Monday, 19 June 2017 09:57

ዘርዐ ያዕቆብን አስቤ እንዲህ አልኩ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

 (የመጨረሻ ክፍል)
 
                        ኮከብ እም ኮከብ ይኸይስ እም ክብሩ
                         
    ስለ ቅዱሳን መጻህፍት ምርምር
ዘርዐ ያዕቆብ ስለ ቅዱሳን መጻህፍት ያደረገውን ምርምር ከተጠቀመባቸው ሦስት መሰረታዊ የሃይማኖት መጻህፍት በመነሳት በሦስት ክፍሎች ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ክፍል ስለ ሙሴ ህግጋት ሲሆን፤ ሁለተኛው ክፍል ስለ ወንጌል ቃል ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ቁርዐንን ይመለከታል። ለዛሬው ግን ነጥቅሉ እንመልከተው፡፡ በፈጣሪ መኖርና አለመኖር ያደረገውን ምርምር ባለፈው ሳምንት አይተነዋልና፤ የዘርዐ ያዕቆብ አማኝ ፈላስፋነት የሚያጠያይቀን አይመስለኝም። ለማንኛውም ግን እርሱ እንዲህ እንዳለን እናስታውስ፡- ‹‹አስቤም አልኩ፤ …ከተትረፈረፈው ትልቅነቱ ትልቆችን ፈጥሯልና፤ ሁሉን የሚያስተውል አስተዋይም ነው፤ ምክንያቱም ከተትረፈረፈው አስተዋይነቱ አስተዋዮች አድርጎ ፈጥሮናልና። ልንሰግድለትም ይገባናል፤ ምክንያቱም የሁሉ ጌታ ነውና። ሁሉን የያዘ ስለሆነ ወደ እሱ ስንጸልይ ይሰማናል።›› ዘርዐ ያእቆብ አምላኩን በዚህ መልኩ ተዋውቆታል፤ ስለሆነም ወደ አምላኩ መጸለይ እንዳለበት አምኗል፤ የፈጠረው አምላክም ያላንዳች ማጉላላት ጸሎቱን እንደሚሰማው እርግጠኛ ሆኗል።
የዚህ ዓለም ህይወትን በተመለከተ፣ የህይወት ተልዕኳችንን ስለማወቅና፣ የህይወት ትርጉምንም በተመለከተ እንዲህ ይመራመራል፡- ‹‹አስቤም አልኩ፤ እግዚአብሔር አስተዋይ አድርጎ ከፈጠረኝ እንዲሁ ለከንቱ ለእንደዚሁ አልፈጠረኝም፤ ተመራምሬ እሱንና ጥበቡን በፈጠረኝ መንገድ እንዳስተውለውና እስካለሁ ድረስ እንዳመሰግነው ነው እንጂ።›› ዘርዐ ያእቆብ እዚህ ላይ እግዚአብሔር ምን እፈይድለት፣ ምን እረባው ብሎ ፈጠረኝ? ብሎ ቀደም ብሎ በውስጡ የሚመላለስን ጥያቄ የያዘ ይመስላል። ለዚያም ደግሞ ምላሽ አላጣም፤ መቼም ዝም ብሎ ለከንቱ ነገር አልፈጠረኝም፤ ይልቁስ ለምን ፈጠረኝ? ብዬ ተመራምሬ ምስጢሩን እንድረዳና እርሱንም በማመስገንና በማምለክ እንድኖር ፈጥሮኛል እንጅ፥ ይልና ለራሱ ምላሽ ይሰጣል። ‹‹ሸክላ ሰሪውን፤ ጆሮዬን እዚህ ላይ አድርግልኝ ሊለው ይቻለዋልን?›› የሚለውን የወንጌል ቃል በልቡ እያመላለሰ የተፈላሰፈ ይመስላል። እዚህ ዓለም ላይ የመገኘታችን ሚስጢር ምንም ነገር ሳይሆን ፈጣሪ እዚህ እንድንሆን ስለወደደ ነው፤ አርፋችሁ ተቀመጡ ይለናል - ዘርዐ ያእቆብ።
