Monday, 19 June 2017 09:25

ህይወት - ከቤተ መንግስቱ ጀርባ!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

“መንግስት ይህንን ወንዝ ወዲያ ይያዝልን”
                          
     የ38 ዓመቷ ዙሪያሽ አዋሽ፤ ተወልዳ ካደገችበት የጉራጌ ዞን እንሙር ወረዳ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ገና በለጋ እድሜዋ ነበር። የአዲስ አበባን መሬት ስትረግጥም ሃሳቧና ህልሟ ያገኘችውን ሥራ እየሰራች ለማደግና ለመለወጥ ነበር፡፡ ስለዚህም ከህይወት ጋር ግብግብ የጀመረችው ባልጠና የልጅ አቅሟ ነበር፡፡
ህይወት አልገፋ ሲላትና የኑሮ ሸክምን ለብቻዋ መሸከም ሲከብዳት፣ ከአንድ ሁለት ይሻላል በሚል ሃሳብ ትዳር መሰረተች፡፡ ከትዳር አጋሯ ጋር ኑሮዋን በመሰረተችበት አዋሬ ገበያ፤ የግንፍሌን ወንዝ ረዳት አድርጋ፣ ከደቀቀ ከሰልና አፈር ድብልቅ እየጠፈጠፈች የምትሰራውን ከሰል፣ እዛው በመንደሯ ለሚኖሩ ሰዎች እየሸጠች ኑሮዋን ተያያዘችው፡፡
ዓመታት አለፉ፡፡ የትዳር አጋሯ ሥራ የሌለው በመሆኑ፣ የቤተሰቡ ሙሉ ተስፋና መተዳደሪያም ይህችው እሷ ጠፍጥፋ በምትሰራው ከሰል የምትገኘው ገቢ ብቻ ነበረች፡፡ የቤተሰቧ ቁጥር ከሁለት ወደ ስድስት ከፍ ሲልም፣ኑሮዋ ይህችን ከአፈር ከሰል ሽያጭ የምትገኘውን ገቢ መሰረት ያደረገች ብቻ ነበረች፡፡ እንዲህ ክረምት ሲሆንና የግንፍሌ ወንዝ ሲቆጣ ደግሞ ቅጣቱ አያድርስ ነው፡፡ ግንፍሌ ወንዙ ዳር እየጠፈጠፈች ያጠራቀመችውን ከሰል ጠራርጎ ከጎርፍ ያደባልቅባታል፡፡ ሃዘኑና ተስፋ ቢስነቱ ሆድ ቢያስብሳትም ነገም ማለዳ ላይ ወጥታ እዛው ወንዝ ዳር ውላ ማምሸቱን ኑሮዋ አድርገዋለች፡፡ የት ይደረሳል? ምን አማራጭ አለ? 1500 ብር ለግለሰብ ቤት እየከፈሉ፣ ስድስት ቤተሰብን ይዞ ለመኖር፣ አራት ልጆቿንም ለማሳደግና ለማስተማር ያላት ብቸኛ አማራጭ ይኸው ሥራ በመሆኑ ያለመታከት ትታትራለች፡፡
ላለፉት 17 ዓመታት በዚህ የአፈር ከሰል ንግድ ስራዋ፣ቤተሰቧን ለማስተዳደርና ልጆቿን ለማስተማር ችላለች፡፡ ከጀርባዋ በሚገኘው ቤተ-መንግስት ውስጥ ህይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ማወቅ እንኳን ሳያጓጓት፣ አኗኗራቸው ሳያስከፋት፣ ባላት ነገር ተደስታ ትኖራለች፡፡ ለእሷ ከባዱ ችግሯና ጉዳቷ፣ ግንፍሌ ሲቆጣ ብቻ ነው፡፡
እንደ ዙሪያሽ ሁሉ እንኳንስ ለኑሮና ለሥራ ለአፍታም በአጠገቡ ለማለፍ እጅግ በሚፈትነው የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ላይ ኑሮአቸውን አድርገው፣ የቤተመንግስቱን ጀርባ እየታከኩ፣ እጅግ በሚያሳዝንና ለማሰብ እንኳን በሚከብድ ህይወት ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ወገኖች አዋሬ ገበያን ሞልተውታል፡፡ ከዘጠና በላይ አባወራዎች እንደሚኖሩበት በሚነገረው በዚህ ሥፍራ ላይ ያሉ መኖሪያ ቤቶች፤ ዙሪያቸውን በቆርቆሮ የተሰሩና መፀዳጃ ቤት አልባ ናቸው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት በሥፍራው በተነሳ የእሳት ቃጠሎ አደጋ፣ ቤቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደሙባቸው የሚናገሩት እነዚሁ ወገኖች፤ መንግስት በቦታቸው ላይ ቤት ሰርተው መኖር እንዲችሉ ስለፈቀደላቸው፣ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆኑና እርስ በርስ የተዛዘሉ ቤቶችን ሰርተው፣ ኑሮአቸውን እዚያው ስፍራ ላይ ቀጥለዋል፡፡ ለካ እንዲህም አይነት ህይወት አለ የሚያሰኙት የአዋሬ ገበያ መንደር ነዋሪዎች፤ እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት፣ የከተማ ጤና ፕሮግራም ከጄኤስ አይ የከተማ ጤና ማጠናከር ፕሮግራምና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ሰሞኑን ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም ውስጥ የተካተተው የአዋሬ ገበያው መንደር፤ የከተማው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የጎበኘውም አይመስልም።
