Monday, 19 June 2017 09:43

በዘፈን ግጥሞች ውስጥ፣ ሰቃይ ስንኞችን ፍለጋ

Written by  እንዳልረሳው ጉሳዬ
Rate this item
(22 votes)

  ሠላም የአዲስ-አድማስ ወዳጆች፣ ሠላሙ ይብዛላችሁ፣ ከድንጋጤ ይሰውራችሁ፡፡ ዘፈን ስሰማ በግጥሞቹ ለመደመም እሞክራለሁ፡፡ እናም ብዙ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት የግጥም ስንኞች በጣም ገዝፈው ወይም በግዝፈት ውስጥ ቀላል ሆነው አገኛለሁ፡፡ ሁሌም ከሚመስጡኝና በዘፈን ግጥም ውስጥ በኔ እይታ ሰቅለው ወይም ወርደው ካገኘኋቸው ውስጥ ጥቂቱን ላካፍላችሁ ወደድኩኝ፤ አብረን እንቆይ፡፡
ከቴዲ አፍሮ እንጀምር፡፡ አንድ - ከቀደመው አልበም፡-
ለባለቤቱ ያለውን ፍቅር፣ ክብርና አድናቆት ለመግለፅ የጀመረበት፣ ግን እንዳልበቃው በሚያስታውቀው “ፀባየ ሰናይ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ (ትንሽ አጠፍ አድርገነው)
ወተን ባለም ከፍታ ምድሪቱን ባናይ
የለም እንዳንቺ ቆንጆ ፀባየ ሰናይ፡፡
እያለ ያወድሳታል፣ ባየው ልክ ያነግሳታል፡፡ እኔ የግጥም ተራቃቂ ወይም አደገኛ ፀሃፊ አይይለሁም፣ ከብዙዎቹ አንዱ አንባቢና የግጥም ወዳጅ ነኝ፡፡ ግን የዚህ ግጥም ሃሳቡ ሳይንሳዊ በሆነ ልኬት አድናቆቱን እንደ መግለጽና የእይታውን ትክክለኛነት ማረጋገጫ የሚያጣቅስበት ሆኖ አይቼዋለሁ፡፡ ተመልከቱ፣ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ጉብሎች በሙሉ የማየት እድሉ የለውም፡፡ ስለዚህ ሃሳቡን፣ በልኩ አድርጎ፣ ሳያጋንን ሲገልፀው (እስኮፑን) ሲወስነው፣ “እኔ በምችለው ከፍታ ላይ ሆኜ፣ በእይታዬ ስር ካለፉት እንስቶች በሙሉ፣ አንቺ አንደኛ ነሽ” አላት፡፡ በዓለም አንደኛ፣ በአፍሪካ ሁለተኛ … አላላትም፡፡ እቅጩን ነው በልኳ የነገራት፡፡
ከአዲሱ አልበሙ አንድ ጨምረን ወደ ሌላ እንሂድ፡-
ስለ አፄ ቴዎድሮስ ማንሳቱ በራሱ ሊሰጠው የሚገባውን የክብር መጠን እንዳናውቅ፣ አስካሪ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በጣም የምቀርባቸው፣ የቤተሰቤ ያህል የሚሰሙኝ ታላቅ ህልም የሰነቁ ንጉሰ ነገስት ነበሩ፡፡ እሳቸውን ማስታወስ ታላቅነት ነው፡፡ እኔ ግን በዚህ የዘፈን ግጥም ውስጥ ያየኋቸውን ተራ እንዲሁም ምርጥ ስንኞችና አገላለፅ አንስቼ ላውራ፡፡
ለእራሱና ለሐገሩ ክብር፣ ራሱንና ህዝቡን ከሐፍረት ለመታደግ ህይወቱን የሰጠን ጀግና፣ የበታቹ የሆነውን ገብርዬን ስላጣው ብቻ “ተዋከበ” በሚል የወረደ ቃልና ሃሳብ፣ ንጉሰ ነገስቱን መሳል ደግ አይደለም፡፡ የእውነት ቴዲ ከፍ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ የዛችን ሰዓት “ውጪ ነብስ ግቢ ነብስ” ውዥቀት ለመከሰት የተጠቀመበት ስዕል፣ ለኔ ቤቱን ከመምታት፣ ወይም የዜማውን ፍሰት ጠብቆ ከመሄድ ያለፈ ፋይዳ የማያሳይ ተራ አገላለፅ ሆኖ በማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡
ይንን ልበ ሙሉ ጀግና-የጀግና ምልክት፣ ያንን ነበልባል እሳት፣ ያንን “ሙሉ” ንጉሰ ነገስት፣ ፍርሃት ያልፈጠረበትን፣ ግርማ ሞገሱ የገጠመን ንጉሰ ነገስት “ተዋከበና …ተዋከበና…” በሚል የሰፈር ግርግር በመሰለ የፈሪ መገለጫ ተራ ሃሳብ ሲገልፃቸው ማየት፣ ሁሉንም በዜሮ ከማባዛት አይተናነስም፡፡
“ባለቅኔው” ቴዲ፣ ወረድ ብሎ ደግሞ “መዋከብ” ብሎ ከገለፀው ሃሳብ መደምደሚያ ስንደርስ “የወገቡን እሳት፣ ከአፎቱ ላይ መዝዞ….” ይለናል፡፡
እኔ የወገብ እሳትን፣ እንደ ሽጉጡ አልስለውም፣ ይልቅ እንደ ወንድነት ነው የምስለው፡፡ “ንጉሱ ወገባቸውን ሊፈትሹ…” ቢባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ “በአማርኛ” ክብር በተላበሰ አገላለፅ ሊፀዳዱ ሄዱ እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ሃሳብ ተነስተን ስንስለው፣ የወገብ እሳት ማለት ከወንድነት፣ ከዘር ማስቀጠል ወዘተ … አንፃር ነው የማየው፡፡ በሽጉጥ መስሎት ቁጭ ሲል፣ አንዳንዴ ረጅም ታሪክ ወይም ሃሳብን ለማሳጠር ሲጥር የሚጎደፍረውን ቴዲን አየዋለሁ፡፡
ግጥሙ የዜማውን ምት እንዳያፈርስበት ሲል ብቻ ረጃጅም ሃሳብ ወይም ቃላቶችን “ፍርስ” የሚያደርግበትና በራሱ አይን ብቻ የሚያይበትን እይታ፣ ሌሎች ላይ ለማስረፅ ሲሞክር ይስተዋላል፡፡
ተመሳሳይ የሃረግ ጉድፈራን፣ በ”ጥቁር ሰው” አልበሙ ውስጥ፣ ስለ እምዬ ምኒሊክ በዘፈነው ዘፈን “… ባልቻ አባቱ ነብሶ፣…” ሲል የጎደፈረውን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ፣ ያንን ዘፈን ስሰማ ከመጨፈር ይልቅ፣ አልቅስ አልቅስ ይለኛል፣ ያስተክዘኛል፡፡ የሆነ የሚያሸብርና የሚያሳዝን የሙሾ ዜማ ነው የሚመስለኝ፤ የእውነት፡፡ እስቲ ስሙት፣ ሆ! ሆ! ሆ! እያልኩ ደረት መድቃት ነው የሚያምረኝ።
ይሄንን የዘፈን ግጥም ሲቀጥል፣ “… የወገቡን እሳት፣ ከአፎቱ ላይ መዞ…” ይላል፡፡ ምን ማለት እንደፈለገ ግልፅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቋንቋንና ጠቅላላ እውቀትን የሚያውቀው በተለያዩ የጥበብ ውጤቶች ነው፡፡
አንዴ በሆነ የጥያቄ እና መልስ ውድድር ላይ አንዲት ወጣት እንዲህ ተጠየቀች፣ “አስመራ ከአዲስ አበባ ምነ ያህል ትርቃለች?” ወጣቷ ለመመለስ ጊዜም አልወሰደባትም፣ “ሺ ሰማንያ” አለች፡፡ “እንዴት በአንዴ አገኘሽው?” ሲላት፣ “ሺ ሰማንያ ከሚለው ዘፈን” አለችው፡፡ ዘፈኑን ስለሰማች እውነተኛውን መረጃ በቀላሉ አስታወሰችው፡፡ ሺ ሰማንያ ጠብቂኝ።
ህፃናት ይህን  የቴዲን ዘፈን ይዘፍኑታል፣ ግጥሙን ያጣጥሙታል፣ “አፎት ማለት የሽጉጥ ማስቀመጫ ነው” ተብሎ በቴዲ አፍሮ ተነግሯቸዋል። የተሳሳተ እውቀት፣ ከዛ ከነሱ ጋር ሙግት፡፡ የሽጉጥ ማስቀመጫና የሰይፍ ማስቀመጫ የተለያዩ መሆኑን ብላቴናው በማህደሩ ውስጥ እንዲያኖረው በዚህ አጋጣሚ እመክራለሁ፡፡
