Print this page
Monday, 19 June 2017 10:24

የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የተስፋ ብልጭታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ክፍል 2

    የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልን አስመልክቶ በክፍል 1 ያቀረብነው ዘገባ ከ224 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሆነባቸውን የስፖርት መሰረተ ልማቶች የግንባታ ሂደቶች በመጠኑ የሚዳስስ ነበር፡፡ በክፍል ሁለት የማሰልጠኛ ማዕከሉን ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶች፤ የአሰልጣኞችን የሙያ እና የብቃት ደረጃ  የሰልጣኞች ምልመላ እና ተያያዥ ሁኔታዎችን  እንመለከታለን፡፡   የማሰልጠኛ ማዕከሉን ፍሬያማነት በማንሳት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የምንገመግመው ሲሆን የሰልጣኞችን ተስፋና የአሰልጣኞችን የብቃት ደረጃን ማሻሻል ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ይህን ልዩ ዘገባ ለመስራት በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የትምህርት፣ የስልጠናና የውድድር ዘርፍ ዲያሬክተር ከሆነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ፤ በአጭርና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም የአንዳንድ የሜዳ ላይ ስፖርቶች አሰልጣኝ ከሆኑት ንጉሴ አደሬ እና ከከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ ማልጎኝ ዊል ጋር ቃለምልልሶች አድርገናል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት  ኃይሌ ገብረስላሴ ጋርም ተጨማሪ ውይይት የነበረን ሲሆን በማሰልጠኛ ማዕከሉ ዙርያ የተሰሩ የጥናት ፅሁፎችን መርምረናል፡፡  መልካም ንባብ፡፡
እንደመግቢያ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው በኢትዮጵያ መንግስት በቢሊዮን የሚተመን በጀት ወጥቶባቸው የተገነቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች አድናቆት የሚገባቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልና ሌሎች ተቋማት የቀድሞ ውጤታማ እና ባለታሪክ አትሌቶች የነበራቸውን ህልምና ፍላጎትን ያሳኩ መሰረተ ልማቶች በመሆናቸው ነው ፡፡
ይሁንና አካዳሚውና የማሰልጠኛ ማዕከሉ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሚሆኑ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት ዋንኛ ዓላማቸው መሆን እንዳለበት የሚያሳስበው ኃይሌ፤ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ተገንብተው ስራ ከጀመሩ በኋላ በሚከተሉት ራዕይና ዓላማ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነትን  ከግምት ውስጥ ባስገባ የአመራር ደረጃ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው፣ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት አሰራር እንዲኖራቸው፤  በአስተዳደራቸው የስፖርቱን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ መስራት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡
በርግጥም የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልና ሌሎችም የስፖርት መሰረተ ልማቶች ተቀብለው በሚያሰለጥኗቸው ስፖርተኞች ብቻ በመወሰን ታጥረው መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ቢያንስ የመሮጫና የልምምድ ትራኮቻቸው፣ የእግር ኳስና የሌሎች ስፖርቶች ሜዳዎች ተገቢውን የቁጥጥር መርሃ ግብር በመዘርጋት ለሁሉም ክፍት መሆን አለባቸው፡፡
