Monday, 19 June 2017 10:23

ኳታር ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ከኤርትራ-ጅቡቲ ድንበር አስወጣች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ኤርትራና ጅቡቲ እነ ሳኡዲን መደገፋቸው ሳያስቆጣት አልቀረም ሞሮኮና ኢራን ለኳታር የምግብ እርዳታ ልከዋል

     ኤርትራና ጅቡቲ በመካከለኛው ምስራቅ በተቀሰቀሰውና ከሰሞኑ ተባብሶ አገራትን ለሁለት በከፈለው የኳታር ጉዳይ፣ ከሳኡዲ አረቢያና አጋሮቿ ጎን እንደሚቆሙ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ኳታር በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት በፈጠረው አካባቢ አስፍራቸው የነበሩ የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ማስወጣቷ ተዘግቧል፡፡
ኤርትራና ጅቡቲ ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ፤ ኳታርን የሽብርተኝነት አጋር በሚል ካገለሉት የእነ ሳኡዲ አረቢያ ቡድን ጎን እንደሚቆሙ በይፋ ማስታወቃቸው የኳታርን መንግስት ሳያስከፋው እንዳልቀረና አገራቱ በይገባኛል ሲጋጩበት ከነበረው የድንበር አካባቢ የሰላም አስከባሪ ወታደሮቹን ለማስወጣት እንደገፋፋው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የኳታር መንግስት የሰላም አስከባሪ ወታደሮቹን ከአካባቢው ማስወጣቱን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ቢያስታውቅም፣ ውሳኔውን ለማስተላለፍ የገፋፋውን ምክንያትም ሆነ ያስወጣቸውን ወታደሮቹን ብዛት በተመለከተ ግልጽ መረጃ አለመስጠቱን ዘገባው ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 ኤርትራና ጅቡቲ በሚያዋስናቸው ድንበር ላይ በሚገኝ አንድ ስፍራ ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ የድንበር ውዝግቡ ወደ ግጭት ማምራቱን ተከትሎ፣ ኳታር የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን በአካባቢው ማስፈሯን ገልጾ፣ አገራቱ በሰሞኑ ውዝግብ ከእነ ሳኡዲ ጎን መቆማቸው ኳታርን ለእዚህ ውሳኔ እንደገፋፋት ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ሞሮኮና ኢራን ሽብርተኝነትንና አሸባሪ ቡድኖችን ትደግፋለች በሚል ከተለያዩ አገራት ውግዘት ወደገጠማትንና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ወደሚያሰጋት ኳታር የምግብ እርዳታ መላካቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሞሮኮ መንግስት ለኳታር የምግብ እህል በአውሮፕላን መላኩን ባለፈው ረቡዕ ያስታወቀ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሰብዓዊ ድጋፍ እንጂ ከፖለቲካ ጋር እንዳይገናኝብኝ ሲል የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አበክሮ ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡ ኢራንም በተመሳሳይ ሁኔታ በአራት የጭነት አውሮፕላኖች የምግብ እህል ወደ ኳታር መላኳን ያስታወቀች ሲሆን፣ በቀጣይም በየዕለቱ 100 ቶን ፍራፍሬና አትክልት ወደ ኳታር ለመላክ ማቀዷን ዘ ኢንዲፔንደንት ጠቁሟል፡፡
የኳታር የፋይናንስ ሚኒስትር ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ የአለማችን እጅግ ሃብታም አገር የሆነቺው ኳታር ከውግዘቱ ጋር ተያይዞ ሊገጥማት የሚችለውን ቀውስ በብቃት መቋቋም የሚያስችላት በቂ ሃብት አላት ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
 ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በኳታርና በጎረቤት አገራት መካከል የተፈጠረው ችግር፣ የየአገራቱ ዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እንዲጣሱ በር የሚከፍት መሆኑን በመጠቆም፣ ሁሉም አገራት የዜጎችን መብት ላለመጣስ እንዲጥሩ፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ዛኢድ ራድ አል ሁሴን ባለፈው ረቡዕ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና ባህሬን፤ ለኳታር ያላቸውን ሃዘኔታ ገልጸዋል ባሏቸው ሰዎች ላይ “የእስርና የገንዘብ ቅጣት እንጥላለን” የሚል ዛቻ እየሰነዘሩ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ አገራቱ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 1973 times