Monday, 19 June 2017 09:54

የጋሽ አያልነህ የአርት አዳራሽ የመገንባት ህልም?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ገጣሚ ባለቅኔና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ከዓመታት በፊት ለእርሱ፣ ለሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ለሌሎችም ታዋቂ የኪነ- ጥበብ ሰዎች የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አንድ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ ‹‹መሬት ውሰዱና
አንድ ነገሩ ስሩ›› የሚል የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ቦታ መርጠውና የሚሰሩትን አስታውቀው፣ ይሁንታውን ቢጠብቁም ለአንዳንዶች ሲሰጥ፣ ለሌሎች ‹‹እምቢም እሺም›› ሳይባል እስካሁን መቆየቱን ጋሽ አያልነህ ሙላቱ በቅርቡ በተደረገው የደራሲያን ማህበር የጥበብ ጉዞ ላይ ቅሬታውን ለጋዜጠኞች ገልጿል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በጉዳዩ
ዙሪያ ከጋሽ አያልነህ ሙላቱ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

    ከግብዣም ባለፈ ካርታ እስከመውሰድ ደርሳችሁ ነበር፡፡ እንዴት እስካሁን ሳይሰጣችሁ ቀረ?
እውነት ነው፤ ወደዚያ ሄደን አንድ ቁም ነገር እንድንሰራ የጋበዘን አቶ ያለው አባተ ናቸው፡፡  ቦታ መርጠን ከጨረስን በኋላ… የከተማው ማዘጋጃ ቤት ካርታ ሰጠን፡፡ ይሄው ሰባትና ስምንት  አመት ሙሉ እምቢም የለም… እሺም የለም፡፡
ለመሆኑ  በቦታው ላይ ምን አይነት ስራ ለመስራት ነበር ያቀድከው?
ያው እኔማ እንግዲህ አዲስ አበባ እየተፈጋፈገ የመጣውን የኪነጥበብ ሙያ፤ እዚህ አንድ የማልመውን አይነት ማዕከል አቋቁሜ፤ ብዙ ተተኪ የኪነ-ጥበብ ወጣቶች ለማፍራት ነበር ሀሳቤ፡፡ ባላውቅኩት ምክንያት እንደዚህ ሆነ እንጂ፡፡
የአንተ ብቻ ነው ወይስ ሌሎቹም ተከልክለዋል?
ለሙላቱ ፈቅደውለታል፡፡ እሱ ቀደም ብሎ መጣ። እኔም እሱን ተከትየው መጣሁ፡፡ ለእኔም ቦታ ምረጥ ተብዬ ቀኑን ሙሉ ስንዞር ውለን፣ አንድ ቦታ ተገኘና ይሄንን መርጫለሁ አልኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ መሀንዲሱ አጣራና ቦታው ባዶ ነው፤ የተያዘ አይደለም አለ፡፡ በ2002 ዓ.ም ካርታ ሰርተው፣ ፊርማ ተፈራርመንና ተዋውለን ቦታውን ተረከብኩኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውክልና ሰጥቼ ወኪሌ ቢመላለስም ምላሽ የለም። ቦታው የአካባቢውን ተወላጆች ለማበረታታት በሚል የተሰጠን በነፃ ነው፡፡ ታላላቅ ሰዎችን ወደ ከተማዋ ለማምጣትም ጭምር ነው፡፡ እኛም ይህ ግብዣ ሲመጣ በጣም ነው ደስ ያለን፡፡ እኔም በግሌ በዚህ ከተማ (ባህርዳር) በዚህ እድሜዬ ሳልሞት፣ አንድ ኤክስፐርመንታል የሆነ የአርት አዳራሽ ሰርቼ፣ ወጣቱ እንዲሰለጥንበት፣ ልዩ የሆነ የኪነ- ጥበብ ዝግጅት እንዲካሄድበትና ለእኔም መታሰቢያ እንዲሆን… ጉዳዩን በደስታ ነበር የተቀበልኩት፡፡
ካርታውን ከወሰድክ በኋላ ማዕከሉን ለመስራት ምን ዝግጅቶችን አድርገህ ነበር?
ለምሳሌ አዲስ አበባ መሀል ከተማ ያለውን ቤቴን ሸጥኩኝ፡፡ አሜሪካ ተጋብዤ በሄድኩበትም ሰዓት ከሆሊውድ ባለሙያዎች ጋር ተነጋግረን፣ የአዳራሹን ዲዛይን ሰራንና ተመልሼ ‹‹መሬቱን ስጡኝ›› ስል ‹‹እዚህ ቦታ ላይ የማንጎ፣ የአቡካዶና መሰል ዛፎች ተተክለዋል፤ የዚህን ዋጋ መክፈል አለብህ›› ተባልኩ፡፡ ካሳ መክፈል አለብህ አይነት ነገር ነው፡፡ ‹‹ስንት ነው የምከፍለው›› ስል፤ ወደ 2 ሚ.ብር ነው ተባለ፡፡ ‹‹2 ሚ.ብር ከከፈልኩ ምኑን በነፃ ሆነ? ነፃ አድርጋችሁ ትሰጡኝ እንደሆነ ስጡኝ›› በሚል ስጠይቅ፣ ቆየሁ፡፡
የመጨረሻ ሙከራ አላደርግህም?