ኃይሌ በአስተያየቱ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በሚሰጡት አገልግሎት የገቢ ምንጮችን እንዲፈጥሩ፤  በአስተዳደራቸው ልምድ ያላቸው ታላላቅ ስፖርተኞች እና ባለሙያዎችን እንዲያሳትፉ፤ በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው የስፖርት አካል ብቻ እንዲሆን፤ የነባርና የቀደም አትሌቶች አስተዋፅኦ እንዲጠናከር መደረግ አለበትም ይላል፡፡ በተለይ የገቢ ምንጮችን በመፍጠር ረገድ በሆላንድ፤ በጣሊያን፤ በጀርመንና በእንግሊዝ ያሉ ተመክሮዎችን በመንተራስ ከጅምሩ የተገነቡት የስፖርቱ መሰረተ ልማቶች በዚያ የሚሰራውን መከተል እንደሚኖርባቸው ሲያመለክት ብሄራዊ ቡድኖች ማዕከሉን ሲገለገሉ የሚያንቀሳቅሳቸው ፌደሬሽን ክፍያ እንደሚፈፅም እና ይህ አሰራር በየደረጃው እንደሚሰራበት ጠቁሞ፤ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ክፍያ የስፖርት መሰረተልማቶቹን አገልግሎት እንዲያገኝባቸው መስራት ተገቢ ነው ብሏል፡፡
የማዕከሉ አሰልጣኞች እና ሳይንሳዊ ስልጠና መንገዶች
በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የትምህርት፣ የስልጠናና የውድድር ዘርፍ ዲያሬክተር የሆነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ነው፡፡ በማዕከሉ ሁለገብ እንቅስቃሴዎች ያለፉትን 7 አመታት ያገለገለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በስፖርት ሳይንስ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት በመጀመርያ ከባህርዳር ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዎች ሁለት ዲግሪዎችን ተቀብሏል፡፡
አሰልጣኝ ጎሳ ሞላን ጨምሮ በጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ላይ  እየሰሩ የሚገኙት 20 አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ከመካከላቸው ሶስቱ በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ 17ቱ አሰልጣኞች ደግሞ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆኑ ከእነሱ መካከል  በማዕከሉ ውስጥ እያገለገሉ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት አምስቱ ናቸው፡፡ ሃያዎቹ አሰልጣኞች በማዕከሉ ለሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች ውጤታማ እና ተመጣጣኝ ስራ ለማከናወን በቂ ናቸው ለማለት አይቻልም፡፡ ከስልጠናው ባሻገር በፊዝዮሎጂ፤ ስነ ምግብና ስነ ልቦና የሚሰሩ ባለሙያዎች ስብስብ ያካተተ አደረጃጀት ወሳኝ እንደሆነ መታወቅ አለበት ፡፡ የአሰልጣኞቹ ብዛት፤ የሙያ ብቃት፤ የትምህርት ደረጃና ልምድ ዓለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ ሁኔታ በማዋቀር የሚሰራበት አዲስ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ከብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከአትሌቲክስና ከሌሎች የስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር በአጋርነት በመንቀሳቀስ መተግበር የሚቻል ይመስለኛል፡፡
አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የማዕከሉ አሰልጣኞች በየጊዜው የሙያ ማሻሻያዎች፤ ስልጠናዎችን በመከታተል ብቃታቸውን የማሳደግ ባህል እያዳበሩ መጥተዋል፡፡ በአትሌቶች ላይ ለሚሰሯቸው ስልጠናዎች ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎች በቅርበት የሚወስዱ በመሆናቸው  በተለያዩ ምርምሮች እና ጥናቶች የመሳተፍ ፍላጎትና አቅም እየፈጠሩ ይገኛሉም ብሏል፡፡   በርግጥ በማዕከሉ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ጋር በተያያዘ ጥናትና ምርምር የሚደረጉባቸው አሰራሮች መሰረት እየያዙ መምጣታቸው የሚያበረታታ ነው። ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበት ፖሊሲ አለመኖሩ ዘላቂ ስኬት የሚመዘገብባቸውን ሁኔታዎች የሚያዳክማቸው ሆኗል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ከሚሰሩ ብሄራዊ ቡድኖች፤ ከክለብ እና ክልል ቡድኖች፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ዩኒቨርስቲዎች፤ ከነባር እና ልምድ ካላቸው ትልልቅ አትሌቶች እና አሰልጣኞች፤ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከፌደሬሽኖች ጋር በአጋርነት በመስራት የማዕከሉን ፍሬያማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፡፡
ማዕከሉ በሚያከናውናቸው ተግባራት እንደትልቅ ተቋም መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ ለወጣት ስፖርተኞች የስራ እድል መፍጠር እና ስፖርቶችን ማስፋፋት እንደገዘፈ ውጤት ከመቁጠር መውጣት አለበት፡፡ ሰልጣኞቹ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የሚበቁ፤ በተለያዩ ስፖርቶች የላቁ ውጤቶችን የሚያስመዘግቡ፤ ሪከርዶችንና የውጤት ክብረወሰኖችን በማሳካት ታሪክ የሚሰሩ መሆን አለባቸው፡፡  የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በስፖርት ዩኒቨርስቲ ደረጃ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል የሚለው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ተቋማቱ በስፖርቱ ምርምርና ጥናት የሚያደርጉ፤ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ የሆኑ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ፤ ምርጥ እና ኤሊት አትሌቶችን የሚያፈልቁ፤ ከዓለም እና ከኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ጋር በተለያዩ መዋቅሮች ተቀናጅተው የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ሁለቱም የስፖርት ተቋማት ዓላማቸው ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው፤ ስነ ምግባራቸውን የጠበቁ ምርጥና ወጣት ስፖርተኞች ማፍራት፤ ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ ለስፖርቱ ጥራት አስተዋፅኦ የሚሆኑ የጥናትና የምርምር ስራዎች ማካሄድና ውጤቶችን ማሰራጨት እንዲሁም ለተለያዩ ስፖርቶች የዕውቀት ማዕከል መሆን ነው፡፡
በርግጥ አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ  ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው በማዕከሉ በሚሰጡ ስልጠናዎች  በሳይንሳዊ አሰራሮች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለመተግበር የሚያግዙ አበረታች ጅማሮዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሰልጣኞች ምልመላ በመስፈርት ላይ የተመረኮዘ መሆኑ የማዕከሉን አሰራር ሳይንሳዊ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ጎሳ ሲያስረዳ፤ ‹‹የትኛው አትሌት ለየትኛው ስፖርት መግባት ይችላል››  በሚል አስተሳሰብ እንሰራለን በማለት ነው፡፡ በማዕከሉ በኩል የአትሌቲክስ ሰልጣኞች የሚመለመሉት   በየዓመቱ በየክልሉ ተዘዋውሮ በማፈላለግ በሚከናወኑ ተግባራት ነው። በተለይ ለአትሌቲክስ ከ17 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ታዳጊና ወጣቶች ይፈልጋሉ፡፡ ምልመላውን የሚያከናውኑት የማዕከሉ አሰልጣኞች  በአትሌቲክስ አሰልጣኝነት በመስራት ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በስልጠና እንለውጣቸዋለን ብለው የሚያስቧቸውን አትሌቶች በየክልሉ የሚያፈላልጉበት አሰራር በተሻለ መዋቅር ማደግ ይኖርበታል፡፡ አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ የምልመላውን ሂደት ሲገልፅ በዕጩ ሰልጣኞች ምልመላ የሚሰማሩ ባለሙያዎቹ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በቅርበት ያላቸውን አቅምና የአካል ብቃት እንደሚገመግሙ፤ ይህን ሂደትም በፎቶ እና በቪድዮ ምስሎች አስደግፈው በሙሉ ሃላፊነት ለማዕከሉ እንደሚያቀርቡም ይገልፃል፡፡ በአሰልጣኞቹ አማካኝነት ከየክልሉ በእጩ ሰልጣኝነት የተመለመሉት  ወደ አካዳሚው ከመግባታቸው በፊት ሌላ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡  የባለሙያዎች ኮሚቴ ምልመላውን ባከናወኑ አሰልጣኞች የሚቀርቡ መረጃዎችን በጥልቀት ይመረምሯቸዋል፡፡ በመጨረሻም በአዳሪነት ገብተው ተከታታይ ስልጠናዎች ለ4 ዓመታት  ወስደው እንዲመረቁ ይደረጋል፡፡ከዓለም አቀፍ ተመክሮዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ምርጥ ፐሮፌሽናል አትሌት በማሰልጠኛ ማዕከል ለማፍራት በትክክለኛው ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደት ከ8-12 ዓመት ይወስዳል። በአጠቃላይ አንድ ሰልጣኝ ፕሮፌሽናል አትሌት ለመሆን 10 ዓመታትን መሰልጠንና መማር አለበት። ይህንን በጥሩነሽ ማዕከል ለመተግበር በሚያስብ ፖሊሲ መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን እዚህ ጋር መጠቆም ግድ ይላል፡፡
በሌላ በኩል  ማዕከሉ ሳይንሳዊ አሰራሮችን እንደሚከተል የሚያመለክት ማስረጃ ስልጠናዎች በእቅድ መመራታቸው ነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ማብራሪያውን ይቀጥላል፡፡ እያንዳንዱ ሰልጣኝ ዓመታዊ የእቅድ መርሃ ግብር እንደሚወጣለት፤ ስልጠናን የመቀበል አቅም እና የእድሜ ደረጃን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ፤ በየእለቱ፤ በየሳምንቱ የሚሰጡት ስልጠናዎች በማማከል የሚነደፉ ናቸው። በተጨማሪም ስልጠናውን በእቅድ ከመምራት ባሻገር ለአትሌቱ ዓመታዊ ግብ በማስቀመጥ መስራታችን ምን ያህል ለሳይንሳዊ አሰራር ትኩረት እንደሰጠን የሚያመለክት ነው የሚለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በተለያዩ የስልጠና ደረጃዎች ለእያንዳንዱ ስፖርተኛ በየስፖርት አይነቱ ዓመታዊ ግብ የሚቀመጥለት ወቅታዊ ብቃቱን በማገናዘብ  እዚህ መድረስ አለበት ተብሎ ነው ብሏል፡፡  በአጠቃላይ በማዕከሉ የስልጠና እቅዶቹ ፤ የልምምድ መርሃ ግብሮች፤ የሚመዘገቡ ውጤቶች እና ተያያዥ አሃዛዊ መረጃዎች በሰነድ እና በዲጂታል ማህደር ከስር በስር የሚከማቹ መሆናቸው ተጠናክሮ መሄድ ያለበት ልምድ ነው ፡፡ የማዕከሉን የስልጠና ሂደት ለመተንተን እና በተለያየ አቅጣጫ ለማስላት የሚያግዝ ሳይንሳዊ አሰራር ነው፡፡
ስልጠናዎች በተለያዩ ወቅቶች መከፋፈላቸውም የሚጠቀስ ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደት ሲሆኑ፤ የመደበኛ ዝግጅት ወቅት፤ የቅድመ ውድድር ወቅት እና የውድድር ወቅት በመከተል የሚካሄዱት የስልጠና ሂደቶች ልዩ ውጤት የሚያስገኙ ይሆናሉ፡፡ በሳምንት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ለሁሉም አትሌቶች 10 የልምምድ መርሃ ግብሮች ያሉ ሲሆን፤  በጠዋት እና ከሰዓት ተከፋፍለው ሰልጣኞች የስልጠናውን ጫና ተቋቁመውና በቂ እረፍት አድርገው እንዲሰሩም ይደረጋል፡፡ የአትሌቱን መቶ ፐርሰንት ብቃት በየደረጃ መለካት የሚቻለው በእነዚህ ወቅቶች ጠብቆ መስራት ሲቻል ነው የሚለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደቶች የሚነደፉት የስልጠና መርሃ ግብሮች በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ከፀደቁ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆኑ በማመልከት ነው፡፡  ከዓመታዊ እቅድ እና ግብ ባሻገር አሰልጣኙ እና ሰልጣኝ አትሌቱ ተስማምተው እየሰሩ መሆናቸውን ተከታተለው የሚያረጋግጡበት መዋቅርም