Sunday, 25 June 2017 00:00

የደራሲያን ድፍርስ ወንዞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 ሰው በየትኛውም መንገድ ራሱን መግለጥ መቻል አለበት ይላሉ፣ ትምህርት ለምን እንዳስፈለገ የፃፉ ደራሲ ‹‹ኮሌጅ መምጣት ለምን አስፈለገ? …ቢያንስ ራስን በንግግርና በጽሁፍ መግለፅ ለመቻል ነው፤›› በማለት ማሳመኛ ነጥቦች ያነሳሉ፡፡ ታዲያ መግለጥ ሲባል ስሜትን ሳይሆን፣ ወግ ባለው ሁኔታና በተቀናጀና በተደራጀ መልክ ነው፡፡ ይህ መልክ ደግሞ ውበትም ነው፡፡ ንዝረትም ነው፡፡
ከጀርባው ደግሞ ጥበብ አለ፡፡ ኪነ ጥበብ የምንለው ውበትና ኃይልም ከዚሁ ጋር የተዛመደ፣ ግን ደግሞ ሌላ መንትያ ነው፡፡ ለምሳሌ ገጣሚ ግጥም ሲፅፍ አንዳች ኃይል ውስጡ አለ፡፡ ውስጡ ያለው ነገር ደግሞ እንደ ሽንኩርት ገላ የተደራረበ ሊሆን ይችላል፡፡ ታላቁ ገጣሚና መምህር ሮበርት ፍሮስት እንደሚል፤ “The poet pretends to be talking about one thing and all the while he is talking about many others.”
ሶመርሴት እነዚህን የተጣመሩ ሰዋዊ ተሰጥዖዎችን ሲያስረዳ፤ “የሁሉም ሰውና የሁሉም ደራሲ ችግር ብዙም የሚለያይ አይደለም፤ እነዚህም ራስን መሆን መቻልና ራስን ያለመሆን እንዲሁም ያለመማር ናቸው።›› ብሏል፡፡
ደራሲው፣ ገጣሚው ወይም ፀሐፌ ተውኔቱ የየራሱ ልምድ፣ ይትበሃልና የምናብ ኃይል አለው። አንዱ ከአንዱ ይለያል፤ አንዱ ከአንዱ ይርቃል፡፡ ጠቢቡ እንዳለው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው በክብር ይልቃል! … ለዚህም ይመስለኛል አንድ የቆየ ደራሲና ኃያሲ ከህይወት ለተለየው እንዲህ ሲል የፃፈው፡፡ ‹‹ድርሰትን ማድቅና መመዘን የየግል ነው፣ ሌላ እንደ አንተ ፅሁፉን የምናነብለት ደራሲ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን ማንም በማንም አይተካም፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር አይነፃፀርም። … ብዙ ደስታና እርካታ እንደሰጠኸንም እናስባለን” ይላል ከሞላ ጎደል፡፡ ይለያያሉ ማለት ነው፣ በአተያይ፣ በአፃፃፍ ይትበሃል፣ በሥነ-ልቡናዊ ቅኝትም፡፡
ዞሮ - ዞሮ በዐሉ ግርማ ሌላ ነው፣ ሀዲስ አለማየሁም ሌላ እንደማለት ነው፡፡ አንዱ ውስጥ ያለው ሌላኛው ውስጥ ላይኖር ይችላል፡፡ የአንባቢ ምርጫ ደግሞ የተለያየ ነው፡፡ ጣዕሙና ፍቅሩ ለየቅል ነው፡፡
