Sunday, 25 June 2017 00:00

ዘቢባ አሊባባ

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(4 votes)

  ከእልህ አስጨራሽ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ በኋላ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዴን የምቀበልበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ። ጉዳዬ ወደተመራበት ቢሮ በተስፋ ጢም ብዬ ገባሁ፡፡
ፍፁም ያልጠበኩት ምላሽ ነበር የጠበቀኝ----
“--አንዳንድ መረጃዎችህ የህጋዊነት ክፍተት ይታይባቸዋል---ማጣራት የሚገባን ጉዳይ ስላለ--”
 “መቼ ነው ተጠርቶ ጉዳዬ እልባት የሚያገኘው» ግልፍ ብዬ ጠየኩት፡፡
 “ሳምንት ምናልባትም ከወር በኋላ---”
የዳተኛው ቢሮክራት ምላሽ ቅስሜን ሰብሮት ከቢሮ ወጣሁ---
-- በአይን የማውቀውን ደላላ አገኘሁት፣ ፒያሳ ጊዮርጊስ  ለመሃላ፤ አይጠፋም፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጠኝ፤ “ምን እግር ጣለህ?» ሲልም ጠየቀኝ ፡፡
የገጠመኝን ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ አጫወትኩት ---- “ቀላል ነው በዛሬው እለት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድህን ትቀበላለህ --- ጉዳዩ  የሚመለከተው ሰውዬ በእጄ ነው----”
በግርምት አስተዋልኩት፤ምን ማለት ነበረብኝ---- ምንስ ይባላል---ደላላው ቀጠለ---
“ከአንተ የሚጠበቀው ተገቢውን ክፍያ መግፋት ብቻ ነው ----”  
 “ተገቢው ክፍያ” የተባለውን የገንዘብ መጠን ጠየኩት፣ቅስም ይሰብራል፤ግን ምን አማራጭ አለኝ? ምንም!
ስሜን --- ዝርዝር መረጃዎችን መዘገበ፤ ለሰውዬው ደወለለት፤ ስልኩን ዘግቶ---
“አድለኛ ነህ፤ ጉዳይህ በሰዓታት ጊዜ ውሰጥ ያልቅልሀል” አለኝ፡፡ ባለማመን በጥርጣሬ አፈጠጥኩበት፡፡ ደላላው ፊቴን አንብቦ----
“የጉዳዩ መፍጠን ጥርጣሬ ውስጥ ሊከትህ ይችላል --- የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድህ በእጅህ ሲገባ ነው፤ ክፍያውን የምትፈፅመው እናም መተማመን ይበጀናል----» ሲል አረጋጋኝ ----
-- ወጣ ብዬ ከባንክ 5,000 ብር አወጣሁ፤ መጠንቀቅ ደግ ነው፤ ያልጠረጠረ ተመነጠረ። የደላላውን እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል አለብኝ፤ በመሀል መቅለጥ አለ --- ወደ መ/ቤቱ ክበብ ገባሁ፡፡ ደላላው ቡና እየጠጣ ጥግ ላይ ተሰይሟል። ገንዘቡን መያዜን ነገርኩት፤ ዲሽ መሳይ ጆሮዎቹ እንደመርገብገብ  አደረጋቸው ልበል--- ቡና የምታፈላውን ሴትዮ ጠራት፤ መጣጣ ከአፍ የወደቀች ጥሬ። ረዥም ታኮ ጫማ አድርጋ፣ ታንክ የምትነዳ ትመስላለች፡፡
“ምን ልታዘዝ?» አለችኝ ----
ዝም አልኩ፤ ደላላው ቀልጠፍ ብሎ “ቡና ይምጣልህ» አለኝ፤ መጠርጠር ደግ ነው፤ የጥቅም ተካፋዩ ልትሆን ትችላለች፤ ቡናው ላይ አፍዝ አደንግዝ ነገር ጠብ! በማድረግ፡፡ --- ቡናውን ጠጥቼ ሰመመን ውስጥ ስገባ አጅሬ ደላላ 5,000 ብሩን ይዞ እብስ! ---- ሴትየዋ ፊት ብነሳትም ንቅንቅ አላለችም፤ የአላማ ጉዳይ ነዋ!