ተዘርግቷል፡፡ አትሌቱ እዚህ እደርሳለሁ ሲል አሰልጣኙም እዚህ አደርሰዋለሁ በሚል ተስማምተው ይሰራሉ፡፡ በየስልጠናው ክፍል  በእቅድ እና በተቀመጠው ግብ መሰረት እንቅስቃሴ መኖሩን የሚመረምሩ ሃላፊዎች አሉ፡፡ በየወቅቱ የውስጥ ምዘናዎች ይደረጋሉ፡፡ ምዘናዎቹ የአካል ብቃት፤ ወቅታዊ አቋም እና የፉክክር ደረጃ የሚፈተሽባቸው ሲሆን አትሌቱ በየጊዜው ስለሚያሳየው ማሻሻያ ክትትትል ለማድረግ የሚያመች ሌላ ሳይንሳዊ አሰራር ነው፡፡ በማዕከሉ የሚሰጡት ስልጠናዎች በሳይንሳዊ መንገድ መካሄዳቸው ከላይ የተዘረዘሩት ስኬቶች ምስጥር እንደሆኑ የሚያስገነዝበው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ፤ ሰልጣኞች በየእለቱ በሚያልፉባቸው የስልጠና መርሃ ግብሮች ምርጥ ውጤት ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉበትን ባህል በማዳበራቸው ወደተለያዩ ውድድሮች ሲገቡ በሪከርድ ስኬት እና በሜዳልያ ውጤት የሚደነቁበትን ታሪክ በተደጋጋሚ የሰሩበትን እድል ፈጥሮታል ብሏል፡፡
በአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የምልመላ ሂደት ያሉትን ዓለም አቀፍ ተመክሮዎች በማጥናት መገንዘብ የሚቻለው የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት ነው። የመጀመሪያው አሳሳቢ ክፍተት ብዙዎቹ ሰልጣኞች ለማዕከሉ የሚመለመሉት በአገር አቀፍ ደረጃ  በሚካሄዱ ውድድሮች ክልብ ወይም ክልል ወክለው ከተሳተፉ በኋላ መሆኑ ነው። በማሰልጠኛ ማዕከል ሳይንሳዊ አካሄድ ሰልጣኞች መመልመል ያለባቸው ምንም አይነት የውድድር ተመክሮ ሳይኖራቸው መሆን ነበረበት፡፡ ከ6-10 በሚሆን እድሜያቸው በየትውልድ ስፍራቸው በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ያልፋሉ፡፡ ከዚያም ከ10-14 በሚሆን እድሜያቸው መደበኛ የስፖርት ስልጠናዎችን ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ያዘወትራሉ። ከእነዚህ ሂደቶች  በኋላ ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ መደረግ አለበት።
ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የስልጠና ሂደቶች በአካዳሚ፣ በማሰልጠኛ ማዕከል፣ በክለብና በክልል ደረጃ ወጥ የሚሆኑበት መዋቅር ካልተዘረጋ ውጤታማ አንሆንም ይላል፡፡ የላቀ ብቃትንና ውጤት የሚያስመዘግብ ፕሮፌሽናል አትሌት ለማፍራት የሚችለው ከስር ተነስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በሚያሳትፍ ብሄራዊ መመሪያ በመስራት ነው ብሎ፤ በቀድሞ አትሌቶች በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው ፌዴሬሽን የነበሩ አሰራሮች እና አመለካከቶች ለመቀየር ቢቸገርም አንዳንድ ስርነቀል ለውጦች ለመፍጠር እየሞከረ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ አትሌቶች የሚያልፉበት የስልጠና ሂደት፤ አሰልጣኞች የሚሰሩባቸው የስልጠና መንገዶች ሁሉ ወጥ አለመሆናቸው ዋናው ፈተና እንደሆነባቸው የሚያስገነዝበው ኃይሌ፣ በዛሬው ትውልድ የአትሌቶች ጥረት እና ትጋት ያነሰ መሆኑን በማስተካከል የአካዳሚና የማሰልጠኛ ተቋማት ሰልጣኞችን የመመልመል ሂደት ከዚያም ለሚሰጡ ስልጠናዎች ስኬት የሚያመች መዋቅር መፍጠር እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡
ለአካዳሚ ወይንም ለማሰልጠኛ ማዕከል የሚሆኑ ሰልጣኞች ተገቢውን የዕድሜ ደረጃና የዕድገት ሂደት ጠብቀው የሚደርሱ መሆን እንዳለባቸው ከዚሁ ጋር በማያያዝ ያስገነዝበው ኃይሌ፤ ከቀበሌ ወደ ዞን ከዚያም በከተማ እና በክልልና በክለብ  ደረጃ በሚዘረጉ መዋቅሮች እና የስልጠና ሂደቶች ስርዓቱን ጠብቀው የሚያልፉ ሰልጣኞችን በመመልመል ውጤታማ ስራ መከናወን ይቻላል ብሎ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራበት ወጥ የአትሌቲክስ መመርያ የመዘጋጀቱን አስፈላጊነት ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ይህን