Sunday, 25 June 2017 00:00

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ቀረቡ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማንሳት ስራ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ሮዝ ቢዝነስ ግሩፕ በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ባለ ሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የጃፓን ቴክኖሎጂን የታጠቁ፣ ባትሪያቸውን በኤሌክትሪክ በመሙላት ብቻ የሚጓጓዙ፣ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ደብረ ዘይት አካባቢ በገነባው ፋብሪካው ማምረቱን የኩባንያው ባለቤት አቶ ሮቤል እስጢፋኖስ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካውን ከአንድ ዓመት በፊት መገንባት እንደጀመሩ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፤በአሁኑ ወቅት በአንድ ሰዓት አንድ የኤሌክትሪክ ባለ ሶስት እግር መኪና ማምረት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ለ4 ሰዓት በተሞላ ባትሪ መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ መንዳት ያስችላል ያሉት ባለቤቱ፤ ኤሌክትሪክ ለመሙላትም 7 ብር ብቻ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
ተሽከርካሪው በዋናነት ከከተማ ውጪ ላሉ አካባቢዎች የሚያገለግል ሲሆን ለሰፋፊ ግቢ የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ፣ ለሽርሽር እንዲሁም ለተለያየ ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ሹፌሩን ጨምሮም 7 ሰዎች የመያዝ አቅም አለው፡፡
ኩባንያው ተሽከርካሪውን ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም ባለቤቱ ባለፈው ሰኞ፣ በተሽከርካሪው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
የኩባንያው መነሻ ካፒታል 24.9 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ለ105 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ሮቤል፤የተሽከርካሪውን ዋጋ በተመለከተ ገዥዎች ሲመጡ ብቻ ቢያውቁት ይሻላል በሚል ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡   

Read 2886 times