ሥፍራውን ለማስጎብኘት አብራን የነበረችው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ፤ በአካባቢው ለሚኖሩት ወገኖች ስለ አካባቢ ንፅህናና ስለ ጤና አጠባበቅ በየጊዜው ትምህርት እንደሚሰጡ ነግራናለች፡፡ አንዳች የመፀዳጃ ቤትና ጠብታ ውሃ በሌለበት፣ እርስ በርሱ በተጠላለፈና በተጨናነቀ መንደር ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖች “ንፅህናችሁን ጠብቁ” ብሎ በማስተማር የሚገኝ ለውጥ ይኖራል ብሎ ማሰቡ ከባድ ነው፡፡
ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች እየተከሰተ ያለው የአተት ወረርሽኝ፤ እዚህ አካባቢ ቢከሰት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ማሰቡ ይዘገንናል፡፡ የግንፍሌን ወንዝ መፀዳጃው አድርጎ፣ ከወንዙ ፍሳሽ የሚያገኘውን ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተጠቀመ የሚገኘው የአዋሬው መንደር ነዋሪ፤ ለዚህ ወረርሽኝ ላለመጋለጡ ምንም ዋስትና የለውም፡፡
ከ15 ዓመታት በላይ በአካባቢው መኖሯን የገለጸችው ወርቅነሽ ወልዴ፤ ለመንደሯ ነዋሪዎች ክረምት በመጣ ቁጥር ከወረርሽኝም ስጋት በላይ የሚያሳስባቸው የጎርፍ አደጋ እንደሆነ ትናገራለች። ግንፍሌ በመንደሩ ዝናብ ዘነበም አልዘነበም፣ ድንገት ተነስቶ ሊያጥለቀልቃቸው ይችላል፡፡ ምሽት አይል ወድቅት፤ ንጋት አይል ቀትር፤ ወንዙ ድንገት ሞልቶ ቤቶቹን ሊያጥለቀልቃቸውና ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡
“የዚህ አካባቢ ነዋሪ እኮ ክረምትን አይተኛም። ባልና ሚስት ከሆኑ ተራ ጠብቀው ያድራሉ እንጂ ለሁለት ማንቀላፋት የለም፡፡ ውሃ ደራሽ ነውና አመጣጡ ድንገት ነው፡፡ በተኛንበት ቢመጣብን ልጆቻችንን ምን ልናደርጋቸው ነው። እናም ተራ ጠብቀን እንተኛለን፡፡.. ባል የሌላቸው ጎረቤቶቻችን፤ ቁጭ ብለው ልጆቻቸውን ሲጠብቁ ያድራሉ እንጂ ጥለዋቸው አያንቀላፉም” ትላለች፡፡
እንደው መንግስት ምን ቢያደርግላችሁ ትመኛላችሁ? ጥያቄያችን ነበር፡፡
 “ይህንን ወንዝ ወዲያ ይያዝልን” የመንደሯ ነዋሪዎች በጋራ የሰጡት ምላሽ ነው፡፡  
ዙሪያውን በዝንብና በቆሻሻ የተሞላው የአዋሬ ገበያው መንደር፤ አፍንጫ በሚተነፍገው መጥፎ ሽታ በሥፍራው መቆየትን ይፈታተናል። ወይ አዲስ አበባ ስንቱን በሆድሽ ይዘሽ ኖረሻል? አሁን እስቲ እንዲህ አይነት መንደር፣ እንዲህ አይነት ህይወት፣ ያውም ከቤተ መንግስቱ አዋሣኝ መንደር ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል? የአፍሪካ ርዕሰ ከተማ ተብላ በምትጠራዋ አዲስ አበባ፣ የነዋሪዎቿን ህይወት በመለወጥና በማሻሻል፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ህዝቦች ተርታ ለመሰለፍ እየተጋች ያለች ከተማ ነች በምትባለው ሸገር፣ ታላላቅ አለም አቀፍ መሪዎችን በምታስተናግደዋ ከተማ፣ ነዋሪዎቿ የመፀዳጃ ቤትና ንፁህ የመጠጥ ውሃ ያገኙበታል ተብላ በምትታሰበዋ አዲስ አበባ ----- ኑሮአቸውን፣ እንጀራቸውንና መፀዳጃ ቤታቸውን ወንዝ ላይ አድርገው፣ በተፋፈነና እርስ በርሱ በተዛዛለ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ከዘጠና በላይ አባወራዎች ይኖሩበታል ቢባል ማን ያምን ይሆን? እውነታው ግን ይኸው ነው፡፡ ከቤተ መንግስቱ ጀርባ፣ በአዋሬ ገበያው መንደር ውስጥ ያለው ህይወት፣ እውነቱ ይኸው ነው፡፡

Read 3758 times