ታሳቢ በማድረግ ዳጎስ ያለ አገር አቀፍ የአትሌቲክስ መመርያ ሲያዘጋጅ ቆይቶ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ መመርያው ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የአትሌቲክስ ባለሙያዎች በየክልሉ የተደረጉ ጥናቶችና ቅኝቶች መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን አትሌት፤ ክለብ፤ አሰልጣኝ እና ስልጠና ምን መሆን አለበት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ በስልጠናው የእድሜ ገደብ፤ የእድገት ደረጃ እና የአሰራር ሂደት በዝርዝር የሚቀመጥበት ሰነድ ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኃይሌ ገብረስላሴ ይህን የአትሌቲክስ መመርያ አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይቶች፤ በቀረቡ ትችቶች እና ግምገማዎች ተጠናክሮ ለህትመት በሚበቃበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየአምስት አመቱ እየዳበረ እና እየተሻሻለ የሚሄድ ነው ብሏል፡፡
የማዕከሉ ፍሬያማነት ሲለካ
የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጉልህ አስተዋፅኦና መነቃቃት መፍጠሩን በተለያዩ ማስረጃዎች ማመልከት እንደሚቻል ለስፖርት አድማስ በዝርዝር ያስረዳው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ፤ በአጭር እና መካከለኛ ርቀት ሩጫዎች እንዲሁም የሜዳ  ላይ ስፖርቶች በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን ያነሰ ትኩረት መቀየሩን፤ ብዙም ትኩረት በማይሰጣቸው ስፖርቶች ክለቦች እና የክልል ፌደሬሽኖች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማነሳሳቱን ይጠቃቅሳል፡፡ በሜዳ ላይ ስፖርቶች፤ በአጭር እና በመካከለኛ ርቀት ተተኪ እና ውጤታማ አትሌቶች እያፈሩ ስለመሆናቸው የማዕከሉ ሰልጣኞች በክለቦች እና በክልል ፌደሬሽኖች ተፈላጊ እየሆኑ እንደመጡ በመግለፅም የማዕከሉን ፍሬያማነት ሊያመላክት ሞክሯል፡፡
ከወር በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጭርና መካከለኛ ርቀት፤ በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች ከተመዘገቡ 10 ክብረወሰኖች ገሚሱን በማዕከሉ ያለፉ ሰልጣኞች ማስመዝገባቸውንና የሜዳልያ ውጤቶችንም በብዛት ማግኘታቸውን የገለፀው አሰልጣኝ ጎሳ ፤  በታዳጊ እና ወጣት ውድድሮች ላይም የማዕከሉ ሰልጣኞች በተለያዩ ጊዜያት  ስኬታማ ሆነዋልም ይላል፡፡ በሌላ በኩል ሰልጣኞች በማዕከሉ ሆነው ከማዕከሉም ወጥተው አገርን በመወከል በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ መሆናቸውንም በማስረጃነት አንስቷል። በ2015 እኤአ ላይ ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የተሳተፉት ጅግሳ ቶሎሳ እና ሃይለማርያም አማረ በማዕከሉ 4 ዓመታትን ሰልጥነው የተመረቁ ናቸው፡፡ በተለይ ሃይለማርያም አማረ በሪዮ 31ኛው ኦሎምፒያ ለመሳተፍ የበቃ መሆኑ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በማዕከሉ በሁለተኛና ሶስተኛ  አመት ሰልጣኝነት የሚገኙ ስፖርተኞች በየክለቦቹ ተሰራጭተው ጠንካራ ውጤት ማስመዝገባቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ማዕከሉ በኮንደሚኒዬም ቤቶች ከ2002 ዓ.ም መስራት ከጀመረበት ጊዜ እንስቶ እስከ 2009 እኤአ ድረስ 445 አትሌቶች  በማስመረቅ ለተለያዩ ክለቦች እና  ቡድኖች አዘዋውሯል፡፡ 113  አትሌቶች  በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች እና የስፖርት ዓይነቶች ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ ሲሆን 31 ወንድና 26 ሴት አትሌቶች በአህጉራዊ ውድድሮች፤   13 ወንድና 11 ሴት አትሌቶች  ደግሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሊሳተፉ በቅተዋል፡፡