እዚሁ “አፄ ቴዎድሮስ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ ደግሞ የምትገርም  ሃሳብ አለች፡፡ “… ግመሌን ላጠጣት ቀይ ባህር ወርጄ…” እያለ ይቆይና፣ እጥፍ ብሎ፣ ”… ግመሌን እንዳልመልሳት አንድ ገመድ አጣሁኝ…” በሚል ሃሳብ ዘፈኑን ይቀጥላል፡፡ “ጋሊ ሂሪረ ዱራቲ ላላ” ይላል ኦሮሞ ሲተርት፡፡ ግመል ከፊት ያለውን መሪ ተከትሎ ይሄዳል እንደማለት፡፡ እና ግመልን ከፊት ያለ ሰው አንዴ አሳይቶ ይመራታል፣ እንበል ያ ሰው ግመሊቱን ምሪት ሲያሳያት፣ መጀመሪያ በገመድ ጎትቶ ይሆናል፡፡ ግመሏን የሚመራት ገመድ አለ ማለት ነው፡፡ እና ቴዲ ዘሎ ስለ ግመል ሲያወራ፣ ቀይ ባህርን መሃል ላይ ምነው ስክት አደረገው? አድንቄዋለሁ፡፡ ቀይባህር ሄዳ የቀረችውን ግመል ለመመለስ አንድ ገመድ እየፈለገ ነው፡፡ ኤርትራን ባላውቃትም ትናፍቀኛለች፡፡ የሚመልሳት አንድ ገመድ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡
አስቴር አወቀ፡
በአንድ ወቀት ስለ ኤች.አይ.ቪ/አድስ ለማስተማር በወጣ የህብረት ካሴት ላይ (ነዋይ፣ ፍቅርአዲስ፣ አስቴር …ወዘተ ያሉበት ካሴት) አስቴር ስትዘፍን በጣመ የሚማርከኝን አንድ ግጥም ላካፍላችሁ፤
“እንደ ልጅነትህ እንደ ልጅነቴ
ላፍቅርህ አፍቅረኝ፣ በቀን ሶስት አራቴ…”    ትላለች፡፡
ይሄንን ግጥምና ሃሳቡን እንዴት እንደምወደው! የልጅነት ፍቅርን አስቡት፡፡ በጣም ንፁህ ነው። ያልተበረዘ፣ ያልተነካካ፣ ሁሌም አንደኛ፡፡ ስንቴ እንደምንጣላ፣ ስንቴ እንደምንታረቅ…. ግን ከሁሉም መጣላትና መታረቅ በኋላ ሁሌም ንፁህ ፍቅርንና መዋደድ እንደነበረን፣ የማይመለስ ልጅነታችንን በትዝታ አምጥተን እንድንደመምበት የሚያደርግ ፈዋሽ ግጥም ነው፡፡
መሐሙድ አህመድ፡
ፍቅሩ እንደሆነች እና ከልብ አፍቃሪዋ እንደሆነ እንድታውቅለት፣ እንዳትጠራጠር፣ እንድታምነው በቻለው መንገድ ሁሉ ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
“ፍቅሬ ለመሆንሽ፣ እርቀሽ ሳትሄጂ
ቃሌን የሰሙትን፣ ጠይቀሽ ተረጂ…”
እያለ ሊያስረዳት ይታገላል፡፡ እሷ ግን በቀላሉ ልትቀበለው የተዘጋጀች አትመስልም፡፡ እናም በጣም በማደንቀው ሃሳብ እንዲህ ይላታል፡-
“ንፋሱን ጠይቂው፣ ያስረዳሽ አብራርቶ
የልቤን አድምጧል፣ ስተነፍስ ገብቶ…”
ንፋስን፣ በቃ ይህ የምንተነፍሰው ንፋስን፣ መሐሙድ ለእማኝነት ቆጠረው፡፡ ምን አይነት ርቅቅ ያለ የውስጥ ስሜትን ገላጭ ሃሳብ ነው! “ልቤ”፣ “ልቤ”፣…. የሚል ያገር ዘፋኝ ባለበት ሃገር፣ ልብና ዘፈንን፣ በፍቅር መግለጫነት እንደ መሐሙድ የተጠቀመ ያለም አይመስለኝ፡፡ ልብ የፍቅር ጭንቅላት፣ እና የፍቅር ሃይል ማስቀመጫ ጥብቅ ሳጥን ነው (ጥብቅ - ጠንክሮ ይነበብ-እንደ ጥብቅ ደን)፡፡ እናም ከልብ አጠገብ ተጎራብቶ ያለ ደግሞ ሳምባችን አለ፡፡ ለመኖር መተንፈስ ያስፈልጋል። እናም፣ መሐሙድ ሲተነፍስ፣ ንፋሱ ከሳምባው ገብቶ ሲወጣ፣ ከልብ ጎረቤት ነውና በግድግዳ በኩል ምን ሲባል እንደነበር፣ ከዛ ጥብቅ ሳጥን ውስጥ የታመቀውን ፍቅርና ሃሳብ አይቷል፡፡ ሰምቷል፡፡
እናም መሐሙድ ይማፀናታል፣ “….ቃሌን የሰሙትን ወዳጆቼን ማመን ካቃተሸ ተይው፣ አላስቸግርሽም….ግን ግን
“ንፋሱን ጠይቂው፣ ያስረዳሽ አብራርቶ
የልቤን አድምጧል፣ ስተነፍስ ገብቶ…” ይላታል። ተቀብላው ይሆን?

Read 8373 times