ለዘርዐ ያእቆብ በቀላል የሚጨበጥ፣ በቀላል የሚከናወን ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ድካምንና ምርምርን ይጠይቃል። ምናልባት የምንተነፍሰው አየር ብቻ ሊሆን ይችላል ያለ ድካምና ምርምር እንዲሁ በስልቹነት የምናገኘው። የእውቀት ማወቂያ ዘዴዎችን በጥልቀት ይመረምራል እንዲህ እያለ፡-
‹‹አስቤም አልኩ፤ ሰዎች ሁሉ ሐሰትን እንጂ እውነትን የማያስተውሉት ለምንድነው? የሰው ተፈጥሮው ደካማና ስልቹ ስለሆነ መሰለኝ። ሰው እውነትን ይወዳል፤ አጥብቆም ያፈቅራታል። የተፈጥሮን ስውር ነገሮች ማወቅ ይፈልጋል። ግን ነገሩ አስቸጋሪ ነው፤ ያለ ትልቅ ጥረትና ትዕግሥት አይገኝም፤ ሰሎሞን እንዳለው፥ ከፀሐይ በታች ስለተፈጠረው ሁሉ ልቤን ለምርመራና በጥበብ ለመፈተን ሰጠሁ፤ ምክንያቱም ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ድካምን ሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ሰዎች መመራመርን አይፈልጉም፤ ከአባቶቻቸው የሰሙትን ያለ ምርምር ማመንን ይመርጣሉ እንጂ።››
የሰው ልጅ ስልቹና ደካማ ቢሆንም እውነትን ግን የተፈጥሮው ያህል አጥብቆ ይፈልጋታል፤ እውቀት ከፈጣሪ እንደሚሰጥ ቢያምንም፥ ፈጣሪ ደግሞ ያለ ድካምና ያለ ምርምር ያንን እውቀት እንድንደርስበት አልፈቀደም። ስለዚህም የሰው ልጅ አእምሮውን ማሰራት እዳ ሆኖ ተፈርዶበታል ይለናል ዘርዐ ያእቆብ፥ ለምስክርነት ጠቢቡ ሰሎሞንን እየጠቀሰ። ለዘርዐ ያእቆብ ማሰብ፣ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለመገንዘብ፣ በእያንዳንዷ አንቀጽ መጀመሪያ ላይ ስንት ጊዜ ‹‹አስቤም አልኩ›› እያለ እንደ ጻፈልን መቁጠሩ ሳይበጀን አይቀርም፤ ምንም እንኳ ድርሰቱን አሰልቺ ያስመሰሉበት ቢመስልም። ማሰብና የሰው ልጅ ኅልውና የተቆራኙ(Metaphysical relation) መሆናቸውን ለማሳየት ግን ጠቅሞታል።
የማሰብንና የመመራመርን ዋጋ ከሰማያዊነት፣ ከአልፋ ኦሜጋ፣ ከአማናዊነት ጋር በጥብቁ የተቆራኙ ናቸው ለዘርዐ ያእቆብ፤ ባሰብነውና በተመራመርነው ልክ ሕይወታችንን እንመራለን፤ በብዙ ድካምና ምርምር እውነትን ብናገኛት ይቺ እውነት ዘላለማዊት ናትና ሰማያዊ ህይወታችንንም እውነተኛ ታደርገዋለች። እውነትን ለማግኘት ከመመራመር ብንሰንፍና በእንቶ ፈንቶ፣ ባሉሽ አሉሽ ሕይወታችንን ብንመራ፥ በሰማያዊ ህይወታችንም የእንቶ ፈንቶ፣ ያሉሽ አሉሽ ሰፈርተኛ እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ከራሱ አንደበት እስኪ እንስማው፤
‹‹አንድ ሰው ደግም ሆነ ወይም መጥፎ እንደፈለገ እንዲሆን እግዚአብሔር የሥራው ባለቤት አድርጎ ፈጥሮታል። አንድ ሰው ክፉና ውሸታም ለመሆን ከመረጠ ለክፋቱ የሚገባውን ቅጣት እስኪያገኝ ድረስ ይቻለዋል። ደግሞ ሰው ሥጋዊ ነውና ለሥጋው የሚሻለውን ይወዳል። ለሥጋው የሚያስፈልጉትን በደግም ሆነ በክፉ ባገኘው መንገድ ሁሉ ይፈልጋል። እግዚአብሔር ሰውን የፈለገውን ለመሆን ምርጫን ሰጥቶ እንጂ ክፉ አድርጎ አልፈጠረውም። በዚህም ምርጫ ደኅና ከሆነ ለዋጋ፥ መጥፎ ከሆነ ለቅጣት የተዘጋጀ ይሁን››