በርግጥ የማዕከሉን ፍሬያማነት ከላይ በተዘረዘሩት መረጃዎች ለማመልከት ቢቻልም ግን ሌሎች አሳሳቢ ነገሮች ተጋርጠዋል፡፡ በተለይ ማዕከሉ አሁን ባለበት ደረጃ በተለያዩ የዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች ተፎካካሪና ውጤታማ አትሌቶችን በሚጠበቅበት ደረጃ እያቀረበ አይደለም። ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ከሚቡት 50 በመቶ ያህሉ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ይወጣሉ፤ ወደ ክለቦች ሲዛወሩ በማዕከሉ ከነበሩበት የስልጠና ደረጃ ወርደው ይሰራሉ፤ በአገር አቀፍ ውድድሮች ያለወቅታቸው እየገቡ ባክነው ይቀራሉ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በዚህ ዙርያ አስተያየት ሲሰጥ፣ ማዕከሉ ፍሬያማነቱን ለመለካት ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን መጥቀስ እንዳማይኖርበት አመልክቶ የሚጠበቀው ውጤት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የሚበቁ ስፖርተኞችን ማፍራት ነው ይላል፡፡
ምናልባትም የማዕከሉ ሰልጣኞችን በአገር አቀፍ ውድድሮች እያገኙ ያሉት ውጤት የሚያበረታታ ቢሆንም በተሟላ መሰረተ ልማት በሚያሰለጥናቸው ስፖርተኞች  ውጤታማ የሆነበትን እድል ከሌሎች ክለቦች ጋር በማነፃፀር እንደስኬት መቁጠሩ ተገቢ አለመሆኑን ሳያስገነዝብ አላለፈም፡፡ በተያያዘ የማዕከሉ ሰፖርተኞች እንደ ክለብ በአገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ መቀየር እንዳለበት የሚመክሩም አሉ የመንግስት ክለብ ተብሎ መወዳደር ተገቢ አለመሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡
በከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ የሆነው ማልጎኛ ዊልና ተስፋው
በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ባደረግኩት  ጉብኝት ከሰልጣኞች አንፃር ብዙ ያደረግኩት ቅኝት እና ውይይት አልነበረም። የሰልጣኞቹን መመገቢያ፤ መኖርያ እንዲሁም የመማርያ ክፍሎችን ተዘዋውሬ ተመልክቼ ነበር። የማዕከሉ ሰልጣኞች ራሳቸውን የሚያስተዋውቅ ወጥ የስፖርት ትጥቅ (ዩኒፎርም) ቢለብሱ ጥሩ ነው፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹን በመንከባከብ፤ በመፀዳጃ ቤት አካባቢ ያሉ የፍሳሽ ችግሮችን በመቆጣጠር በሚመሩበት ዲስፕሊን አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ግን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
ከሰልጣኞቹ መካከል ግን አንዱን በማነጋገር ምን አይነት ስፖርተኛ ከማዕከሉ እየወጣ መሆኑን ለመገንዘብ ሞክሪያለሁ፡፡ የከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ የሆነው ማልጎኝ ዊል ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ጋምቤላ ክልልን ወክሎ  በመሳተፍ  ስፖርተኛነቱን ጀምሮ ዛሬ  በማዕከሉ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡   
በማዕከሉ በምከታተለው ስልጠና ከፍተኛ ለውጥ እያሳየሁ እና እያደግኩ ነው በማለት ለስፖርት አድማስ የሚናገረው ማልጎኝ ተስፋው ተመርቆ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፍበትን ደረጃ በማሳካት ክብረወሰን እስከማስመዝገብ ነው፡፡ በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በከፍታ ዝላይ 1.95 ሜትር በማስመዝገብ  የብር ሜዳሊያ ያገኘው ማልጎኝ፤ በከፍታ ዝላይ የኢትዮጵያ ሪከርድ የሆነው 2.07 ሜትር እና በዓለም አቀፍ ውድድር ለመካፈል የሚያበቃው ሚኒማ ደግሞ 2.10 ሜትር መሆኑን ጠቅሶ በማዕከሉ ባሳለፈው የሁለት ዓመት ቆይታ 1.95 ሜትር መዝለሉ ወደ እነዚህ የውጤት ደረጃዎች የሚደርስበትን ሁኔታ የሚጨበጥ እንዳደረገውም ተናግሯል፡፡  ከ4 ዓመታት በኋላ ከማዕከሉ ተመርቆ ሲወጣ አገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ መወከል እንደሚችል ምናልባትም በከፍታ ዝላይ የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር  እንደሚችል እርግጠኛ እየሆነ መጥቷል፡፡