“ምንም ነገር አልፈልግም---» አልኳት፣ ፊቴን ገደል አስመስዬ፡፡ ቀንዷን እንደተመታች ላም መለስ!  አለች፡፡
“--- ሁሉም ነገር ተጠናቆ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድህ ዝግጁ እንደሆነ በስልኬ መልእክት ልኮልኛል፤ ወደ ቢሮው ጎራ ብለህ ትቀበለዋለህ ግን---» ብሎ ንግግሩን ቆም አደረገና ለጥቆም፤
“እኔ እንደላኩህ እርግጠኛ እንዲሆን መግባቢያ ኮድ አለን-- የይለፍ ቃል! ልብ ብለህ አድምጠኝ --- አንተ እንደ ኬክ በወረቀት የተጠቀለለ የብሩን እሽግ እያሳየኸው  ‹ዘቢብ ኬክ ይዣለሁ› ትለዋለህ--- ሰውየውም  ‹ዘቢብ ኬክ እወዳለሁ፤ የሚስቴ ስም ዘቢባ አሊባባ ነው› ብሎ ሰነዱን ይሰጥሀል፤ አንተም ገንዘቡን--- እጅ በእጅ፤ ግልጽ ነው»  
“እንከን አልባ» ስል መለስኩለት---
“---እንከንማ አለበት፤ ከይለፍ ቃሉ ጋር እንዲስማማ ገንዘቡ እንደ ኬክ መታሸግ አለበት» ብሎ ቢጫ ወረቀትና ፕላስተር ሰጠኝ፡፡ 5,000 ብሩን ጠቅልዬ በፕላስተር አሸግሁት፡፡
“---አሁን ወደ 4ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 2 መንቀሳቀሻህ ነው --» ሲል እንደ ወታደር ትእዛዝ ሰጠኝ ---- ወደ ሊፍቱ አመራሁ፤ ደላላው ከተል ብሎኝ “ቢሮው በር መድረስህን በ011536----- ደውልለት --- ቁጥሩን ይዘኸዋል?»
“አልያዝኩትም»
ቀይ ብዕር ከኪሱ አወጣና ልፃፍልህ ብሎ እሸግ ብሩን ተቀበለኝ፤ በቀይ ብዕር ቢጫ ወረቀቱ ላይ ስልኩን ፅፎ መለሰልኝ፡፡----
ብሩን የውስጥ ኪሴ አስገባሁ፤ የጃኬቴን ዚፕ ዘጋሁ--- በጥድፊያ ሊፍቱ ውስጥ ገባሁ፡፡
---ሊፍቱ ውስጥ ሁለት ጠብደል ወጣቶች ነበሩ፤ ፀጉረ ጨበሬ ጭራቅ መሳይ ፍጡራን።  በአይኖቻቸው የሆነ መልእክት ሲለዋወጡ አየሁ፤ አለቀልኝ!! ደላላው ስልክ ቁጥር ልፃፍልህ በሚል ያዘገየኝ ጊዜ መግደያ ነበር፤ ጭራቆቹን መጠባበቂያ። አንዱ ከኋላዬ ቆመ፤ ሌላው ከፊት ለፊቴ፡፡ መሀል አስገቡኝ፤ ሁለተኛው ፎቅ ከሊፍቱ ዘልዬ መውረድ አለብኝ፡፡----
ሁለተኛ ፎቅ በደረስንበት ቅጽበት፣ ሀሳቤ የገባው አንደኛው ጨበሬ፤ የሊፍቱን መውጫ ዘጋብኝ፤  ልቤ ቀጥ አለች፡፡ ዘና ብሎ ከሊፍቱ ወጣ። ከቀረው ጋር ተፋጠጥን፣ አንድ ለአንድ-- ማን ከማን ያንሳል፡፡ የእጆቹን ጣቶች አንቋቋቸው፤ በጥፍጥፍ እጆቹ አንገቴን አንቆ ሲጥ! ሊያደርገኝ ተጠጋኝ! የአልሞት ባይ ተጋዳይነት--- የሞት ሽረት ፍልሚያ የማይደረግበት--- ሳይነካኝ በግርምት አይቶኝ ከሊፍቱ ወጣ፡፡
በራሴ አፈርኩ፡፡ እንዲህ ሳር ቅጠሉን መጠርጠር ጤነኛነት ነው? አራተኛው ፎቅ ላይ ከሊፍቱ ወጣሁ፤ ገንዘቡን ከጃኬት ኪሴ አውጥቼ በእጄ ያዝኩት፡፡ ወደ ቢሮ ቁጥር 2 አቀናሁ፡፡ ኮሪደሩ እንደ ዋሻ ጨለምለም ያለ ነው፡፡ አንድም ሰው አይታይም፤ ፍፁም ፀጥታ። የሚቀፍ የዝምታ አዚም ነግሷል፡፡ የቢሮ በር ድንገት ተከፍቶ አንዲት ሴት ብቅ አለች፤ መልሳ ጥልቅ፡፡ ቆም ብዬ ዙሪያዬን በጥንቃቄ ቃኘሁ። ያችው ሴት ከዚህያው ቢሮ ወጣች፤ ቁመቷን የሚያክል የቆሻሻ መጣያ ቅርጫ ይዛለች፡፡ ስትራመድ ኮቴዋ እንደ ጥላ አይሰማም፤ ቀትረ ቀላል---ጥላቢስ፡፡ ከሌላ ፕላኔት የመጣሁ ይመስል በግርምት አፈጠጠችብኝ፡፡
