Saturday, 24 June 2017 10:55

“ሀኮማል” እና “ሰንሴት ሆምስ” በጋራ የገነቧቸውን አፓርታማዎች አስመረቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “ሀበሻ ኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ ልማት” እና “ሰንሴት ሆምስ” በጋራ የገነቧቸውን 10 የመኖሪያ አፓርታማዎች ባለፈው ቅዳሜ አስመረቁ፡፡ ወሰን ግሮሰሪ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አለፍ ብሎ በሰንሻይን መኖሪያ ቤቶች ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ላይ የተገነቡት በአጠቃላይ 95 መኖሪያ ቤቶችን የያዙ ሲሆን 80ዎቹ ተጠናቅቀው ተመርቀዋል፡፡ ለእነዚህ ቤቶች ግንባታ 80 ሚሊዮን ብር እንደወጣና ቀሪዎቹ 15 ቤቶች ሲጠናቀቁ ወጪው ከመቶ ሚሊዮን ብር እንደሚልቅ የሀበሻ ኮንስትራክሽን ማቴሪያልስና ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ሀይሉ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱ የተመረጡ ሶስት ቤቶች የተጎበኙ ሲሆን እያንዳንዱ ቤት ሰፋ ያለ ሳሎን፣ አንድ ዋና መኝታ ቤት፣ ሁለት መጠነኛ መኝታ ቤቶች፣ ማብሰያና መፀዳጃ ቤቶችን ያሟሉ ናቸው፡፡ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ ቤታቸውን ተረክበው መኖር የጀመሩ ነዋሪዎች፤ ቤቱን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ መንግስት ጥርጊያ መንገድን ጨምሮ የመብራትና የውሃ አቅርቦት በፍጥነት እንዲያሟላላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከ6 ዓመት በፊት የተቋቋመው ሀኮማል፤ ከ2 ሺህ በላይ ባለ አክሲዮኖች ያሉት ኩባንያ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ቢዝነሶቹ ይልቅ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት 10 የቤቶች ግንባታ እያከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ 1500 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በፍጥነት እየገነባ እንደሆነና በቀጣዩ ዓመት አራቱን የቤት ግንባታዎች አጠናቅቆ ለባለቤቶቻቸው እንደሚያስረክብም ተናግረዋል፡፡
‹‹በከተማዋ የተንሰራፋውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ የሚያደርገው ጥረት በመንግስት ይበልጥ መደገፍ አለበት›› ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በተለይ የመሬት አቅርቦትና የፋይናንስ እጥረት ሀኮማል በእቅዱና ባሰበው ሰዓት ግንባታዎችን ለማከናወን እንቅፋት እንደሆኑበት ገልፀዋል፡፡
 “ሰን ሴት ሆምስ” ቦታውን ከመንግስት በሊዝ የወሰደ ሲሆን “ሀኮማል” ደግሞ ቤት ገዢዎችን በማሰባሰብና ግንባታውን በማካሄድ በጋራ መስራታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 901 times