ወደ ገጣሚያኑ ስንመጣ፣ የፀጋዬ ገብረመድህን የቃላት ውበትና የጥበብ ሹሩባ የሚጥመውን ያህል የገብረክርስቶስ ዜማ ነፍሱን የሚነቀንቀው አለ፡፡ የደበበ ሰይፉን ከፀጋዬ፣ የፀጋዬን ከገብረክርስቶስ አንድ የሚያደርጋቸው የለም፡፡ አንባቢዎችም እንደዚያው ይለያያሉ፡፡
በማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወትም ይለያያሉ፤ ደበበ ሰይፉ አብዮት አጓጉቶት፣ የጭቁት ህዝብ ተስፋ ነው ብሎ ስላመነ፤ ከአብዮቱ ጋር በፍቅር እፍፍ ብሎ ከንፏል፡፡ ምክንያቱም ሲጀመር የትኛውም አብዮት የጭቁን ህዝብ አጋር የሆኑ ከያንያንን ያባብላል፡፡ ያጓጓል፡፡
ፀጋዬ ደግሞ በወንዞች፣ በተራሮችና በተፈጥሮ ፍቅር ወድቋል፡፡ በታሪክ ጉጉት ማልሏል፡፡ ገብረክስርቶስ ደግሞ ዝንቅ ነው፡፡ በፍቅር ዓለም ይዋትታል፡፡ ይስቃል፤ ያለቅሳል፡፡ ያኔ ዐለም አብራው ትስቃለች ጎበዝ አቅሙ ይርዳል፤ ነፍሱ ትበንናለች፡፡
የሰፈር አኗኗራቸውም ይለያያል፡፡ ጋሽ ስብሀት ታች ወርዶ ይኖራል ከደሀው ጋር ተረት ሰፈር፣ እሪ በከንቱ እያለ ይዋትታል፡፡ በዐሉ ግርማ ደግሞ በመኳንንት ሰፈር ወዲያ ወዲህ ይላል፡፡ ግን ደግሞ ልቡ ታች ትውላለች፡፡ … ከቢሮ የሚያወጣው የጥበብ ንፋስ ይወስደዋል፡፡ ከያኔ እንዲያ ነው፡፡
እንደ ዩዶራ ዌልቲ! ቶዶራ ዌልቲ የተመሰጠች ደራሲ ናት፡፡ ያገሯን ጉዳይ የህዝብዋን ኑሮ ትፅፋለች። ሰፈርዋ ደግሞ አበባ ትወዳለች፣ አበባ ታሳምራለች፡፡ ለሰፈሯ ማህበራዊ ህይወት ያን ያህል ታታሪ አይደለችም፡፡ እንዲህ ነው ከያኒና ህይወቱ፤ እንደ ቶልስቶይ በድሆች ሰፈር ጉድ ጉድ የሚሉ ሞልተዋል፡፡ እንደ ሔሜንጌዌይ የአሳ አጥማጅ ህይወት ውስጣቸው ገብቶ የሚኮረኩራቸውና የኪነት ችቦ የሚለበልባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሌዎኖራ ስፔየር እንደሚሉት የተወለዱበት ደም የተነካካ ነው፤ የተለከፈ ነው፡፡ እረፍት የማይሰጥ ነው፤ የሚያሳድድ ነው፡፡ እንደቱርጌኔቭ ሀገር የሚያስናፍቅ፣ ያገር አፈርን አፍንጫ ስር የሚያመጣ በሽታ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ነው፡፡
ደብልዩ ኤች ኦደን ደግሞ የደራሲው አካባቢ፣ ማህበረሰብ፣ እምነትና ባህል ደራሲው ስራ ላይ ጥላ ይጥላል፡፡ ያደገበት አካባቢና መልክ በጽሑፉ ውስጥ ብቅ ይላል ይላሉ፡፡ የጋሽ ስብሀት ማሚት እሹሩሩ፤ የበዓሉ ግርማ፣ ሉሊት፣ የዳኛቸው ወርቁ ፂዮኔ ከዚያው ከነበሩበት አካባ ጋር የተቆራኘ ነው። የዳኛቸው ወርቁን አደፍርስ በሂስዊ ቅኝቱ የቃኘው ብርሃኑ ዘርይሁን ያለው ይህንኑ ነው፡፡ የአደፍርስን መቸት እንዲያ አድርጎ ውስጡን ቆፍሮ ለመተረክ፣ አድባራቱን ለመቃኘት፣ ዳኛቸው ወርቁ ብቻ ትክክለኛ ሰው ነው፡፡፡ ከላይ የጠቀስኳት እንስት ደራሲ ዩዶራ ዌልቲ እንዳለችው፤ “ድርሰት ከአካባቢ ይወለዳል፡፡