በያዝኩት ገንዘብ ላይ አይኖቿ እንደ ማስቲሽ ተጣብቀው ቀሩ፡፡ በሆነ ነገር የእርግጠኝነት ድባብ ፊቷ ላይ ይነበባል፤ ‘ተፈላጊው ሰው ደርሷል› በሚል አተያይ፣ ወደ ኮሪደሩ ጥግ አሻግራ አማተረች ዘውር አልኩ፤ ሁለት ሰዎች ወደ እኔ ራመድ ሲሉ አንድ ሆነ!! ድንገት ስላየኋቸው ተደናግጠው ቆም አሉ፤ አንዱ ጉጠት መሰል ብረት፣ ሌላኛው ገመድ ይዟል። ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ ታየኝ --- ገንዘቤን መዝረፍ፣ አንገቴን በገመድ በማነቅ፣ እንደ ቆሻሻ ወደ ተዘጋጀልኝ ቅርጫ መወርወር----
ከቆሙበት አልተንቀሳቀሱም፤ የሆነ ትእዛዝ የሚጠብቁ ይመስላል፡፡ ሴትየዋ በከፍተኛ ድምጽ አስነጠሰች፤ ‘ፈጠን በሉ እንጂ› የሚል መልእክት መሆኑ ነው፤ ትክክል! በጥድፊያ ወደ እኔ ተንቀሳቀሱ፤» በእኔና በሞት መሀል አንድ እርምጃ» ቀረ እንዳለው ንጉስ ዳዊት--- የሞት ጠረን አፍንጫዬ ስር ደርሷል፡፡ ቆም አሉ፣ የቢሮ በር አንኳክተው ገቡ። አንዱ ተመልሶ ወጣ፤ የኤሌክትሪክ ቆጣሪውን መለሰው፡፡ ለካስ የኤሌክትሪከ ባለሙያዎች ናቸው!! ዳግም በራሴ አፈርኩ፡፡ በሀገር አማን፣ ሰው በጤናው እንዲህ ተደናብሮ ይቀባዥራል? ---- የቁም ቅዠት ለተባለ የአእምሮ ህመም፣ የሰብእና መዛባት ሳልጋለጥ አልቀረሁም፡፡
ወደ ቢሮ ቁጥር 2 እያመራሁ ----- ደላላው የነገረኝን የይለፍ ቃል፤ በአእምሮዬ አሰላሰልኩ፤
ዘቢብ ኬክ ይዣለሁ------- ዘቢብ ኬክ እወዳለሁ፤ የሚስቴ ስም ------- ማን ነበር ያለኝ?
 ወዲያውኑ፣ ትዝ አለኝ፤ ዘቢባ አሊባባ! ----
ቢሮ ቁጥር 2 ደረስኩ፤ ደላላው የፃፈልኝን ስልክ ደወልኩ፤ ስልኩ ይጠራል፤ የሚያነሳው የለም፤ አያሌ የጥርጣሬ ሀሳቦች ወደ አእምሮዬ ብቅ አሉ፤ደግሜ ደወልኩ፤ ስልኩ ተነሳ፤
“ሀሎ ጤና ይስጥልኝ---» ተስረቅራቂ የእንስት ድምጽ፡፡ ጆሮዬ የጠበቀው የወንድ ድምጽ ስለነበር ግራ ተጋብቼ፤ “ሀሎ የት ነው ?»
“የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ነው---»
በድንጋጤ ኩም አልኩ፡፡ ---- ገንዘቡን የያዝኩበት የእጄ ጣቶች አንዳች የሚቀፍ መልእክት ወደ አእምሮዬ ላኩ፡፡ በደመነፍስ ቢጫውን ወረቀት ቀዳደድኩት፡፡ ደጋግሜ ቦጫጨኩት--- እንኳን 5,000 ብር አንዲት የብር ኖት የሌለበት የታጨቀ ወረቀት! ደላላው እንዴት ሸወደኝ? -- ከመቅጽበት ትውስ አለኝ-- ስልክ ልፃፍልህ በሚል የገንዘቡን እሸግ በተቀበለኝ ሽርፍራፊ ሰከንድ! በሌላ በወረቀት በታጨቀ ተመሳሳይ እሽግ ለወጠው! አይን በአይን፤ በብርሀን ፍጥነት!!
ሴትየዋ የተቦጫጨቀ ወረቀቱን ከወለሉ ላይ አንስታ ቅርጫ ውስጥ እየጨመረች፤ “ወፈፌ እንደሆነ እንዳየሁት ቀልቤ ነግሮኛል”
አፈ ቅቤ፣ ልበ ጩቤው ደላላ ሊያመልጠኝ አይገባም፡፡ ሊፍቱ ውስጥ ዘው ብዬ ገባሁ፡፡
ከሊፍቱ ወጣሁ፡፡ ወደ ክበቡ ገባሁኝ፣ ላይ ታች! ባማትርም የደላላው ደብዛ የለም ፡፡
 ‘ዘቢብ ኬክ’ ---- ‘ዘቢባ አሊባባ’--- ‘የቆላ ዝንብ’ --- ‘የገንዲ በሽታ’ የሚሉት ቃላት አእምሮዬ ላይ ታትመው የህይወቴ ቅዠት ሆነዋል---፡፡

Read 2761 times