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ብዙ የደብዳቤ መፃፃፍ ከተደረገ በኋላ፣ ባለፈው ሶስት ወር ለባህርዳር ዩኒቨርስቲ ‹‹ለአዝማሪ ፕሮግራም›› ተጠርቼ መጥቼ በነበረበት ወቅት ሳነጋግራቸው፣ ቦታው የጣና ባፈርዞን ስለሆነ መሬቱ አይሰጥም ብለው አረፉ፡፡ አንደኛ እኔ የመረጥኩት ቦታ ጣና ዳር ሳይሆን አባይ ነው፡፡ ሁለተኛ 2002 ዓ.ም የተሰጠ መሬት፤ ከ7 ዓመት በኋላ እንዲህ ዓይነት ምላሽ መስጠት ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ነው አልኩና፤ የመጨረሻ ደብዳቤ ፅፌላቸው ወጣሁ፡፡ አሁንም እምቢታ የሚባል ነገር የለም፤ ፈቃደኛ ሆነው ሊሰጡኝም አልቻሉም፡፡
ቦታው አሁን ምን እየተሰራበት ነው?
ቦታው አሁንም ባዶ ነው፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ 30 እና 40 እየሆኑ በቡድን ጫት እየቃሙበትና ሙዚቃ በሀይል እየተከፈተ፣ መደነሻና ጥሩ መንፈስ የሌለው ቦታ ሆኗል፡፡ እንደውም ሄዳችሁ አይታችሁ ያለበትን ሁኔታ ‹‹የትውልድ መበላሻ››  መሆኑን ለሚመለከተው አካል ብታስገነዝቡ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ የጋዜጠኛ አንዱ የስራ አካል ይመስለኛል፡፡ ይህ ቦታ ተሰጥቶኝ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ስንት ወጣት የኪነ- ጥበብ ሰዎችን ባፈራሁበት ነበር፡፡ እንደምታውቁት እኔ አዲስ አበባ፣ በቀንዲል ቤተ ተውኔት በርካታ ደራሲያንን፣ የቴአትር ባለሙያዎችንና ገጣሚዎችን፣ አፍርቻለሁ፡፡ አሁን አሉ የሚባሉ ትልልቅ ደራሲያን፣ የቴአትር ሰዎች፣ ገጣሚዎች፣ አብዛኛዎቹ ከኔ የወጡ ናቸው፡፡ በዚህም አካባቢ ይህንን መንፈስ ይዤ መጥቼ እሰራለሁ የሚል ህልም ነበረኝ፡፡ መጨረሻ ላይ ወደ ስድስት ገፅ ደብዳቤ ፅፌ ለክልሉ ፕሬዚዳንትም ለማዘጋጃ ቤቱም አስገብቻለሁ፡፡ ይሄንን ነገር ለእናንተ ለጋዜጠኞች ስናገር፤ አቤቱታ እያሰማሁ ሳይሆን በቃ ያለውን እውነታ ሁሉም ይወቀው ብዬ ነው፡፡ አንድ የከተማ አስተዳደር ወዶና ፈቅዶ መሬት ከሰጠና ማዘጋጀ ቤቱ ካርታ አውጥቶ ካስረከበ በኋላ፣ ሰባት አመት ሙሉ ማጉላላት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ይሄ ሆን ተብሎ ታስቦበት የተደረገ ሴራ መሆኑን ግን ሁሉም ይወቀው ፡፡
አሁን ምን አስበሀል?
ምን አስባለሁ? ለማንስ አቤት ይባላል? አንድ ጊዜ የከተማው መሬት ልማት ድርጅት 3 ነገሮችን ፅፎላቸው ነበር፡፡ አንደኛ፡- በአስቸኳይ መሬቱ ላይ ያለውን ካሳ ከፍላችሁ፣ መሬቱን መልሱለት የሚል ሲሆን ሁለተኛው ይሄ ካልሆነ ተመሳሳይና ተመጣጣኝ ቦታ ፈልጋችሁ ስጡት የሚል ነው። ሶስተኛውን አሁንም ዘነጋሁት እንጂ ከነዚህ ሀሳቦች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁንም ለዚህ ሁሉ መልስ የለም፡፡  ይህን ጉዳይ ከላይ እስከ ታች ያሉ ባለስልጣናትና ሀላፊዎች ያውቁታል፡፡ ለምን ምላሽ እንዳልሰጡኝ ምንም የሚገባኝ ነገር የለም፡፡ ከእኛ መሀል ለሙላቱ ሰጥተውታል፡፡ አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መጀመሪያም መጥቶ አልጠየቀም፡፡
ካርታውን ሲሰጡህ መጓተትና ማመላለስ ነበረው?