ባለፉት ዓመታት ተወዳጅ የነበረው  ደረጀ በቀለ “ህያው ፍቅር” ረጅም ልቦለድም እንዲሁ አካባቢን ያጠቀሰ እንደነበር በቅርቡ ከኔ ጋር በናሁ ቴሌቪዥን ባደረገው ቃለ ምልልስ አረጋግጦልኛል፡፡ ፍል ውሃ አካባቢ ስላደገ፣ ያንን ህይወት ያውቀዋል። ውስጡም ላይ አድጓል፡፡ ስለዚህ እነ ‹‹ናፖሊዮን›› ቁጭ አደረጋቸው በጥበብና ፈጠራ ሞሽሮ አስነበበን፤ ከያኒና አካባቢ፣ እንደ አድማስ ናቸው፣ የተቆራኙም፣ የተለያዩ፡፡ በምናብ አንዳንዴ የሚራራቁ፣ በህይወት የተሳሳሙ፡፡
አንዳንዶቻችን አይ አይ ራቢ እንደሚሉት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ዓይነት ነን፡፡ እርሳቸው እንዲህ ነው የሚሉት፤ “We are like the city boy who likes milk but is afraid of cows.” ወተት ሲወድድ ነፍሱ ይወጣል፤ ግን ደሞ ላሚቷን እንደ ጅብ ይፈራታል፡፡
የከያኒ (ደራሲ) መሳሪያ ቃላት ናቸው፡፡ የሳይንቲስቱ መሳሪያ fact/እውነታ እንደሆነ ሁሉ፡፡
ታዲያ ስነጽሑፉም አንዳንዴ እንደ ሳይንሱ አሮጌው አዲሱን በቀላሉ አይቀበልም፡፡ አዲሱን የወይን ጠጅ አሮጌ አቁማዳ አይችለውም፡፡ ይፈነዳልና! ይሁን እንጂ አዲሱ አሮጌውን ወይም የቀደመውን እያሸነፈ መሄድ ግድ ነው፡፡ በእኛ ሀገርም የሆነው እንዲህ ነው፡፡ ሀዲስ አለማየሁና ዳኛቸው ወርቁን የመሳሰሉ ደራሲያን ይዘው የመጡት ሥነ-ጽሑፍ በአሮጌው ሥነ ጽሑፍ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሣድሮ በአዲስ መንገድ ቀጠለ፡፡
በሳይንስ ዐለም የዚህ ዐይነት ተከታታይነት ያለው የሳይንስ ግሥጋሴ ይዞ መጥቷል የሚባለው የጋሊሊዮ ሣይንሳዊ ግኝት ብቃት ነው፡፡ ‹‹Gallis the progress of science has conttined with out a breaki›› ይላሉ ራቢ፡፡ የሚገርመው ግን በተመቻቸ ሁኔታ አልነበረም የቀጠለው፡፡ አብዮቶች፣ ጦርነቶች በርካታ ውዝግቦች ነበሩ፤ ግን እሣቱ ከተለኮሰ በኋላ ብርሃኑ መሥፋቱ አልቀረም፤ እንዲያውም ሊቃውንቱ እንደሚሉት፤ ትልልቅ ፈተናዎች ባሉበት ዘመን፣ ትልልቅ የፈጠራ ሥራዎች ብቅ ይላሉ፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ትልልቅ ሁነቶች በተመሳሳይ ክፍለ ዘመን ይፈፀማሉ፤ ለዚህም እንደ ዋቢ የሚጠቅሱት የዊልያም ሼክስፒርን ሞት ተከትሎ በግማሽ ምዕተ አመት ውስጥ፤ የአይዛክ ኒውተን ታላቅ ሣይንሳዊ ግኝት ብቅ ማለቱን ነው፤ በዚያም ብቻ አያበቃም፤ በአጠቃላይ