በታላቁ መጽሐፍ እንደተጻፈውም፣ ብዙ ፈላስፎች እንደሚሉትም፣ የሰው ልጅ የነፃ ፈቃድ ባለቤት መሆኑን ያምናል። ሲዖል ገብቶ በእሳት መጋየት አሊያም በገነት ውስጥ መፍነሽነሽ ለሰው ልጅ እኩል የተሰጠ እድል እንጅ ፈጣሪስ ለማንም አያዳላም፤ ምነው ቢሉ እግዚአብሔር የስራውን ውጤት እንዲያገኝ አድርጎ ሰውን ፈጥሮታል ይለናል ዘርዐ ያእቆብ።  የሰማያዊ ፍርድ እና መከራ የሚጠብቃቸው ከሆነ የሰው ልጆች ስለ ምን ይዋሻሉ? እያለ ምርምሩን የቀጠለ ይመስላል - ዘርዐ ያእቆብ። በምርምሩም የደረሰበትን መደምደሚያ እንዲህ ያካፍለናል፡-
‹‹ገንዘብ ወይም በሰው ዘንድ መከበርን የሚፈልግ ውሸተኛ ሰው፤ ይኸንን በውሸት መንገድ የሚያገኘው ከሆነ ውሸትን እውነት እያስመሰለ ይናገራል። ምርምርን ለማይፈልጉ ሰዎችም እውነት ይመስላቸዋል። ጽኑ በሆነ እምነትም ያምኑበታል። ለተመራማሪ ግን እውነት ፈጥና ትገለጣለች፤ ምክንያቱም ፈጣሪ በሰው ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ንጹሕ ልቦና የሚመረምር የተፈጥሮን ሥርዐትና ሕጎች አይቶ እውነትን ያገኛል።››
እውነትን መመርመር ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው ብሎ ስለሚያምን፣ ዘርዐ ያእቆብ፤ ከእውነት ጋር ያለንን ግንኙነት ኅላዌአዊ ያደርገዋል። እውነትን መርምረን ደክመን ለፍተን የምናገኘው ገንዘብና ክብር ንጹህና የሚገባ መሆኑን ባይክድም፤ በውሸት መንገድ ያለ ድካምና ያለ ምርምር የሚገኝ ገንዘብም ሆነ ክብር ግን እዳ አለበት ይለናል። “ልማታዊ” ባለሃብትና “ልማታዊ” ፖለቲከኛ ወዮልሽ! ይላል - ዘርዐ ያእቆብ፡፡ እዚህ ላይ፤ ልማታዊ ባለሃብት ገንዘብ ፈልጎ፣ ልማታዊ ፖለቲከኛም በሰዎች ዘንድ መከበርን ፈልጎ ውሸቱን እውነት እያስመሰለ ይናገራልና። ፈጣሪ ለሁሉም በልቡ ውስጥ ንጹሕ ልቦና ፈጥሮለታልና፣ ከዚች ልቦናው ያልመነጨን እውነት የተጎነጨ ሁሉ የእዳው ባለቤት ነው ይላል። እንዲህ ያለ ሰው እራሱ ተሳስቶ ብቻ አይቀርም ሌሎች ደካሞችን፣ እውነትን ለመመርመር የሰለቹትን ሁሉ ይዟቸው ገደል ይገባል፤ ምክንያቱም ሰነፎች እውነት መስሏቸው በጽኑ እምነት አምነውበት ይከተሉታልና። ገንዘብን ወይም በከንቱ መከበርን የሚሻ ሰው እራሱም ተሳስቶ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታል።
ፈጣሪ በሴት ላይ ያደረገው የተፈጥሮ የመውለድ መቻል ምልክት እንዲሆን በየ28 ቀኑ ደም ይፈሳታል፤ ይህ የፈጣሪ ጥበብ ሆኖ ሳለ ሙሴ ግን ሴቲቱ ደም በሚፈሳት ወቅት የረከሰች ናት ይላል። ይህ ከፈጣሪ ስራ ጋር ይጋጫል፥እንዴት የራሱን ስራ ያረኩሳል ይለናል- ዘርዐ ያእቆብ። ጉዳዩ ለክርክር እንዲመቸው ወደ አላስፈላጊ ፅንፍ ያንፏቀቀው ይመስላል። ለሙግት እንዲመቸው ብሎ እንጅ ሲጀምር ሙሴ የሴቶች