አሰልጣኝ ንጉሴና ሙያቸውን የማሳደግ ጥያቄያቸው
አሰልጣኝ ንጉሴ አደሬ በማዕከሉ የአጭርና መካከለኛ ርቀት  እንዲሁም የሜዳ ላይ ስፖርቶች አሰልጣኝ ሆነው  እያገለገሉ ናቸው፡፡  በሜዳ ላይ ስፖርቶች  እንዲሁም በአጭርና በመካከለኛ ርቀት ቀድሞ ከነበሩት የተሻሉ ስፖርተኞችን ማዕከሉ በማውጣት  እየተሳካለት መሆኑን ለስፖርት አድማስ የተናገሩት አሰልጣኙ፤ በስራቸው የሚከተሏቸው የስልጠና ሂደቶች  የሙያ ብቃታቸውን  በሚያሳድጉበት አቅጣጫ እየወሰዳቸው መሆኑን ይመሰክራሉ።  ከኮተቤ የመምህራን ማሰልጠኛ በስፖርት ሳይንስ ተመርቀው ከዚያ በአሰልጣኝነት ሙያቸው በማገልገል ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናቸው፤ ከጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማዕከል በፊት በኦሮሚያ ክልል እና በለገጣፎ የአትሌቲክስ ቡድኖች በሙሉ ሃላፊነት የሰሩበትም ልምድ እንዳላቸው ፤ በ800፣ በ1500 ሜትር በዝላይ እና በውርወራ ያሰለጠኗቸው ስፖርተኞች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድር በመሳተፍም እንደተሳካላቸው አሰልጣኝ ንጉሤ አደሬ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በኦል አፍሪካን ጌምስ እንዲሁም በዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ በቻይና ናይጂንግ 2015 ላይ ዋና አሰልጣኝ ሆነው በመስራት አመርቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝነት የሶስተኛ ደረጃ 3 ሰርተፍኬት አለኝ የሚሉት አሰልጣኝ ንጉሴ ግን በማዕከሉ ቆይታቸው የብቃት ደረጃቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች የሚያሳድጉበት እድል እንዲፈጥርላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ሆኖ ለመስራት   ደረጃ 4 የአሰልጣኝነት ማዕረግ ማግኘት ይኖርብኛል በማለት  ለስፖርት አድማስ የተናገሩት አሰልጣኝ ንጉሴ፤  ለዚህ አይነት የአሰልጣኝነት ደረጃ በመብቃት የተሻለ ለመስራት አቅም እንዳላቸው ለማስገንዘብ በማዕከሉ በሚገኝ ቢሯቸው ተገኝተን ስራቸውን እንድንታዘብ አድርገው ነበር።  በርግጥም የአሰልጣኝ ንጉሴ አደሬን ቢሮ ለጎበኘ  በአጭርና በመካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ እንደሆነና ስኬታማ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ለመረዳት አይቸገርም፡፡ የሰልጣኞቻቸውን የልምምድ ፕሮግራሞች፣ የውጤት ታሪክና የመሻሻል ሂደቶች በየዕለቱ እየመዘገቡ በአጀንዳቸው ያሰፍራሉ። በቢሯቸው በተለያዩ ቦታዎች በተቀመጡ ቦርዶችና ግድግዳዎች ላይ የተለያዩ ቻርቶች፣ ግራፎች እና ሌሎች  አሀዛዊ መረጃዎች ለጥፈዋል፡፡ ተገቢውን የሙያ ማሻሻያ  የሚያገኙ ከሆነ ያለጥርጥር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአጭርና መካከለኛ ርቀት፣ እንዲሁም በሜዳ ላይ ስፖርቶች የላቁ ውጤቶችን እንደሚያስመዘግቡ በልበ ሙሉነት መመስከር ይቻላል፡፡
በተለይ ከስልጠና ስራቸው ጎን ለጎን ከአሰላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአትሌቶች አመጋገብ ላይ ልዩ ጥናትና ምርምር እያደረጉ መሆናቸውም የሙያ ማሳደግ ጥያቄያቸውን ተገቢነት የሚያመለክት አብይ ማስረጃ ነው፡፡ አትሌቶች የተጠና የአመጋገብ ስርአት እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው፡፡
ይቀጥላል

Read 2805 times
Administrator

Latest from Administrator