በፍፁም፡፡ ይገርማችኋል… ካርታውን ሰርተው የሰጡኝ በአንድ ቀን ጀንበር ነው፡፡ በጣም አጣድፈው ነው የሰጡኝ፡፡ ይሄኔ ነው መሀል አዲስ አበባ የነበረ መኖሪያ ቤቴን ተንደርድሬ የሸጥኩት፡፡ ደግሞ ይሄ ቤት ቢገነባ የኔ አይደለም፤ የቀሪው ትውልድ ነው እኔ ነገ አልፋለሁ፡፡ የሚገርማችሁ ቤተሰቤም ይህንን ማዕከል እንዳይወርስ ኑዛዜ ሁሉ አድርጌ ነበር፡፡ ይሄ እኔን ሳይሆን ትውልዱን እውቀትና ጥበብ መከልከል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የሚቆረቆረኝ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች ሲሞቱ የምንተነፍስበት የቴአትር መድረክ እንኳን አልሰጡንም፡፡ ያው የመንግስት ቴአትር ቤት ነው፡፡ መንግስት ሲፈልግ ውጣ ይላል፤ ሲፈልግ ይቀበላል ሲፈልግም የአይንህ ቀለም አላማረኝም ብሎ ያባርርሀል፤ የምታውቁት ነው፡፡ ከዚህ ነፃ ልንወጣ የምንችልበትን መድረክ ሳልሰራ እንደ ሎሬት ፀጋዬ፣ መንግስቱ ለማ ዝም ብዬ መሞት አልፈልግም። እነዚህ ትልልቅ ሰዎች ለእኛ ነፃ መድረክ ትተውልን አላለፉም፤ ከመሞቴ በፊት የባህር ዳር ከተማ ራሱ መጥቶ እድል ሲሰጠኝ፣ ይህን እውን አድርጌ ማለፍ ፈለኩኝ፡፡
እኔ ለዚህ ከተማ አስተዳደር በፃፍኩት ደብዳቤ ላይ፣ አብሬ ያያዝኩት አዲስ አበባ ላይ መንግስት 6 ሺህ ካሬ ቦታ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የሰራበትን ቦታ ከብዙ  ጊዜ በፊት ሰጥቶኛል። ካርታውንም ሁሉንም አዘጋጅቶ ሰጥቶኛል፡፡ ከዚያም 70 በመቶውን መንግስት ራሱ፣ 30 በመቶ የግንባታውን ወጪ ራሴ እንድከፍል ጠየቀኝ፤ 30 በመቶውን መክፈል አልቻልኩም፡፡ 30 በመቶው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሰላ፣ ወደ 5 ሚ. ብር ደረሰ፤ ይሄን ከየት አመጣለሁ? መንግስት ግን የሚችለውን ያህል ተባብሮኛል፡፡ ያንን ጥዬ ነው የመጣሁት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የታመቀ ቴአትር ቤትና የቴአትር ባለሙያ አለ፡፡ ለምን ባህር ዳርና አካባቢው ይህን እድል አያገኝም ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ አሁን ግን ተስፋ ቆረጥኩ፡፡
ምናልባት ቦታና ካርታው ከተሰጠህ በኋላ ፈጥነህ ወደ ግንባታው ሳትገባ ቀርተህ ይሆን?
በፍፁም፡፡ ይሄማ የአባት ነው፡፡ መጀመሪያ ፈጥነህ ወደ ስራ መግባት አለብህ የለብህም ለማለት መሬቱን ማስረከብ አለባቸው፤ አላስረከቡኝም፡፡ እኔማ ካርታው ሲሰጠኝ፣ ቦሌ ላይ ያለውን ቤቴን መሸጤን ነገርኳችሁ እኮ!
አሁን ቤቱ የተሸጠበት ብር የት ሄደ? አንተስ ቤትህን ሸጠህ የት ነው እየኖርክ ያለኸው?
ብሩ ተቀምጧል፤ ያ ብር የኔ አይደለም፤ ባህር ዳር ላይ ለሚገነባው ኤክስፐርመንታል ቴአትር ቤት ግንባታ የሚውል ነው፡፡ ቤተሰቤም አይወርሰውም። የት ነው የምትኖረው ላላችሁት? ከመሀል ቦሌ ወጥቼ፣ ትንሽ ኤልሼፕ ቤት ሰርቼ እዚያ ወድቄያለሁ፤ ይሄው ነው፡፡ በጣም ማዘኔን ግን አልደብቃችሁም። አሁንም እንድታውቁት ነው፤ ክስ አይደለም፤ ይህ አራት ሺ ካሬ ሜትር አሁን ያለበት ሁኔታ ያሳዝናል፤ ሄዳችሁ ብታዩት ጥሩ ነው፡፡

Read 2095 times