Sunday, 25 June 2017 00:00

አቤቱታ…እንደገና!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ እንደገና አቤቱታ ይዞ የአንድዬን በር ያንኳኳል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ አንተ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እኔ ነኝ፣ አንድዬ…
አንድዬ፡— አሀ! ምስኪኑ ሀበሻ…ድምጽህ ተለወጠብኝና ነው እኮ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን ያልተለወጠ ነገር አለ…አንድዬ፣ ምን ያልተለወጠ ነገረ አለ ነው የምልህ! ሁሉም ነገሬ ተለውጧል…
አንድዬ፡— ያው እንደተለመደው፣ እንደተለመደው ልበል እንጂ፣ ለአቤቱታ ነው የመጣኸው
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አቤቱታ ብለህ አታቅለው…የእኔ ነገር ከአቤቱታም የባሰ ነው፡፡
አንድዬ፡— ለነገሩማ አሁን፣ አሁን የእናንተ ነገር እኔም ግራ እየገባኝ ነው፡፡ ዘላለም የሚጨቀጭቁኝ ለምንድነው ብዬ ስከታተላችሁ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አየህ አይደል! ኑሯችንን አየህልኝ አይደል!
አንድዬ፡— አየሁ እንጂ…ግራ እስኪገባኝ አየሁ እንጂ! እውነቱን ልንገርህና በእኔ ስም ፎርጅድ ሰዎች የፈጠረ አለ ወይ እስክል ድረስ ነው ግራ የገባኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይሄን ያህልማ አትቆጣ…እኛ እኮ ልጆችህ ነን፡ በታላቁ መጽሐፍ ስማችን ስንት ጊዜ የተነሳ እኮ ነን…‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’ ተብሎ ለአንተ ያለን ፍቅር የታወቀልን እኮ ነን!
አንድዬ፡— እኔም እኮ እሱ እሱ ትዝ እያለኝ ነው ግራ የተጋባሁት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አንተ ግራ ተጋባሁ ስትል እኛም እኮ ይከፋናል…
አንድዬ፡— የአንተና የወገኖችህን ጉድ ስከታተል ከርሜ ምን እንደሆንኩ ታውቃለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይበቃቸዋል… ከእንግዲህማ ብቻቸውን አውላላ ሜዳ ላይ አልተዋቸውም፣ አቅፋቸዋለሁ…እደግፋቸዋለሁ… አልክ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— እንደሱ አላልኩም…ይልቅ ልንገርህና ተስፋ ነው የቆረጥኩት..
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ቆይ! አስጨርሰኝ እንጂ፣  እያወራሁ አይደል እንዴ!  ይሄ እኮ ቀደም፣ ቀደም ማለታችሁ ነው ወደ ኋላ እየጎተታችሁ ያለው፡፡ ሁሉ ነገር ላይ አንደኛ ካልሆንን፣ ካልቀደምን እያላችሁ ነው፡፡ ሲፈልጋችሁ ከጎረቤቶቻችሁ፣ ሲብስባችሁም ከዓለም ጋር ምናምነኛ ነን እያላችሁ የህልም ደረጃ እያወጣችሁ … ራሳችሁን ካላባበላችሁ አይሆንላችሁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ታዲያ ምን ክፋት አለው…
አንድዬ፡— ከህልም ዓለም ውጡ! ከህልም ዓለም ውጡ ነው የምላችሁ፡፡ መጀመሪያ እስቲ ራሳችሁን ለፉክክሩ ብቁ አድርጉ፡፡ እስቲ መጀመሪያ በልታችሁ ጠግባችሁ እደሩ፣ እስቲ ቀን ስትሠሩ ዋሉና ማታ እቤታችሁ ስትገቡ እፎይ ማለት ልመዱ! ሳትሠሩ አንደኛ፣ ምናምነኛ ምን አመጣው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ መሞከራችን መች ቀረ ብለህ ነው!…ችግራችን አንድ ሺህ አንድ ሆነና አስቸገረን እንጂ!…
አንድዬ፡— ምነው ሁሉ ነገር ላይ የተለያችሁ ሆናችሁ?…እስቲ ንገረኝ፣ እኔ ለእናንተ ከሌላ የተለየ አእምሮ ነው የገጥምኩላችሁ!….
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ…እንደውም የሰጠኸን ከሌሎች የተሻለ አእምሮ…
አንድዬ፡— እሱን እንኳን ተወው፣ እኔ ለማንም አብልጬም አሳንሼም አልሰጠሁም። አሁን፣ አሁን ሳያችሁ ወይ የእናንተን አእምሮ ስፈጥር፣ ባእድ ነገር ተሳስቼ ከትቼበት እንደሁ እላለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— እውነቴን ነው የምልህ… እኔ እኮ አእምሮ የሰጠኋችሁ፣ እንድታስቡበት፣ እንድትመራመሩበት፣ ብስሉን ከጥሬ እንድትለዩበት፣ ደጉን ከክፉ እንድትለዩበት ነው፡፡ ለክፋት ከሆነ፣ ለመጠፋፋት ከሆነ፣ ለመፈነጋገል ከሆነ ምን አእምሮ ያስፈልጋችኋል! አንደኛውን ባዶ ቀፎ አድርጌ እፈጥራችሁ አልነበር!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይሄን ያህል አስከፍተንሀል እንዴ!
አንድዬ፡— ለምንድነው ሁልጊዜ ገዳዳ ገዳዳውን የምታስቡት! ለምንድነው ከደግነት ይልቅ ክፋት ብቻ የምታስቡት! ለምን ወገናችሁን ቀና ከማድረግ ይልቅ ትደፍቁታላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተ እኮ እንዲህ ስትቆጣ እኛም ስጋት ይገባናል…
አንድዬ፡— ‘የተማረ ይግደለኝ’ እያላችሁ ስትተርቱ ኖራችሁ፣ ምነው ታዲያ የተማረውም፣ ያልተማረውም አስተሳሰቡ አንድ አይነት ሆነ! ምነው ተመሪ እንጂ መሪ ያጠራት አገር አደረጋችኋት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱማ እኛንም ግራ እየገባን እኮ ነው..
አንድዬ፡— ለምንድነው አእምሯችሁን የጎደለውን ስለሙመላት፣ የተዛነፈውን ስለማቃናት፣ የተሰነጠቀውን ስለመድፈን የማያስበው! ለምንድነው ዘላለማችሁን ስለማፍረስ፣ ስለማፍረስ ስለማፍረስ ብቻ የምታስቡት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኛም አኮ ምን ጋኔን ቢመታን ነው እያልን ነው፡፡
አንድዬ፡— ምንም ጋኔን አልመታችሁም…ጋኔን እናንተ ዘንድ ምን አደረሰው!  የእሱን ሥራ ራሳችሁ እየሠራችሁለት ለምን ጊዜውን እናንተ ላይ ያጠፋል!
ምስኪን ሀበሻ፡— ተው ግዴለህም አንድዬ፣ አንተ ሳታውቅ እሱ ሰፍሮብን ይሆናል…
አንድዬ፡— ይልቅ ሳታውቁ አዋቂ፣ ሳትጸልዩ ጻድቅ የሆናችሁ እናንተ፣ ያላረሳችሁትን መሬት ሰብል አምጣ የምትሉት እናንተ፣  በባዶ ሆድና በባዶ አእምሮ አሼሼ ገዳሜ የምትሉት እናንተ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በእርግጥ ብዙ ነገሮች ተሳክረውብናል...
አንድዬ፡— ጎሽ እንዲሀ ጥሩ አገላለጽ አምጣ፡፡ ሁሉ ነገር ተሳክሮባችኋል…ደግሞ እስቲ አንተ ንገረኝ…እናንተ ላይ የተገጠመው ምላስ እኔ ምን አጉድዬ ፈጠርኩት?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አልገባኝም..
አንድዬ፡— የእናንተ ምላስ እኮ በሴኮንድ ሺህ ጊዜ ነው የሚርገበገበው፣ ደግ ነገር አይለፍበት የተባለ ይመስል፣ በመረረ አረቄ እያራሳችሁ የመረረ ነገር ብቻ ነው የምታንከባልሉበት … ለምንድነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የዚህን ምስጢር ባውቀውማ አንተንም አላስቸግርም ነበር…
አንድዬ፡— አሁንማ…አሁንማ ሰው መሆን አቅቷችሁ ጭራሽ የእኔንም ስልጣን በጉልበታችሁ እየወሰዳችሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደሱ አትበል…
አንድዬ፡— እውነቴን ነው የምልህ…  የእኔንም ዙፋን የምታስቡ እየመሰለኝ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይኸው ደጅህ እየመጣን እያለቀስን አይደል እንዴ!