ደም መፍሰስ የፈጣሪ ስራ መሆኑን አንድም ቦታ ላይ አልካደም፤ ሲቀጥል ሙሴ የፈጣሪን ስራና ትዕዛዝ በማክበሩ ‹‹በግብፅ ላይ አምላክ አድርጌ ሾምኩህ›› የተባለ ነብይ ነውና፤ የፈጣሪን ስራ የሚያፈርስበት አንዳች ምክንያት አይኖረውም። እኔ እንደሚመስለኝ፣ በዚህ ወቅት ሴት የሚፈሳት ደም ቆሻሻነት ስላለውና ለእርሷም የአምልኮ ስርዓት ለመጠበቅ ወደ ቤተመቅደስ ለመሄድ ስለማይቻላት፣ በተለየ ሁኔታ ከስርዓተ አምልኮው መቅረት የምትችልበት የተፈቀደ የእረፍት ጊዜ እንዲኖራት ሙሴ በዘዴ ጉዳዩን ከእርኩሰት ጋር አያይዞ አስቀምጦታል።
ግብረ አወስቦን በተመለከተ ዘርዐ ያእቆብ ፈታ ብሎ የሚፈላሰፍ ይመስላል፥ ይችን ይችንማ አትንኩብን የሚል ቅላጼ አለው - ሃሳቡ። እንዲህ ይላል፡-‹‹እግዚአብሔር በሰው የተፈጥሮ ሕግ ውስጥ ያቆመው ይኸ ግንኙነት እርኵስ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም የእጁን ሥራ አያረኲስም። ሙሴ ግን ግንኙነት ሁሉ እርኲስ ነው  አለ። ግን ይኸንን የሚል ውሸተኛ እንደሆነና ይኸንን የፈጠረውንም ውሸተኛ እንዳደረገው ልቦናችን ይነግረናል።›› ወንድ ልጅ ወደ ሴት ፥ሴት ልጅ ወደ ወንድ የመሳብ ሁኔታ ተፈጥሯዊና ከፈጣሪ የተፈቀደ እንጅ ሙሴ እንደሚለው የረከሰ ተግባር አይደለም ይላል - ዘርዐ ያእቆብ። ይህንን የተፈጥሮ የመሳሳብ ገፊ ኃይል እንቋቋማለን ቢሉ ግን በዝሙት ወድቀው እናገኛቸዋለን ይለናል፤ እርሱ ጨላጣ አራዳ ስለሆነ ይቺን ጥቅስ እያጣቀሰ ጥገኝነት የገባበትን የአቶ ሐብቱን አገልጋይ (በዘመናችን ቋንቋ ገርዳሜዋን) አገባና ላይፉን ይቀጫል። አራዳው መነኩሴ ዘርዐ ያእቆብ፤ ከዚህ የዘለለ አመክንዮ ያለው አይመስለኝም፤ የሙሴም፣ የጳውሎስም በእርሱ መከሰስ ምክንያት ይኸው ነው። ጳውሎስ ላይ የሰነዘረውን ወቀሳና አበሳ ትቶ፣ ‹‹ያልቻለ ያግባ›› ብሏል የምትስማማውን የጳውሎስ ጥቅስ መርጦ ማግባት ይችል ነበር መጀመሪያውኑ። እርሱ ግን ክሱን እንዲህ ያወርደዋል፡-
‹‹ዳግመኛም፥ የክርስቲያን ሕግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት አሉ። ለማስረጃዋ ታምራትም ተገኝተዋል። ግን ጋብቻ ፈጣሪ ሥርዐቶች ውስጥ እንደሆነ ልቡናችን ይነግረናል፤ ያስረዳናልም።  ምንኲስና ታዲያ የፈጣሪን ጥበብ ይሽራል፤ ምክንያቱም ልጆች መውለድን ይከለክላል፤ የሰውንም ፍጥረት ያጠፋል። የክርስቲያን ሕግ፤ ምንኲስና ከጋብቻ ይሻላል ስትል ውሸት ተናግራለች።››
አጥንት የሚያረሰርስ ዜማ፤ እንደ ቅዱስ ያሬድ ባያዜምልንም፣ እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሃይማኖትን ፈትፍቶ ባይጽፍልንም፣ እንደ ተዋኔ ቅኔ ባይቀኝልንም፣ ዘርዐ ያእቆብ ያቅሙን ምርምር አቆይቶልናልና ፥ የኮከብና ኮከብ ክብር ቢለያይም ፥ከከዋክብት እንደአንዱ ያድርገው እንላለን። ቸር እንስንብት።      

Read 1541 times