የእንግሊዝ ሳይንሳዊ ግሰጋሴም የፈጠነው በአንደኛው የዓለም ጦርነትና በጄኔራል ናፖሊዮን የጦርነት ግለት መካከል ነበር፡፡ ታዲያ የተፋፋመ የጦርነት ጊዜ የሀገሪቱ ወርቃማ የስነ ግጥም ዘመን ነበር፡፡ It was also a period of great poetry›› ይላሉ፡፡
በተመሳሳይ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ግዙፉ የአሜሪካ ምሁር ፖለቲከኛና ዲፕሎማት ቤንጃሚን ፍራንሊን ዘመንም እንደዚሁ የጥበብና የሳይንስ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም፣ ሳይንስና ጥበብም እንደ ሰደድ እሳት ድንበር እየተሻገሩ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። የጀርመን ሳይንስ ከፈረንሳይ፤ የፈረንሳይ  ከሩሲያ አይራራቁም ፤ባዕድም አይሆኑም፡፡ ስነ ግጥሙና ሌላው ስነጽሑፍም እንደዚሁ ነው፡፡ ሶኔት ጣሊያን ተወልዶ የእንግሊዝ ባለቅኔዎች ዘውድ እንደጫኑበት ሁሉ ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡ የጊዜው ፍልስፍናና ስነ-ልቡናም በተለይ በከተሞች ለመወራረስ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በፕሬሶች በመጻሕፍትና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች አድማስ አሣብረው ይዘልቃሉ። ክሊፍተን ፋዲማን የተባሉት ፀሀፊ ደግሞ ከላይ የጠቃቀስኩትን ሀሳብ አድምቀው ያሠምሩበታል። ‹‹The greatest books rise from a profound level of wonder and terror›› በማለት እንግዲህ ሀገር ብቻ አይደለችም፤ ደራሲ/ከያኒ በሚፅፉበት ጊዜ ደስተኛ ነበር የተሣካላት፡፡ ማለት አይቻልም፡፡ በደበረው ሰዐት ሊፅፍ ይችላል፡፡ እንደ ኤድጋር አለን በዕዳ ተዘፍቆ ሊፅፍ ይችላል፡፡ ከሚስቱ ተኳርፎ ወዘተ
እንግዲህ ከሞላ ጎደል የደራሲዎች ህይወት፤ ኑሮና አካባቢ እንደጉሽ ጠላ ድፍርስ ነው፡፡…. እየተጠነቀቁ የሚጠጡት!... ይህንንም አደባባይ፣ ይህንንም የገፆች ላይ ሥዕል ለማግኘት መሠላሉን ሲወጡ በመሠቀቅ፤ በጥረትና በትጋት ነው፡፡ ማንበብ ማጥናት፣…ተሰጥዖን ለመኳል መውጣት መውረድም አለ፡፡
ስለዚህ ደራስያን ይህንን ስንቅ ይዘው ይወጣሉ፤ እንቅፋቶችም አያቆሟቸውም! .. ዕጣ ክፍላቸውን ያገኛሉ፡፡ ተሰጥዖዋቸውን እንደሰንደቅ አደባባይ ላይ ይሠቅላሉ፡፡
‹‹እንቅልፍና ህልም›› የሚለው የዮናስ ኪዳኔ ግጥም ለዚህ የልብ አድራሻ ነው እንዲህ ይላል፡-
ከእንቅፋቶች በስቲያ ጉዞ እንድትቀጥሉ
ከግር ከፍ አርጋችሁ ህልማችሁን ስቀሉ
ወድቆም፤ ተንገዳግዶም
ደግሞ መራመድ ነው፤ በቀንም በማታ
ድንጋይ እግር እንጂ ራእይን አይመታ!

Read 1951 times