቅጣጫ በመፍጠር ካልሆነም ከዓለም አቀፍ የትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ጋር ስፖንሰርሺፕ ውሎችን በመስራት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡
ከመሰረተ ልማቶቹ ጋር በተያያዘ መጠቀስ ያለባቸው አንዳንድ አሳሳቢ ችግሮችም አሉ፡፡ የመጀመርያው  በተለይ ለሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚሆኑ የመነሻ ሳንቃዎች፤ ፍራሾች ዱላዎች፤ የመሰናክል አግዳሚዎች በትራኩ ላይ አለመተከላቸው ነው፡፡ ይህ ችግር የገጠመው አስፈላጊ  ግዢዎች የተፈፀሙ ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያለው ሂደት ጊዜ ስለሚወስድ  ነው ተብሏል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የማዕከሉ የቤት ውስጥ ግዙፍ ጅምናዚዬም በከፍተኛ ደረጃ ዘመናዊ በሆኑ  የስፖርት ቁሶች እየተሟላ ቢሆንም አጠቃላይ ርክክቡ ባለመጠናቀቁ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሊጀምር አልቻለም፡፡ ይህም በማዕከሉ የሚከናወኑ ስልጠናዎችን እንዲቋረጡ ባያደርግም ሊያፋጥናቸው ግን አልቻለም፡፡
ማዕከሉን ወደ የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ የወደፊት አቅጣጫዎች
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች አትሌት እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በስሟ የተከፈተው የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልም እንደሷ የላቀ፣ ከፍ ያለ ውጤት የሚያስመዘግብ መሆን ይኖርበታል፡፡ በእኔ እምነት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከረጅም ርቀት ሩጫ ባሻገር በማሰልጠኛ ማዕከሎች፤ በአካዳሚዎች፤ ደረጃቸውን ጠብቀው በተደራጁ ክለቦች በመስራት ረገድ ያልተነካ አቅም አለው፡፡ ይህን አቅም በፈርቀዳጅነት እየሰራበት የሚገኘው የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊደገፍ ይገባል፡፡  ማዕከሉ የብዙ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ህልም መሆን አለበት፡፡ ስፖርተኛነት ፕሮፌሽናል ሙያ መሆኑ እንዲታወቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም በማዕከሉ ራዕይ ዙሪያ ነባርና ታዋቂ አትሌቶች ባለድርሻ አካላት ሆነው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት ማዕሉን ወደላቀ ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ የወደፊት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
በረጅም ርቀት ለመስራት
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በአጭርና መካከከለኛ ርቀት እንዲሁም በተለያዩ የሜዳ ላይ ስፖርቶች ስኬታማ ቢሆንም ለሌሎች ስፖርቶችም በሩን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በምትታወቅበት የረጅም ርቀት፤ የአገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይሩጫ እንዲሁም የማራቶን ውድድሮች ለመስራት ማተኮር ይገባል፡፡ በርግጥ አሁን ማዕከሉ እየሰራባቸው ያሉት የስፖርት መደቦች በየአራት ዓመቱ ብቁ አትሌቶችን ለማፍራት የሚቻልባቸው በመሆናቸው ተመራጭ ተደርገዋል፡፡ በረጅም ርቀት ለመስራት ደግሞ ሰልጣኞችን ከ8 እስከ 10 ዓመት በማዕከሉ ማቆየት ግድ ይላል፡፡
ሰልጣኞችን በዝውውር ክፍያ መልቀቅ
በማዕከሉ በተለያዩ የስልጠና ደረጃዎች የሚገኙ ሰልጣኞች ተፈላጊነት ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከማዕከሉ 4 ዓመታትን ተምረው የሚመረቁ ሰልጣኞችን ብቻ ሳይሆን   ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዓመት ላይ የሚገኙ ሰልጣኞችም ለማዘዋወርና ለመቅጠር የሚፈልጉ ክለቦችና ቡድኖች የበዙ ሲሆን እንውሰዳቸው ልቀቁልን በማለት ማመልከቻ ያስገቡ ጥቂት አይደሉም፡፡
ይሁንና ማዕከሉ በየጊዜው በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ሰልጣኞቹን የሚለቅበት አሰራር ብዙ ክፍተቶች ይስተዋሉበታል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ሰልጥነው የተመረቁት ሆነ በሂደት ላይ የሚገኙ ሰልጣኞችን  ለመልቀቅ ምንም አይነት የዝውውር ክፍያ አለመጠየቁ አሳሳቢ ሂደት ሊሆን ይችላል፡፡   ማዕከሉ ወጭ አውጥቶ፤ ብዙ የደከመባቸውን ሰልጣኞቹን በተለያዩ ጊዜያት በሚቀርቡ የቅጥር ማመልከቻዎች እየለቀቀ የሚሰራበትን አቅጣጫ በጊዜያዊነት እየሰራበት የሚገኘው በዓላማው እንደተቀመጠው ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ሰልጣኞቹ በተለያዩ ክለቦች ተቀጥረው ደሞዝተኛ መሆናቸው፤ የውድድር እድል ማግኘታቸው እና ውጤታማ መሆናቸው ለአገሪቱ አትሌቲክስ እድገት ወሳኝ መሆኑን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡
በርግጥ ማዕከሉ ለእነዚህ ሰልጣኞች ከምልመላው አንስቶ በ1ኛ፤2ኛ ፤ 3ኛ እና አራተኛ ዓመት ደረጃ በሚያልፉባቸው የስልጠና ሂደቶች ብዙ ወጭ እንደሚያወጣባቸው መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ወደፊት የዝውውር ክፍያ የሚጠይቅበትን ህጋዊ ደንብና መመርያ በመከተል እንዲንቀሳቀስ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ምናልባት ወደፊት አስፈላጊው መመርያ እና ደንብ ወጥቶ ከማሰልጠኛው ስፖርተኞችን የሚወስዱ ክለቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የማዕከሉን ቀጣይ አቅም የሚያሳድጉ ክፍያዎችን በተመጣጣኝ ሁኔታ የሚከፍሉ ከሆነ የማዕከሉን የገቢ ምንጭ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ ማሰልጠኛ ማዕከሉ እስካሁን በሚከተለው አሰራር ሰልጣኞቹን ለሌሎች ክለብ ሲለቅቅ በየስፖርት መደባቸው ያሏቸውን የስልጠና ታሪኮች እና ተያያዥ አሃዛዊ መረጃዎች በትራንስክሪፕት መልክ አዘጋጅቶ በመስጠት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በየዓመቱም የማሰልጠኛው ማዕከል ሰራተኞች ወደ ተለያዩ ክለቦች እተዘዋወሩ አትሌቶችን በመጎብኘት ያሉበትን ደረጃ ይገመግማሉ፡፡ በተሻሻሉት ላይ ማበረታቻ ይሰጣሉ፤ ለውጥ በማያሳዩት ላይ ደግሞ በየክለባቸው የሚሰራው ስራ እንዲጠናከር ይመክራሉ፡፡ በማዕከሉ ያገኙትን የስልጠና ስኬት በየክለባቸው እያሻሻሉ መቀጠል ስላለባቸው ነው፡፡
ለብሄራዊ ቡድኖች ካምፕ ቢሆንስ…
በሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለዓለም አቀፍ ውድድር ብሄራዊ ቡድኖች የሚኖራቸውን ዝግጅት ከከተማ ውጭ የማድረግ  እቅድ ነበረው፡፡ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ለብሄራዊ ቡድኖች የካምፕ ዝግጅት ዋናው እጩ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገለፀ ቢቆይም በዚህ አቅጣጫ የሚያበረታቱ ጅምሮች የሉም፡፡ በባለድርሻ አካላት መካከል መዋቅር ተዘርግቶ ማዕከሉ የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድኖች ለሚያደርጓቸው ዝግጅቶች ተመራጭ ቢሆን የሚያስደስት ውሳኔ  ይሆናል፡፡   የማዕከሉ የስፖርት መሰረተልማቶችና የአካባቢው አየር ንብረት  ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሚደረጉ ዝግጅቶች ብቁና የሚመጥን ነው፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ በተለይ ለዓለም ሻምፒዮና በማዕከሉ በመክተም ቢዘጋጅ የአትሌቶችን ወቅታዊ ብቃት ጠብቆ ወደ ውድድር ለማቅናት የሚረዳ እና  ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድር ሲዘጋጁ በአንድ ማዕከል ተሰባስበው መስራታቸው የሚያስገኘው የቡድን ህብረት እና ዲስፕሊን ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ በከተማ አካባቢ የተበከለ አየር ንብረት የዝግጅት አቅማቸው እንዳይቃወስ የሚያግዝ መሆኑ ፤ በቂ የማገገሚያ እና የእረፍት ጊዜ እንዲኖራቸው ማስቻሉን ከግምት በማስገባት የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በፍጥነት መወሰን ይኖርበታል፡፡
ሌሎች….
ማዕከሉ በስፖርት ትጥቅ የተሟላ አቅም እንዲኖረው የታላላቅ አትሌቶች ሁለገብ ተፅዕኖ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ታላላቅ አትሌቶች የስልጠናው አካል የሚሆኑበት መዋቅር መዘርጋት አለበት፡፡ በየጊዜው ከሰልጣኝ አትሌቶች ጋር እየተገናኙ የሚወያዩበት መድረክ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል የማዕከሉ አሰልጣኞች የብቃት ደረጃ ለማሻሻል ዓለም አቀፋዊ  ግንኙነቶች መጠናከርም አለባቸው፡፡ አሰልጣኞች የዓለም አትሌቲክስ ወቅታዊ እውቀትን ሊያገኙ የሚችሉበት መዋቅርም መዘርጋት ይኖርበታል፡፡
በሰልጣኞች የፕሮፌሽናልነት  ደረጃ ዙሪያም ብዙ ተግባራት መከወን አለባቸው፡፡ ከማዕከሉ ተመርቀው ስኬታማ የሚሆኑ ስፖርተኞች ስላገኙት ስልጠና የሚመሰክሩበት አንደበት ሊኖራቸው ተገቢ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ሚዲያ የሚሆን የኮሚኒኬሽን ተሰጥኦ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በማዕከሉ ልዩ ሙዚየምና የመረጃ ማዕከልም ቢኖርም ጥሩ ነው፡፡ ሙዚየሙ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ታሪክ የዓለም አትሌቶችን በፎቶ በቪዲዮ እና በህትመት የሚያቀርብ ሊሆን ይችላል፡፡
የስፖርት መሰረተልማቱን ከማስፋፋት አኳያ መያዝ ያለባቸው የወደፊት አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ600 በላይ ሰልጣኞች የማስተናገድ አቅም ያለው ማዕከሉ የማደርያ ካምፑ ሊስፋፋ ከቻለ የሰልጣኞችን ቁጥር እስከ 1200 ድረስ ማሳደግ ይቻላል፡፡

Read 1452 times