አንድዬ፡— እኔ አልቅሱ አልኩ? እኔ በሬ ላይ እንባችሁን አፍስሱ አልኩ?…ለነገሩ እዛው ምድር ላይ አዳኝ ነን፣ ፈዋሽ ነን የሚሉ ተፈጥረውላችሁ የለ!…
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ…
አንድዬ፡— እስቲ ንገረኝ…ይሄ እናንተ ለሆነ ነገር ላለመካካድ የምትፈራረሙበት…ይሄ ውለታ የምትፈጽሙበት ቦታ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ውልና ማስረጃ…
አንድዬ፡— ጎሽ፣ አመጣህልኝ፡፡ ውልና ማስረጃ ሄደን፤ ‘የማዳን ስልጣኔን ሁሉ በውክልና አስተላልፌላቸዋለሁ’ ብዬ የፈረምኩት ነገር አለ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ ምን በወጣህ!
አንድዬ፡— ታዲያ በየቦታው አዳኝ ነኝ፣ ፈዋሽ ነኝ፣ ከእግዚአብሔር የተላክሁ ነኝ እያላቸሁ ለምን ስሜን ታረክሳላችሁ..
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እሱን ልክ ነህ… በአንተ ስም እኮ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት ዘመን ነው፡፡…ምን የመሰለ ቪላ ይሠራል፣ አገር ለአገር መንሸራሸር ይቻላል… ምን ልበልህ፣ ብልጦቹ ዓለም ዘጠኝ እያሉ ነው፡፡
አንድዬ፡— እና ታዲያ እናንተ ይሄን ሁሉ ጉድ ይዛችሁ በሬን ስታንኳኩ ትንሽ ይሉኝታ አይሰማችሁም..
ምስኪን ሀበሻ፡— የት እንሂድ ታዲያ… አንድዬ ገሚሶቹ በአንተ ስም ቢነግዱም እኛ ሚሊዮኖች ደግሞ ዘወትር የአንተን ቡራኬ እንፈልጋለን፡፡
አንድዬ፡— እነሱ እየዋጧችሁ ነዋ!…ይገርማል እኮ፣ እናንተ ተበደልን ስትሉ እኔ ዘንድ አቤት ትላላችሁ… እኔ ማን ዘንድ ሄጄ አቤት ልበል!…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ተው፣ ተው እንደ እሱ አትበል…
አንድዬ፡— አንደኛውን እኮ ‘የለህም ብለው የካዱኝ ይሻላሉ..
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኧረ በስመአብ በል!…ይቅርታ ለማለት የፈልግሁት…
አንድዬ፡— ግዴለም ለማለት የፈለግኸውን አውቄያለሁ… አየሀ የካዱኝ እየመጡ በሬን እያንኳኩ አይጨቀጭቁኝም፣ በእኔ ስም ህዝቤን አያሞኙም…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ጊዜው እኮ ተበላሸና ነው…
አንድዬ፡— የትም ስፍራ ያለው ጊዜ ያው ነው፡፡ እናንተም ዘንድ ያለው፣ ሌላም ዘንድ ያለው ጊዜ ተመሳሳይ ነው፡፡ የምታበላሹትም፣ የምታሳምሩትም ራሳችሁ ናችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…ለአንዳንዶቹ ቶሎ ትደርስላቸዋለህ…
አንድዬ፡— ይኸው ነው ችግራችሁ፣ ሁልጊዜ እናንተ ላይ ተንኮል የሚሠራ፣ እናንተ ላይ ሸፍጥ የሚሠራ ታስመስሉታላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን ቆርጦኝ ነው እናንተን እንደዛ…
አንድዬ፡— ግዴለም፣ ግዴለም…ብቻ የእናንተ ነገር ተተርትሮ የማያልቅ ስለሆነ አሁን ባታደክመኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ተመልሼ ብመጣ ቅር አይልህም?
አንድዬ፡— ለምን ብዬ! አትምጣ ብልህስ እንደማታርፍ እያወቅሁ ለምን ቅር ይለኛል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይመችህ በለኝ!…
አንድዬ፡— ምን በለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይቅርታ ባርከኝ ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
አንድዬ፡— እንግዲያው በአንተው ቋንቋ… ይመችህ።

Read 4107 times